የዚህ ሳምንት አንዱ ሀገራዊ አጀንዳ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ሀገር አቀፍ የፈተና ውጤት ነበር:: ከዚህ በፊት ከነበሩት ዓመታት አንፃር ብዙ ተማሪ ዝቅተኛ ውጤት ያመጣበት ዓመት ነው:: ከ50 በመቶ በላይ ያመጡት 3.3 በመቶ ተማሪዎች ብቻ ናቸው::
በነገራችን ላይ የዘንድሮ የትምህርት ሚኒስቴር ዝርዝር መግለጫ ለብዙ ፖሊሲዎች ግብዓት የሚወጣው ነው:: በፆታ፣ በአካባቢ፣ በትምህርት ቤቶች አይነት፣ በትምህርት መስኮች አይነት፣ በከተማና ገጠር…. በአጠቃላይ በየዘርፉ ምን ይመስል እንደነበር ዝርዝር መግለጫ ሰጥቷል:: ራሳቸው የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደገለጹት፤ በየዘርፉ ያሉ አካላት ‹‹ለምን ሆነ?›› የሚለውን ወስደው ሊሰሩበት ይገባል::
የኔ ትዝብት ግን ወዲህ ነው:: የፈተናውን አኃዛዊ መረጃዎች ለባለሙያዎች እንተወውና ተማሪዎችን የሚጎዱ አላዋቂ ልማዶቻችንን ግን እንታዘብ::
ከፈተናው በፊት አንድ የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ለተማሪ ወላጆች የጻፈው ነው የተባለ ደብዳቤ በማኅበራዊ የትስስር ገፆች ላይ ሲዘዋወር አገኘሁት:: ደብዳቤውን ቃል በቃል እንደሚከተለው እናስነብባችሁ::
‹‹… ወድ ቤተሰቦች!
የልጆቻችሁ ፈተና በቅርቡ ይጀምራል:: የልጆችዎ ፈተና ጉዳይ እንዳስጨነቀዎ ይገባናል::
ነገር ግን፣ እባክዎን ይህን ያስታውሱ::
ለፈተና ከሚቀመጡት ተማሪዎች መካከል በሂሳብ መራቀቅ የማይጠበቅበት አርቲስት ይኖራል:: ስለታሪክ እና ሥነጽሑፍ ግድ የማይሰጠው የነገ ሥራ ፈጣሪም አለ:: የኬሚስትሪ ውጤቱ ከፍ አለ ዝቅ አለ በሕይወቱ ላይ ለውጥ የማያመጣበት ሙዚቀኛም ከተማሪዎች መካከል አለ::
ከፊዚክስ ይልቅ የአካል ብቃቱ ጉዳይ ወሳኝ የሆነበት አትሌትም ይኖራል::
ስለዚህም ልጅዎ በፈተና ከፍተኛ ውጤት ካመጣ ጥሩ! ዝቅተኛ ውጤት ካመጣ ግን እባክዎን በራስ መተማመኑን እና ክብሩን አይንጠቁት:: ምንም ማለት አይደለም በሏቸው ይልቅ!
ከትምህርት ቤት ፈተና ለላቀ ታላቅ ጉዳይ ወደዚህ ዓለም እንደመጡ ንገሯቸው:: የትኛውንም ውጤት ቢያመጡ እንደምትወዷቸው፤ ዝቅተኛ ውጤት አመጡ ብላችሁ እንደማትፈርዱባቸው ንሯቸው::
አዎን! እባክዎን ይሄን ያድርጉ … አንድ ፈተና ወይም አነስተኛ ውጤት ሕልምና በራስ መተማመናቸውን፣ ክህሎታቸውን እንዲያሳጣቸው አታድርጉ::
እናም እባከዎን … ልጆችዎ ገና ለገና ዶክተር እና ኢንጂነር ካልሆኑ ደስተኛ አይሆኑም ብላችሁ አታሰቡ!
ከሞቀ ሰላምታ ጋር…››
ይላል ደብዳቤው:: ይህን ደብዳቤ ሳነብ በቀጥታ በአካባቢያችን ይደረጉ የነበሩ ልማዶች ናቸው ትዝ ያሉኝ:: አሁንም የ12ኛ ክፍል ውጤት መለቀቅን አስመልክቶ የሚሰሩ ቀልዶችና ተስፋ አስቆራጭ መልዕክቶች ናቸው የታዩኝ::
በተማረውም ይሁን ባልተማረው ማኅበረሰባችን ውስጥ ያለው አስተሳሰብ ለዕውቀት የተዛባ ቦታ አለው:: ልማዳችን በተለይም ለተሰጥዖ ቦታ የለውም:: አንድ ተማሪ ጎበዝ ነው የሚባለው ሒሳብ፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ፣ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ… ትምህርቶችን ጎበዝ ከሆነ ብቻ ነው::
በተለይ የእጅ ሙያ (ሥዕልና ቅርጻቅርጽ)፣ የድምጽ ሙያ፣ የትወና ብቃት፣ የአካል ብቃት(ስፖርት)፣ የአስቂኝነት ተሰጥዖ፣ ወይም ሌላ ለየት ያለ ችሎታ እንደ ብቃት አይታዩም:: እንዲያውም በተቃራኒው የቦዘኔነት ምልክት ተደርገው ነው የሚታዩ:: እውቀት ማለት እነዚያ የትምህርት አይነት ተብለው በክፍለ ጊዜ ተከፋፍሎ የሚሰጡት ብቻ ናቸው::
አዎ! እንደ ፊዚክስ፣ ሒሳብና ኬሚስትሪ የመሳሰሉ ትምህርቶች ዓለምን እዚህ የረቀቀ ቴክኖሎጂ ላይ ያደረሱ ወሳኝ መሠረታዊ የሳይንስ ትምህርቶች ናቸው:: ዳሩ ግን ሕይወት ማለት ደግሞ በእነዚህ ትምህርቶች ጎበዝ መሆን ማለት ብቻ አይደለም::
የአገራችንንም ሆነ የዓለምን ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን ማየት በቂ ምስክር ነው:: ከፊዚክስ ተራቃቂው አልበርት አንስታይን ያላነሰ የእግር ኳስ ኮከቡ ሊዮኔል ሜሲ ዝነኛ ነው፣ ተወዳጅ ነው፣ ሀብታም ነው:: ዘፋኙ ማይክል ጃክሰን ከሳይንስ ሊቁ ስቴቨን ሀውኪንግ በላይ የዓለም መነጋገሪያ ነበር::
ታሪካቸውን በቅርበት የምናውቃቸው በየተሠ ማሩበት ዘርፍ ጀግና የሆኑ የሀገራችንን ዝነኞችም ማየት እንችላለን:: ዘፋኞቹ ጥላሁን ገሠሠ ወይም ቴዲ አፍሮ ዝነኛ እና ተወዳጅ የሆኑት በፊዚክስ ወይም ኬሚስትሪ አይደለም:: የተሰጣቸውን ተሰጥዖ ለተገቢው ዓላማ ስላዋሉት ነው:: እነ ኃይሌ ገብረሥላሴና ቀነኒሳ በቀለ ‹‹ጀግና›› ተብለው የሀገር ባለውለታ የሆኑት በታሪክ ጥናትና ምርምር ወይም በሒሳብ ሊቅነት አይደለም:: የተሰጣቸውን ተሰጥዖ በተገቢው ዓላማ ስላዋሉት ነው::
እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሀገርንም ጠቅመዋል ማለት ነው:: የፈጠሯቸው የሥራ ዕድሎች ለሕዝብ ጠቅመዋል ማለት ነው::
አዎ! ሀገራችን የሳይንስ ተመራማሪዎች ያስፈልጓታል:: የአንዲት ሀገር ዕድገት የሚለካው በሳይንስ ዕድገት ነው:: ይህ የሚሆነው ግን በትንቅንቅ ሳይሆን በችሎታ ነው:: የሀገሪቱ ተማሪ በሙሉ የሳይንስ ተመራማሪ ሊሆንልን አይችልም:: ስለዚህ ያለውን የግል ተሰጥዖ እንዲጠቀምበት ዕድል መስጠት አለብን ማለት ነው:: ማሸማቀቅና ምንም የማይጠቅም እንደሆነ መናገር ሞራሉን ይነካል:: የተሰጥዖ ሥራዎች ደግሞ ሞራል የሚፈልጉ ናቸው::
ሌላው የተዛባው አመለካከታችን ብዙ የእጅ ሥራ ውጤት የሆኑ የዕደ ጥበብ ሥራዎች እንደ ሳይንስ የማይታዩ መሆኑ ነው:: አፈርን አቡክተው፣ ከጭቃ ጠፍጥፈው የሸክላ ሥራዎችን የሚሠሩ እናቶቻችን እንደ ሳይንስ ተመራማሪ አይታዩም:: የሳይንስ ውጤት የሚባለው ፈረንጅ የሠራው ሲሆን ብቻ ነው::
እነዚያ ከአገልግሎታቸው በተጨማሪ ለዓይን እንኳን የሚማርኩ የጅማ የእንጨት ውጤቶች እንደ ሳይንስ ሥራ አይታዩም:: ሸክላ፣ የጥጥ ፈትል እና የእንጨት ሥራዎች ‹‹ባለ እጅ›› እየተባሉ እንደኋላቀር ይታያሉ፤ ይሄ የአስተሳሰባችን ኋላቀርነት እንጂ የረቀቁ ሳይንሶች ናቸው::
ሰሞኑን ይፋ የሆነው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት የተፈተኑባቸውን የትምህርት አይነቶች ውጤት ብቻ ነው የሚገልጽ:: በእነዚያ ሰባት የትምህርት አይነቶች ውስጥ፤ ሙዚቃ የለም፣ አትሌቲክስ ወይም እግር ኳስ የለም፣ ሥዕል የለም፣ የአገራችን የዕደ ጥበብ ሥራዎች የሉም:: ስለዚህ አንድ ተማሪ በእነዚያ ፈተናዎች ወደቀ ማለት ምንም ችሎታ የለውም ማለት አይደለም::
እስኪ ልብ እንበል! ጅማ በእንጨት ሥራ ላይ የተሠማራ አንድ ወጣት፣ ወይም ሽሮ ሜዳ በሽመና ሥራ ላይ የተሰማራ አንድ ሸማኔ፣ 4 ነጥብ አምጥቶ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ከተቀጠረ ሰው የተሻለ ኑሮ አይኖሩም? አንድ ቧንቧ ጠጋኝ ባለሙያ ከፍተኛ ውጤት አምጥቶ ሦስትና አራት ዓመት ሥራ ፍለጋ ከሚኳትን ባለዲግሪ አይሻልም?
ስለዚህ ዕውቀት ማለት የእጅ ወይም የአዕምሮ ሙያ እንጂ የግድ የተሸመደደ የቲዎሪ ትምህርት ስቃይ(ከፍተኛ ነጥብ) መሆን ብቻ አይደለም:: እንዲያውም ሥርዓተ ትምህርታችን ራሱ ይህን ነገር ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት:: የተማሪዎች ትምህርት ተሰጥዖን እና አገር በቀል የሆኑ የዕደ ጥበብ ሥራዎችንም ያካተተ ሊሆን ይገባል:: በዚህ በኩል የኦሮሚያ ክልል ሊመሰገን ይገባል፤ የክህሎት ትምህርት ማሰልጠኛዎች እየተከፈቱ እንደሆነ ሰምተናል::
በአጠቃላይ አንድ ሰው ስኬት ላይ የሚደርሰው በተሽመደደ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን በብዙ ተሰጥዖዎች ጭምር ነውና ተማሪዎችን ማሸማቀቅ ይቁም!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥር 24 ቀን 2015