የዓለም አትሌቲክስ ከሚያዘጋጃቸው ዓመታዊ የዙር ውድድሮች መካከል አንዱ የቤት ውስጥ የቱር ውድድር ነው:: ይህ ለሁለት ወራት የሚካሄድ ውድድር ትኩረቱን በመም እና በሜዳ ላይ ተግባራት ያደረገ ሲሆን፤ በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የፈረንጆች ወር አንስቶ መደረጉን ቀጥሏል:: የወርቅ፣ የብር እና የነሃስ ደረጃ በተሰጣቸው በእነዚህ የዙር ውድድሮች ላይም በርካታ አትሌቶች ተሳታፊ ይሆናሉ:: እአአ ከ2016 ጀምሮ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ውድድሩ እንደ ዳይመንድ ሊግ በዙር በማካሄድ የቤት ውስጥ የመምና የሜዳ ተግባራትን ለማጠናከር ታስቦ የሚደረግ ነው::
በመርሃ ግብሩ መሰረትም ከሁለት ሳምንታት በኋላ በፈረንሳይ ሌቪን በተለያዩ ርቀቶች ውድድሮች ይካሄዳሉ:: በዚህ ውድድር ላይም ተሳታፊ ከሚሆኑ አትሌቶች መካከል ኢትዮጵያውያን ውጤታማ አትሌቶች የሚገኙበት ሲሆን፤ በስፍራው የደመቀ ታሪክ ያላት የዓለም የ5ሺ ሜትር ቻምፒዮኗ ጉዳፍ ጸጋይ ናት:: አትሌቷ በአንድ ማይል እና 1 ሺ500 ሜትር ተሳትፎዋን በአሸናፊነት ስትፈጽም፤ በ1 ሺ500 ሜትር ከሁለት ዓመት በፊት ያስመዘገበችው 3:53.09 የሆነ ሰዓት የዓለም ክብረወሰን በመባል ተመዝግቦላታል::
ጉዳፍ ዘንድሮም በዚህ ርቀት ሌቪን ላይ እንደምትሳተፍ የዓለም አትሌቲክስ በድረገጹ አስፍሯል:: በኦሪገኑ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በክብር ላይ ክብርን በመደረብ አስደናቂ ውጤት ያስመዘገበችው ጉዳፍ በዚህ ውድድር ላይ ያለፈውን ዓመት ጣፋጭ ድል ለመድገም አልማለች:: የ26 ዓመቷ ወጣት አትሌት ያለፈውን ዓመት በስኬት ያሳለፈች ሲሆን፤ በቤልግሬዱ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በምትታወቅበት 1 ሺ500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት መሆኗ ይታወሳል::
ከወራት ልዩነት በኋላም በ18ኛው የኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተሳትፎዋ በ5ሺ ሜትር የወርቅ እንዲሁም በ1 ሺ 500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ ከሁሉም የላቀውን ድሏን ማጣጣሟ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው:: አትሌቷ ከአንድ ዓመት በፊት በጃፓኗ ቶኪዮ በተከናወነው ኦሊምፒክ እንዲሁም እአአ በ2019 ዶሃ ባዘጋጀችው የዓለም ቻምፒዮና በዚሁ ርቀት የነሃስ ሜዳሊያ ለሀገሯ ማስገኘት ችላ ነበር::
ጉዳፍ በምትታወቅበት መካከለኛ ርቀት ያላት ፈጣን ሰዓት 3 ደቂቃ ከ54 ደቂቃ ከ01 ሰከንድ ሲሆን፤ በቤት ውስጥ ቻምፒዮና ደግሞ በአንድ ደቂቃ ፈጥና በመግባት የዓለምን ክብረወሰን በእጇ ለማስገባት ችላለች:: ሌቪን ላይ ከሚሳተፉ በርካታ የዓለምና የኦሊምፒክ ቻምፒዮን አትሌቶች መካከል የራሷን ሰዓት በማሻሻል አስደናቂ ውጤት ታመጣለች በሚል ከወዲሁ የምትጠበቅ ሆናለች::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም