ትራንስፖርት የሀገር የምጣኔ ሀብትና ዕድገት መሠረት ነው። አንዳንዶች ትራንስፖርትን የአንድ ሀገር ምጣኔ ሀብት የደም ሥር ነው ይሉታል። ጤና፣ ትምህርት፤ግብርና፣ ኢንዱስትሪ የሚሠምረውና ስኬት የሚኖረው የትራንስፖርት አቅርቦቱ የተሟላ ሲሆን ነው።
ትራንስፖርት የተቀላጠፈ፤ ለሕዝብ ተደራሽ ፤ ክፍያውም ተመጣጣኝ ሲሆን ትሩፋቱ ብዙ ነው ። ንግድ ይሳለጣል ፤ ማለትም ግብይቱ መሸጥ መለወጡ፣ ማውረድ መጫኑ ይሟሟቃል። የሕዝብ ለሕዝብ መስተጋብርም ይጠናከራል። በአጠቃላይ አገልግሎቱ ያማረና የሰመረ ይሆናል።
በዚህ መልክ የአዲስ አበባን የትራንስፖርት አገልግሎት ብንመለከት ሁኔታው ለዘርፉ ልንሰጥ የሚገባውን ከፍያለ ትኩረት አጉልቶ አመላካች ነው። የትራንስፖርት ፈላጊው ረጅም ሰልፎች ፤ የክፍያ ታሪፍ ዝብርቅርቅ መሆን ፤ ከተፈቀደ ተሳፋሪ በላይ መጫን …ወዘተ የእለት ተእለት ሀይ ባይ ያጣ ትእይንት ነው ።
መንግሥት አለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋን ታሳቢ በማድረግ የሚያደርጋቸውን የትራንስፖርት ዋጋ ማሻሻያን ተከትሎ የሚፈጠረው ዝብርቅርቅ ያለ አሰራርና በአንዳንድ ነዳጅ ማደያዎችም ወቅታዊ ሁኔታዎችን ተከትሎ የሚከናወኑ ህገወጥ ተግባራት የዚሁ በዘርፉ የሚስተዋለው ችግር አካል ነው ።
ይህ ሁሉ በአደባባይ እየሆነ ባለበት ሁኔታ ዘርፉን ለመቆጣጠር ስልጣን የተሰጠው የአስተዳደሩ የትራንስፖርት ቢሮ ከእሳት ማጥፋት እርምጃ ያለፈ ዘላቂና ጠንካራ እርምጃ መውሰድ አለመቻሉ በራሱ ሌላው ችግር ስለመሆኑ ለመናገር ሌላ ተጨማሪ ድፍረት የሚጠይቅ አይደለም።
የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ችግር ብናወራው የማያልቅ ሰበዝ መምዘዝ ስለሚሆንብን የተወሰነውን ብቻ ለማየትና ለማሳየት ልሞክር ። ከላይ እንደጠቀስነው አጠቃላይ የሆነው ችግር እንዳለ ሆኖ፤ ታክሲዎች የጉዞውን ርቀት ወይም መስመር ቆራርጠው የሚጭኑበትን ህገወጥ ስራ እንመልከት ።
አሁን አሁን ርቀት ባላቸው የስምሪት መስመሮች በተቀመጠው የስምሪት መመሪያ መሰረት አገልግሎት ማግኘት በቀላሉ የሚታሰብ ፤በተለይም ከመሸ ፈጽሞ የሚሆን አይደለም ።በትንሹ መስመሩ ሁለትና ሦስት ቦታ ይቆራረጣል ፤ በዚህ መንገድ የመንገዱ ህጋዊ የጉዞ ክፍያ ከሁለት እጥፍ የማይተናነስ ይሆናል።
የትራንስፖርት ቢሮው ሥራውን በመንግስት የስራ ሰአት ጨርሻለሁ ብሎ ነገረ አለሙን እንዳወጣ ያውጣው ብሎ በሩን የዘጋ እስኪመስል ፤ ዘርፉ በየቦታው በአብዛኛው በማህበር ስም በተደራጁ ሳንቲም ከመልቀም ያለፈ ሀላፊነት በማይሰማቸው የታክሲ ሰልፍ ተቆጣጣሪዎች እንዲሁም የታክሲ ሾፌሮችና ረዳቶች ሰጥተው ለእይታ እንኳን የሚናፈቁበት ሁኔታ ይፈጠራል ።
በዚህ ሂደት ውስጥ ስለ ህጋዊ መብታችሁ ለመጠየቅ ከሞከራችሁ ሊያመናጭቋችሁ ፤ ከዛም የባሰ አፋቸውን የፈቱበት የሚመስለውን እና በጽሁፍ የማልጠቅሰውን አጸያፍ ስድብ የሚሳደቡም አይጠፉም። ለድብደባ እጃቸውንም የሚሰነዝሩ እንደሚያጋጥሟችሁ አትጠራጠሩ።
በቅርቡ ታክሲ ስሳፈር ያጋጠመኝን እንደ አንድ ተጨባጭ ማሳያ ላቅርበው ። ከአራዳ ጊዮርጊስ ወደ አውቶቡስ ተራ ወረፋ ጠብቄ ከቀኑ 11 ሰዓት ተኩል አካባቢ ተሳፈርኩ ። በኪሴ ውስጥ ድፍን ሃምሳ እና አስር ብር ይዣለሁ ። የትራንስፖርት ክፍያው ሦስት ብር ነው። ድፍን አስር ብር ለረዳቱ ሰጠሁት። (በነገራችን ላይ አጭር ርቀት ክፍያ ማለትም 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ከጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ትራንስፖርት ቢሮ ባወጣው የዋጋ ማሻሻያ ክፍያ 4 ብር ሆኗል።) አምስት ብር ሰጠኝ።
መልስ ይቀረኛል ብዬ መልሴን እንዲሰጠኝ ጠየኩት፤ ረዳቱ ምንድነው የምትለው? በሚል እያመናጨቀ ጠየቀኝ፤ መልስ እንደሚቀረኝ ነገርኩት። ‹‹ድፍን አስር አምጥተህ ታዲያ ምን ላርግህ ? ›› አለኝ። ‹‹ምንድነው የምትለው? ›› ስለው ‹‹ እናትህ …››የሚለውን ከአፋቸው የማይጠፋውን ስድብ አከለልኝ።
አውቶቡስ ተራ እንደወረድኩ ተናድጄ ስለነበር ተጋጨኹት። አንድ ሁለቴ እንደመታሁት ሹፌሩም በተራው ሊመታኝ መጣ። ወዲያው ፖሊሶች መጡ፤ አንደኛው ተስማሙ አለ።ሌላኛው ፖሊስ ገና እንዳስረዳሁት ረዳቱን ገጨት አደረገውና አስር ብር መልስለት ብሎ፤ አስር ብር አሰጠኝ። ቀደም ብሎ የሰጠኝም 5 ብር ስለነበር ቢሰድበኝም በነፃ እንዳሳፈረኝ ቆጥሬ ወደምሄድበት ሄድኩኝ።
የታክሲ አሽከርካሪዎች የህዝቡን የትራንስፖርት እንግልቱን እንደ ሠርግና ምላሽ የሚጠብቁት እና የሚናፍቁት ይመስለኛል ። ታሪፍ ለመጨመር ምቹ አጋጣሚ ይሆንላቸዋል። ቀን ቀን ረጅም ሰዓት ተሸከርካሪዎቻቸውን በየመንደሩ አቁመው የሚቅሙ ጥቂት አይደሉም ። ቀን በመቃምና በመቀምቀም ያጠፉትን የሥራ ሰዓት የሚክሱት፤ ለሱሳቸው ያባከኑትን ገንዘብ የሚመልሱት ፤በምሽት ሰው በሚበዛበት ሰዓት ታሪፍ ጨምረው ያለ ልክ ጭነው በማሽከርከር ነው።
የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግር ጎልቶ የሚታየው ማለዳ ላይና አመሻሽ ላይ ነው። ምሳ ሰዓት ላይም በተለይ ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ስምንት ሰዓት ድረስ አገልግሎት የማይሰጡት የአንበሳ እና የሸገር ትራንስፖርት ተሸከርካሪዎች ማየት የተለመደ እየሆነ ነው። ሰው በምሳ ሰዓቱ ከሥራ ቦታው ቅርብ ርቀት ሄዶ የሚመለስበት ጉዳይ ቢኖረው አልያም ወደ አንድ የመንግሥት ተቋም ለመሄድ ቢፈልግና አንበሳ አውቶቡስ መጠቀም ቢፈልግ ከላይ በተጠቀሰው ሰዓት ተሸከርካሪ ለማግኘት ”ሱሪ በአንገት” ይሆንበታል።
እርግጥ ነው ተሸከርካሪዎቹም አገልግሎት ሰጥተው የተወሰነ ሰዓት ማረፍ አለባቸው። አሽከርካሪዎቹና ረዳቶቹ ማለትም ቲኬት ቆራጮቹ ምሳ በልተው እረፍት መውሰድ አለባቸው። መቼም እየደከሙ ቢያሽከረክሩ በራሳቸው፣ እንዲሁም በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ አደጋ ያስከትላሉ። ሳያርፉ ያሽከርክሩም የሚል ዕሳቤ ያለው ሰው የለም። ማረፍ እንዳለባቸው ይታመናል ። ነገር ግን ሕዝብ በሚበዛበት በምሳ ሰዓት አካባቢ ግማሾቹ እየሠሩ ግማሾቹ ቢያርፉ መልካም ነው። ይህን ነገር ለማየት ስታዲ የም፣ መገናኛ፣ አሜሪካ ግቢ እና መርካቶ ዋና የአንበሳ አውቶቡስ ተራ በመሄድ መታዘብ ይቻላል።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም