አቶ ታደሰ በላይ የልብ ህመም አጋጥሟቸው የህክምና ክትትል ማድረግ ከጀመሩም አስር ያህል ዓመታትን አሳልፈዋል። አሁን ላይ መድሃኒታቸውን በአግባቡ እየወሰዱና በሃኪም ክትትል እያደረጉ በሙሉ ጤንነት ስራቸውን በመስራት ላይ ቢሆኑም ያኔ የልብ ህመም ሲጀምራቸው ያጋጠማቸውን ነገር ግን መቼም አይዘነጉትም።
‹‹የዛሬ አስር ዓመት አንድ ቀን ጠዋት ከመኝታዬ ተነስቼ ወደ ስራዬ ለመሄድ ስነሳ አንድ የማላውቀው የህመም ስሜት ደጋግሞ አመመኝ፤ በተለይ ደረቴ አካባቢም ከባድ የሆነ ስሜት ተሰማኝና ለቤተሰቦቼ ስነግራቸው ‘አይ ብርድ ሽው ብሎህ ይሆናል’ ብለው በቤት ውስጥ ሊያስታግሱልኝ ሞከሩ›› በማለት አቶ ታደሰ ያስታውሳሉ። ነገር ግን ሁኔታ እየጨመረ ሲመጣ መቋቋም የማይችሉት ስሜት በደረታቸውና በግራ እጃቸው አካባቢ እንደተሰማቸው ይገልፃሉ።
ከዚያ በፊት ከባድ ራስ ምታት እንኳን አሟቸው የማያውቁት አቶ ታደሰ በሆነው ነገር ተደናግጠው ፈጥነው ወደ ሆስፒታል አመሩ፤ በድንገተኛ ገብተው ሲታዩም ችግሩ ከልብ ጋር የተያየዘ ሊሆን እንደሚችል ተነግሯቸው ከፍ ወዳለ ሆስፒታል ተላኩ።
‹‹በድንገተኛ ያየኝ ሀኪም በጣም በመደናገጥ በቶሎ ወደልብ ህክምና መሄድ እንዳለብኝ ነገረኝ፤ ህመሙ በጣም ፍጥነት ያለው በመሆኑ በእግሬ ሆስፒታል ገብቼ ወዲያው በተሽከርካሪ ወንበር ታግዤ መሄድ ጀመርኩ። እንደ እድል ሆኖ የሄድኩበት የልብ ህክምና ማዕከል በቶሎ ስለ ችግሬ ለመረዳት ቻሉ›› በማለት ይናገራሉ። በዚህም የልብ ቧንቧቸው በኮሌስትሮል ምክንያት መዘጋቱንና በወቅቱ ደም መዘዋወር እንዳቃተውና በአስቸኳይ ቀዶ ህክምና ተሰርቶላቸው ቱቦው መስፋት እንዳለበት ተነገራቸው።
በፍጥነት ህክምና በማግኘታቸው በአንድ ቀን ከህመማቸው መዳናቸውን የሚናገሩት አቶ ታደሰ ከአራት ቀናት የሆስፒታል ቆይታ በኋላም ቤታቸው መግባታቸውን ያስታውሳሉ። ዛሬ መድሃኒቶቻቸውን በአግባቡ እየወሰዱ በቀጠሯቸው ቀን ሄደው ከሀኪማቸው ምክር እየተቀበሉ በሰላም በጤና ስራቸውን ይሰራሉ።
አቶ ታደሰ እንደሚሉት፤ በየጊዜው የጤና ምርመራ የማድረግ ልምድ ቢኖራቸውም እንዲሁም የኑሮ ዘዬያቸውን ቢያስተካክሉ ኖሮ ለዚህ አይዳረጉም ነበር። ዛሬ ላይ በርካታ ሰዎች የእሳቸውን መሰል ችግር ያጋጥማቸው፤ እድለኛ ያልሆኑትም በተኙበት ቀርተዋል። በመሆኑም ሰዎች በአገሪቱ ከምን ጊዜውም በላይ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እጅግ ስር እየሰደዱ በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማዘውተር፣ ለአመጋገብ ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በትንፋሽ፣ በደም እና በአካል ንክኪ ከሰው ወደ ሰው የማይተላለፉ፣ ስር የሰደዱ ለማዳንም ረዥም ግዜንና ብዙ ገንዘብን የሚጠይቁ ናቸው።
በ 21ኛው ክፍለ ዘመን በዝምታ ብዙዎችን እየገደሉ ያሉ ህመሞች ናቸው። ተላላፊ ያልሆኑ በመባል ከሚታወቁት ህመሞች መካከል ዋነኞቹ የልብ ህመም፣ ካንሰር፣ የመተንፈሻ አካላት ችግር ፣ የደም ግፊትና የስኳር በሽታ ተጠቃሽ ናቸው።
እንደ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) መረጃ በዓለማችን 40 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝብ በየዓመቱ ተላላፊ ባልሆኑ ህመሞች /NCD/ ሕይወቱን ያጣል። 31 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑት በዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የሚገኙ ናቸው። 46 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በ 30 እና በ 69 እድሜ ክልል ውስጥ መሆናቸው የችግሩን አሳሳቢነት ያሳያል።
የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ የ2016 ዓ.ም መረጃ እንደሚያመለክትው፤ 17 ሚሊዮን በልብ ህመም ፣ ዘጠኝ ሚሊዮን በካንሰር፣ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን በመተንፈሻ አካላት ህመም ፣ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በስኳር ሕይወታቸውን አጥተዋል። በኢትዮጵያ በዚሁ ዓመት ብቻ 275 ሺ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ጠቅላላ ሞት ተመዝግቧል። ከዚህ ውስጥ 140 ሺ 600 ወንዶች ሲሆኑ 132 ሺ 400 ደግሞ ሴቶች ናቸው። ከዚህ የሞት ቁጥር ውስጥ የልብ ህመም 16 በመቶ ፣ ካንሰር ህመም 7 በመቶ፣ የመተንፈሻ አካላት ህመም 2 በመቶ ፣ የስኳር ህመም 2 በመቶ እንዲሁም ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች 12 በመቶ የየራሳቸውን ድርሻ ይይዛሉ።
በአሁኑ ወቅት ስኳር ፣ የልብና የደም ቧንቧ ችግር ፣ ግፊት ፣ ካንሰር ፣ ኩላሊትና የአዕምሮ ጤና ችግር አሳሳቢ እየሆኑ መምጣታቸውን ግልጽ ነው። ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለማከም ግን የአንድ ዘርፍ ወይም የጥቂት አካላት ስራ ብቻ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በተለይ በከተሞች አካባቢ እየተረሳ የመጣውን የእግር ጉዞና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያለማድረግ፤ አልኮል፤ ሲጋራ ማጨስ፤ ስኳርና የቅባት ምግቦች በስፋት መመገብ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭት እንዲስፋፋ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል። በአገሪቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለማከምና ለመከላከል የሚያስችል አዲስ ስትራቴጂ ቢዘጋጅም ችግሩን ግን መፍታት አልተቻለም ። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ያለው የተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ግንዛቤ አነስተኛ መሆን ነው።
በተለይም ህብረተሰብ አቀፍ ንቅናቄ መፍጠርና የሕዝቡ የአመጋገብ ዘይቤ እንዲለወጥ፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የዕለት ተዕለት ተግባር እንዲሆንና እንዲዳብር ጭምር በጋራ መስራት ይገባል። ይህንን ማድረግ ከተቻለ ደግሞ የበሽታውን ስርጭት በ50 በመቶ መቀነስ እንደሚቻል የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ ።
በመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ላይ መንግሥት በሙሉ አቅም እየሰራ ቢሆንም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ እንደ ካንሰር ፣ ልብና ስኳር በመሳሰሉ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እየደረሰ ያለው የጤና እና የኢኮኖሚ ጫና እየጨመረ ይገኛል። የጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ጉዳትና ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነት ላይ ሰሞኑን ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክከር አድርጎ ነበር። የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ጥምረት በጋራ ያዘጋጁት ዳሰሳዊ ጥናትም የሚያሳየው ይህንን ነው።
በምክክር መድረኩ ላይ ሃሳባቸውን የሰጡት የህክምና ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው አካላት እንዳሉትም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አሁን ላይ በመጠንም፤ በአይነትም አጅግ እየጨመሩ በመሆኑ ችግሩ ከዚህ ከመባሱ በፊት ከፍተኛ የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ይገባል።
የህብረተሰብ ጤና ባለሙያው ዶክተር ውባዬ ዋለልኝ እንዳሉት፤ ህሙማን የበሽታዎቹን ምልክቶች እንኳን እያዩ በቶሎ ሄደው አይታከሙም። ታካሚዎች ህመም ሲሰማቸው የተለያዩ ምልክቶችን ሲያዩ ወደጤና ተቋም በፍጥነት የማይሄዱበት የተለያዩ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በታካሚዎች በኩል ያለው የእውቀት ማነስ ዋነኛው ነው። ይህ ምናልባትም በባለሙያውና በፖሊሲ አውጪዎች ጭምር የሚስተዋል ነው። የገንዘብ ችግር ፤ የጤና ተቋማት ተደራሽነት አለመኖርና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው።
ታካሚዎች የሚያማቸው ነገር ቢኖር እንኳን በተለይም ከከተማ ወጣ ባሉ አካባቢዎች ላይ ህክምና ተቋም ብሄድም መፍትሔ አላገኝ ይሆናል ብሎ ማሰብም ለተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መባባስ አይነተኛ ምክንያት እየሆነ መምጣቱም ይገልፃሉ። በመሆኑም ህብረተሰቡ በእነዚህ ድምጽ አልባ ገዳይ በሽታዎች ከመጎዳቱ በፊት እንደ አገር ብዙ ስራዎችን መስራት በተለይም ተደራሽነት ላይ ትኩረት አድርጎ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግል ነው ያስገነዘቡት።
እንደእርሳቸው ገለፃ፤ በፍጥነት እየተዛመቱ የመጡትን የማይተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል በተለይም በጤና ኬላዎች አካባቢ እንዲጀመሩ መደረጉ አበረታች ነው። ከዚህም ባሻገር በአሁኑ ወቅት በመጠንም፤ በአይነትም እየጨመሩ ለመጡት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከያ አይነተኛ መንገድ ነው። በተጨማሪም እየሰጠናቸው ካሉ ሌሎች የህክምና አገልግሎቶች ጋር ተቀናጅተው እንዲሰጡ በማድረግ የህክምናው አገልግሎቱ ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል።
በጤና ሚኒስቴር የጤና መድህን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉቀን አርጋው በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቁጥር ከዕለት ወደዕለት በጣም እየጨመረ በመምጣቱ ሕይወታቸውን የሚያጡ ዜጎች ቁጥር በዛው ልክ እያሻቀበ ነው።
በመሆኑም እነዚህን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ባይቻልም ስርጭታቸው ከዚህም እንዳይሰፋና የሚያስከትሉት ጉዳትም እንዳይባባስ ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚገባ ይገልፃሉ። የህብረተሰቡን ግንዛቤ እንዲዳበር የተለያዩ የግንዛቤ ማስፋፊያ ስራዎችን በተጠናከረ መልኩ መስራት እንደሚያስፈልግም ነው ያብራሩት።
የተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መስፋፋትን ከመግታት አኳያ የፋይናንስ ውስንነትን እንዲሁም የተደራሽነትና ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ችግር ላይ በትኩረት መሰራት አለበት። ይህንን ማድረግ ካልተቻለ በሽታዎቹ ጉዳታቸው ከፍተኛና የህክምና ወጪያቸውም ከባድ ነው የሚሆነው። በመሆኑም በተለይም ቅድመ መከላከሉ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራቱ ወሳኝ ነው።
በተለይም የጤና ባለሙያዎች የህብረተሰቡን ግንዛቤ በሚጨምሩ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርገው መስራት ይጠበቅባቸዋል። ይህን መስራት ከተቻለም በችግሩ ተጠቅተው ወደህክምና ተቋም የሚመጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ቁጥር ይቀንሳል። በህክምና አሰጣጡ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችና ክፍተቶችም ያንሳሉ።
‹‹አራቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አስቀድመን ብዙ ወጪ ሳናወጣ ልንከላከላቸው የምንችላቸው ችግሮች ናቸው›› ያሉት ደግሞ ዶክተር አህመድ ረጃ ናቸው። ጤናማ የሆነ አመጋገብ በመከተል ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማድረግ፣ ከልክ ያለፈ ውፍረትን በመቀነስ፣ አልኮል ባለመጠጣት፣ ሲጋራ ባለማጨስ 80 በመቶ የሚሆነውን የበሽታዎቹን መምጫ መንገድ መከላከል እንደሚቻል ይጠቁማሉ።
በተጨማሪም ከፍ ባለ ደረጃ ሕዝቡን በማስተማር የአስተሳሰብን ለውጥ እንዲያመጣ በማድረግ በሽታዎቹም ስር ሰደው ዜጎቻችን እንዳይጨርሱ፤ የአገር ሀብትም እንዳይባክን ማድረግ እንደሚቻልም ነው ዶክተር አህመድ የተናገሩት።
በዓለም ላይ በተለያዩ በሽታዎች ምክንያት ከሚሞቱት ሰዎች መካከል 71 በመቶ የሚሆኑት በተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የተያዙ መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎች ያመለክታሉ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥር 20 ቀን 2015 ዓ.ም