ሀገራዊ ሰላማችን በአዋሽ ወንዝ ተምሳሌታዊነት፤
ወንዝና ሰላምን ምን ያገናኘዋል? ምንም። ይሁን እንጂ፡- “ነገርን በለዛው፤ ጥሬን በለዛዛው” እንዲሉ ኮምጠጥና ጠነን ያሉ ርዕሰ ጉዳዮችን በምሳሌ ማዋዣ ለማፍታታት መሞከር፤ በአንባቢውም ሆነ በአድማጩ ልቦና ውስጥ መልእክቱ የመሰንበት አቅም ስለሚኖረው በዚህ ጽሑፍ ውስጥ አዋሽ ወንዝ ለሀገራችን ሰላም በተለዋጭ ዘይቤነት አገልግሎት ላይ እንዲውል መልካም መስሎ ታይቶናል።
እንቀጥል፡- አዋሽ ወንዛችን እንደ ተወዳጁ ደራሲያችን እንደ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን አገላለጽ ከምድረ መጫ ማህፀን ተፀንሶ ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዞ በአፋር በረሃ አሸዋ ውስጥ ቀስ በቀስ እየሰረገ በመግባት ህልውናው እስኪያከትም ድረስ በጉዞ ሂደት በርካታ ትዕይንቶች ይከወኑበታል።
ይሄው “ሆደ ባሻ” የአዋሽ ወንዛችን የጉዞ ዝግመቱ ሌጣና ልሙጥ አይደልም። አንዳንድ ቦታ መንገደኞች በእግር ይሻገሩታል፣ ዝቅ እያለ ሲሄድ ወርድና ጥልቀቱ እየሰፋና እየተለጠጠ ይዘረጋና አይደፈሬ ይሆናል:: በክረምት ወራት ደግሞ እየፎገላ ከእኔ ወዲያ ለአሳር በማለት በፈረሰኛ ውኃው ግሳንግሱን አግበስብሶ እያንኳተተ የደረሰ እርሻ ያጠፋል፤ የአዳም ልጆችን አፈናቅሎ ያስለቅሳል። በበጋ ወቅት ደግሞ እንደ ተከፋ መንገደኛ ወይንም ስካሩ እንዳሳቀቀው ጠጭ አንገቱን ደፍቶና ዘልሶ በፀፀትና በአርምሞ ድምጹ ኮሽ ሳይል ጉዞውን ይቀጥላል።
አዋሽ በዚህን መሰሉ የጉዞው ምዕራፎች ላይ ለተለያዩ ጉዳዮች አገልግሎት ላይ መዋሉም አይዘነጋም። በአንዳንድ አካባቢዎች ብርቱና ታታሪ የአካባቢው ነዋሪዎች ጠልፈውና ቦይ ሰርተው ለፈለጉት የልማት ጉዳይ ያስገብሩታል። በአንዳንድ አካባቢዎች ለከብቶች የውኃ ስንቅ ሆኖ ያገለግላል። በአንዳንድ አካባቢዎች ታዳጊ ልጆች ይንቦጫረቁበታል ወይንም ይዋኙበታል።
በሌላ አካባቢ ሲደርስ የሰውነት ወይንም የልብስ እድፍ ማስወገጃ ሆኖ ለማኅበረሰቡ ግልጋሎት ይሰጣል። በአንዳንድ አካባቢዎች በመስኖ ተጠልፎ ከፍ ላሉ ሀገራዊ ልማቶች እየዋለ ብዙ ጣፋጭ ፍራፍሬዎች ይዘመሩበታል። ዝቅ እያለ ሲጓዝም የኤሌክትሪክ ብርሃን ምንጭ ሆኖ ጨለማ ይገፋል፤ ኃይል ይሰጣል። በወንጂ አካባቢ ሲደርስ ለሸንኮራ አገዳ እርሻ ውሎ በጣፋጭ “ነጭ ወርቅነት” የሚታወቀው ስኳር ይመረትበታል። አዋሽ እንዲህና እንዲህ እየሆነና እየተሆነበት ለተለያዩ ጉዳዮች ግልጋሎት ይሰጣል። የጉዞውና የአገልግሎቱ ባህርይ እየተለዋወጠም ወደማይቀረው ፍጻሜው በመድረስ አሸዋ ከድኖት ታሪኩ ይደመደማል። ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን አዋሽን ከገለጸባቸው ስንኞች ጥቂቱን እናስታውስ!
አዋሽ ህመምህ ምንድን ነው?
ህመምክስ አንተስ ምንድነህ?
ከውኃ ወዝ የተለየ መቸስ ልዩ ንግርት የለህ፣
እንደ-ሴቴ ሸረሪት ፅንስ፣
ራስክን በራስህ ዋጥ ያለህ።
እስከ መቼ ይሆን አዋሽ?
ሲያሳድድ ሲያቅበዘብዝህ
ላትዘልቀው ላያዘልቅህ፣ አሸዋ ለአሸዋ ድኸህ፣
ውስጥ ለውስጥ ምሰህ ጠልቀህ፣
የምድር ማኅፀን ቦርቡረህ፣
ዋልታውን ቁልቁል ሰንጥረህ፣
እናትህ ውቂያኖስ ማኅፀን፣ ላትገባ ትባክናለህ።
የሀገራችንን ሰላም በተመለከተ ከአዋሽ ወንዛችን ዝንጉርጉር የጉዞ ውሎዎች ጋር በተመሳስሎ ለማነጻጸር የተሞከረው እውነታው ከወቅቱ ጠዝጣዥ ህመማችን ጋር በእጅጉ የሚቀራረብ ስለመሰለን። የአዋሽ ወንዝንና ታማሚውን ሰላማችንን በተመለከተ አንባቢው ከዚህ ውስን ማነጻጸሪያ በተሻለ አፍታቶ እንዲመረምረው እናበረታታለን።
የጸሐፊውን ምልከታ እነሆ!፡- የቆሰለችውን የሀገራችንን የሰላም ርግብ ጉዳይ በተመለከተ እያንዳንዱ ዜጋ እንደምን በሀዘንና በተስፋ መቁረጥ ላይ እንደወደቀ መግለጹ “ለቀባሪ የማርዳት ያህል” ያስገምታል። አንዳንድ ቡድኖች ወይንም ግለሰቦች የሰላም ወንዛችንን ከማደፍረስ አልፈው ተርፈው ልክ የአዋሽ ዳርቻ ነዋሪ ታዳጊ ወጣቶች ወንዙን ለመራገጫነትና ለመፈንጫነት እንደሚጠቀሙበት የእኛዎቹ ጨቅላ ዓላማ ቢስ የፖለቲካ “ሰካራሞች” ወይንም የሰላምን ዋጋ ያረከሱ ባለ እድፋም አስተሳሰቦች አጀንዳቸውን ሲተገብሩበት ማስተዋል ተስፋ ማስቆረጥ ብቻ ሳይሆን እምባችንን ለማዝራትም ግድ ቢለን ሊገርም አይገባም።
በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ከሰብእና ውጭ “በእንስሳነት ባህርይ የሚፈረጁ” ጥቂት ግለሰቦችና ዓላማ ቢስ ቡድኖች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው ወይንም “ማን አለኝ ከልካይ” በሚል ድፍረት የሰላም ወንዛችን በጸጥታ እንዳይጓዝ በማደፍረስ በምንም ውስጥ የሌሉ የንጹሃን ዜጎች ደም በከንቱ እንዲፈስና ምስኪን ወገኖቻችን እንዲፈናቀሉ በጨለማ ውስጥ ተሸሽገው የግፍ ትራዤዲያቸውን እያቀናበሩ መተወን በሀገራችን የሚታይ የዕለት ተዕለት “ትርዒት” ከሆነ ሰነባብቷል።
አንዳንዶችም፡- ባልፈለግነውና ሀገራችንን በማይመጥን ደረጃ የሰላም ወንዛችንን “በውራጅና በሰልባጅ አይዲዮሎጂያቸው እድፍ” ሲበክሉ፣ “በቆሸሸ የአክቲቪዝም ተንኮል ሲያንቦጫርቁ” ማስተዋል እንግዳችን አይደለም። ይህን መሰሉ እኩይ ድርጊታቸው የሀገርን ሉዓላዊነት እስከ ማናጋት ደርሶ ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን ያልመሸበት የትናንቱና የዛሬው ታሪካችን ምስክር ነው።
በአንጻሩም፡- በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች የሰላም ወንዛችን ዋጋ ከፍ ብሎና ከራስ ፍላጎት ልቆ ልክ እንደ አዋሽ ወንዛችን “የብርሃን ወጋገን” የሚሆን ተስፋ ሲያመነጭ መመልከት እርካታ እንበለው ኩራት፤ ብቻ የሆነ የኢትዮጵያዊነት የስሜት ሙቀት ውስጣችንን እያረሰረሰ ሲያለመልመን ይታወቀናል። ይሄም ብቻ አይደለም፤ የሰላሙ ወንዛችን ተረጋግቶና ለበጎነት ውሎ የተንዠረገጉ የልማት ፍሬዎችና ትሩፋቶች ሲዘመርላቸው ስናደምጥ፣ ወይንም በስኬት የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ሲመረቁ ስንሰማና ስናስተውል የዜግነታችን ክብር ከፍ ብሎና ደምቆ የፈካ ስለሚመስለን አንገታችንን ቀና በማድረግ ለኢትዮጵያዊነታችን ክብር ከፍ ያለ ዋጋ እንሰጣለን።
አንዳንዴም፡- የሸንኮራ አገዳና ስኳር እንደሚመረትበት እንደ ታችኛው የአዋሽ ተፋሰስ ሁሉ ሀገራዊ ሰላማችን የነገሮች “በጎ ማጣፈጫ ቅመም” ሆኖ ስናስተውል የውስጥ እርካታ እያረሰረሰን “ብሔራዊ መዝሙራችንን ከፍ ባለ ድምጽ ዘምሩ፣ ዘምሩ ያሰኘናል”። የሀገራችን ዝንጉርጉር የሰላም መልክ በእንዲህና እንዲያ አብከንካኝ ቀለማትና ባህርይ በተለበጡ እውነታዎችና ውጤቶች የተሸመነ ነው – ልክ እንደ አዋሽ ወንዛችን መሆኑን ልብ ይሏል።
ሀገራዊ የሰላም ወንዛችንን ለማደፍረስ፣ ለማቆሸሽና ለማሳደፍ ቀን ከሌት የሚተጉ የማሕበረሳባችን ብካይ ግለሰቦችና ቡድኖች ራሳቸው “የሰላም እንቅልፍ ተኝተው ያድራሉ ወይ?” ብለን ብንጠይቅ ምላሹ ምን ሊሆን እንደሚችል አይጠፋንም። የሰላምን ርግብ ለመግደል የሚያልሙ የክፋት አዳኞች የጠብመንጃ ቃታቸውን የሚያነጣጥሩት ወደ ራሳቸው አዙረው እንደሚሆንም የገባቸው አይመስልም።
በሰላም ተቀራርቦ መነጋገር ወግ ነው። በሰላም መወቃቀስም የሀገር ባህል ነው። ተገፋሁ ወይንም ተጎዳሁ፣ ትኩረት ተነፈገኝ ወይንም አሳቢ አጣሁ የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ጣት ከሚጠቋቆሙባቸው አካላት ጋር ጠረጴዛ ስበው ለውይይት መቀመጥ የስልጣኔ ምልክት ብቻ ሳይሆን የብስለትም አንዱ መገለጫ ነው።
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የንጹሐንን ደም በማፍሰስ፣ የዜጎችን ንብረት በመቀማትና በማውደም አሸናፊ መስሎ መታየት ግን የማታ ማታ እንደሚያዋርድ፣ በፍትሕ ሚዛን ላይ አስቀምጦም የእጅን ዋጋና የጥፋትን ምንዳ እንደሚያስከፍል የሰላም ጠንቆቹ ይጠፋቸዋል ተብሎ አይገመትም። ጊዜ የፈቀደለት “ቅል” ድንጋይ መስበሩ እውነት መሆኑ ባይካድም፤ “ከእኔ ወዲያ ለአሳር” እያለ የፎከረው “ባለጊዜ ቅል” ወረቱን ተነጥቆና ቀን ከድቶት የልቡ እብጠት መሟሸሽ ሲጀምር በዶሮ ላባ በሚመሰል ልምጭ እንክትክቱ እንደሚወጣ ቆም ብሎ ማሰቡ ሳይበጅ የሚቀር አይመስለንም።
የሰላምን ርግብ በማቁሰል እጁ በደም የታጠበ ማንም ግለሰብም ይሁን ቡድን የተሸከመውን ጠብመንጃ በማውረድ በጨለማ ተጋርዶ ማሸለብ ሲጀምር የሚያስቃዠው እንደ ድል ቆጥሮ “ጉሮ ወሸባዬ” ያለበት ፉከራ ሳይሆን ያፈሰሰው የንጹሐን ደም እሪታ ነው። የቅዱስ መጽሐፉን ሰማዕት የሐዋርያውን የቅዱስ ዮሐንስ ራዕይ በዚህ ቦታ መጥቀሱ ይበልጥ ሃሳቡን ያጎላ ይመስለናል።
“የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሰዊያው በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም፤ ደማችንንስ ‹በግፈኞቹ› ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? ‹በማለት ቀንና ሌሊት ይጮኻሉ።›” ይህ ጩኸት በወንድሙ በቃየን የግፍ ጭካኔ ከተገደለው ከአቤል ደም ጀምሮ እስከ እኛ ዘመን ድረስ በቅን ፈራጅ ፈጣሪ ዙፋን ሥር እንዳስተጋባ አለ። ልዑል አምላክም ፍርዱ የዘገየ ይምሰል እንጂ የእያንዳንዱ ጽዋ ሞልቶ ሲትረፈረፍ ሁሉም የእጁን መቀበሉ አይቀርም።
ጊዜና ወቅት እድል የሰጣቸው ብዙ ጡንቸኛ አምባገነን ልበ ድፍኖች ከአሁን ቀደም “ጽዋቸው ሲሞላና ሲገነፍል” በዓለማችንም ሆነ በሀገራችን ታሪክ ውስጥ ፍጻሜያቸውና መጨረሻቸው በምን እንደተደመደመ ታሪካቸውና ታሪካችን በሚገባ ያስታውሰናል። የዛሬዎቹም የሰላም ፀሮች “በለስ የቀናቸው” እየመሰላቸው በአዋሽ የመሰልነውን ሰላማችንን ያሳደፉና ያቆሸሹ፣ ያንቦጫረቁና የበከሉ ቢመስላቸውም ውሎ አድሮ መሪሩን ዋንጫ መጎንጨታቸው አይቀሬ ነው።
እናስ የሰላም ወንዛችን የሚደፈርሰው ምን ስለሆነ ነው? መልሱ ከላይ በዝርዝር ቀርቧል። በአጭሩ ለመጠቅለል ካስፈለገ ግን፤ የሰላም ወንዛችንን ክፉዎች እንዲፈነጩበት፣ እንዲያንቦጫርቁት፣ እንዲያሳድፉት፣ የጉዞውን አቅጣጫ አስተውም በጥፋት አውሎ ነፋስ የሚያናውጡት ጊዜውና ክፉ እድል ስለፈቀደላቸው መሆኑ ያግባባ ይመስለናል።
ነፍሰ ኄሩ የሀገራችን ደራሲ ከበደ ሚካኤል ዘመናቸውን በሄሱበት አንድ ግጥማቸው ውስጥ የገለጹትን አባባል ተውሰን ከዛሬው ዐውዳችን ጋር በሚገባ ስለሚገጥም አለፍ አለፍ እያልን እንደሚከተለው ስንኞቹን እናስታውሳለን።
“ሰላም ተሰደደች ፍቅር ጭራሽ ሞተ፣
ጠብመንጃ መትረየስ መድፍ አፉን ከፈተ።
እንደ በግ እንደ ከብት ተነድቶ እየሄደ፣
አገር ቄራ ሆና ያዳም ልጅ ታረደ።
ይረገጡ እያለ ተዋርደው ይገዙ፣
ጠላት አፌዘብን ሣቀብን በብዙ።
የሕዝቡ ንጹሑ ደም መቼ ከንቱ ቀረ፣
በሰፈረው ቁና ግፉን ተሰፈረ፣
ፍርድ የእርሱ መሆኑን አምላክ መሰከረ።
ዛሬም በእኛ ጀንበር ድፍርስ የመሰለው የሰላም ወንዛችን ሳይርቅ በቅርቡ ጠርቶና ኩልል ብሎ ኢትዮጵያ የሀዘን ጭርቋን ጥላ፣ ሕዝቧም ወደሚመኘው የተረጋጋ ሕይወት ተመልሶ ፊቱን ወደ ልማት እንደሚመልስ ተስፋችን ጽኑ ነው ብለን ብናረጋግጥም ስጋቱ ግን ፈጥኖ የሚላቀቀን አይመስልም።
ይህ አምደኛ ስለ አንዳንድ ወንዞቻችን ለየት ያሉ ስያሜዎች ባሰበ ቁጥር ፈጥነው ወደ አእምሮው የሚመጡለት ሁለቱ የአዲስ አበባ አካባቢ ተጎራባች ወንዞች ናቸው – ግንፍሌና ቀበና። ግንፍሌ ወንዝ ስሙን ያገኘው በትንሽ በትልቁ በትዳር አጋሩ ላይ ግንፍል እያለ እንደሚነጫነጭ ትዕግሥት አልባ አባወራ ሁሉ ዝናብ ጠብ ባለ ቁጥር ግንፍል፣ ግንፍል የሚለውን ባህርይውን ለመግለጽ ነው።
በአንጻሩ “ቀበና” የሚለው የኦሮምኛ ስያሜ “ቀበና – Qeebbena” ከሚለው የአፋን ኦሮሞ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም “ቀዝቀዛ፣ የረጋና የተረጋጋ” ማለት ነው። ሁለቱ ወንዞች ለዘመናት አብረው ተጎራብተው ኖረዋል። ከአራት ኪሎ ወደ መገናኛ የሚጓዝ መንገደኛ ሁለቱንም ወንዞች የሚያቋርጠው በተቀራራቢ ርቀት ነው። የሀገራችን የሰላም ጉዳይም እንዲሁ “ቀበና” ነው ስንል “ግንፍሌ”፤ “ግንፍሌ” ነው ስንል “ቀበና” እየሆነ እስከ መቼ ግራ እንዳጋባን እንኖራለን?
“ከመፈቅፈቅ ማለቅለቅ” አለ ገጣሚው ክፍሌ አቦቸር (ሻለቃ)፤ እውነት ብሏል። ከግጥሙ ጥቂት ስንኞች ቆንጥረን እናስታውስና የንባብ ጉዞችንን እናጠናቅቅ፡-
“ሀ” ሲባል “ሀ” ቢባል፤
ጅምሩ ቀድሞ ቢዳሰስ፣
ቀድሞ! ቀድሞ ቢቀነጠስ፤
መፈልፈያው ቢደፈን፣
ሥሩ ማለዳ ቢበጠስ፤
የውስጥ ውስጡ የላይ ላዩ፣
ቃርሚያው በወጉ ቢነሣ፤ ባልነበረ ነበር፣
የዛሬው ክምር አበሣ።
የችግሩ “ችግር” ይህ ነው፤
ሽምቅታው ነው የበደለን፣
የ”ሣመን” ነው “የነከሰን”፤
የ“ሣቀ” ነው የገደለን።
ያለፈው ቀድሞ አለፈ፤ ዛሬ ለነገ እንዲቀነስ፣
ድራድሩን ነው መበጠስ፤
አስኳሉን ነው መፈርከስ።
ይኼው ነው። “ኦ! ሰላም በስምህ ስንት ግፍ ተሠራ!” ያለው ጠቢብ እውነት ብሏል። ሰላም ለሀገራችን! በጎ ፈቃድ ለሕዝባችን
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥር 20 ቀን 2015 ዓ.ም