ገና በለጋ እድሜያቸው የድህነትን ክፉ ገጽታ ተመልክተዋል። የማጣት አስከፊ ክንድ እየደቆሳቸው፣ በከባድ ድህነት ከተጎሳቆሉ መንደሮች ነው የተገኙት። ችግሮቻቸውን ዋጥ አድርገው በትንንሽ እግሮቻቸው ኳስን በአቧራማ ሜዳዎች ሲያንከባልሉ ለተመለከታቸው ዛሬ የደረሱበት የስኬትና የሃብት ማማ ላይ ይቀመጣሉ ብሎ ሊገምት አይችልም። ሆኖም እንደ በርካቶቹ የእግር ኳስ አለም ፈርጦች ሁሉ ችግሮቻቸውን በስፖርት አሽቀንጥረው በመጣል ክፉውን የድህነት ህይወት ድል ነስተዋል፡፡ ከታላቁ የእግር ኳስ ሊቅ ፕሌ እስከ ዘመናችን የእግር ኳስ ቁንጮ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ትላንታቸው እንደቋጥኝ በከበደ ድህነት የተጫነው ነበር፡፡ ለችግሮች እጅ አለመስጠትና ነገ ትልቅ ደረጃ ደርሳለሁ ብለው በውስጣቸው ያሳደሩት የመንፈስ ጥንካሬ ግን ጥሎ አልጣላቸውም። ይህም የግል ህይወታቸውን በኢኮኖሚ ከመቀር አልፎ የበርካቶችን ተስፋ ለማለምና ከወደቁበት ለማንሳት አስችሏቸዋል።
ስፖርት በዓለም ላይ ካሉና ከፍተኛ ገንዘብ ከሚያስገኙ ዘርፎች መካከል አንዱ እንደመሆኑ በርካቶች ከተጣባቸው ድህነት ለመለያየት የሚመርጡት መንገድ ነው፡፡ የዛሬዎቹ ከዋክብትም ሆኑ ነገን በተስፋ ለሚያልሙ ወጣት ስፖርተኞች፤ ግባቸው በሚወዱት ስፖርት ስኬታማ መሆን ብቻም አይደለም። ህይወታቸውን መለወጥም ትልቁ አላማቸው ነው። ኬታቸውም በዚህ ብቻ አይገታም፤ እነርሱ ባለፉበት መንገድ እየተፈተኑ ለሚገኙ ምንዱባን በመድረስ ማህበራዊና ሰብዓዊ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ ስፖርት ከአካላዊ እንቅስቃሴና የውድድር ምድረክነቱ ባለፈ የሰዎችን ህይወት በመለወጥ እንዲሁም ተስፋን በማስረጽ ከፍተኛ ሚና ያለው ለመሆኑም ከዚህ በላይ ምስክር አያሻም፡፡
ስፖርት ህብረተሰብን በማነቃቃት እንዲሁም ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ያለውን ብርቱ ክንድ የተገነዘበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ‹‹ስፖርት ለልማትና ሰላም›› በሚል ርዕስ ስትራቴጂ በማዘጋጀት እየሰራበት ይገኛል፡፡ በዓለም ላይ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ረድኤት ለሚያስፈልጋቸው አካላት ከሚያውሉ ልባሞች መካከል ስፖርተኞች ተጠቃሽ ናቸው። ከእነዚስ የስፖርቱ ዓለም ኃያላን መካከልም የምንጊዜም ተቀናቃኞቹ ሊዮኔል ሜሲ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በዚህም በእግር ኳስ ችሎታቸው ባሻገር ለብዙዎች ተምሳሌት ለመሆን ችለዋል፡፡
ሁለቱ የእግር ኳስ ፈርጦች በተለያዩ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ውስጥ አምባሳደር በመሆን ከመስራት ባለፈ በግላቸውም ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በማስገንባት ይታወቃሉ፡፡ ዓለም የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለማጥፈት ሲያደርግ በነበረው ርብርብ ላይም ሁለቱ ተጫዋቾች የነበራቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማስታወስ ይቻላል፡፡ ሁለቱ ተጫዋቾች በየፊናቸው ከ1ነጥብ 1ሚሊየን በላይ ዶላር ከመለገስ ባለፈ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሆቴሉ ለማገገሚያነት እንዲውል አድርጓል፡፡
በቅርቡ የዓለም ዋንጫን ያሳካው ሜሲ እአአ ከ2004 ጀምሮ በዩኒሴፍ በገንዘብ እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ድጋፉን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፤ እ.አ.አ ከ2010 ጀምሮ ደግሞ አምባሳደር በመሆን ሰርቷል፡፡ በዚህም በኤችአይቪን በመከላከል፣ በትምህርት እንዲሁም በአካልጉዳተኛ ህጻናት ዙርያ በርካታ ስራ ማከናወን ችሏል፡፡ አስደናቂው ተጫዋች ከዚህም ባለፈ የራሱን የእርዳታ ድርጅት በማቋቋም በጤና፣ በትምህርት እንዲሁም በታዳጊዎች ስፖርት ላይ ይሰራል፡፡ የጤና እክል ያለባቸው ህጻናት ባሉበት ድረስ በመሄድ ከእርዳታው ባለፈ ተስፋን በመስጠትም ምስጉን ስም መትከል የቻለ ተጫዋች ነው፡፡ በተወለደበት አካባቢ የሚገኙ የታዳጊዎች እግር ኳስን፣ ክለብን እንዲሁም የአርጀንቲናን የእግር ኳስ ማህበር በገንዘብ በመርዳትም ይታወቃል፡፡
የተጫዋቹ ቀና ልብ አሁን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ የዞረ ሲሆን፤ ዓይነ ስውራን ዜጎችን ለመርዳት የተቋቋመውን ኦርካም ቴክኖሎጂ ጋር በጋራ ለመስራት መስማማቱ ከሰሞኑ ተሰምቷል። ቴክኖሎጂው በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ለመለወጥ እንዲሁም ህልሞቻቸውን እንዲያሳኩ የሚሰራም ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የቀዳማዊ እመቤት ጽህፈት ቤት የዚህ ቴክኖሎጂ ውጤት የሆነ 2ሺ መነጽሮችን አስረክቧል። ተጫዋቹም ይንን ንቅናቄ በመቀላቀሉ ክብር የሚሰማው መሆኑንም በማህበራዊ ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
ሌላው መልካም ልብን የታደለና ለሌሎች ችግር በመድረስ የሚታወቀው ተጫዋች ክርስቲያኖ ሮናልዶም የማይነጥፍ የእርዳታ ስራን ለዓመታት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ የተጫዋቹ ደግ ልብ ብዙዎች የሚመኙትና የጠንካራ ስራ ውጤት የሆነውን የባሎን ድ ኦር ሽልማቱን አጫርቶ በመሸጥ ለበጎ አላማው እስከማዋል ይደርሳል፡፡ በተፈጥሯዊ አደጋ ለተጎዱ ሰዎች ከመድረስም ባለፈ ለካንሰር ማዕከላትንና ሆስፒታሎች የገንዘብ ድጋፍ በማድረግም ይታወቃል፡፡ ከተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመሆንም በሱስ ለተጎዱ ህጻናት፣ ኤችአይቪ ኤድስ፣ ወባ እና ከመጠን በላይ ለሆነ ውፍረት የተጋለጡ ሰዎች ላይም ይሰራል፡፡ የሴቭ ዘ ቺልድረን አምባሳደር የሆነው ሮናልዶ በዚህ ምግባረ ሰናይ ተግባራቱም ዕውቅና ማግኘትም ችሏል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም