በሰላም ድርድር የተቋጨውና በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተፈጥሮ የነበረው ጦርነት አገሪቱን ብዙ ዋጋ አስከፍሏት አልፏል። ጦርነቱ ያስከፈለንን ውድ ዋጋ ለጊዜው እናቆየውና ከጦርነቱ ሊወሰድ የሚገባ ትምህርት ላይ እናተኩር። ከጦርነቱ ሦስት ቁልፍ ትምህርቶች ሊገኝ ይችላል ብዬ አስባለሁ። አንደኛው ኢትዮጵያ ከሚታሰበው በላይ ጠንካራ እና ችግሮችን ተቋቁማ መሻገር የምትችል አገር መሆኗን ነው። ኢትዮጵያ ብዙ ተግዳሮቶችን ተቋቁማ የመሻገር አቅም ያላት አገር መሆኗ ከመቼውም አጋጣሚ በላይ ለወዳጅም ለጠላትም ግልጽ የሆነበት ነው። ብዙዎች አገሪቱ ከአውዳሚው ጦርነት በኋላ አንድነቷ ተጠብቆ የመዝለቅ ዕድል አይኖራትም በሚል ስጋታቸውን ሲገልጹ ነበር። የአንዳንዶቹ ስጋት ከቅን ልቦና የመነጨ ሲሆን የአንዳንዶቹ ግን ፖለቲካ የተጫነው ምኞት ነበር። የሆነው ሆኖ የአገሪቷን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመገመት የተቸገሩ በርካቶች ነበሩ። አገሪቱ ከነበረችበት ሁኔታ አንጻር እንዲህ ዓይነት ግምቶች መኖራቸው የሚደንቅ አይደለም።
አገሪቱ ችግሮችን የመቋቋም አቅም ባይኖራት በአገሪቱ ላይ በስውር እና በግልጽ ተከፍቶባት የነበረውን መደበኛ ጦርነት፣ የሀሰት መረጃ ስርጭት እንዲሁም የኢኮኖሚ ጫና፤ ተቋቁማ ልትሻገር ባልቻለች ነበር። ይህ የአገሪቱ ችግሮችን ተቋቁሞ የመሻገር አቅም በቀላሉ የተገኘ አይደለም። ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በደስታና በኀዘን የገነቡት በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ማህበራዊ መስተጋብሮች እና በኢኮኖሚያዊ ትስስሮች ውጤት እንጂ።
ሁለተኛው ኢትዮጵያ ሁልጊዜም በዋናነት የምትፈተነው እና የምትሞከረው በውስጣዊ ፈተናዎች መሆኑን ትምህርት ሊወሰድ ይገባል። ውስጣዊ ችግሮች በአግባቡ መፍትሄ ሳያገኝ ሲቀር የአገሪቱ ተጋላጭነት ከፍ እንደሚል ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የቡድኖች እና ጥቅሞች በአገረ መንግሥቱ ወይም በሌሎች ቡድኖች የተያዘበትን መንገድ በጥርጣሬ ዓይን መመልከት ሲጀምሩ አገሪቱ ለግጭት ብሎም ለእርስ በርስ ጦርነት ተጋላጭ ልትሆን እንደምትችል በታሪክ ተደጋግሞ ታይቷል።
በንጉሡ እና በደርግ ዘመን የቡድኖች በተለይም ከብሔሮች መብት ጋር ተያይዞ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ አለማግኘታቸው በብሔር የተደራጁ ኃይሎች ሕዝቡን ማታገያ ምክንያት እንዲያገኙ፣ ብሔር እንደ መሣሪያ የተጠቀሙ ቡድኖች መንግሥትን ገርስሰው የራሳቸውን መንግሥት እስከ መመስረት የደረሰ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል። በወቅቱ እነዚህን ቡድኖች ማታገያ ማሳጣት ቢቻል ዛሬ ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ላትገኝ ትችል ነበር። በተመሳሳይ በ2010 ዓ.ም ሪፎርም የተካሄደው ለውጥ በኢትዮጵያ ታሪክ መሠረታዊ ለውጥ ቢያመጣም ለውጡን በሙሉ ልቡ ያልተቀበሉ ቡድኖች ለውጡ መጣብኝ በሚል ስሜት ውስጥ በመግባቱ አገሪቱ በብረቱ እንደትፈተንና ውድ ዋጋ እንድትከፍል አስገድዷታል።
ስለሆነም በቀጣይ አገሪቱ የሚያጋጥማትን መሰል ተግዳሮቶችን ለመከላከል በቡድኖች ውስጥ የሚፈጠረውን ጥርጣሬ ለማስወገድ የሚችል ዴሞክራሲያዊ መርህና ተግባር ላይ የተመሠረተ ሥርዓት ለመገንባት መትጋት ያስፈልጋል። የሕግ የበላይነት፣ ግልጽነትን እና ተጠያቂነት የመሳሰሉ የዴሞክራሲ መርሆዎች ላይ የተመሠረተ ሥርዓት መመስረት ከተቻለ የቡድኔ መብት አልተከበረም ብሎ የሚያስብ ኃይል የሰላማዊ ትግል አማራጭን እንዲመርጥ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ብሎም የቡድኔ መብት ሊነካብኝ ነው በሚል ምክንያት ማህበራዊ መሠረቱ ለጥፋት የሚያነሳሳ እና ነፍጥ አንግቦ ጫካ የሚወርድ ኃይል እንዳይኖር መንገድ ይዘጋል። በአሁኑ ወቅት የሕግ የበላይነት፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት የሰፈነበት ሥርዓት ለመገንባት መንግሥት የሚያደርገው ጥረት መጠናከር አለበት። የሕግ የበላይነት፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት ላይ መሠረቷን የጣለች አገር መገንባት መቻል አገሪቱ ከዚህ በፊት ያጋጠማት ዓይነት አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል መፍትሄ ሊሆን ይችላል።
በሦስተኛ ደረጃ ወጣት ኢትዮጵያውያንን የአገራቸው ራዕይ ተጋሪ እና ባለቤት ማድረግ ያስፈልጋል። አገራችን በአንድ በኩል የአኩሪ ታሪኮች ባለቤት ናት። በሌላ በኩል የአገሪቱ ታሪክ በበርካታ ፈታኝ እና አከራካሪ ክስተቶችም የተሞላ ነው። ለዚህም የአገሪቱን ታሪክ ከጥላቻ አራማጆች ነፃ መውጣትና በጋራ ጉዳዮች ላይ ማተኮር አለበት። ታሪክን የሚያጣምሙ እና ለማግለል ጥረት የሚያደርጉት አካላት ራሳቸው ገሸሽ መደረግ አለባቸው። የውድቀት ታሪክን ብቻ እያስታወሱ ማላዘንና ቂም እየፈጠሩ ሕዝብን ማጋጨትም ሊቆም ይገባል። በሌላ በኩል በአንጸባራቂ ታሪክ ብቻ ወደ ፊት በማምጣት ትውልዱ የታሪክ እስረኛ እንዲሆንና ዛሬ ላይ ጠንክሮ እንዳይሰራ ማድረግም ተገቢ አይደለም። የውድቀት ታሪክን ብቻ ማጉላትም ሆነ የስኬት ታሪኮችን ብቻ እየመረጡ ማዜም ፋይዳው እምብዛም ነው። ከድክመት መማር እና ጠንካራውን ማስቀጠል ይገባል። ወጣቱ ትውልድ ያለፈው ትውልድ ያበላሻቸውን ነገሮች ማስተካከል እና ያለፈው ትውልድ ያሳካቸው ስኬቶች ትሩፋቶች ላይ ሊኮራ ይገባል። ያለፈው ትውልድ ያበላሻቸውን እያስተካከሉ እና ያሳካቸው ስኬቶች ላይ እየኮሩ በዚያ ላይ ተጨማሪ ታሪኮችን እየሠሩ መሄድ ካልቻሉ ወቅታዊውን እና የወደፊት ፈተናዎችን እየተሻገረች የምትቀጥል አገር በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት አዳጋች ይሆናል። ስለሆነም በስኬቶቻችን ኮራ ብለንና ሌሎች አሁናዊ ስኬቶችን ጨምረንባቸው እንዲሁም ካለፉ ህጸጾቻን ተምረን አገራችንን በብልጽግና መንገድ ማራመድ ይጠበቅብናል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ጥር 20 ቀን 2015 ዓ.ም