መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች – ከአዲስ አበባ እስከ ጅማ

1990 ዓ.ም የተቀረጸው የኢትዮጵያ የስፖርት ፖሊሲ ቀዳሚ አላማ ያደረገው በየደረጃው መላውን ኅብረተሰብ በስፖርት በማሳተፍ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት ነው። ለእዚህም መላው ኅብረተሰብ በሚኖርበት፣ በሚሠራበትና በሚማርበት አካባቢዎች በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን በየደረጃው ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር በሚል ግልፅ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ይህን የፖሊሲ አቅጣጫ ስኬታማ በሆነ መልኩ ለመፈጸም የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ፅንሰ ሃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ 1996 ዓ.ም ላይ ተጠነሰሰ። ጨዋታው ገና ከጅምሩ የኦሊምፒክና የመላ አፍሪካ ጨዋታዎችን መርህ መነሻ በማድረግ ከስፖርታዊ ውድድር ባሻገር ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንድ መድረክ ተገናኝተው ባሕልና እሴቶቻቸውን እንዲለዋወጡ ታስቦ መቀረጹን ሰነዶች ያመለክታሉ።

ይህን መሠረታዊ ዓላማ መነሻ በማድረግ በ1997-98 ዓ.ም መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ቢደረግም በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ ቀርቷል። በ1998 ዓ.ም ግን ቀደም ሲል የነበረውን ጥረት በመከለስና ሁሉንም ሀገር አቀፍ የስፖርት ማህበራት አስተያየቶች በማካተት የመጀመሪያው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች 1999 ዓ.ም ላይ በ17 የስፖርት ዓይነቶች እንዲካሄድ ስምምነት ላይ ተደረሰ።

በወቅቱ በነበረው ጥናት መሠረት ኢትዮጵያ በኦሊምፒክና በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ያስመዘገበችው ውጤት፣ እያንዳንዱ ስፖርት የነበረበት የእድገት ደረጃ፣ በእያንዳንዱ ስፖርት ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የነበራቸው የመሳተፍ አቅምና የመሳሰሉት ከግምት ውስጥ ገብተው ነው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች በ17 የስፖርት ዓይነቶች እንዲካሄድ የተደረገው። በእዚህም መሠረት የመጀመሪያው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ አዘጋጅነት ከመጋቢት 2 እስከ 16 1999 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን፤ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊ ሆነዋል። በእዚህም ቀደም ሲል በቻምፒዮና መልክ በተናጠል ሲካሄዱ የነበሩ ውድድሮችን በአንድ መድረክ በማሰባሰብና በተቀናጀ መልኩ በኦሊምፒክ አምሳያ እንዲካሄዱ መሠረት መጣል ተችሏል።

በመጀመሪያው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ከ3480 በላይ ስፖርተኞችና የስፖርት ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል። አዘጋጇ አዲስ አበባ 142 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ቀዳሚ ሆና ነበር ያጠናቀቀችው። ኦሮሚያ ክልል በ115 ሜዳሊያዎች፣ አማራ ክልል ደግሞ በ57 ሜዳሊያዎች ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች የኦሊምፒክን ፍልስፍና መሠረት በማድረግ የተጀመረ እንደመሆኑ በየአራት ዓመቱ ለማካሄድ ነበር የታሰበው። በእዚህም መሠረት ሁለተኛው ጨዋታ ከመጋቢት 04 እስከ 18 2002 ዓ.ም ሲካሄድ አዲስ አበባ ዳግም የማዘጋጀት እድሎችን አግኝታለች። 250 አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ከመጀመሪያው ጨዋታ የበዛ ተሳታፊም ነበር። ኦሮሚያ ክልል፣ አዲስ አበባና አማራ ክልል በኦሊምፒክ ስፖርቶች ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዘው ነበር የፈጸሙት።

ማህበረሰቡ በመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች የመሳተፍ ፍላጎቱ በመጨመሩና መድረኩ ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራት ረገድ አስፈላጊነቱ ስለታመነበት በየሁለት ዓመቱ እንዲካሄድ ተደረገ። በእዚህም ሦስተኛው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት በአዳማ፣ አሰላና ቢሾፍቱ ከተሞች ከመጋቢት 02 እስከ 15 /2004 ዓ.ም ሊካሄድ ችሏል። 3284 ስፖርተኞችም ተሳታፊ ሆነውበታል። በ16 የኦሊምፒክ ስፖርቶች በተደረጉ ፉክክሮች ኦሮሚያ፣ አማራና አዲስ አበባ ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

አራተኛው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች በአማራ ክልል ባሕርዳር ላይ ከመጋቢት 7 እስከ 21/2006 ዓ.ም ተካሂዷል። በትልቅና ዓለም አቀፍ ደረጃ ባለው ባሕርዳር ስቴድየም ሲካሄድም የመጀመሪያ ነበር። 3470 ስፖርተኞች ተሳታፊ በነበሩበት ውድድር በኦሊምፒክና በፓራሊምፒክ ስፖርቶች አማራ ክልል ቀዳሚ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፤ ኦሮሚያና አዲስ አበባ ተከታዩን ደረጃ መያዝ ችለዋል። ቀጣዩን ጨዋታ የማዘጋጀት ኃላፊነትም ደቡብ ክልል ነበር የተረከበው።

በሀዋሳ አዲሱ ስቴድየም በተካሄደው 5ኛው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች አማራ ክልል የአጠቃላይ አሸናፊ በመሆን ሲያጠናቅቅ፤ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ሁለተኛ እና ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡

በ2010 ለሚካሄደው ውድድር አዘጋጅነቱን የትግራይ ክልል የተረከበ ቢሆንም፤ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይካሄድ ቀርቷል። ለዘጠኝ ዓመታት ተቋርጦ ዘንድሮ እንደ አዲስ በጅማ ከተማ ሲጀመር አራት አዳዲስ ክልሎችን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ4500 በላይ ስፖርተኞችን በ26 ስፖርቶች እያፎካከረ ይገኛል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You