የወራቶች መጀመሪያ መስከረም ወር ላይ ነው። የዝናብ ወቅት አብቅቶ ደማቋ ፀሀይ ፈራ ተባ እያለች የምትወጣበት ጊዜ። ሙቀቷ በስስት ደበስበስ እንደሚያደርግ እንደ የእናት እጅ ለስለሶ በደስታ ጣሪያ ላይ የሚያንሳፍፍ አይነት ፀሀይ ፍንትው የምትልበት ነው ወርሀ መስከረም። ሜዳው ተራረው ሸንተረሩ አረንጓዴ ካባ በቢጫ ወርቀ ዘቦ ጥልፍ ደርበው በውበት የሚገማሸሩበት ጊዜ ነው። ብዙዎች የአዲስ አመት ተስፋ የሚሰነቁበት፣ አንዳንዶች ደግሞ ያለፈውን መጥፎ ጎናቸውን ለማረም ቃል የሚገቡበት፣ የዓመት መጀመሪያ ወር ነው።
ወርሀዊዎቹ ሀምሌና ነሀሴ ጎርፍ ያደፈረሳቸው ወንዞች እየቀነሱ የሚሄዱበት፤ ውሃውም እየጎደለ ዘመድ ከዘመዱ የሚጠያየቅበት ውብ ወር ነው መስከረም። ፍጥረት በሙሉ በአዲስ ተስፋ የሚሞላበት፤ ከብቶቹ በለመለመው መስክ ግጠውና ጠግበው የሚፈነጩበት ፤ ሰው እሸትን መቋደስ የሚጅምርበት አይን በልምላሜ ተስፋ የሚመላበት ወር ነው። የበዓላት መደራረበ ያለበት፤ ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱበት ተማዎችም ከትምህርት ገበታቸው ጋር ተገናኝተው የዘመኑን ትምህርት አሀዱ የሚሉበትም ጊዜ ነው። ስለ መስከረም ብዙ ማለት ይቻላል። የዛሬው መነሻዬ ግን ያንን ሁሉ መዘርዘርና መስከረምን ማወደስ አልነበረም። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንደሚባለው ሆነና በመስከረም ውስጥ የሆነን ክስተት አስመልክቶ ከፍትህ ሚኒስቴር የፌስ ቡክ ገፅ ያገኘሁትን ላካፍላችሁ ነው።
ወቅቱ መስከረም 15 ቀን የመስቀል በዓል ዋዜማ ነበር። አዲሱ አመት መጀመሪያ እንደመሆኑ ትምህርት በአዲስ መንፈስ የተጀመረበት ጊዜ ነበር። የትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ፅድት ብሎ ለተማሪዎች መማሪያ የሚሆን የትምህርት መርጃዎች የተሟሉበት አመት ቀርቦላቸው፣ በምገባ ፕሮግራም ቁርስና ምሳቸውን እየበሉ በደስታ ትምህርታቸውን በናፍቆት ስሜት ቀጥለዋል። መስከረም 15 ቀን ግን ለተማሪዎቹም ሆነ ለመምህራኑ በአጠቃላይ ለትምህርት ማህበረሰቡና ለወላጆች ጭምር ጥሩ ዜና አልተሰማም።
ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ በትምህርት ቤቱ ቀድሞ ይማር የነበረ ወጣት ከተማሪዎች ጋር ተቀላቅሎ የግቢውን ሁኔታ ሲያጠና ሰንብቷል። ጥናቱንም ለመልካም ሳይሆን ለስርቆት ለማዋል አስቧል። ወጣቱ አዲስ አመትን የጀመረው በሌብነት እንዴት ሊከብር እንደሚችል እቅድ አውጥቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ ሰነባብቷል። ከሞባይል ነጠቃ ጀምሮ እስከ ትልቅ ዘረፋ ሊያደረግ ያሰበው ወጣት ከባዱን ዘረፋ ቀድሞ ከተማረበት ትምህርት ቤት ለመጀመር በመወሰን ወደእዚያው አምርቷል። በትምህርት መጀመሪያው ቀን ምሽትም ለመዝረፍ ዝግጅቱን አጠናቆ መምሸቱን ይጠባበቅ ጀመር።
በዝርፊያ የተሰማራው ወጣት
አባት እቁበጽዮን ግርማ በወጣትነት ዘመናቸው ላባቸውን አፍስሰው ባገኙት ጥሪት ጎጆ ቀልሰው በደስታ ይኖሩ ነበር። በላባቸው የሚያገኙትን ገንዘብ አብቃቅተው የመኖር ጥበብ የታደሉ፤ በልካቸው መኖርን የተማሩ ታላቅ አባት ነበሩ። ሀቀኝነት መርሃቸው የሆነ ለወዳጅ ጎረቤት ምሳሌ የሆኑ ተጠሪ ሽማግሌ ነበሩ። ከወለዷቸው አምስት ልጆች መካከል አራቱም የአባታቸውን ፈለግ ተከተለው ገሚሱ በትምህርት ከፍ ሲል ገሚሱ ደግሞ በስራ ራሳቸውን የቀየሩ ጠንካራ ዜጎች መሆን ችለዋል።
መቼስ ከአንድ ቤት አንድ በጥባጭ አይጠፋም ይሉት ነገር ደርሶባቸው ልጇቸው ናሆም መማርም መስራትም የማይፈልግ ልጅ ሆነ። ናሆም የቤቱ አምስተኛ ልጅ ስለነበር ከፍ ያሉት ወንድሞቹ እያሞላቀቁ ነበር ያሳደጉት። በአነስተኛ ኑሮ አንዳንዴም ፆምም እያደሩ ያደጉት ወንድሞቹ ታናሻቸው ያንን እንዳያይ በትምህርቱ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ የኑሮን ሸክም እነሱ ተሸክመው ቀለል ያለ ኑሮ እንዲኖር ያደርጉ ነበር።
በትንሽ እድሜው ጎበዝ የነበረ ቢሆንም ከፍ እያለ ሲሄድ ግን እንደ ሀብታም ልጆች መልበስ መኖር ያምረው ጀመር። ከአባቱም ከወንድሞችም በለስ ሲቀናው አራዳ በሚሉት አገላለጽ “ፈልጦ” ወይም ለምኖ፤ ካልሆነ ደግሞ ሰርቆ ካላቅሙ ውድ ካፌዎችና ሬስቶራንቶች መዞር ስራው አደረገ።
እዛም ከሚያያቸው ልጆች ጋር ለመወዳደር የማይፈነቅለው ድንጋይ አልነበረም። ትምህርቱንም ወደ ጎን ትቶ በአቋራጭ የሚከብርበትን መንገድ ያፈላልግ ጀመር። ከካፌና ሬስቶራንት አልፎ በየጫትና ሺሻ ቤቱ መመሽግ ከጀመረ ሰነባበተ። በዚህም አጋጣሚ ካገኛቸው ልጆች ጋር አንድ ላይ በመሆን ወደ ስርቆቱ ለመግባት ወሰነ። ውሳኔውንም በተግባር የቀየረው ወጣት ሳይያዝ ለአመታት በመቆየቱ ህጋዊ ስራው እየመሰለው ሄደ።
ያልጠበቁት አጋጣሚ ለህይወት መነጠቅ
ጎስቆል ደከም ያሉ አባት ናቸው። እድሜያቸው ከጉልምስና ባያልፍም ህመምና ድካም የደቋቆሳቸው አባት ቀለል ያለ ስሜት ሲሰማቸው አይታይም። ዘወትር ከሚያነቡት የፀሎት መጽሐፋቸው ውጭም ከሰው ጋር ብዙ የማይነጋገሩ ድምፃቸው የማይሰማ ሰላማዊ ሰው ናቸው።
የጥበቃ ስራ በሚሰሩበት ትምህርት ቤት የሚማሩትን ልጆች እንደወለዷቸው ልጆች በስስት ነበር የሚመለከቷቸው። ሲወጡ ሲገቡ በአባታዊ ፍቅር ከማናገር ያለፈ እንኳን ዱላን ቁጣን አሳርፈውባቸው አያውቁም ነበር። ሁሉም የግቢው ማህበረሰብ የሚያከብራቸውና የሚወዳቸው አዛውንት ናቸው።
እኚህ ተወዳጅ አባት የምሽት ተረኛ በሆኑበት በመስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም ነበር በስራቸው ላይ እያሉ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ባልተመለደ ሁኔታ እንቀስቃሴ የሰሙት። ቦታው ገላን ቁጥር ሁለት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው። የመስኮት መሰበር ድምፅ ከሰሙ በኋላ ወደ ቦታው ፈጥነው የደረሱት አባት ከአንድ ኮምፒውተርና የኮምፒውተር እቃዎች ከያዘ ልጅ ጋር ድንገት ተገጣጠሙ።
እሳቸው በድንጋጤ ልጁን ሲመለከቱት የሚያውቁት ወጣት ሆነባቸው። ያኔ “ ልጄ አትሳሳት እባክህ አቁም” እያሉ በፀባይ ልጁ ችግር ውስጥ እንዳይገባ ይለምኑት ገቡ። በፍፁም አባታዊ ፍቅር ልጁን ከስህተት እየታደጉት ያሉትን አባት ሃሳብ ከመጤፍ ሳይቆጥር በቆሙበት ባላሰቡትና ባልተዘጋጁበት ሁኔታ ጥቃቱን ይሰነዝርባቸው ጀመር።
ያልታሰበ ውርጅብኝ
መስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ልዩ ቦታው ገላን ቁጥር ሁለት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ነው። ወጣት ናሆም የትምህርት ቤቱን መስኮት ሰብሮ በመግባት የተለያዩ ኮምፒውተሮችን እና የኮምፒውተር ክፍሎችን ነቃቅሎ በመውሰድ ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላ ሲሄድ የትምህርት ቤቱ ጥበቃ ከነበሩት አቶ ታምረማርያም ጋር ፊት ለፊት የተገጣጠሙት።
እኚህ አባት በትምህርት ቤቱ ዝርፊያ እየተካሄደ እንደሆነ አይተውት እንዳይገባ ለመከላከል ሲሞክሩ በዱላ ጭንቅላታቸውን በመምታት ይጥሏቸዋል። ከወደቁበት ለመነሳት ፋታ እንኳን ሳይሰጣቸው ይዞት በነበረው ጩቤ ፊታቸው ላይ በመውጋት ያደክማቸዋል። በመቀጠል ሁለቱንም እጃቸውን ወደ ኋላ አስሮ ይዘውት የነበረውን ቴክኖ ሞባይል ከወሰደ በኋላ በድጋሚ ወደ ትምህርት ቤቱ የኮምፒውተር ክፍል ውስጥ በመግባት ሃርድ ዲስኮችን ከኮምፒውተሮች በመንቀል አውጥቶ ከአካባቢው ይሰወራል።
ወጣቱ የዘረፈው አጠቃላይ 36 ሺ 500 ብር የሚያወጣ ንብረት ሲሆን ዝርፊያውን ለመከላከል የሞከሩትን ጥበቃ ጉዳት በማድረስ በዕለቱ ህይወታቸውን ሊያጠፋ ችሏል።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ የትምህርት ቤቱን መዘረፍ ካወቀ በኋላ ምርመራ ማካሄድ ይጀምራል። በምርመራውም አቅጣጫ በሙሉ ወደ አንድ ወጣት ማምራትን የተመለከተው ፖሊስ ባደራጀው የወንጀል ምርመራ ቡድን ንብረቱ ሳይሸጥ በቁጥጥር ስር ሊያውለው ችሏል።
የፖሊስ ምርመራ የደረሰው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በገላን ቁጥር ሁለት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ መስኮት ሰብሮ በመግባት ኮምፒውተሮች እና ሃርድ ዲስኮችን ይዞ ሊወጣ ሲል የደረሰበትን የትምህርት ቤት ጥበቃ ደብድቦ የገደለው ናሆም እቁበጽዮን ላይ ክስ መስርቶበታል።
የፍርድ ቤት ክርክር
ክርክሩን የመራው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ሲሆን፤ የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ናሆም እቁበጽዮን ግርማ የተባለው ተከሳሽ መስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ልዩ ቦታው ገላን ቁጥር ሁለት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት ቤቱን መስኮት ሰብሮ በመግባት የተለያዩ ኮምፒውተሮችን እና የኮምፒተር ክፍሎችን ነቃቅሎ በመውሰድ ከአንዱ ክፍል ወደሌላ ሲሄድ የትምህርት ቤቱ ጥበቃ የነበሩት ሟች ታምረማርያም ግርማ አይተውት እንዳይገባ ለመከላከል ሲሞክሩ በዱላ ጭንቅላታቸውን በመምታት ይዞት በነበረው ጩቤ ፊታቸው ላይ በመውጋት ሁለቱንም እጃቸውን ወደ ኋላ አስሮ ይዘውት የነበረውን ቴክኖ ሞባይል ከወሰደ በኋላ በድጋሚ ወደ ትምህርት ቤቱ የኮምፒውተር ክፍል ውስጥ በመግባት ሃርድ ዲስኮችን ከኮምፒውተሮች በመንቀል አውጥቶ አጠቃላይ 36 ሺ 500 ብር የሚያወጣ ንብረት የወሰደ እና ለመከላከል የሞከሩትን ጥበቃ ጉዳት በማድረስ በዕለቱ ህይወታቸው ያለፈ በመሆኑ በፈፀመው ከባድ የውንብድና ወንጀል በዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቷል።
ተከሳሹ የተከሰሰበት ክስ በችሎት ተነቦለት ድርጊቱን አልፈፀምኩም ያለ ሲሆን ዐቃቤ ህግም ተከሳሹ ክዶ የተከራከረ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ ክሱን በበቂ ሁኔታ አስረድቷል። ይህን ተከትሎ እንዲከላከል በተሰጠ ብይን ተከሳሹ አንድ የመከላከያ ማስረጃ አቅርቦ ቢያሰማም የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ቃል እና የሰነድ ማስረጃዎች ያላስተባበለ በመሆኑ ተከሳሹ ይከላከል በተባለበት ድንጋጌ ስር የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቶበታል፡፡
ውሳኔ
ታህሳስ 10 ቀን 2015 ዓ.ም ቅጣቱን ለመወሰን የተሰየመው ችሎትም ተከሳሽን ያርማል ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያስተምራል ያስጠነቅቃል ያለውን በተከሳሹ ላይ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ እንዲሁም ማህበራዊ መብቶቹ ለዘወትር እንዲሻሩ ሲል ወስኖበታል፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም