የጥር ወር ብዙ የአገራችንን ባህሎች የምናይበት ነው።ባለፈው ሳምንት የከተራ፣ ጥምቀት እና ቃና ዘገሊላ በዓላትን አክብረናል።እነዚህ በዓላት ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ባህላዊ ይዘትም እንዳላቸው ብዙ ተብሎለታል።ስለዚህ የጥር ወር የባህል ዓውደ ርዕይ ነው ማለት ይቻላል።
ሌላው የዚሁ የጥር ወር መገለጫ ደግሞ ሰርግ ነው።የከተማ ሰርግ ዘመናዊ መልክ ቢኖረውም በገጠሩ ማህበረሰብ ዘንድ ግን ቱባ ባህላዊ ይዘቱ ይታያል።
የጥምቀት ዕለት የአገራችንን የቴሌቪዥን ቻናሎች እያቀያየርኩ ሳይ ነበር የዋልኩ።በእንዲህ አይነት አጋጣሚዎች የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ማየት ሙሉ ኢትዮጵያን እንደማየት ማለት ነው።የሚዲያ ሚና ማለትስ ይህ አይደል?
ታዲያ እነዚህን የአገራችንን ውብ እና ድንቅ ባህሎች ሳይ (አብዛኞቹ ቀደም ብየም የማውቃቸው ቢሆኑም) ትዝ ያለኝ ከቀናት በፊት አጀንዳ ሆነው የነበሩ ሁለት ጉዳዮች ናቸው።አንደኛው፤ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ያወጣው ቁምጣ ሱሪ መልበስን የሚከለክል ትዕዛዝ ነው።በእርግጥ ባጋጠመው ተቃውሞ መግለጫውን አንስቶታል።ሁለተኛው ደግሞ የሴት ሽማግሌዎች የላከው ዘማሪ ጉዳይ ነው።
ሁለቱንም አጋጣሚዎች ለመነሻ ሀሳብ ተጠቀምኳቸው እንጂ ስለእነርሱ ለማውራት አይደለም፤ ዳሩ ግን መነሻ ሀሳብ ይሆናሉና እግረ መንገድ ስለባህል አብዮት እናውራ።
ከምሥራቅ ጎጃሙ የቁምጣ ክልከላ እንጀምር!
የባህል አብዮት እንደሚያስፈልግ አምናለሁ።ድሮ እንዲህ ነበርንና አሁንም በዚያው እንቀጥል አይባልም።ምክንያቱም አሁን ያለው ሁኔታ የድሮውን አኗኗር ለመኖር አይፈቅድም።የዘመኑ ባህሪ እና ነባራዊ ሁኔታ ያስገድዳል።ለምሳሌ፤ የድሮ ባህላችን አገር አቋራጭ ጉዞ በእግር መሄድ ነበርና አሁንም እንሂድ አይባልም፤ ምክንያቱም የዛሬው ትውልድ እንኳን አገር አቋራጭ ጉዞ 10 ኪሎ ሜትር እንኳን መሄድ የሚከብደው ነው።
በአጠቃላይ የባህል አብዮት ይኖራል፤ ዳሩ ግን የባህል አብዮት የሚመጣው በሂደት እንጂ በትዕዛዝ አይደለም።ለምሳሌ፤ ቁምጣ ሱሪ በብዙ የገጠር አካባቢዎች እየቀረ ነው፤ የቀረው ግን በትዕዛዝ ሳይሆን በሰዎች ፍላጎትና አመለካከት መቀየር ነው።የሥራ ዘርፍ እና የአኗኗር ዘይቤ ሲቀይሩ ነው።
ሌላው ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ ለሥራ የሚያመች ምርጫን ያላገናዘበ መሆኑ ነው።ገበሬው ቁምጣን የሚፈልገው ለቅልጥፍና ነው።ረጅም ሱሪ አድርጎ በጭቃ እየጎተተ እርሻ ማረስ አይመቸውም።ይህን የሚያደርገው ሱሪ መግዣ ተቸግሮ ወይም ኋላቀር ሆኖ አይደለም፤ ለቅልጥፍና የሚመቸው ቁምጣ ስለሆነ ነው።ይህ ደግሞ ገበሬው ብቻ ሳይሆን ማንም የተማረ እና የሰለጠነ የሚባል ሁሉ የሚያደርገው ነው።ኳስ ጨዋታ ላይ ቁምጣ የሚለበሰው ለዝነጣ ተብሎ አይደለም፤ ቀለል እና ቀልጠፍ ያለ ስለሆነ ነው።የውሃ ዋና እና ሌሎች የስፖርት ዓይነቶች ቀለል ባለ አለባበስ የሚደረጉት የሥራው ባህሪ ስለሆነ ነው።የጋራዥ ሰራተኛ ሙሉ ቱታ የሚለብስ የሥራው ባህሪ ያንን ለመልበስ ስለሚያስገድድ ነው።ብዙ የሥራ ዘርፎች የየራሳቸው መለያ ልብስ አላቸው።ስለዚህ የባህል ለውጥ እናምጣ ሲባል ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ መሆን አለበት፡፡
በዚሁ እግረ መንገድ ግን አንድ ትዝብት ላስቀምጥ።በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ተቋማት(በተለይም የዞን እና ወረዳ) የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ሲጠቀሙ ለትዝብት የሚዳርጉ ነገሮች እየታዩባቸው ነው።የወረዳ ገፆች የማህበራዊ ሚዲያ መሳቂያ እየሆኑ ነው።ስለዚህ ጠበቅ ያለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ያስፈልጋቸዋል።ምክንያቱም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ስለሆነ እንደ ተራ ግለሰብ ተንቆ የሚታለፉ አይደሉም፤ ኃላፊነት አለባቸው።ዝም ብሎ ድንገት ትዝ ያላቸውን ነገር በስሜት ሊለጥፉ አይገባም።
ሁለተኛው ትዝብቴ የሴት ሽማግሌዎች ነገር ነው።ዓለም አቀፉን መገናኛ ብዙኃን ቢቢሲ አማርኛ ጨምሮ ብዙ አካላት ነገሩን በስህተት የተረዱት ይመስለኛል።ቢቢሲ ‹‹የሴት ሽማግሌ›› መባሉን ያልተለመደ እና አዲስ ፈጠራ አስመስሎ ነው ያቀረበው።ከትርጓሜው እንነሳ።
‹‹ሽማግሌ›› የሚለው ቃል በእማሬያዊ ትርጉሙ በዕድሜ የገፋ ወንድ ማለት ነው።ዳሩ ግን በሂደት በማህበረሰቡ ተደራቢ ትርጉም ተሰጥቶታል።ሽማግሌ ማለት አስታራቂ፣ ሚዛናዊ፣ አዋቂ፣ ብልህ፣ በሳል አስተሳሰብ ያለው… ማለት ነው።በዋናነት ደግሞ አስታራቂ በሚለው ይታወቃል።
ከእነዚህ ትርጓሜዎች በመነሳት ባደኩበት ማህበረሰብ ውስጥ በዓይኔ ያየሁትን እና በጆሮዬ የሰማሁትን ባህል ልናገር።
እናቴ ‹‹ሽማግሌ ሆኜ›› ስትል ሰምቻት አውቃለሁ።ይህን የምትለው የተጣሉ የአካባቢ ሰዎችን ለማስታረቅ ስትሄድ ነው።ብዙ ሴት አስታራቂዎችን በአካባቢያችን አይቻለሁ።ለማስታረቅ ሲያስቡ ‹‹እናሸማግላቸው›› ነው የሚሉት።እንዲያውም ወንዶች ሳይሰሙ ተብሎ (ወደ ጠብ ስለሚወስዱት) በሴቶች ብቻ የሚያልቅ የእርቅ ሽምግልና አለ፡፡
በሌላ በኩል ሽምግልና የዕድሜ ጉዳይም አይደለም።ታላቅ ወንድማችን የ60 እና 70 ዓመት አዛውንቶች በአካባቢ እያሉ ገና በ30 ዓመቱ ሽምግልና ይቆጠር ነበር።መስፈርቱ ፆታ እና ዕድሜ አይደለም ለማለት ነው።ማን መናገር ይችላል፣ ማን ማሳመን ይችላል የሚለው ነው መስፈርቱ።አሸማጋይ የሚለውን ቃል negotiator የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል ነው የሚተካው እንጂ Old የሚለው አይሆንም።
ብዙ ሰዎች በነገሩ ሲገረሙ የነበረው ሴት ሆነው እንዴት ሽማግሌ ይባላሉ በሚለው ነው።‹‹ልጅህን ለልጄ›› በሚለው ባህል ውስጥ የሴት ሽማግሌ መላክ አግባብ ነው አግባብ አይደለም የሚለውን ለጊዜው መወሰን ባይቻልም ሽማግሌ የሚለው ቃል ግን ለሂደቱ እንጂ ለፆታና ዕድሜ አይደለም።
ስለባህል አብዮት ስናወራ፤ ባህል በዘመን እና በሁኔታዎች መቀያየር የሚቀየር እንጂ ባለበት የሚቆይ አይደለም።የሰው ልጅ ከዛሬ አንድ ሺህ ዓመት በፊት የነበረበት ሁኔታ እና የዛሬው አንድ አይደለም፤ ከዛሬ አንድ መቶ እና አንድ ሺህ ዓመት በኋላም አሁን ባለበት አይገኝም።ምናልባትም ከዛሬ መቶ ምናምን ዓመታት በኋላ ቀሚስ የወንድ መገለጫ፣ ሱሪ ደግሞ የሴት መገለጫ ሊሆን ይችላል።ምክንያቱም ከዛሬ መቶ እና ሺህ ምናምን ዓመታት በፊት የነበሩትን ስንሰማ ‹‹ይደረግ ነበር እንዴ!›› ብለን ተገርመናል።
ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስን እና አጼ ዮሐንስ አራተኛን የምናውቃቸው በሹሩባ ነው።ይህ የሆነው ከ160 ምናምን ዓመታት በፊት ነው።ዛሬ ሹሩባ የሴት መገለጫ ነው።ሹሩባ የተሰራ ወንድ ሲታይ ‹‹ሴታሴት!›› እየተባለ ይሰደባል።ማን ያውቃል ከ200 ምናምን ዓመታት በፊት ሹሩባ የወንድነት መገለጫ የነበረ ቢሆንስ? መሪዎቹ ታዋቂ ስለሆኑ ታሪካቸው ተቀምጦ እንጂ ተራ ወንዶች ሁሉ ሹሩባ ይሰሩ የነበረ ቢሆንስ?
በዚያ ዘመን ሹሩባ የወንድነት መገለጫ ይሁን አይሁን አናውቅም፤ ሀቁ ግን ባህል በዘመን ሂደት ሙሉ በሙሉ ተቃራኒ ገጽታ ሊይዝ ሁሉ ይችላል።ይህ የሰው ልጅ ዝግመተ ለውጣዊ ሂደት ነው።እንኳን ውጫዊ የሆነውን ባህል፣ ሥጋዊ የሆነው የሰውነት ቅርጽ እንኳን በሂደት ነው አሁን ያለውን ገፅታ የያዘው፡፡
ስለዚህ ባህል የሚለወጠው በሂደት እንጂ በኃይል ስላልሆነ የሰዎችን ባህል መከልከል ወይም መቃወም አግባብ አይደለም።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም