የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለ11ኛ ጊዜ ነገ በአሰላ ይጀመራል፡፡ እድሜን በሚመለከትም ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠበት ውድድር መሆኑንም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሆናቸው ወጣት አትሌቶች ብቻ የሚካፈሉበት ይህ ቻምፒዮና ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ በአሰላ ከተማ አረንጓዴው ስታዲየም ይካሄዳል፡፡ ከነገ አንስቶ ለስድስት ቀናት በሚካሄደው በዚህ ውድድር ተተኪዎችን ለማግኘት እንደሚረዳም ተስፋ ተደርጎበታል። በውድድሩ ላይ 7 ክልሎች፣ 1 ከተማ አስተዳደር፣ 24 ክለቦችና ተቋማት 606 ወንዶችና 444 ሴት አትሌቶች በድምሩ 1 ሺ50 አትሌቶች የሚሳተፉበት መሆኑን የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።
በዚህና በመሰል የዕድሜ ገደብ ያለባቸው ውድድሮች ላይ በስፋት የሚታየው ዋነኛው ችግር ከዕድሜ በላይ የሆኑ አትሌቶችን ማሳተፍ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም የተነሳ ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብ የሚስተዋል ሲሆን፤ በዚህ ውድድር ግን ፌዴሬሽኑ ዕድሜ ላይ በከፍተኛ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በዚህም መሰረት ዕድሜያቸው 20 እና ከዚያ በላይ የሆናቸውን አትሌቶች ማሳተፍ ከፍተኛ የአትሌቲክስ ሕግ ጥሰት ስለሚሆን የትኛውም አሳታፊ አካል በእድሜ ተገቢነት ዙሪያ ከፍተኛ ትኩረት አድርጎ መቅረብ ይገባዋል፡፡ ፌዴሬሽኑ አፋር ሰመራ ላይ ባካሄደው 26ኛው ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በዚሁ ጉዳይ ላይ መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን፤ ፌዴሬሽኑም በዚህ ረገድ ቁርጠኛ አቋም ይዞ አስፈላጊ እርምጃ እንደሚወስድ ተጠቁሟል።
የውድድሩ ዓላማም የውድድር ዕድሎችን በማስፋት ወጣትና ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ክለቦችና የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ተቋማት የሥልጠናና የውድድር አቅማቸውን እንዲሁም የሠልጣኞቻቸውን አቋም ለመለካት እንደሚያግዛቸው በማሰብ የሚካሄድ ቻምፒዮና ነው፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም