ሽንቁሮቻችን ብዙ ናቸው። በዚህኛው ስንደፍን በወዲያኛው በኩል የሚያስተነፍስ ቀዳዳ እልፍ ነው። ጥንቃቄ የሚያሻቸው፣ ሊታከሙ የሚገባቸው ቁስሎቻችን እዚህም እዚያም አመርቅዘው ይታያሉ። ቅድሚያ የሚሹ አንገብጋቢ ጉዳዮቻችን እየበዙ ነው። እንደ ህዝብ ብዙ ይጠበቅብናል። ሆደ ሰፊነት፣ ታጋሽነትና መተባበር ምግባራችን ሊሆኑ ይገባል። ከመንግስት እንቅልፍ ማጣትን የሚጠይቅ ቁርጠኝነት ያስፈልገናል። እያንዳንዱን ሰኮንድ፣ ደቂቃና ሰዓት ለችግሮቻችን መፍትሄ ለመፈለግ መጠቀም ያለብንና ምርጫ የሌለው ጉዳይ ነው።
“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ በዚህ በኩል ሉአላዊነታችንን የሚፈትኑ ጉዳዮች ሲገጥሙን በዛኛው ዳር ደግሞ ስንፍናና ሌብነት ምጣኔ ሃብታችንን እያደቀቁ ይገኛል። ይህ ደግሞ እንደ ህዝብ እንደ አገር እያጣነውና እየተሸረሸረ ከመጣው የሞራል ልእልና ጋር ሲደመር መንገዳችንን ከባድ፣ መፍትሄውን እሩቅ ያደርገዋል። ይህም ሆኖ ለሺህ ዘመናት እንደ ላሊበላና አክሱም ሃውልት ሳይገረሰስ የቆየው የኢትዮጵያዊነታችን ምሰሶ ወቅታዊ ማእበልና ውሽንፍር ሳይነቀንቀው በጥበብና በብልሃት እያሳለፈን ነው። ይህ ታላቁ ምሰሶ ግን እስከመቼ እንደፀና ይቆይ ይሆን?።
አገር በጠንካራ ስነ ምግባር፣ ባህል፣ እምነትና አንድነት ይገነባል። ቀን ከሌት የሚሰሩ፣ ቆፍረው፣ ዘርተው የሚያጭዱ እጆች፣ በጥበብ ብሩህ አእምሮን የሚቀርፁ ሊቆችና ምሁራን መነባበር አገርን የማትደፈርና ሃያል ያደርጋታል። እምነትና ባህል ደግሞ ይህንን ሃቅ የሚያፀኑና ሰብአዊ ማንነት የሚፈጥሩልን መቋጫዎች ናቸው። ለዘመናት “ኢትዮጵያ” የሚል ታላቅ አገርን ያቆየልን ይሄው ሃቅ ነው። በሂደቱ ግን ብዙ ፈተናዎች፣ መሰረቶቻችንን የሚንዱ አጋጣሚዎች አልተፈጠሩም ማለት አልነበረም።
ጠላት ውቂያኖስ አቆራርጦ፣ በረሃ ተሻግሮ ዳር ድንበራችን ደርሶ ህልውናችን ተፈታትኖ ነበር። አንድነታችን ላልቶ፣ መተባበራችን እክል ገጥሞት ጦር ሰብቀን እናውቃለን። የተፈጥሮ አደጋዎች ደግመው ደጋግመው ፈተና ሆነውብን ያውቃሉ። ወዳጆቻችን ጠላት ሆነው ከጀርባ ወግተውናል። ያጎረስንበት እጃችንን የነከሱ እልፍ ነበሩ። ከጉያችን የወጡ “ባንዳዎች” ገበናችንን አጋልጠው እደጅ እስጥተውት ነበር። መንገድ እየመሩ ቀዬአችንን ለመናድ ቅጥራችንን ለማፍረስ ተባብረውብን ያውቃሉ። እነዚህን ሁሉ ግን በጠንካራ አገረ መንግስት፣ በአገር በቀል ጥበብ እና ምሰሶዎቻች ተመክተው ከስመዋል፤ ዛሬስ? ።
ልክ እንደ ትናንቱ ዛሬም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን የሚፈትኑ አያሌ አባጣ ጎርባጣዎች እዚህም እዚያም ይታያሉ። ላለፉት 50 እና 60 ዓመታት የብሄር ጉዳይ ትልቁ የአገር ጋሬጣ ሆኖ እያንገዳገደን ይገኛል። እንዳንፀና፣ ፊታችን ወደ እድገትና ስልጣኔ እንዳናቀና ጋሬጣ ከሆነብን ሰነባበተ።
ድንበር የሚጋሩንም ሆነ ብዙ ሺህ ኪሎሜትሮች የራቁን የጥቅም ተጋሪዎቻችን ጥሬውን እኛ ብቻ ካልጫርነው በሚል ልዩነቶቻችንን ለማጉላት ደፋ ቀና ይላሉ። ከመስላሉ ጫፍ ያሉ ሃያላን ተስፋና ፅናታችንን ሊገድሉብን ካስማችን ለመናድ በብዙ ሴራዎች ውስጥ ተጠምደው ያሉ ቢሆንም ላይ ላዩን ግን ወዳጅ ይመስላሉ።
በኢትዮጵያ ወስጥ ትንንሽ ሉአላዊነትን ለመፍጠር ላይ እታች የሚሉ ብዙሃን ናቸው። በቀበሌና በጎጥ ከፋፍለውን የንዋይ ጥማቸውን የሚያረኩ ቡድኖች እያንሰራሩ ሃይል እያከማቹ እያየን ነው። የት እንደሚደርሱ ባናውቅም ለዛሬ ግን እዚህም አዚያም ቀውሶችን በመፍጠር በህዝቦች መካከል ሽብልቅ ለማስገባት እየተፍጨረጨሩ ነው። በእርግጠኝነት ግን ይህ ህልማቸው ከዳር ሳይደርስ ይከሽፋል።
ዛሬ ማህበራዊ ስነልቦናችንን የሚፈትን፣ ህግና ስርዓትን የሚንዱ፣ ከቀኖና፣ ባህል ትውፊታችን ጋር የሚጋጩ ድርጊቶች ላይ የሚሳተፉ ጋሬጣዎችን እየተመለከትን ነው። ሰዎች ይታገታሉ። ከጫፍ ጫፍ ለመንቀሳቀስ እንዳይችሉ የሙስናና የውንብድና ተግባር ላይ በተሰማሩ ሃይሎች እንቅፋት የሚሆኑ ብዙ ናቸው።
ብሄራዊ ጥቅማችንን ከሚያስቀሩ ተግባር ላይ ብዙዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ። ምንም እንኳን መንግስትና ዜጎች በጋራ ይህን መሰል እኩይ ተግባር ላይ የተሰማሩትን ለማረቅ እየሰሩ ቢሆንም ሰንሰለታቸውን ለዓመታት የዘረጉ በመሆኑ ጊዜ መውሰዱ የማይቀር እንደሆነ እሙን ነው።
ከዋና ዋና የአገር ምሰሶዎች ውስጥ ኢትዮጵያዊ ስነ ምግባራችን ፣ጠንካራ ባህላችን፣ ሃይማኖታዊ ስርዓታችንና ሌሎች የጋራ እሴቶቻችን እንደ አገር ያቆሙን ምሰሶዎች ናቸው። ይሁን እንጂ እኩይ አላማን ታቅፈው ደፋ ቀና የሚሉት አካላት ወደ እነዚህ እሴቶች ለመደርመስና ምኞታቸውን ለማሳካት እየተፍጨረጨሩ ነው። ህዝቦችን እንደ ሰንሰለት የያዙ የመከባበር፣ የአንድነትና በፅናት አብሮ የመቆም ልምዶቻችንን እየተገዳደሩም ይገኛሉ።
የአገር ምሰሶዎችን ለመጠበቅ ቀይ መስመር ልናበጅ ይገባል። በእርግጥ ኢትዮጵያዊያን እዚህ ጋር ስንደርስ ሁላችንም በአንድነት በመቆም እንታወቃለን። ይህን ለማወቅ የታሪክ ዶሴዎችን ማገላበጥ ብቻ በቂ ነው። ነገር ግን በጥፋት አጀንዳ ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦቸንና ቡድኖች መሰሶዎቹን ለማነቃነቅ እየሞከሩ ነው።
ቀደም ባሉት ዘመናት ግጭቶችን፣ አለመግባባቶችን የምንፈታበት ባህላዊ የሽምግልና ስርዓቶች ነበሩን። አሁንም ድረስ አሉ። የተጣላን የሚያስታርቅ “አንተም ተው እናንተም እረፉ” በሚል የሚገስፅ፣ የተጎዳን የሚክስ እውነትን ከፍትህ ጋር የሚያገናኝ እሴት ነው። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን አባቶቹን የሚንቅ፣ ለባህላዊ ህግና ስርዓትየማይገዛ፣ ለግል ጥቅሙና ፍላጎቱ ያደረ አፈንጋጭ ሃይል ይህንን የጋራ እሴትና ታላቅ ምሶሶ ለመናድ እየሞከረ ነው። ይህ ድርጊት አደገኛ በመሆኑ “ሃይ” ሊባል ይገባል።
ሌላው “ኢትዮጵያዊ ስነምግባር” (ሞራል) ነው። ይህ ምሰሶ አብረን ለመፅናታችንና ለመቆማችን ምክንያት ነው። “ኢትዮጵያዊ ጨዋነት” አለን የምንለው ለሺህ ዘመናት በገነባነው የስነ ምግባር እሴት ምክንያት ነው። የሰው አለመፈለግ፣ ሃቅን አለመብላት፣ መብትን አለመጋፋት፣ ፍፁም ሰብዓዊነትን መላበስ ከስነ ምግባራችን የሚቀዳ ነው። ይህን ካስማ ዛሬ ላይ ለማንገዳገድ ብዙዎች እየሰሩ ነው።
ከሰብዓዊነት ያፈነገጡ ድርጊቶችን የሚያለማምዱን ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች እዚህም እዚያም እየተፍጨረጨሩ ነው። ይህ ቀይ መስመር ነው። ለፍቶ የሚያድር፣ ህዝብን የሚያገለግል ነጋዴ እንዳለ ሁሉ ቀምተውና ዋጋን አንረው የዜጎችን መከራ ለማብዛ የሚራወጡት እንደ በረሮ አምሳያቸውን በፍጥነት እየፈለፈሉ ነው።
ከማግባባት ይልቅ በዘርና በጎጥ ፖለቲካዊ ልዩነት ፈጥረው ህዝብን ከህዝብ የሚያናክሱና ከስነ ምግባር ያፈነገጡ ድርጊቶች እንዲፈፀሙ የሚያበረታቱ “የፖለቲካ ነጋዴዎችም” እንዲሁ በየስፍራው አሉ። እነዚህና ሌሎች ኢትዮጵያዊ ስነምግባራችንን የሚፈታተኑ ምግባሮች ናቸው። ይሄ ቀይ መስመራችን ሊሆን ይገባል። ምሰሶውን የሚነካ ሳይሆን የሚጠጋ እራሱ ትምህርት የሚሰጥ ተግሳፅና ቅጣት ያሻዋል።
ኢትዮጵያ ብዝሃ ሃይማኖት ያለባት አገር ነች። ኦርቶዶክስም ሆነ ሙስሊሙ አንዲሁም ሌሎች ሃይማኖቶች ተከባብረውና የጋራ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን አክብረው ለሺህ ዘመናት የኖሩባት ምድር ነች። ይህ ማስረጃ ማቅረብ የማያሻው ጥሬ ሃቅ ነው። ይህንን ማህበረሰብ ከላይ ካነሳናቸው የስነ ምግባር፣ ባህልና ሌሎች እሴቶች በተጨማሪ በምሰሶነት የያዘው እምነቱና ለፈጣሪው ያለው አክብሮት ነው። የሞራል ልእልና ከፍታን ከሚያጎናፅፉ መካከልም እምነት ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳል። ሰብዓዊነትና ርህራሄን ያላብሳል።
ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን ይህንን ምሶሶ ለመናድ ያሰፈሰፉ እኩያንን እየተመለከትን ነው። አገር እንዳይፀና ከተፈለገ መሰል እሴቶችን ያለርህራሄ መገርሰስ ያስፈልጋል። ስለዚህ በክፋት የተላወሱ አካላት ቀይ መስመሩን ለመሻገር ድፍረት የተሞላበት ድርጊት መፈፀም ከጀመሩ ሰነባበቱ። ሃይማኖትን ከሃይማኖት ለማቃረን ተደጋጋሚ ሙከራዎች ሲደረጉ አስተውለናል። ለሺህ ዘመናት የተገነባ ስብእናና ህጋዊ ሰውነት ያላቸው ተቋማትን መነቀፍና መዝለፍ ልምድ እየሆነ የመጣ ይመስላል። ይህ ሙከራ መሰሶዎችን ለመናድ የሚደረገው ቀጣዩ የድራማ ክፍል ነው። ለዚህ ነው “ቀይ መስመር ልናበጅ ይገባል” የምንለው።
“ኢትዮጵያዊ መልክን” እና ማንነትን ከሚያጠፉና ከሚንዱ ተግባራት መካከል የሚመደበው ማህበረሰቡን “ጭካኔና ከፍተኛ ውንብድና” ለማለማመድ የሚሞክሩ የቡድኖች ሴራ ነው። ዜጎች ለራሳቸው ፍቃድ ብቻ እንዲገዙ፣ ፍፁማዊ እራስ ወዳድነት እንዲጠናወታቸው፣ በብሄር ጥላ ውስጥ ብቻ እንዲሸሸጉ የሚያለማምዱና ሴራ ሲጎነጉኑ የሚውሉ ቡድኖች በየአካባቢው እየተመለከትን ነው። ይህን ከኢትዮጵያውያን ያልሆነ ባህሪ ማስረፅ የቻሉ ቀን አገር እንደሚያፈርሱ ሙሉ እምነታቸው ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት የተገነባውና ወደፊትም የሚቀጥለው በእነዚህ ጠንካራ ስነምግባሮች እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቁታልና።
ስለዚህ ምንም ያህል ብንፈተን በኢትዮጵያዊነት ያለን እምነት እንደፀና ሊቆይ ይገባል። ብልሃትን፣ጠንካራ ስብእናን ገንዘባችን ልናደርግ የግድ ይለናል። ከሁሉ በላይ ግን ምሰሶዎቻችን እንዳይነቃነቁ አጠንክረን ልናቆማቸው ያስፈልጋል። በየግዜው ለኢትዮጵያዊ ስነምግባር፣ ጨዋነት፣ ፈጣሪን መፍራት፣ ሉአላዊነትን ማስቀደም (አርበኝነት)፣ ለባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን ተገዢ መሆናችንን ማሳየት ይጠበቅብናል።
የቀደመው ያባቶቻችን አገር ከመስራት ባሻገር ለትውልድ የማሻገር ጥበብ ልንወርስ ይገባል። ይህ ሲሆን የኢትዮጵያን መዳከም፣ ጭራሹኑ መፍረስ እና ተበታትኖ ማየት የሚሹ አካላት ህልም እንደ ጉም እንዲበተን እናደርጋለን።
ተቃራኒውን ከመረጥን ውጤቱም ያው ይሆናል። በጥቃቅን ሴራ ከተጠለፍን እሴቶቻችንን አሳልፈን ከሰጠን ጠንካራ ሳትሆን ቀስ እያለች የምትከስም አገር ይኖረናል። ምሰሶዎቻችን እንዲናዱ ከፈቀድን የአባቶቻችንን አደራ ቀርጥፈን እንበላለን። “የጥቅም ተጋሪዎቻችን ናቸው” ብለው ለሚያስቡ የውጪ ሃይሎች ሲሳይ ከመሆን አንድንም። ከዚህ የተነሳም ምሰሶዎቹ አይደለም እንዲፈርሱ እንዳይነቃነቁ በአንድነትና በጠንካራ እምነት እንቁም። ሰላም!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም