ዘውዴ መታፈሪያ ራሱ በከተማ አስተዳደሩ በአንዱ ወረዳ ውስጥ እየሰራ የሚኖረው ደግሞ በሌላ ወረዳ ላይ በመሆኑ እንደፈለገው ከወረዳው በፍጥነት አገልግሎት ማግኘት አልቻለም። እርሱም የሚታየው እንደሌላው ተገልጋይ በመሆኑ መታወቂያ ማግኘት እልህ አስጨራሽ ትዕግስትን ጠይቆታል። ሰሞኑን ለአንድ ጉዳይ ለመመዝገብ የግድ የታደሰ መታወቂያ ያስፈልግሃል መባሉን ተከትሎ ወደሚኖርበት ወረዳ ጎራ አለ። እንደቀልድ አምስት ሰዓት አካባቢ ከሥራው ወጥቶ ወደ ወረዳው ሔደ፤ በዛ ፍጥነት እንኳን መታወቂያ ሊያገኝ ቀርቶ የሚያናግረውና ቀጠሮ የሚሰጠው ሰው አላገኘም። የወሳኝ ኩነት ሰራተኞች ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ሰማ።
በማግስቱ ከስራ አስፈቅዶ አራት ሰዓት አካባቢ በወረዳው ተገኘ፤ ሆኖም ከእርሱ በፊት በአስሮች የሚቆጠሩ ተገልጋዮች እንደርሱ መታወቂያ ለማሳደስ ወረፋ ይዘው እየተጠባበቁ መሆኑን አወቀ። ‹‹በምን ያህል ሰዓት ይደርሰኝ ይሆን?›› ሲል ለራሱ ግምት ለማስቀመጥ አንድ ሰው ገብቶ ሂደቱን አጠናቅቆ እንደሚወጣ ለማረጋገጥ ሞከረ፤ ሆኖም ተስፋ አስቆራጭ ሆነበት። ከአምስት ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ወረፋ ቢጠብቅም ከሶስት በላይ ሰው መታወቂያ አላደሰም። በአንድ ሰዓት ውስጥ ሶስት ሰው ብቻ መታወቂያ ካላሳደሰ ሰላሳ ሰው የሚደርሰው በትንሹ ከሶስት ቀን በኋላ ይሆናል ብሎ ለራሱ ገመተ። በስጨት ብሎ ችግሩ እንዲቃለል በመገመት ወደ ኃላፊው ቢሮ ጎራ ለማለት አስቦ ከተገልጋዮቹ ሃሳብ መሰብሰብ ጀመረ።
ሲያጠያይቅ መታወቂያ ለማደስ የተመደቡት ሰራተኞች ሥራውን የማያውቁ ከተገልጋዩ ቁጥር ጋር የማይመጣጠኑ መሆናቸውን ሰማ። ሌሎችም የጋብቻ፣ የልደት ሰርተፍኬት የሚያወጡ ሰዎችም በተመሳሳይ መቸገራቸውን አረጋገጠ። ለምሳ ሲወጡ እና ሁሉም ሲበተኑ እስኪ ሲረጋጋ ብሎ እርሱም ምሳ ለመብላት ወጣ። የሚበላውን በልቶ ማወራረጃውን ጠጥቶ ወደ ወረዳው ሲገባ ወረዳው የቅቤ ገበያ መስሏል። ጭራሽ ጫጫታው በዝቷል። ገሚሱ የመጣሁት በጠዋት ነው፤ ሲል ገሚሱ ትናንት መጥቼ ስላልደረሰኝ ነው ይላል። ጭራሽ በአንድ ሰዓት ሶስት ሰው ማስተናገድ ቀርቶ እስከ አስር ሰዓት ምንም ዓይነት ሰው እንዳልተስተናገደ ሲያውቅ ወደ ኃላፊው ቢሮ ለመሄድ አላመነታም ነበር። ነገር ግን ኃላፊውም በቢሮ አልነበረም። አልፎ ለመሄድ ወስኖ ወደ ወረዳው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቢሮ አቀና። ሆኖም ፀሐፊዋ ዋና ስራ አስፈፃሚው ወደ ወረዳው ማህበረሰብ ለስራ መውጣቱን ነገረችው። በሁኔታው ተማሮም ወደ ማምሻ ቤቱ ሔደ።
እንደልማዳቸው ተሰማ መንግስቴ፣ ገብረየስ ገብረአምላክ ቀድመው እየተጨዋወቱ እና እየጠጡ ጠበቁት። ውሎውን ሲነግራቸው እየሳቁ ተሰማ ለዘውዴ ‹‹አንተም ያው ነህ።›› አለው። ዘውዴ በጣም ተበሳጨ። ‹‹ምን ማለትህ ነው? ›› ሲል ደነፋ። ተሰማ አልተበሳጨም። ‹‹ይኸው አንድ መታወቂያ ለማውጣት ሁለት ቀን ሙሉ በሥራ ሰዓት ቢሮህ አልተገኘህም። በተዘዋዋሪ ሌላው አገልግሎት ፈልጉ እዚህ የመጣው ሰው በአንተ እየተማረረ ነው›› ሲል መለሰለት። ‹‹ይሄ እና የእኔ ሥራ የሚገናኝበት ሁኔታ የለም። እኔ ባልኖርም የምሰራውን ስራ ከእኔ በታች ሊሠራው ለሚችል ሰው ውክልና ሰጥቻለሁ። ማንም ተገልጋይ የሚንገላታበት ሁኔታ የለም።›› አለ።
ገብረየስ በበኩሉ ‹‹ሆኖም ይሄ ችግር አንተን ብቻ ሳይሆን መላው የከተማዋን ነዋሪ ያሰቃየ ነው። ስለዚህ መፍትሔ ለማምጣት አንተ ምን አደረግክ?›› ሲል ጥያቄ አቀረበ። ዘውዴ ተገልጋዮችን ጠይቄ ኃላፊዎችን ለማግኘት ሞክሬያለሁ ነገር ግን አልተሳካልኝም አለ። ተሰማ እየሳቀ፤ ‹‹ያው እነርሱም ለመገልገል ሔደው ይሆናል።›› አለ። ዘውዴ ተበሳጨ። ለተሰማ፤ ‹‹ አንተ ነገሩን ቀልድ አድርገኸዋል ነገር ግን ቀልድ አይደለም።›› አለው።
ተሰማ ‹‹ ምን ላድርግ የኢትዮጵያም ሆነ የአዲስ አበባ የመንግስት ተቋማት ችግር ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ትኩረታቸው ተገቢውን አገልግሎት በፍጥነት እና በጥራት ከመስጠት ይልቅ ዓላማ እና ፍላጎታቸው የተለያየ ነው።›› አለው። ዘውዴ ደግሞ ‹‹ እርሱስ እውነትህን ነው። ሕዝቡ ሲንገላታ አቋራጭ መንገድ ይፈልጋል። ያ ደግሞ የገቢ ምንጭ ከሆነ ውሎ አድሯል። ነገሩ እንኳን የመንግስት ሰራተኞች አንዳንድ ጊዜ አሰራር ላይም ችግር መኖሩ የሚካድ አይደለም።›› አለ።
ገብረየስ በበኩሉ ‹‹ለዛች ሱቄ የንግድ ፍቃድ ዕድሳት ታኅሣሥ 30 ያልቃል ሲባል፤ ታኅሣሥ 27 ሔድኩኝ ስብሰባ ላይ መሆናቸው ተነገረኝ። ታኅሣሥ 28 ብሔድም የገባ ሰራተኛ አልነበረም። ታኅሣሥ 29 እና ታኅሣሥ 30 የእረፍት ቀናት ናቸው። ጥር 1 ለማሳደስ ቢሯቸው ስሔድ፤ ለዕድሳቱ መክፈል ያለብኝ 102 ብር ብቻ ነበር። ቀኑ ስላለፈ 2ሺ ስድስት መቶ ብር መክፈል ግዴታህ ነው አሉኝ። ምን ማለት ነው? እኔ ቀኑን አላሳለፍኩም ቀኑን ያሳለፋችሁት ራሳችሁ ናችሁ። ብልም ምላሽ የሚሰጠኝ አልነበረም። ምክንያቱም እነርሱ ጥግብ ያሉ አገልጋዮች ናቸው። ደንበኛ ንጉስ ነው የሚለውን አባባል አባባል ብቻ አድርገውታል። የምን ንጉስ። አገልጋይን ማን ይቆጣል? አቤቱታ ቢቀርብ መልሱ በቅሎ ገመዷን በጠሰች በራሷ አሳጠረች እንደሚባለው ይሆናል።
አቤቱታ ማቅረብ ችግርን ማቃለል፤ መፍትሔ ማግኘት ሳይሆን በራስ ጥፋት ችግር ላይ እንደመውደቅ ነው። ለኃላፊው ለምን ፈጣን አገልግሎት አይሰጥም? በገዛ ጥፋታችሁ አመላልሳችሁን እንዴት ራሳችሁ መልሳችሁ ትቀጡናላችሁ? ብዬ ጠይቄ ነበር። ሆኖም ደረሰኙ የሚቆረጠው በዛሬው ቀን በመሆኑ በ102 ብር ዛሬ ላይ የፍቃድ ማደስ ክፍያን ማስፈፀም አንችልም አለኝ። ከ200 እጥፍ በላይ ስታስከፍሉን እንዴት እፍረት አይሰማችሁም? ብለን ብንጠይቅም ችግራችንን ከማየት እና አቤቱታችንን በተገቢው መንገድ ከመመለስ ይልቅ ማመናጨቅ ጀመረ። ጭራሽ ያቀረብነው ጥያቄ ወሬ ሆኖ ሰራተኞቹ ጋር ተዛብቶ ተራባ።
መቼም የሃቀኛ ስንቁ እውነት ነውና እኔም ስንቄን ቋጥሬ ጥያቄዬ ትክክል ነው ብዬ ነገር ግን ምላሽ አጥቼ ባላጠፋሁት ጥፋት መክፈል ካለብኝ ሌላ 250 እጥፍ ተቀጥቼ የንግድ ፍቃዴን አሳደስኩ።›› ብሎ ምሬቱን ሲያጠናቅቅ ተሰማ ቀጠለ፤ እኔ ደግሞ ቢቆይም ካርታ ለማግኘት ያየሁትን መከራ ለመግለፅ ይቸግረኛል። ተገልጋይን እንደጠላት የምናየው፤ ግን ምን ሆነን ነው? መሃንዲሱ ወይ በእጅህ ና አላለኝ፤ ወይ ተገቢውን አገልግሎት አልሰጠኝ፤ ካርታ ይቀየርልኝ የገበርኩበት መሬት ይካተት ብልም ማን ሰምቶኝ? ለተመሳሳይ ጎረቤቶቼ ሁሉ ካርታ ተሰጥቶ እኔ ግን ለዓመታት ተመላለስኩ በመጨረሻ እንደምንም ከስሼ ተጣልቼ ተለማምጬ ደጅ ጠንቼ ምላሽ አገኘሁ። አሁን ተገልጋይ መሆንን ሳስብ የምመኘው ሞትን ብቻ ነው።›› አለ።
ዘውዴ ደግሞ የሚጠጣውን እየተጎነጨ፤
‹‹ከሰው ጋር ሲኖር አገልግሎት ሲሰጥ መተሳሰብ እና መረዳዳት እንጂ የራስን ጥቅም ለማስቀደም መሞከር ተገቢ አይደለም። አጉል ብልጠት አያዋጣም። ሰበብ እየፈለጉ ተገልጋይን በማንገላታት በእጅ መንሻ ለመስራት መሞከር ብዙ ርቀት አያስኬድም፤ የሚያስከትለው ጭራሽ ውድቀትን ነው። አንድ አገልጋይ አንድ ሰሞን ሲያንገላታኝ ከረመ፤ ጉዳዬን በስንት ምልጃ በጨረስኩ በሶስተኛው ቀን እኔው ጋር ሊገለገል መጣ፤ የበላበትን ወጪት ሰባሪ የተደረገለትን ውለታ የሚረሳ ውለታ ቢስ ያስተማረውን ሕዝብ የሚያሰቃይ ከሃዲ እንደሆነ አስቤ ሕዝብን ሲያንገላታ ለኖረ ተገልጋይ እያንገላቱ ማሳየት ነው። ብዬ ለራሴ አሰብኩኝ፤ ግን ደግሞ አገልግሎትን በማጓተት እምነት የማይጣልበት ሰው ሆኖ መገኘትን ሳስብ ቀፈፈኝ።
እርግጥ ነው፤ ጥጋብ ወደ ርሃብ ይነዳል፤ ከልክ ያለፈ ጥጋብ ወደ ችግር መግፋቱ አይቀርም። ምንም እንኳ በጥጋቡ ሲያንገላታኝ ቢከርምም ዋጋውን ማግኘቱ አይቀርም ብዬ በተገቢው መልኩ አገለገልኩት ግን ደግሞ በተገቢው መልኩ ማገልገሌን የተቀበለበት መንገድ የሚያስቅ ነበር። ‹እኛ እኮ የገባን ነን ፤ መቅጣት ያለብንን እንቀጣለን› ብሎ ሳንቲም ሊያስጨብጠኝ ፈለገ። አይሆንም ስለው ነገሩ ጥርስ እና ከንፈር ሲደጋገፍ ያምራል፤ መደጋገፍ ጉልበት ይሆናል እንደጋገፍ ብዬ እንጂ ማታለሌ ወይም ሙስና መስጠቴ አይደለም አለኝ ፤ ስቄበት አሰናበትኩት፤ የለመደች ጦጣ ሁልጊዜ ሸምጣጣ እንደሚባለው፤ አንዳንድ ሰው አንድ ጊዜ ጥቅም ባገኘበት መንገድ ሁልጊዜ የሚሳካለት ይመስለዋል።
እርሱ ሕዝብ እያታለለ ስለሚዘርፍ ሌሎች እርሱን በሚያባብሉበት መንገድ እኔን ለማባበል እና ለማታለል ሞከረ። እኔ ግን ትክክለኛውን መንገድ ተከትዬ ተገቢውን አገልግሎት ሰጥቼዋለሁ። በመጨረሻም የአገር ልጅ የማር እጅ ብዬ ለሀገራችን በእውነተኛ መንገድ እንስራ ወገን ሀገርን የሚረዳና በችግር ጊዜ የሚደርስ አለኝታ ነውና በችግር ጊዜ እኔን እና መሰል ተገልጋይ ዜጎችን ከምታንገላታ ሁሉም እጅ ላይ የምትወድቅበት ጊዜ ሊያጋጥም ስለሚችል ተጠንቀቅ ብዬ አስተምሬ ሸኘሁት ።›› አለ።
ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹የመታወቂያው ጉዳይ የተወሳሰቡ ችግሮች ያሉበት ነው። ለረዥም ጊዜ አገልግሎቱ ተቋርጦ ነበር። በትንሽ ማረሻ ትልቅ እርሻ የሚል ብሒል ተይዞ በቀላል ወጪ ብዙ ጥቅም ማስገኘት ኢኮኖሚን ይገነባል ተብሎ የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶች ተዘረጉ፤ ነገር ግን በተለይ መታወቂያ ማደስ ቆሞ ስለነበር ከተከማቸው ስራ ጋር የሚመጣጠን የሰው ሃይል አላሰማሩም። በተጨማሪ አንዳንዶቹ ገና የአሰራር ስርዓቱ ያልገባቸው አዲሶች ናቸው፤ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ተደማምረው ተገልጋይ ላይ ችግር ይፈጥራሉ። ዕድሉን ለመጠቀም የሚሞክሩ ደላሎች ሲጨመሩበት ያለ ሳንቲም በትክክለኛው መንገድ መታወቂያም ሆነ ሌሎች አገልግሎቶችን ማግኘት ብርቅ መሆኑ አያስገርምም።›› አለ።
ዘውዴ እንደልማዱ ከመቀመጫው ቀድሞ እየተነሳ ከሌሊቱ አስር ሰዓት ተነስቶ ወረፋ ይዞ መታወቂያ ማሳደስ የግድ መሆኑን ስለተረዳ ቀድሜ ወደ ቤቴ ሄጄ በሌሊት ብነሳ ይሻለኛል፤ ምንም እንኳ የሚተካኝን ሰራተኛ ወክዬ ስራዬ ላይ ባልገኝም ተወካዬ ሙሉ ለሙሉ እኔን ወክሎ ሊሰራ የሚችልበት ሁኔታ ሊስተጓጎል ስለሚችል በጊዜ ወደ ቤት መሔድ ይሻለኛል ብሎ ጠረጴዛውን ተመርኩዞ ተነሳ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም