ፋሲካ እየደረሰ ነውና “እንኳን አደረሳችሁ!” ልበል … በጣም ፈጠንኩ መሰለኝ፤ … ግዴለም 10 ቀን ምን አላት? … እንኳን አደረሳችሁ! …
ፋሲካን ጨምሮ ሌሎች በዓላት ሲደርሱ በከተማው ውስጥ የሚታየው ግርግር “10 ቀን ጨለማ ሊሆን ነውና የሚያስፈልገውን ነገር ቀድማችሁ አዘጋጁ” የተባለ ይመስል እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ ዶሮን ጨምሮ ዶሮውን ወደምግብነት ለመቀየር የሚያገለግሉ ግብዓቶችን በብዙ ሰዎች እጆች ላይ ማየት የተለመደ ነው፡፡ እኔ ዶሮን ጠቀስኩ እንጂ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች የበሬና የበግ መነኻሪያዎችም ይሆናሉ፡፡
በተለይ ደግሞ የፋሲካ በዓል ሲደርስ የሚደረገው ዝግጅት “የሁለቱን ወር ፆም በአንድ ቀን ለመበቀል” የሚደረግ ዘመቻ ይመስላል፡፡ ለወትሮውም ቢሆን ውጣ ውረድን መገለጫዋ ያደረገችው አዲስ አበባ በበዓል ሰሞን ይብስባታል፡፡ እንዲያው ለመሆኑ ለዓድዋ ጦርነትስ እንዲህ ዓይነት ዝግጅት ተደርጎ ይሆን? አይመስለኝም!
በዓላቱ የሚደረገው ዝግጅትና ሽር ጉዱ መብላትና መጠጣት የበዓል ሰሞን ብቸኛ አጀንዳዎች ሆነው የተወሰኑ ያስመስላቸዋል፡፡
በተለይ በዓሉ የሚከበረው ከጾም ጊዜያት በኋላ ከሆነ በበዓሉ ዕለትና በበዓሉ ሰሞን የከተማውን ሬስቶራንቶች ከሚያጨናንቃቸው ሰው መካከል አብዛኛው በጾሙ ያልተሳተፈው (ያልጾመው) ነው ይባላል፡፡ እኔ’ማ አንዳንድ ጊዜ “ከበዓሉ በኋላ ምግብ መብላት በአዋጅ ይከለከላል እንዴ?” ብዬ እራሴን እጠይቃለሁ፡፡
ሌላው ደግሞ በበዓላት ሰሞን ከምንታዘባቸው ጉዳዮች አንዱ የመገናኛ ብዙኃን ፕሮግራሞች ናቸው፡፡ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ለበዓላት ሰሞን የሚያዘጋጇቸውና የሚያሰራጯቸው ፕሮግራሞች በይዘትም ሆነ በአቀራረብ ተመሳሳይና ተደጋጋሚ ናቸው፡፡ እስኪ ጥቂቶቹን እንመልከት …
የበዓሉ ቀን ከመድረሱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የሚደመጡት የፕሮግራም ማስታወቂያዎች እንዲህ የሚሉ ናቸው …
1. “ … ፕሮሞሽን ከ … ቴሌቪዥን ጋር በመተባበር የሚያቀርበው ልዩ የበዓል ፕሮግራም በበዓሉ ቀን በ…ሰዓት ይቀርባል…”
2. “ … ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ከ … ሬዲዮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ልዩ የአውዳመት መሰናዶ በ … ሬዲዮ ጣቢያ … በፕሮግራሙ መጠጥን ጨምሮ በርካታ አጓጊ ሽልማቶች ስለሚኖሩ ፕሮግራሙ እንዳያመልጣችሁ …” ወዘተ.
ቀኑ ደርሶ ማስታወቂያ የተሰራላቸውን የበዓል ፕሮግራሞች የማዳመጥና የመመልከት እድል ከገጠማችሁ ተመሳሳይ የሆነ ይዘት ካላቸውና አሰልቺ ከሆኑ ዝግጅቶች ጋር ለመፋጠጥ ትገደዳላችሁ፡ ፡ እንደአሸን የፈሉት … ፕሮሞሽን/ሚዲያና ኮሙኒኬሽን የሚባሉ “ድርጅቶች” ከንግድ ተቋማት በሚያገኙት የስፖንሰርሺፕ ገንዘብ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን “ፕሮግራሞች” በላይ በላዩ ይደራርቧቸዋል፡ ፡
የፕሮግራሞቹ ይዘት ከሙዚቃና አስቀያሚ በሆነ መንገድ ከሚቀርብ አሰልቺ ቃለ ምልልስ አያልፍም፡፡ “አርቲስት …ን ጋብዘነው/ጋብዘናት ከእርሱ/ከእርሷ ጋር አጠር ያለ ቆይታ እናደርጋለን …” ይሉና አብዛኛውን የፕሮግራሙን ሰዓት ይሸፍኑበታል፡፡
ከዚያማ ምኑ ቅጡ! በየመሐሉ ሽልማት ይባልና ጥያቄ መሰል ነገር ይጠየቃል … መልሱ ይመለስ አይመለስ ችግር የለም፡፡ ጥያቄውን እመልሳለሁ ብሎ የሞከረ ሰው ሞልቶ ከተረፈው የቢራ ምርት ሁለት ወይም ሦስት ሳጥን ቢራ ይበረከትለታል፡፡ መገናኛ ብዙኃኑም ገንዘብ የሚያስገኝ ይሁን እንጂ ስለ ፕሮግራሙ ይዘት፣ ጥራትና ፋይዳ የሚጨነቁ አይመስሉም፡፡
እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው ነገር “የበዓል ፕሮግራም” ተብለው በሬዲዮና በቴሌቪዥን ከሚቀርቡ ዝግጅቶች መካከል አብዛኞቹ ስፖንሰር የሚደረጉት በቢራ አምራች ድርጅቶች ነው፡፡
የአልኮል መጠጦች በብሮድካስት በመገናኛ ብዙኃን ያለምንም ገደብ ሲተዋወቁ የቆዩበት አሰራር ገደብ ተጥሎበታል፤ ይህም አሰራር ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ተግባራዊ ስለሚደረግ “የበዓል ፕሮግራም” ተብለው በሬዲዮና በቴሌቪዥን የሚቀርቡ ዝግጅቶች ምን እንደሚውጣቸው አላውቅም፡፡
እንዲያው ይኸ የአልኮል መጠጦች በብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን ያለምንም ገደብ ሲተዋወቁ የቆዩበት አሰራር ላይ ገደብ የሚጥለው አዲሱ አዋጅ”‹ልዩ የበዓል መሰናዶ” እየተባሉ የሚያላግጡብንንና መሰሎቻቸውን የገንዘብ ምንጫቸውን በማድረቅ እነዚህን “ፕሮግራሞች” ከገበያ አስወጥቶ ረፍት ይሰጠን ይሆን?!
እስኪ አሁን ደግሞ በበዓላት ሰሞን በሬዲዮና በቴሌቪዥን ጣቢያዎች የምንሰማቸውን ዜናዎች በጥቂቱ እንመልከት፤
1. “ሕዝበ ክርስቲያኑ/ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ …”
2. “ኅብረተሰቡ በዓሉን ያለምንም የመብራት ችግር እንዲያሳልፍ ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የመብራት ኃይል መስሪያ ቤት አስታወቀ …”ወዘተ.
ጥያቄ አለኝ … ሕዝበ ክርስቲያኑ/ሙስሊሙ የተቸገሩ ወገኖችን መርዳትና ማሰብ ያለበት በበዓላትን ቀን ብቻ ነው እንዴ? እንዲህ የሚልስ የኃይማኖት አስተምህሮ አለ? መገናኛ ብዙኃኑስ እንዲህ ዓይነት ዜናዎችን ደጋግሞ ማስተጋባት የሚሰለቻቸው መቼ ነው?
የመብራት ኃይል ደግሞ በጣም ያስገርማል። መብራት ጠፍቶ መዋል በበዓላት ቀን እንደሚብስ መብራት ኃይል አያውቅም እንዴ?
እግረ መንገዴን አንድ ነገር ልጠቁማችሁ … የፋሲካ በዓል ከ10 ቀናት በኋላ ይከበራል፡፡ ሰሞኑን ከላይ ለተጠቀሱት ዜናዎችና ማስታወቂያዎች በመገናኛ ብዙኃን ተደጋግመው መደመጣቸው አይቀርምና ራሳችሁን አዘጋጁ፤
አሉ ደግሞ አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን “በዓሉ የሰላም፤ የጤና፤ የፍቅር፤ የደስታ፤ የመተሳሰብ፤ የመቻቻል፤ የእድገት፤ የብልፅግና፤ የአንድነት … ይሁንልን” ብለው አሰልቺውን ያገራችንን ባለስልጣናት ንግግር የሚያስመሰግን ምኞት የሚመኙ፤ ቆይ ግን “የእድገትና የብልፅግና በዓል” ምን ዓይነት በዓል ነው?
በበዓላት ሰሞን ምርቶቻቸውንና አገልግሎ
ቶቻቸውን በመገናኛ ብዙኃን የሚያስተዋውቁ ድርጅቶች ከሚያስነግሯቸው ማስታወቂያዎች ውስጥም ብዙ አስገራሚና አስቂኝ ነገሮች ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፤ ያህል በዓሉ የሚከበረው ሚያዚያ 20 ቢሆንና በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለአንድ ወር ያህል (ለምሳሌ ከመጋቢት 25 እስከ ሚያዚያ 25 ድረስ) የሚቆይ ሽልማት ያዘጋጀ ባንክ ወይም የዋጋ ቅናሽ ያደረገ ሱፐርማርኬት የሚያስነግረው ማስታወቂያ ግንቦት 10 ወይም ሰኔ 5 ላይም እንሰማዋለን/እናየዋለን፡፡ እስኪ አስቡት “በዓሉን ምክንያት በማድረግ እስከ ሚያዚያ 25 የሚቆይ ሽልማት/ዋጋ ቅናሽ አዘጋጅተናል/አድርገናል …” የሚል ማስታወቂያ ግንቦት 10 ወይም ሰኔ 5 ላይ ስትሰሙ ምን ትላላችሁ? የእናንተን ባለውቅም እኔ ግን እናደዳለሁ፡፡
ሌላ ደግሞ አንድ ነገር ልጨምር፤ … መገናኛ ብዙኃን በበዓላት ሰሞን “እንኳን በሰላምና በጤና አደረሳችሁ” የሚሉት ነገር ብዙም አይዋጥልኝም፡ ፡ በእርግጥ ይህ መልዕክት ሰላም ርቆትና ጤና አጥቶ ለበዓሉ ቀን የደረሰውን ሰው ይመለከታል? አሁን ደግሞ አብዛኛው ያገራችን ሕዝብ ሰላም ርቆታል፡፡ ታዲያ ይህን የኅብረተሰብ ክፍል “እንኳን በሰላም አደረሰህ” ማለት ከልብ የመነጨ የደስታ መግለጫ ነው ወይንስ ሹፈት?
የበዓላት ሰሞን የስራ ሰዓት አከባበር’ማ አይወራም፡ ፡ ዘግይቶ ወደ ስራ ቦታ መግባትን፤ ከስራ ቦታ ፈጥኖ መውጣትን፤ ከነጭራሹም ከስራ መቅረትን የበዓላት ሰሞን መገለጫዎች አድርገናቸዋል፡፡ “እንኳን ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ” እንዲሉ ወትሮም ቢሆን የሥራ ሰዓት አከባበራችን አያምርበትም፡፡ በዓላት ሲጨመሩበት ደግሞ የባሰ ያስጠላል፡፡
ለማንኛውም … በድጋሚ … እንኳን አደረሳችሁ! ብያለሁ፤ መልካም በዓል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2011
በአንተነህ ቸሬ