የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ባካሄዱት የጋራ ልዩ ስብሰባ በንብረት ላይ የሚጣል ታክስ ስልጣን ለክልሎች እንዲሰጥ ተወስኗል። በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ መሰረት በንብረት ላይ የሚጣል ታክስ ስልጣን ለክልሎች የሚሰጥ ሆኖ ክልሎች ደግሞ ባላቸው ህገ-መንግስታዊ ስልጣን ለአካባቢ መስተዳድሮች እንዲሰጡ የሚል ነው።
የንብረት ታክስ በከተሞች እና በክልሎች ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማስፈን፣ ሌብነትን ለመከላከል፣ የታክስ አማራጮችን ለማስፋት፣ ክልሎች ከድጎማ ተላቅቀው የመልማት እድላቸው እንዲሰፋ፣ ለከተሞች የመሰረተ-ልማት አቅርቦትና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለማጠናከር እና በከተሞች የስራ አጥነት ችግር እንዲቀረፍ የሚያግዝ የውሳኔ ሀሳብ ስለመሆኑ በስፋት ተብራርቷል።
ለመሆኑ የንብረት ታክስ በኢትዮጵያ ሲተገበር አንድምታ ምንድን ነው፤ ምን ጥቅም፣ ምንስ ስጋት አለ፤ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ምን ይመስላል በሚለው ዙሪያ መረጃዎችን አገላብጠን ባለሙያዎች አነጋግረን የሚከተለውን ትንታኔ አዘጋጅተናል።
የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የንብረት ግብር (ፕሮፐርቲ ታክስ) ማለት፤ አንድ ግለሰብ አሊያም ሕጋዊ አካል ለሚጠቀምበት ንብረት ለመንግሥት የሚከፍለው ገንዘብ ማለት ነው። በአብዛኛዎቹ የዓለም አገራት የንብረት ግብር የሚለካው ንብረቱ በየዓመቱ ተተምኖ የሚኖረውን ዋጋ መሠረት በማድረግ ነው። በርካታ የዓለማችን ከተሞች የንብረት ግብር ጥለው በሚሰበስቡት ገንዘብ ራሳቸውን ይደጉማሉ። አብዛኛውን ጊዜ የንብረት ግብር የሚጣልበት መሬት እና ሕንፃ ቢሆንም ተሽከርካሪዎች ላይም ግብር የሚጥሉ አገራት አሉ።
የንብረት ግብር አሜሪካ ውስጥ የማዕከላዊው መንግሥት እና ክልላዊ አስተዳደሮች ከሚሰበስቡት ገቢ 30 በመቶውን ይይዛል። ነገር ግን አሜሪካ ዝቅተኛ የንብረት ግብር ከሚያስከፍሉ አገራት መካከል ስትሆን፣ ቤልጂዬም እና ስፔንን የመሳሰሉ አገራት ደግሞ ከፍተኛው የንብረት ግብር በማስከፈል የሚታወቁ አገራት ናቸው።
የባንክ ባለሙያው አቶ ታምራት ዓለሙ እንደሚሉት፤ የንብረት ግብር (ፕሮፐርቲ ታክስ) ማለት፤ አንድ ግለሰብ አሊያም ሕጋዊ አካል ለሚጠቀምበት ንብረት ለመንግሥት የሚከፍለው ገንዘብ ነው። የንብረት ታክስ ዘርፈ ብዙ ትንታኔዎችን የሚጠይቅ ስለመሆኑም ይናገራሉ። ፕሮፐርቲ ታክስ ሥርዓት ከአገራት የገቢ ማግኛ ስልቶች ውስጥ ቀዳሚው ሲሆን ሥርዓቱ በአግባቡ አንዴ ከተዘረጋ ገንዘቡን ለመሰብሰብም ብዙ አስቸጋሪ የማይሆን ስለመሆኑም ያብራራሉ። የዚህ ግብር በባህሪው ለመሰወር የማይመችና በብዛት መሬት ወይንም ቤት ነክ በሆኑ ንብረቶች ላይ የሚጣል ግብር ነው። ይህም ደግሞ የኢኮኖሚ ትልቁ ምንጭ በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ያብራራሉ። እንዲሁም የቴክሎጂና የሳይንስ ዕድገት መገለጫ ጭምር ነው።
የንብረት ታክስ ሲሰበሰብ ከሞላ ጎደል ሥርዓቱ የፋይናንስ ህግን ተከትሎ የሚሰራ እና ገንዘብ ዝውውሩንም ወደ ባንክ ሥርዓት የሚያመጣው ስለሚሆን የፋይናንስ ተቋማትን አቅም ለማጎልበትም የራሱ የሆነ ፋይዳ አለው። ገንዘብ ወደ ባንክ ስርዓት ከመጣ ደግሞ መንግስትና ህዝብ የሚጠቀሙበት ዕድል ሰፊ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ ዜጎች ቁጠባን እንዲለማመዱ አሊያም ደግሞ ብክነትን ለማስቀረት ያግዛቸዋል የሚል እምነት አላቸው። በአንድ አገር ውስጥ የገቢ ዕድገት ማምጣት ማለት የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የመመለስ አቅምን ከማሳደጉም በላይ በአንድ አገር ጠቅላላ ምርት ዕድገት እና በአገር ጠለላ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይም የራሱ አወንታዊ ሚና ይኖረዋል።
እንደ አቶ ታምራት ማብራሪያ ከሆነ፤ የገቢ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ አማራጮችን እየፈለጉ ገንዘብ መሰብሰብ የሚበረታታ ቢሆንም በጥቅሙ ልክ ጉዳትም እንዳለው ግን ማጤን ይገባል ይላሉ። መንግስት ብር ከዜጎች በብዛት በሰበሰበ ቁጥር ለብዙ ነገር ስለሚያውለው በተቃራኒው የገንዘብ መጋሸብን የማስከተል ዕድል ይኖረዋል። ታክሱ በበዛ ቁጥር ሰዎች ቤት የመግዛት ዕድል ሊቀንስ እና በዚያው ልክ የገንዘብ ፍሰትን ሊገድብ ስለሚችል ይህም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ይሆናል። የመንግስት ገቢ ቢጨምርም የሚመጣው ገቢ በምን ሁኔታ መቆጣጠር ይገባል የሚለው ደግሞ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ያሳስባሉ።
የንብረት ታክስ አዋጭ እና ስኬታማ ሊሆን የሚችለው የኢኮኖሚውን ምህዋር ሊዘውሩ የሚችሉ ሥርዓቶችን መቆጣጠር ከተቻለና እና የሚመጣው ገንዘብ በምን አግባብ ወደ ኢኮኖሚው መግባት አለበት የሚል ሳይንሳዊ ስሌትን ሲከተል ነው። ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን የንብረት ታክስ ጉዳት ሊኖረው ይችላል የሚል ሙያዊ አስተያየት አላቸው።
በኢትዮጵያ ውስጥ ማመን ከሚቻለው በላይ ቤቶች በውድ ዋጋ ተገንብተው በውድ እየተሸጡ ነው። ዳያስፖራውን ጨምሮም በርካቶች ንብረታቸውን ወደማይንቀሳቀስ ንብረት እየቀየሩ ነው። ይህ በራሱ የሚያመላክተው መንግስት በንብረት ላይ የሚጥለው ታክስ የተወሰነ መሆኑን ነው። ይሁንና በእነዚህና መሰል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ የንብረት ግብር መጣሉ የሚበረታታ ቢሆንም በጣም የተጋነነ የንብረት ግብር የሚጣል ከሆነ ግን የሪል እስቴት ወይንም የቤት ግንባታ ስርዓትን እንዳያቃውሰው መጠንቀቅ እንደሚገባም ያብራራሉ።
በሌላ ጎኑ ደግሞ መንግስት በንብረት ላይ የሚጥለውን ታክስ ለማካካስ ሲባል፤ የህንፃ ባለቤቶች ወይንም የቤት ባለንብረቶች በተከራዮች ላይ ዋጋ የሚጨምሩ ይሆናል። ይሄ ሲሆን በኑሮ ውድነቱ ላይ ሌላ እክል የሚፈጥር በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የማስከተል ዕድል እንዳለውም ይጠቁማሉ። ይህ ደግሞ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎችን እስከመገደብ አቅም ያለው እንደሆነም ያስረዳሉ። በመሆኑም የንብረት ግብር ሂደቱና ውጤቱ በድምር ውጤት አገራዊ ትርጉም ያለው በመሆኑም ጥንቃቄ የተሞላው አሰራር መዘርጋት እንዳለበት ይጠቁማሉ።
የህግ ባለሙያው አቶ በፍርዴ ጥላሁን በበኩላቸው፤ ምንም እንኳን በጠንካራ ህግና አሰራር ላይ የተመሰረተ ባይሆንም፤ የንብረት ግብር ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን መንግሥት መሆኑን ያስታውሳሉ። በዘመነ ደርግ ደግሞ ይህ ሥርዓት በተወሰነ ደረጃ መልኩን ቀይሮ የመሬት እና የጣሪያ ግብር ዜጎች እንዲከፍሉ ማድረግ የተጀመረ ቢሆንም በገቢ ደረጃ ግን አጥጋቢ የሚባል አለመሆኑንም ይናገራሉ። በዘመነ ኢህአዴግም እንደ ሁኔታው የግብር ክፍያ በሚል ክፍያዎች ይከናወኑ እንጂ መንግስትን በመጥቀም ደረጃ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ሆኖም በአሁኑ ወቅት የንብረት ታክስ ጉዳይን በአዲስ መንገድ ለማየት መመከሩ ክፋት የለውም ባይ ናቸው።
የንብረት ታክስ ሲባል ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እሳቤዎችን ያዘለ መሆኑን የሚጠቁሙት አቶ በፍርዴ፤ ይህ ሥርዓት የንብረት ግብር በኢትዮጵያ ሁኔታ የጣሪያ እና ግድግዳ ግብር በሚል ቀደም ሲል በወጣ አዋጅ እስካሁን ድረስ የሚከፈልበት አግባብ የነበረ ሲሆን መንግስት የሚያገኘው ጥቅም እጅግ አነስተኛ የሆነበት አሰራር ነው።
በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሰዎች የጣሪያ እና ግርግዳ በሚል ከሚከፍሉት እጅግ ዝቅተኛ ገንዘብ ውጭ ንብረቱ የራሳቸው በመሆኑና በዚያው ልክ በሚያገኙት ጥቅም ግብር አለመክፈላቸው አግባብ እንዳልነበር ይጠቁማሉ። በዘመነ ኢህአዴግም ይህ ህግ ጠንካራ መሠረት ኖሮት አገር እና ህዝብ የሚጠቀምበት ሥርዓት ሳይዘረጋ መቆየቱን ያስታውሳሉ። ታዲያ ይህ በመቅረቱ አገር ማግኘት ከነበረባት ጥቅም ብዙ ቢሊዮን ብሮችን ማጣቷን ይጠቁማሉ። የንብረት የግብር ዓይነት በአሁኑ ወቅት አንዱ የገቢ ማግኘት ስልት ተደርጎ መወሰዱና በአሁኑ ወደ ትግበራ የሚያስገቡ ምዕራፎችን ለመዳሰስ መሞከሩ የሚበረታታ ነው፤ እንዲያውም እጅግ በጣም የዘገየ ጉዳይ ስለመሆኑም ያብራራሉ።
አቶ በፍርዴ እንደሚሉት፤ በየትኛው ዓለም መንግስታት ገቢያቸውን የሚሳድጉበትን አማራጭ በሰፊው ይመለከታሉ። ይሁንና በምን ሁኔታ እና አግባብ እንጠቀም የሚለው ግን ፈተና ሊሆንባቸው ይችላል። በዚህ አግባብም የኢትዮጵያ መንግስት የንብረት ታክስን ተግባር ላይ ለማዋል ማሰቡ የሚበረታታ መሆኑን በመጠቆም ምን ዓይነት ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ የሚለውን ግን በጥልቀት ማሰብ እንደሚገባ ያሳስባሉ።
የንብረት ግብር በብዛት የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረትን ያካተተ ቢሆንም በብዛት ውጤታማ የሚሆነው ግን በማይንቀሳቀሱት ላይ ስለመሆኑም ይጠቁማሉ።
በርካታ ሰዎች በስማቸውም ይሁን ካለስማቸው ከፍተኛ ሃብት ያጋበሱ ሲሆን፤ ይህ የንብረት ታክስ ግን በአግባቡ ከተሰራበት ለዚህም መፍትሄ ሊያመጣ የሚችል ይሆናል። ከዚህም በዘለለ ንብረቱ የማነው ብሎ በትክክል ለመለየትና ለመቆጣጠርም ጭምር ያግዛል። ይህ አካሄድ ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ ሊፈፀም የሚችልን የንብረት ስወራ እና ሙስናንን በማስቀረት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። የንብረት ታክስ መንግስት ገቢ ከሚያገኝባቸው በርካታ አማራጮች ውስጥ አንዱ ሲሆን፤ መሰረት ልማቶችን ለማስፋፋት፣ ከህዝቡ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ጠንካራ የፋይናንስ መሰረት እንዲኖረውም የሚያደርግ መሆኑን ያብራራሉ።
የባንክ ባለሙያው አቶ ታምራትም ሆኑ የህግ ባለሙያው አቶ በፍርዴ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ትኩረት መደረግ አለበት ሲሉ ይናገራሉ። የንብረት ታክስ ህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ አካላት የሚጠቅም ወይንም የሚጎዳ ነው ብሎ ከወዲሁ ከመበይን ይልቅ ከሁሉም በፊት የታክሱ መጠንና የስሌት አውዱ መታወቅ አለበት። በሌላ ጎኑ ደግሞ ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ይህ የግብር አጣጣልና ብያኔ የተለመደ እና በርካታ አገራትም እየተጠቀሙበት ስለመሆኑም ማወቅ ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ነው።
ይህም በመሆኑ መንግስት ከአፍሪካ ብሎም ከሌሎች አገራት ተሞክሮ በመቅሰም ወደ ተግባር መቀየር አለበት። ይሁንና በትግበራ ወቅት ፈተናዎች ሊያገጥሙ ስለሚችሉም የመውጫ መንገዶችን ከወዲሁ ማሰብ እንደሚገባም ይጠቁማሉ። የተጋነነ የንብረት ታክስ ሆነ ከመጠን የወረደ የንብረት ታክስ አጣጣልም እንዳይከሰት ከወዲሁ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል የሚል ሙያዊ ምክረ ሀሳብ አላቸው።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ጥር 16 ቀን 2015