ጥምቀት መጣ፣ ጥምቀት ጻዳ፣
ለሀገር ባህል፣ ባገር ምንዳ፣
ከሞላበት፣ ከውበት ጓዳ፣
እንገናኝ፣ ሽሮ ሜዳ።
የጥምቀት በዓል መጣሁ መጣሁ ሲል በበዓሉ አምሮና ተውቦ መታየት የሚፈልግ ሁሉ ሃሳቡ ወደ ሽሮሜዳ ይነጉዳል። ምክንያቱም እዛ ሁሉም አለ። ሽሮ ሜዳም ‘ምን አጥቼ፣ ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ ኑ! ሁላችሁም በሀገር ባህል ልብሶቼ ተዋቡ፣ አጊጡ፣ ዘንጡ’ ትላለች:: ሽሮ ሜዳ አፍ አውጥታ ባትናገርም ከጫፍ ጫፍ ያለው ድባቧ ይህንኑ ያረጋግጣል። ሽሮ ሜዳና ጥምቀት በአዲስ አበቤው ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያውያንና በውጭ ጎብኚዎች ጭምር አንዳች ቁርኝት አላቸው:: በጥምቀት ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም ሽሮ ሜዳ ላይ መገናኘታቸው አይቀሬ ነው።
በዘንድሮው የጥምቀት በዓል ሽሮ ሜዳ እንዴት ሰነበተች? በባህል አልባሳት ፋሽኖች ምንስ አዳዲስ ነገሮችን ይዛ መጣች? ስንል ዞር ዞር እያልን ድባቧን ቃኘት አድርገናል። ከወትሮ በተለየ ሽሮ ሜዳ ከሰሞነኛው የጥምቀት በዓል ሌላ ሆናለች። ወዲያ ወዲህ እየተራወጠ አልባሳት ለመግዛትና ለመሸጥ ሽር ጉድ ከሚለው ገዢና ሻጭ በስተጀርባ ነጥሎ እሷነቷን ማየት ለቻለ ሰው ሽሮ ሜዳ በልዩ ልዩ ቀለማትና አልባሳት አምራና ተሞሽራ ንጉሷን የምትጠበቅ ንግስት መስላለች። በሽሮ ሜዳ ላይ ያበቡ አበቦች በጃን ሜዳ ይፈካሉና የውበት ጓዳ የሆነችው ሽሮ ሜዳ በከተራና ጥምቀቱ እንዲሁም የሰርግ ዝግጅቶች በሚበዙባት በወርሃ ጥር የተንቆጠቆጠች አበባ መስላ ሁሉንም እንደምርጫው ለማስተናገድ መሰናዳተ በጉልህ ይታያል።
እኛም በቅኝታችን መሃል የባህል አልባሳትን ለመግዛት በተለያዩ ፋሽንና ዲዛይኖች ላይ አይናቸውን ተክለው ከነበሩት መሃል ጠጋ ብለን የሽሮ ሜዳን የጥምቀት ግብይትና ዝግጅት ምን ይመስላል ስንል ጠየቅናቸው። “ በጣም ሞቅ ደመቅ ብላለች” አለች ከደራው ግርግር መሃል ከጓደኛዋ ጋር ቆማ ለጥምቀት የሚሆናትን ልብስ ስትመራርጥ ያገኘናት መቅደስ፤
ከወከባና ትርምሱ ይልቅ አልባሳቱ አይን ስለማያስነቅሉ አይኑን ከአልባሳቱ ተክሎ ሲተላለፍ እርስ በእርሱ የሚጋጭም ሞልቷል። ማየት እንጂ መርጦ ማየት የሚባል ነገር የለም። ቀጠለች መቅደስ “ከጓደኛዬ ጋር ለበዓል የሚሆነንን ልብስ ለመግዛት የመጣነው ሰባት ሰዓት ላይ ነበር ግን አይን አዋጅ ሆኖብን ይሄው እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ እዚሁ ነን፣ በጣም የሚገራርሙ አዳዲስ ፋሽኖች ጭምር አሉ።” ታዲያ እነዚህ ፋሽኖች ነባሩን ኢትዮጵያዊ ባህል ከማንጸባረቅ አንጻር እንዴት አየሻቸው? ቀጣዩ ጥያቄያችን ነበር፣ “እኔም የባህል ልብሶች አድናቂ ስለሆንኩኝ አልባሳቱን እንድወዳቸው ያደረገኝ ዋነኛ ምክንያትም የባህል እሴታችንን የጠበቁና ኢትዮጵያዊነትን የሚያንጸባርቁ በመሆናቸው ነው።” በማለት ምላሽዋን ሰጠችን።
ከአንደኛው የባህል አልባሳት መሸጫ ሱቅ በር ላይ ከላይ እስከታች በሀበሻ ልብስ ዝንጥ ብሎ የፋሽን ትርኢት በሚመስል መልኩ አብረውት ለነበሩት ጓደኞቹ እየዞረ ሲያስቃኝ የነበረው ወጣት ቀልባችንን ሳበውና ጠጋ ብለን ልናነጋግረው ፈለግን። “አማኑኤል በላይ እባላለሁ ከሳምንት በፊት ያዘዝኩትን ጃኖ ለመውሰድ መጥቼ እየለካሁት ነበርና ይሄው እንደምታየው ዛሬ እንዲህ አምሮብኛል።” ሲልም ሃሳቡን አካፈለን:: ከዋጋው አንጻርስ የአልባሳቱ ሁኔታ እንዴት ነው? ብለን የጠየቅነው ወጣት “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ አይደል የሚባለው… በጊዜው ብር ስላነበረኝ ከሶስቱ ጓደኞቼ ተበድሬ ነበር ያሰራሁት ያው ለጥምቀት ያልሆነ ብድር….››። አማኑኤል ልብሱን በአዲስ ዲዛይን እራሱ መርጦ ያሰራው በመሆኑ ዋጋውም ቢሆን ያን ያህል ውድ የሚባል እንዳልሆነ ነግሮናል::
አማኑኤልና ጓደኞቹን አልፈን ወደሱቅ ዘልቀን ገባን‹‹ ክፍሏ ከአቅሟ በላይ ሰው ታጭቆባታል:: አንዳንዱ ለመግዛት ዋጋ ይደራደራል፣ ሌላው ይለካል፣ ከፊሉ ቆሞ በአይኑ ይቃኛል:: ከየጥጉ ደግሞ የአልባሳት ጠበብት ባለሙያዎች በስራ ላይ ተጠምደዋል። ከዚህ ሁሉ ግርግር መሃል እንደምንም ተጋፍተን ጥያቄያችንን ለባለሙያዎቹ አቀረብን:: ከባለሙያዎቹ መካከል ያነጋገርነው ዘሪሁን “እስከዛሬ ለአምስት ዓመታት ያህል ለጥምቀት በዓል የሚሆን ልብስ ስሰፋ ኖሬያለሁ፣ እንደዚህ ሱሪ በአንገት ሆኖብኝ ግን አያውቅም። ጥምቀትን ይዛ የምትመጣው የጥር ወር ደግሞ በሀገራችን በብዛት የሰርግና ልዩ ልዩ ዝግጅቶች የሚበዙበት ወቅት በመሆኑ የአልባሳት ስራው ለጥምቀት እለት ብቻ ሳይሆን በጥምቀት ማግስትም እንደደራ ይቀጥላል። ድሮ የነበሩት የባህል አልባሳት በውጭ ፋሽኖች እየተወረሩ ቢመጡም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን መልሰው እያንሰራሩና ተፈላጊነታቸውም እየጨመረ መጥቷል። ወደፊትም ሙሉ ለሙሉ ወደባህላዊ አልባሳቶቻችን እንደምንመለስ ተስፋ አለኝ” በማለት አስተያየቱን ሰጥቶናል::
በጥምቀት መንፈሳዊና ባህላዊ ክዋኔዎቹ እንዳሉ ሆነው የጥምቀት በዓልን ልዩ ያደረገውና የዓለም ሕዝብ ሁሉ እንዲወደው፣ ብሎም በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ላይ ለመስፈሩ ምክንያት ባህላዊ አልባሳቶቻችን የተጫወቱት ሚና እጅግ በጣም ትልቅ ነው። የኢትዮጵያን ባህላዊ አልባሳት ባህላዊ ይዘታቸውን ጠብቀው ከዘመኑ ጋር በሚሄድ መልኩ ለማዘመንም የጥምቀት በዓል ትልቅ እድልን ፈጥራል። በዘርፉ ላሉት ባለሙያዎችም ስራቸውን ከአደባባይ አልፎ ለዓለም ለማሳያት ከዚህ የተሻለ ምንም መንገድ አይኖርም። ጥምቀት ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብሮችን በአንድነት አጣምሮ የያዘ ዘርፈ ብዙ በዓል እንደመሆኑ ኋላ በእጅ ያለ ወርቅ ሆኖብን ይህን ውብ ባህል ችላ እንዳንል፣ በተሻለ መንገድ ልንጠብቅና ልናስተዋውቅ እንዲሁም ልናስቀጥለው የግድ ይለናል። በዚህ ሁሉ ግን ልዩ ትኩረት ለባህል አልባሳትና ለተዋቡ የባለሙያ እጆች እንላለን!
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም