መቼም አዲስ አበባ ላይ የቤት አከራይና ታክሲዎች በሕዝብ ላይ ያላቸውን ስልጣን ያህል መንግስት ያለው አይመስለኝም። ተከራይ በህግ ያለው መብት ምንም ይሁን ምን አከራይ ካለ አለ ነው። ታክሲም ላይ እንደዚያው። መንግስት የተከራይን መብት ለማስጠበቅ የቱንም ህግ ቢደነግግ የሚሰራው አከራይ በራሱ የሚያወጣው ያልተፃፈ ህግ ስለመሆኑን ለማንም የተደበቀ አይደለም።
ለዛሬ ትዝብቴ መነሻ የሆነኝን የአከራይና ተከራይ ህግ ዙሪያ ሰሞኑን የገጠመኝን ላውጋችሁ። ኮንዶሚኒየም ተከራይቶ የሚኖር አንድ ለህግ ቅርብ የሆነ ጓደኛዬ ቤት ሊቀይር መሆኑን ነገረኝ፣ እኔም ምነው አሁን ያለህበት አልተመቸህም? ስል ጠየኩት። የሰጠኝ ምላሽ ግን ፈጽሞ አንድ ለህግ ቅርብ ከሆነ ሰው ያልጠበኩት ነበር። “በአንድ ጊዜ ሶስት ሺ ብር ጨምር ወይ ልቀቅ ተባልኩ” ነበር ያለኝ። እንዴ መንግስት የትኛውም አከራይ በተከራይ ላይ እንዳይጨምር ለስድስት ወራት የሚቆይ ህግ ተሻረ እንዴ? ብዬ ጠየኩት። መልሱ አጭር ነበር፣ “አከራይ ካለ አለ ነው፣ በገዛ ቤቱ የፈለገውን ቢያደርግ ለማነው አቤት የሚባለው፣ ምንስ ላመጣ” የሚል ነበር።
ይሄ የአንድ ሰው ብቻ ችግር አይደለም፣ እኔን ጨምሮ የሁሉም አዲስ አበቤ ተከራዮች ፈተና ተመሳሳይ ነው። ፈተናው ብቻም ሳይሆን ተከራዮች ያለንን መብት በማስጠበቅ ረገድ ተመሳሳይ ነን። አከራይ ጭማሪ እንዳያደርግ የወጣ ህግ ቢኖርም ተከራይ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ይህን መብት ለማስጠበቅ ከመታገል ይልቅ የተባለውን ለመቀበል ዝግጁ ነው። አንዳንዱ የተባለውን የሚቀበለው መብቱን ለማስጠበቅ ህግ ቦታ ቢሄድም ‹‹ምንም አልፈጥርም›› ከሚል ጥርጣሬ ነው። የህግ ሂደቱ ውጣውረድ የበዛበትና ምንም የማያመጣ ከሆነ ደግሞ ትርፉ ከአከራይ ጋር መበሻሸቅ ብቻ ይሆናል ማለት ነው። ‹‹ልትከሰን ነበር›› በሚል የበለጠ በክፉ አይን ያዩኛል ብሎ ይፈራል፤ በተለይም ልጆች ላለው ሰው ደግሞ አስቸጋሪ ነው። ሌላው ደግሞ ህግ ቦታ ሄዶ መብቱን ለማስጠበቅ ከሚገጥመው ውጣ ውረድ ይልቅ መብቴ ቢጣስ የተሻለ ነው ብሎ ስለሚያስብ ነው። አንዳንዱ ደግሞ በስንፍናም ነው።
ከዚሁ ከአከራይ ተከራይ መብት ጋር በተያያዘ ህጉ ምን ያህል ተፈጻሚ ይሆናል የሚለው ጥያቄ ሌላ ጉዳይ ነው። ይህን ለማረጋገጥ መጀመሪያ ወደ ህግ ቦታ መሄድ ይቀድማል። ገና ለገና መብቴን ለማስጠበቅ ወደ ህግ ብሄድም ምንም አላመጣም ብሎ ማሰብ የራስን ድክመት ወይም ስንፍና ያጎላል እንጂ ህጉ ተፈፃሚነት ላይ ያለውን ክፍተት ሊያሳይ አይችልም። በእርግጥ እዚህ ጋር በህግ አስፈፃሚዎች በኩል ክፍተት የለም ማለት አይደለም። በተመሳሳይ ጉዳይ መብታቸውን ለማስጠበቅ ወደ ህግ የሄዱ ሰዎች በህግ አስፈፃሚዎች በኩል ተደራደሩ ወይም ተስማሙ ከማለት ውጭ ፍትህ እንደማያገኙ ይናገራሉ። እነዚህ ሰዎች ፍትህ አላገኙምና እኔም ምንም አልፈጥርም ማለት ግን አይደለም። አንዳንድ ቸልተኛ የህግ አስፈፃሚዎች እንዲህ አይነት ክፍተቶችን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ሁሉ የህዝብን መብት ለማስጠበቅ እስከ ጥግ ድረስ የሚጓዙ እንዳሉ ግን መካድ አይቻልም።
ከዚሁ ከአከራይ ተከራይ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወትሮም አንድ ችግር አለ። አንድ አከራይ ተከራዩን ቤቴን ልቀቅ ማለት መብቱ ነው። ተከራዩ ደግሞ ልቀቅ ተብሎ ሌላ ቤት አፈላልጎ ለማግኘት የሶስት ወር ጊዜ ኪራይ ሳይጨምርበት የመኖር መብት አለው። ግን ይሄን መብት ተከራዩ ሲጠቀምበት አይስተዋልም። በብዛት ወይ ኪራይ ጨምሮ ይቀጥላል ወይ ደግሞ በቻለው ፍጥነት የሶስት ወር ጊዜውን ሳይጠቀም ለቆ ይገላገላል። በዚህ ረገድ አልፎ አልፎ በዜና የምንሰማቸው አንዳንድ ጠንካራ ሰዎች አሉ። ከቤት ኪራይ መብት ጋር ባይያያዝም የመንግስትን አገልግሎት ፈልገው የሆነ ቢሮ ያቀኑ ሰዎች ጉዳያቸው እንዲፈጸም አላግባብ የተጠየቁትን ገንዘብ አንከፍልም በማለት ጉዳዩን ለፖሊስ ጥቆማ ሰጥተው እንዲንገላቱ ያደረጉ ግለሰቦችን እጅ ከፈንጅ ሙስና ሲቀበሉ እንዳስያዙ እንሰማለን።
ይህ ታክሲም ላይ ይሰራል። የቤት ኪራይና ታክሲ የዘወትር የሕዝብ እሮሮ ስለሆኑ ለአብነት ይነሱ እንጂ መንግስት ደንግጓቸው እኛ ግን ያልተጠቀምንባቸው መብቶች ቁጥር ስፍር የላቸውም። ይሄ በህግና በህግ አስፈፃሚው ላይ እምነት የማጣት ጉዳይ ብቻ አይደለም። እንደ ማህበረሰብ መብታችንን እስከ ጥግ ድረስ ሄደን የማስከበር ትልቅ ችግር አለብን። የነቃና የበቃ የሚባለው የከተሜ ነዋሪ ላይ እንዲህ አይነት ችግር ካለ በሌላው በኩል ያለውን መገመት ከባድ አይሆንም።
ብዙ ጊዜ እንደ ማህበረሰብ ጥቃቅን የግለሰብ መብቶቻችንን ለማስጠበቅ ሳይሆን የቡድንና ትልልቅ የፖለቲካ መብቶችን ለማስጠበቅ መጠመዳችንን መካድ አይቻልም። ይህ ለቡድንና ለትልልቅ ፖለቲካዊ መብቶቻችን እንታገል ማለት አይደለም። ግን ጥቃቅኗን የግል መብቶቻችን ለማስከበር ጥረት ካላደረግን እንዴት ለቡድንና ለትልልቁ የፖለቲካ መብት መታገል እንችላለን? የሚለው ነው ዋናው ጥያቄ። መቼም ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርአት የሚገነባው በሂደት መሆኑን ምሁራን ደጋግመው ሲነግሩን ሰምተናል። አገራችን እንዲፈጠር የምንፈልገው ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርአት እንዲህ በግለሰብ ደረጃ ጥቃቅን የሚባሉ መብቶችን በማስከበር ከወዲሁ ካልተጀመረ የነገ መዳረሻችን የት ሊሆን ይችላል? ብለን ማሰብ አለብን።
መብት ማስከበር ለዛሬው ብቻ አይደለም፤ ለነገ ጭምር ነው። የነቃ እና የሰለጠነ፣ በመብት የሚያምን ዜጋና ባህል መፍጠር ስላለብን ነው። ለዛሬው ለአንድ ጉዞ ምናልባትም አንድ ብር ብቻ ሊሆን ይችላል ያልተመለሰልን፤ ዳሩ ግን በየዕለቱ ሽርፍራፊ ብሮችን እናጣለን ማለት ነው። በዓመት ደግሞ ብዙ ይሆናል። ስለዚህ የዕለቱን ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ልማድ መሆኑን ነው ማሰብ ያለብን።
አከራዮች ተከራይ መብት የሌለው አስመስለው የሚያዩት መብት የመጠየቅ ባህል ስላላዳበርን ነው። አንድ እና ሁለት ሰው ብቻ ቢናገራቸው ምንም አያመጣም፤ ግን መብት መጠየቅን ባህል ብናደርገው መጀመሪያውኑም አያስቡትም፤ ከፍሎ የሚኖር ተከራይ እንደ ባሪያ ሊታይ አይችልም።
ስለዚህ ለዛሬው ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም የመሰልጠን መለያ ነውና መብት የመጠየቅ ባህልን እናዳብር!
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 20 ቀን 2015 ዓ.ም