በአለማችን ያሉ ሴቶችን በብዛት ከሚያጠቁ የካንሰር በሽታዎች አራተኛውን ደረጃ የያዘው የማህፀን በር ካንሰር ነው፡፡ ይህን በሽታ ለየት የሚያደርገው ከ80 በመቶ በላይ የሚያጠቃዉ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሃገሮች ላይ የሚኖሩ ሴቶችን መሆኑ ነው፡፡
በ2020 የተጠና ጥናት እንደሚያሳየው በዓለም አቀፍ ደረጃ 6 መቶ ሺ በላይ እናቶች በየዓመቱ ይያዛሉ ፡፡ ከእነዚህ ውስጥም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ችግሩ በተለይም ሰብ ሰሃራ ተብለን በምንታወቅ አገራት ከላይ ጡንጫው የበረታ ሲሆን ማሌዢያ ደቡብ አሜሪካና ሌሎችም ችግሩ በመጠኑ የሚታይባቸው ናቸው፡፡ በተለይም ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ እናቶች ችግሩ እንኳን ቢታወቅላቸው ወደ ህክምና ተቋም የሚደርሱት ዘግይተው በመሆኑ የሞት ምጣኔው ከፍ ያለ ነው፡፡
የማህጸን በር ካንሰር ኢትዮጵያ ውስጥም ከጡት ካንሰር ቀጥሎ ትልቁ የሴቶች ችግር ሲሆን በ 2020 የተጠና ጥናትን ዋቢ አድርገን ባገኘነው መረጃ መሰረት 7 ሺ445 ሴቶች በየአመቱ በማህጸን በር ካንሰር ይያዛሉ፡፡ የሞት መጠኑም በዛው ልክ ከፍ ያለ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጤና ሚኒስቴር በ2030 ችግሩን ሙሉ በሙሉም ባይሆን ቢያንስ ግንዛቤውን አስፍቶ ከ 20 ዓመት ጀምሮ ያሉ ሴቶች ግንዛቤው ኖሯቸው ወደጤና ተቋማት በመሄድ ምርመራውን ያደርጉ ዘንድ እየሰራ ሲሆን የጥር ወርም የማህጸን በር ካንሰር የግንዛቤ ማስጨበጫ ወር እንደሚሆኑ የተለያዩ ስራዎች በመከናወን ላይ ነው። “አስቀድሞ በመመርመር የማህጸን በር ካንሰርን መከላከልና ማጥፋት ይቻላል” በሚል መሪ ቃል እየተሰራ ይገኛል፡፡
ነገር ግን ቅድሚያ በሚሰጡ ክትባቶች እንዲሁም በግዜ አግኝቶ ለማከም የሚረዳውን (papsmear) የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምርመራ በማድረግ መከላከል ይቻላል፡፡ እኛምይህንኑ በተመለከተ በጤና ሚኒስቴር የማህጸን በር ካንሰር ፕሮግራም አስተባባሪ የማህበረሰብ ጤና ባለሙያ ታከለች ሞገስ ጋር ቆይታን አድርገናል፡፡
አዲስ ዘመን፦ የማህጸን በር ካንሰር ምንድን ነው?
ታከለች፦ በማህጸን በር ዙሪያ ያሉ የሰውነታችን ህዋሳት ከተለመደው ውጪ ያለቁጥጥር መራባት ሲጀምሩ ሲሆን ይህም በየጊዜ እያደገ የሚመጣ ቁስለትና እባጭን በማህጸን በር ላይ ሲፈጥር ነው ለበሽታው ተጋላጭ ሆነናል የሚባለው።
ለማህጸን በር ካንሰር ዋነኛው መንስኤ ማለትም 99 ነጥብ 7 በመቶው ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ነው። በነገራችን ላይ ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ማለት ኢንፌክሽን ሲሆን ኢንፌክሽኖች ደግሞ ለሌሎች የካንሰር አይነቶች መፈጠርም አስተዋጽኦን ያደርጋሉ። በመሆኑም ዋነኛው አጋላጭ ምክንያት ኢንፌክሽን ነው።
ኢንፌክሽን መሆኑ ደግሞ የበሽታው መተላለፊያ መንገድ እንዲታወቅ አስችሏል። በዚህም ለማህጸን በር ካንሰር ዋነኛ መተላለፊያ መንገዱ ልቅ የሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት ነውⵆ በማህጸን ዙሪያ ያሉ የሰውነታችንን ክፍል የሚሸፍኑ ህዋሳት ላይ የሚመጣና በልየታ ምርመራ ወቅት ባለሙያ ሊታይ የሚችል ግልጽ ለውጥ ነው። የማህጸን በር ቅድመ ካንሰር ደረጃ ላይ ያሉ ሴቶች ብዙ ጊዜ ምንም የህመም ምልክት አያሳዩም። ነገር ግን በጊዜ ታውቆ ህክምና ካላገኙ ወደ ካንሰር ደረጃ ተሸጋግሮ ከፍተኛ የጤና ጠንቅ ሊያመጣ ይችላል። እዚህ ላይ ግን የማህጸን በር ካንሰር በጊዜ ከተለየ ካንሰር ደረጃ ሳይደርስ በቀላሉ መታከምና መዳን የሚቻልበት ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ለማህጸን በር ካንሰር ትኩረት መስጠት ለምን አስፈለገ?
ታከለች፦ የማህጸን በር ካንሰር የሴቶች እንዲሁም ከፍ ያለ የማህበረሰብ የጤና ችግር መሆኑ ሲሆን በተለይም በታዳጊ አገራት በካንሰር ምክንያት ከሚሞቱ ሰዎች መካከል በማህጸን በር ካንሰር ምክንያት የሚሞቱት ሴቶች ቁጥር ከፍተኛ ነው።
ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ካንሰር ህመም ምልክቶቹ እስከሚታዩባት ያለው ሂደት በዝግታ የሚጓዝ ስለሆነ በተለይም በሽታን የመቋቋም ሀይሏ ከፍተኛ በሆነ ሴት ላይ ካንሰር ደረጃ እስኪደርስ ድረስ ከ 10 እስከ 20 ዓመት ሊወስድበት ይችላል። ለምሳሌ አንዲት ሴት በ20 ዓመቷ ከሆነ በሽታው ወደ ሰውነቷ የገባው ምናልባት ወደካንሰርነት የሚቀየረው ሴትየዋ እድሜዋ ከ35 እስከ 40 ዓመት በሚደርስበት ጊዜ ነው።
ይህ እድሜ ደግሞ ሴቶች ብዙ የሚሰሩበት የወለዷቸውን ልጆች የሚያሳድጉበት ከመሆኑ አንጻር በሽታው የሚያሳድረው ተጽእኖ ከራሷ አልፎ ቤተሰቧን ብሎም አገርን የሚጎዳ የሚሆነው በዚህ ምክንያት ነው።
አዲስ ዘመን ፦የማህጸን በር የቅድመ ካንሰር ምርመራ እንዴት ይሰጣል?
ታከለች፦ ምንም እንኳን ህመሙ ከተከሰተ በኋላ በባለሙያ በምርመራ ለመታየት ቀላል ቢሆንም እዛ ደረጃ ላይ እስከሚደርስ ጊዜ ድረስ ግን ህመሙ የያዛት ሴት ምንም ዓይነት ምልክት አታሳይም። ህብረተሰቡም ማወቅና መጠንቀቅ ያለበት ቅድመ ካንሰር ምንድነው ምርመራው የሚለውን ነው። ለምሳሌ እኔ አሁን ቀድመ ካንሰር ምልክቱ ሊኖርብኝ ይችላል ነገር ግን አለ የለም የሚለውን ሊያየው የሚችለው የሰለጠነው ባለሙያ ብቻ ነው። ካንሰር ከሆነ በኋላ ግን በጣም ሽታ ያለው ፈሳሽ። የወገብ ህመምና ሌሎች ምልክቶችን ሊታዩ ይችላሉ። ነገር ግን ቅድመ ካንሰር ላይ ምንም ዓይነት ምልክት አታሳይም፤ በዚህም ምክንይት ብዙ ሴቶችን እያጣንበት ያለ በሽታ ነው።
በመሆኑም ሁሉም ሴቶች እድሜያቸው ከ 15 እስከ 49 ዓመት ሲሆኑ ምርመራውን ማድረግ ያለባቸው ሲሆን በተለየ ሁኔታ ደግሞ በደማቸው ውስጥ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ያለባቸው ሴቶች ደግሞ ምርመራውን ማድረግ ይኖርባቸዋል።በሌላ በኩል ደግሞ የማህጸን በር ካንሰር ልየታ ተደርጎላቸው ምልክቱ ያልተገኘባቸው በተለይም ደግሞ ኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ያሉ ሴቶች እድሜያቸው 49 ዓመት እስኪሆን ድረስ በየ 2 ዓመቱ ምርመራውን ማድረግ አለባቸው።
በተጨማሪም በማህጸን በር ካንሰር ምርመራ በሽታው ሊገኝባቸው ይቻላል ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎች አስፈላጊውን ተጨማሪ ምርመራና ህክምና በትስስርና በቅብብሎሽ እንዲያኙ ማድረግ ያስፈልጋል። በምርመራው መሰረት የማህጸን በር ካንሰር እንዳለባቸው የተለዩ ሰዎች አስፈላጊው ህክምና እንዲሁም ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ እንክብካቤዎች እንደሚያስፈልጋቸው የሙያ ስነ ምግባሩ ያዛል።
አዲስ ዘመን፦ የማህጸን በር ካንሰርን እንዴት መከላከልና መቆጣጠር ይቻላል ?
ታከለች፦ ከላይ እንደገለጽነው ትልቁ የበሽታው መከላከያ ቅድመ ካንሰር ምርመራዎችን በተለይም እድሜያቸው ከ 20 ዓመት ጀምሮ ያሉ ሴቶች እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው። ቫይረሱ ከገባ በኋላ ደግሞ ወደካንሰር እንዳይቀየር የቅድመ ልየታና ህክምና ማድረግ ያስፈልጋል። በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም እድሜያቸው ከ 30 እስከ 49 ዓመት የሆኑ ሴቶች የቅድመ ልየታ ምርመራውን ማድረግ ግዴታ ያስፈልገኛል ብለው እንዲያስቡ ማድረግ ያስፈልጋል ማለት ነው።
ምናልባት በዚህ የልየታ ወቅት ሴትየዋ በሽታው ከተገኘባት አሁን ላይ በአገራችን አብዛኛው የህክምና ጣቢያ ላይ ህክምናው ስለሚሰጥ በአፋጣኝ ህክምናን ማድረግ ይቻላል። ነጻ ከሆነችም ከ3 እስከ 5 ዓመት ድረስ እየቆየች ራሷን ማወቅ ምርመራውን ማድረግ ከችግሩ ሙሉ በሙሉ ለመዳን ያግዛል።
በሌላ በኩል ግን ከ 9 እስከ 13 ዓመት ያሉ ልጃገረዶችን የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት በመስጠት ፤ከ20 ዓመት በታች ያሉ ሴቶች የማህፀን በራቸው ያልዳበረና ለኤች አይቪ መስፋፋት አመቺ በመሆኑ ሴቶች ከ 20 ዓመት በፊት የግብረ ስጋ ግንኙነት እንዳይፈጽሙ (እንዳይጀምሩ) ማስተማር፤ የማህጸን በር ካንሰር ቅድመ ልየታ ለማድረግ የሚመጡ ሴቶች የቅድመ ካንሰር መልክቱ ከተገኘባቸው በዛው ህክምናውን እንዲያገኙ ማስቻል፤ ሌሎች ለማህጸን በር ካንሰር ተጋላጭ ሊያደርጉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ማለትም ከአንድ በላይ የወሲብ አጋር መያዝና ከተለያዩ የአባላዘር በሽታ አምጪ ሁኔታዎች ራስን ማራቅ የመከላከያ መንገዶቹ መሆናቸውን ማስተማር ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፦ለማህጸን በር ካንሰር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እነማን ናቸው?
ታከለች፦ ማንኛዋም የግብረ ስጋ ግንኙነት ፈጽማ የምታውቅ ሴት ሁሉ ለበሽታው ተጋላጭ ናት። ምክንያቱም ዋነኛ መንስኤ ለሆነው ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ የመጋለጥ አጋጣሚዋ ሰፊ ስለሆነ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የበሽታ የመከላከል አቅማቸው አነስተኛ የሆኑ ሰዎች ለምሳሌ ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኝ ፤የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም የሚቀንሱ መድሃኒቶችን የሚጠቀሙ ፤ የሚያጨሱ ፤ ቀደም ብለው የቅድመ ካንሰር ምርመራውን አድርገው ራሳቸውን ማወቅ ያልቻሉ ሴቶች ይበልጥ ለበሽታው የመጋለጥ እድላቸው ከሌሎች አንጻር ሲታይ ከፍ ያለ ነው።
አዲስ ዘመን፦ የማህጸን በር ካንሰር ምልክቶቹ ምን መልክ አላቸው?
ታከለች፦ ምልክቶቹ ብዙ ናቸው፤ አንዳንድ ጊዜ በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት የደም መፍሰስ ሊያጋጥም ይችላል፤ ያልተለመደ የማህጸን ፈሳሽ በብዛት ይፈሳል፤ በሽታው እየተባባሰ ሲሄድ ደግሞ ችግሩ በተከሰተበት የማህጸን አካባቢ ላይ ህመሞች ይኖራሉ፤ በሌላ በኩልም የሆድ ህመም፣ የደረት ህመም፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ የሆድ ድርቀት ወይም ሌሎች የጨጓራና ትራክት ችግሮች፣ ሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት ፣ በዳሌ አካባቢ የህመም ስሜት መሰማት፣በወሲባዊ ግንኙነት ወቅት ህመም መሰማት ሲሆኑ እንደዚህ አይነት መልክቶችን ያየች ሴት በቶሎ ወደጤና ተቋም መሄድ ያስፈልጋታል።
በነገራችን ላይ በተለይም በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል እንደዚህ አይነት ህመም የሚታመሙ እናቶችን ከመኖሪያ ቤታቸው አርቀው ጎጆ በመስራት ከቤተሰቧ እንድትለይ ትደረጋለች። ይህ የሚሆነው ደግሞ የሚፈሳት ፈሳሽ ከባድና ሽታውም ከሰዎች ጋር አብሮ የሚያኖር ባለመሆኑ ነው። ይህች ሴት በህይወት አስካለችም እዛው ብቻዋን የሚሰጧትን እየበላች የሞቷን ቀን መጠባበቅ ይሆናል ኑሮዋ።
ይህ የሚሆነው በሽታው ሲባባስ ነው፤ ነገር ግን በሽታው እዚህ ደረጃ ላይ ሳይደርስ ለማቆም ከአንዲት ሴት የሚጠበቀው ቅድመ ምርመራን ማድረግ ብቻ ነው። ምርመራዋን አድርጋ ራሷን ካወቀች ደግሞ ህክምናውም ቢሆን በጣም ቀላል ነው።
አዲስ ዘመን ፦ የካንሰር ችግሩ የተገኘባቸው ሰዎች የሚያገኙት ህክምና ምን መልክ አለው?
ታከለች፦ እንግዲህ ሰዎች ቀድመው በመጠንቀቅ በየጊዜው ምርመራቸውን በማድረግና ራሳቸውን በማወቅ መከላከል ይችላሉ። ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ በሽታው ከተገኘ እንደ አገር በሶስት አይነት መንገድ ህክምናው ይሰጣል። እዚህ ላይ ግን እነዚህ ህክምናዎች ውጤታማ የሚሆኑት ሴትየዋ ምልክቱ ታይቶባት ሳትዘገይ ወደህክምና ተቋም የምትመጣ ከሆነ ብቻ መሆኑም ሊታወቅ ይገባል።
ህክምናዎቹ አንዱ በማቀዝቀዝ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከፍ ባለ ሙቀት ማከም ነው ፤ሶስተኛው ደግሞ የቅድመ ካንሰር ምልክት ወይንም ደግሞ ቁስለት ያለበትን ቦታ ቀፎ በማውጣት የሚደረግ ህክምና ነው። እነዚህ ህክምናዎች በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ እንኳን በ107 ጤና ጣቢያዎች ላይ ይሰጣሉ። ሁሉም የሰለጠነ ባለሙያ ከሙሉ መሳሪያው ጋር ያላቸውም ናቸው።
አዲስ ዘመን፦ ጤና ሚኒስቴር በሽታውን በመከ ላከሉ ግንዛቤውን በማስፋቱ በኩል ምን እየሰራ ነው?
ታከለች፦ መንግስት የማህጸን በር ካንሰርን ለመከላከል በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ነው፡፡ ትኩረት የተሰጠበት ምክንያትም አሁን ላይ የማህጸን በር ካንሰር የማህበረሰባችን ዋነኛ ችግር እየሆነ በመምጣቱ ሲሆን ስራዎችንም በተቀናጀ መልኩ ለመስራት የመከላከሉንም ቅድመ ካንሰር ምርመራውንም እንዲሁም በሽታው ከተገኘ በኋላም ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች በተለይም ሴቶች የጠራና ግልጽ የሆነ መረጃን እንዲያገኙ ሰፋፊ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የማህጸን በር ካንሰርን መከላከል ያስፈልጋል ብሎ እ.ኤ.አ በ 2009 በ5 ጤና ተቋማት ላይ ከፓዝ ፋይንደር ጋር በመቀናጀት የጀመረው ስራ እ.ኤ.አ በ 2013 ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን እ.ኤ.አ 2015 ላይ ፕሮግራሙን ለህዝብ ይፋ ከማድረጉም በላይ እ.ኤ.አ በ 2022 ወደ 4 ሺ 218 የህክምና ተቋማት አገልግሎቱን የሚሰጡበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ሆኗል። ይህ ደግሞ በየወረዳው ቢያንስ አንድ ጤና ተቋም አገልግሎቱን መስጠት በሚችልበት ሁኔታ የሰለጠነ የጤና ባለሙያ እንዲሁም መሳሪያ እንዲሟላ ተደርጓል።
አዲስ ዘመን ፦ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዚህን ያህል ደረጃ ጥረት ካደረገ የህብረተሰቡ ግንዛቤስ ምን ደረጃ ላይ ነው ማለት ይቻላል?
ታከለች፦ እንግዲህ የግንዛቤው ሁኔታ በጣም ገና ቢሆንም በ2007 ዓም በተጠና ጥናት ግን የካንሰር ልየታ የተደረገላቸውና በዳታ ቋት የገቡ ሴቶች ቁጥር 33ሺ 502 እናቶች ሲሆኑ አሁን 2014 ላይ ደግሞ ቁጥራቸው ወደ 3መቶ 50 ሺ እናቶችን መመርመር መቻሉን መረጃዎች ያሳያሉ። ይህም ቢሆን ግን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፈጠረው ምቹ ሁኔታ እንደርስበታለን ብሎ ካስቀመጠው ግብ አንጻርም መጠኑ በጣም አነስተኛ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ለመረጃው እናመሰግናለን።
ታከለች ፦ እኔም አመሰግናለሁ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም