የኢትዮጵያን እግር ኳስ ጠንቅቀው የሚያውቁ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ‹‹በሀገሪቷ ቡድን እንጂ ክለብ የለም›› ሲሉ ይሰማል። ምክንያቱ ደግሞ በዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማትም ሆነ በሀገሪቷ የስፖርት ፖሊሲ መስፈርትን የሚያሟሉ ክለቦች ባለመኖራቸው ነው። በእርግጥ እንደ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ስፖርት ላለማደጉ በዋናነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ የአደረጃጀት ችግር መሆኑ ይታወቃል። ይህ ሁኔታ በተለይ የሚስተዋለው እንደ እግር ኳስ ባሉ ስፖርቶች ሲሆን፤ ክለቦች አሁንም ድረስ ራሳቸውን የመቻል ጥረት ሲያደርጉ አይታይም ።
በመሆኑም እጅግ ከፍተኛ የሚባል ገንዘብ አሁንም ድረስ ከመንግስት ካዝና ወጥቶ ስፖርቱ ይፈሳል። ይህም ለህዝብ ሊሟሉ የሚገባቸው በርካታ መሰረተ ልማቶች እያሉ በዚህ ደረጃ ስፖርቱ ላይ መዋእለ ንዋይ መፍሰሱ ተገቢ አይደለም በሚል ለትችቶች በር ከፍቷል። የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በቅርቡ ባስጠናው ጥናት ይህንን ያረጋገጠ ሲሆን፤ በፕሪምየር ሊጉ የሚጫወቱት 16 ክለቦች (ከሁለቱ በስተቀር ሁሉም የመንግስት ናቸው) በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በየዓመቱ ፈሰስ ይደረግባቸዋል። ከዚህ ውስጥ 70 ከመቶው የሚውለው ደግሞ ለተጫዋቾች ደመወዝ ነው። ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ የተካሄደውን ጥናት የመሩት ዶክተር ጋሻው አብዛ በገለጻቸው ወቅት ይህንኑ አስገንዝበዋል።
የጥናቱ ግኝት እንደሚያመላክተው ከሆነ አንድ የሊግ ክለብ በአማካይ ለተጫዋቾች ደመወዝ ብቻ 40ሚሊየን ብር ያወጣል። ይኸውም በክለቡ ከሚታቀፉት 25 ተጫዋቾች ቢባዛ በዓመት አንድ ክለብ 1ነጥብ6 ሚሊየን ብር ወጪ ያደርጋል ማለት ነው። ይህ ቁጥር ሲሰላም አንድ ተጫዋች በወር የሚያገኘው ደመወዝ 133ሺ334 ብር ወይም 2ሺ667ዶላር (1ዶላር በ50 ብር ቢተመን) ይደርሳል። ይኸው በአፍሪካ ካሉ የሊግ ክፍያዎች በጥቂቶቹ ተበልጦ ከምስራቅ አፍሪካ በቀዳሚነት እንዲቀመጥ ያስችለዋል። ደመወዝን ጨምሮ በአጠቃላይ የሊጉ ክለቦች ዓመታዊ በጀት ሲደማመርም እስከ 1ቢሊየን ብር ይደርሳል። በመሆኑም ልማትን ያማከለ የደመወዝ ክፍያ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ነው በጥናቱ ምክረ ሃሳብ የተመላከተው።
ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብም የሚመደበው ከመንግስት ካዝና በመሆኑ፤ በጥናቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ይህ የገንዘብ ምንጭ ዘላቂነትና ተጠያቂነትን በተላበሰ መልኩ መስመር መያዝ እንደሚገባውም ነው የገለጹት። ይኸውም ሊሆን የሚችለው ክለቦቹ ራሳቸውን ለመቻል ጥረት ካደረጉ አሊያም የተጫዋቾች የደመወዝ ጣሪያ ሲወሰን ነው። ነገር ግን በኢትዮጵያ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም። ጥናቱ በቀረበበት መድረክ ተሳታፊ የሚመለከታቸው አካላትም ክፍያው በጥናቱ ላይ ከተገለጸውም እንደሚልቅ ጠቁመዋል። በመሆኑም ክፍያን በሚመለከት የህግ ማዕቀፍ እንዲሁም ሀገር በቀል የተጫዋቾች ክፍያና ዝውውር ስርዓት ማበጀት ተገቢ ነው። በተጨማሪም መንግስት ላወጣው ወጪ ኦዲት ማድረግ አስፈላጊ ሲሆን አክሲዮን ማህበሩም የክለቦቹን ገቢና ወጪ የመፈተሽ ኃላፊነት እንዳለበት ተጠቁሟል።
ሌላው ከዚህ ጋር ተያይዞ ከተሳታፊዎች የተነሳው ሃሳብም የተጫዋቾች ክፍያ ሊጋነን የቻለው የሊጉ ክለቦች ወጣት ተጫዋቾችን በማሳደግ ሳይሆን በዝውውር ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው። በወኪሎችና በደላሎች የሚከናወነው አግባብ ያልሆነ አሰራር ንረቱን ከማምጣት ባለፈ ገንዘቡ በትክክል ተጫዋቾች ጋር ስለመድረሱም አጠራጣሪ ሁኔታዎች አሉ። ስፖርቱን በበላይነት የሚመራው ፌዴሬሽንም ቢሆን የካፍ መመሪያዎችን በትክክል እየተገበረ አይደለም። በመሆኑም ጥናቱ እንዲሁም የሊጉ አክሲዮን ማህበር እነዚህን ጉዳዮች በተጨማሪነት እንዲያጤናቸው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ መቶአለቃ ፈቃደ ማሞ፤ የፋይናንስ ችግር የክለቦችን ህልውናን ከሚፈትኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ ክለቦች ከመንግስት በሚያገኙት ድጎማ ይቀጥላሉ ወይስ መጠነኛ ገቢ በማመንጨት ህዝባዊ ይሆናሉ የሚለው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል። መቶ አለቃ ፍቃደ አክለው እንደገለጹት፣ ክለቦች ራሳቸውን የማይችሉ ከሆነም ላለፉት ዓመታት ሲንገዳገድ የቆየው እግር ኳስ በነበረበት ይቀጥላል። በመሆኑም ራሳቸውን የሚችሉና ገቢ የሚያመነጩ ክለቦች ማቋቋም አስፈላጊ ነው፤ ለዚህም መሰል ጥናቶች ከፍተኛ ሚና አላቸው። ካልሆነ ግን በቅርብ ጊዜ ውስጥ የስፖርት ቤተሰቡ የሚመኘውን የዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎ ቀርቶ በሀገር ውስጥ ውድድሮች የሚኖራቸው ተሳትፎም ጥያቄ ውስጥ የሚገባበት እድል ሰፊ ነው። በመሆኑም አክሲዮን ማህበሩ ባስጠናው ጥናት ላይ ባለድርሻ አካላቱ የሰጡትን አስተያየት እንደ ግብዓት በማካተት ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቶ በቅርቡ ወደ ተግባር ለመግባት ጥረት እንደሚያደርግ የቦርድ ሰብሳቢው አረጋግጠዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 15/2015