የበዓላት ፋይዳ፤
ሰሞንኞቹ የክርስትና ሃይማኖት በርካታ በዓላት በሰላም ተከብረው “’ለዓመቱ በሰላም ያድርሰን!” በሚሉ ምርቃቶች ተጠናቀው የ2015 ዓ.ም ምዕራፋቸው ተዘግቷል።በሰላም ካደረሰን ቀሪዎቹን በዓላትም ወደፊት እንደምናከብር ተስፋ እናደርጋለን።የትናንትናና የትናንት ወዲያዎቹ ክብረ በዓላት በሰላም ተከናውነው እንዲያልፉ በፀጥታ አጠባበቁ ላይ ኃላፊነታቸውን በብቃት ለተወጡት የሰላም ዘቦች በሙሉ ልባዊ ምሥጋና ያለማቅረብ ንፉግነት ነው።ስለሆነም በዓላቱ በሰላም ተከብረው እንዲያልፉ ድርሻ ለነበራቸው የፀጥታ ክፍሎችና ለአባላቶቻቸው በሙሉ ትጋት ስለተሞላበት ሕዝባዊ አገልግሎታቸው አክብሮታችን ይድረሳቸው፡፡
ሃይማኖታዊ፣ መንግሥታዊም ይሁኑ ሕዝባዊ በዓላት በቋሚነት መከበራቸው ለአንድ ሀገር ሕዝብ ትሩፋታቸው በርካታ እንደሆነ በብዙ ጥናቶች ተረጋግጧል።በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ይህ አምደኛ ከአሁን ቀደም ዘርዘር ያለ ጽሑፍ ማቅረቡ በጋዜጣው ቋሚ አንባቢያን ዘንድ በሚገባ የሚታወስ ይመስለናል።በተለይም እኛን መሰል በጦርነት ፍዳ ሰላም ርቆን ለሰነበትነው፣ መፈናቀልና የየዕለቱ የንጹሐን የሞት መርዶ የባህል ያህል ቤተኛ እስከ መሆን ለተጣባን ዜጎች የበዓላቱ በሰላም መከበር በቀላሉ ሊታይ የሚገባ አይመስለንም።የአምናና ሃቻምናን መሰል በዓላት በምን ዓይነት ሀገራዊ ስቅቅ እንዳከበርነው ማስታወሱ በቂና ከበቂ በላይ ማስረጃ ሊሆን ይችላል።ለማንኛውም ከበዓላት አከባበር ጋር የተያያዙ በርካታ ፋይዳዎች ቢኖሩም እንደ መልካም አብነት የሚጠቀሱትን ሁለቱን ዋና ጉዳዮች ብቻ እንደሚከተለው እናስታውስ፡፡
ማሕበራዊ ፋይዳቸው፤
የሀገራችን ቤተሰባዊና ማሕበረሰባዊ አቋም የጠነከረና መስተጋብሩም እጅግ የተቀራረበና የተቆራኘ ስለሆነ በዓላት በጋራ ሲከበሩ ቀደም ሲል የነበረውን ጠንካራ አቋም ይበልጥ እያጠናከረ ነባር እሴቱ ባህል ሆኖ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በተለያዩ ሀገራዊ ፈተናዎች ውስጥ ተጨናንቆና ተወጥሮ የሰነበተው የሕዝባችን አእምሮ ፈታ ብሎ እንዲሰክንና እንዲረጋጋ የበዓላት መከበር አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
በበዓላት ወቅት የቤተሰብ አባላት ተነፋፍቀው መገናኘታቸው፣ የተጣሉና በሰበብ አስባቡ የተጋጩ ወገኖች ለመታረቅና ለመቀራረብ ጥሩ አጋጣሚ መፈጠሩ፣ ስጦታ በመለዋወጥ ወዳጅነትንና ፍቅርን ማጎልበቱ ወዘተ. ከሚጠቀሱ መሰረታዊ ፋይዳዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በዓላት በሚከበሩበት እለትና በማግሥቱ በሥራ የደከመ አእምሮንና የዛለ ስሜትን የማፍታታትና የማደስ አቅማቸውም ከፍ ያለ ነው።በፍቅር እየተሳሰቡ “አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ” መባባልም የበዓላት ልዩ መገለጫዎች ናቸው።ከመብልና ከመጠጡ፣ ከአልባሳቱ ውበትና ከመቆነጃጀቱ ባልተናነሰ ሁኔታ በበዓላት ሰሞን የውስጥ ስሜት በእኩልነት በሀሴት ይረሰርሳል፣ የጠወለገ ተስፋም ይለመልማል፡፡
በበዓላቱ እለት ብቻም ሳይሆን በተለየ ሁኔታ የዋዜማው ሽርጉድና ዝግጅትም በስሜት ላይ የሚያሳ ድረው በጎ ተጽእኖ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም።ከግልና ከቤተሰብ የስሜት እርካታና እፎይታ በተጨማሪም በበዓላት አከባበር ወቅት ታሪክ ይታወሳል፣ ትውስታ ይዘከራል፣ መንፈሳዊ እምነት ይነቃቃል፣ ባህልና ትውፊት ሥር ሰዶ መሠረታቸው እንዲጠብቅ ያግዛል፡፡
ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው፤
በዓላት ለሀገራዊ ኢኮኖሚው መነቃቃትም ድርሻቸው ከፍ ያለ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን አስረግጠው ይመሰክራሉ። ግብይቱና ልውውጡ በፈጣን ሁኔታ ስለሚካሄድ በገበያ ውስጥ የሚሽከ ረከረው የገንዘብ ዝውውር ትንፋሽ እስከሚያሳጣ ድረስ ፈጣን የሚሰኝ ነው።ለገበያ የሚቀርቡ የእርድ ከብቶች ክብካቤ እየተደረገላቸው የሚደልቡት በዓላትን ተስፋ በማድረግ ነው።
ታዳጊ ወጣቶች አዳዲስ አልባሳትና መጫዎቻዎች በእርግጠኛነት እንደሚገዛላቸው ተስፋ የሚያደርጉት በበዓላት ላይ ተስፋ ጥለው ነው።ምግብ አስቤዛውና የቤት ቁሳቁሱ ሸመታም በራሱ ብዙ የሚባልለት ነው።ከእነዚህ ቋሚ እውነታዎች በተጓዳኝ የበዓላትን ወቅት ገበያ ከአዘቦት ቀን ውሎ ለየት የሚያደርገውን ልዩ ባህርይም ማስታወሱ አግባብ ይሆናል።
በበዓለት ዕለትም ሆነ በዋዜማ ተገበያያዎች መካከል የሽያጭና የግዢ እንካ ሰላንትያው (ምልልሱ) የሚከናወነው በሰላምና በፍቅር ድምጸት እየታጀበ እንጂ እንደ አዘቦት ቀናት የገበያ ውሎ በምሬት ወይንም በማጉረምረም ጭምር የሚከወን አይደለም።ገዢ የሻጭን የዋጋ ተመን የሚጠይቀውና ሻጭም ለገዢው ምላሽ የሚሰጠው ሰላምና መረጋጋት ባረበበት የቋንቋ አጠቃቀም እንጂ እንደ ወትሮ ቀናት በብሶት ቃላት እየተተጋተጉ አይደለም።
“እናንተ ነጋዴዎች ምን ታደርጉ ኑሮውን የምታንሩት መንግሥት አይዛችሁ ብሎ ፊት ስለሚሰጣችሁ ነው።አይ ዘመን! ያለቀበት ጊዜ ላይ እንድረስ? አሁን ይሄ ዕቃ የጠየቃችሁትን ዋጋ የሚያወጣ ነው? ወዘተ.” የሚሉ ዓይነት የገበያተኛው የምሬት ብሶቶች በበዓላት ዋዜማና ዕለት አዘውትረው እጅግም አይደመጡም።
ነጋዴውም ቢሆን “እቃ እኮ ጠፍቷል።ይህን ያህልም የተገኘው በመከራ ነው።መደብራችንን ከምንዘጋ ብለን እንጂ የምንሸጥላችሁ አዋጥቶን አይደለም” እየተባለ በበዓላት ሰሞን የሚሰጠው “ውሃ የማያነሳ” ምክንያትና የቀንስ አትቀንስ ክርክሩ የሚካሄደው አብዛኛውን ጊዜ በመከባበርና በፈገግታ በታጀበ አቀባበል እንጂ “በዐይንና በናጫ” በሚመሰል የሸማችና የሻጭ ቋንቋ አይደለም፡፡
እርግጥ ነው በአንዳንድ ቤተሰቦች ዘንድ በዓላትን አድምቆ ለማሳለፍ በሚደረገው ሩጫና ግርግር ምክንያት ወይንም ከማን አንሼ ፉክክር ከወር ወር የታቀደን የጓዳ ገመና ማሳሳቱ ወይንም ማናጋቱ፣ የኪስ ነዋይም መራቆቱ የማይካድ እውነት ነው።“ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” እንዳለችው ወ/ሮ ለሠላሳ ቀናት የተተመነውን የወር አስቤዛ ለአንድ ቀን በዓል አድፋፍቶ ማዕድ ማስቀየሙ የብዙ ቤተሰብ የበዓል ማግሥት ክስተት መሆኑም አይካድም።
ኪስንና ጓዳን ያለ እቅድ በበዓላት አከባበር ሰበብ አራቁቶ ዓይንን በአበዳሪ ላይ ማቁለጭለጭ እንደማያስመሰግን ለማንም ሰው ይጠፈዋል ተብሎ አይገመትም።ቢሆንም ግን እነዚህ ሁሉ በዓላት ነክ ህጸጾች እንዳሉ ሳንክድ በጥቅል ምልከታ ሃሳቡን የምንደመድመው የበዓላት ትሩፋት ከተዘረዘሩት አሉታዊ ምክንያቶች ከፍ ብሎ ፋይዳቸው እጅግ ጠቃሚ መሆኑንና በስሜት ላይ የሚያሳድረው አጠቃላይ ድባብም በጎ የሚሰኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ መመስከር ይቻላል፡፡
ለሀገር የሚበጁ የበዓላት ማግሥት አንድምታዎች፤
እነ እከሌ ተብሎ ስማቸው ባልተገለጸ ባለትዳሮች መካከል ግጭት ተፈጥሮ ለረጅም ቀናት ተኳረፉ ይባላል።ባልና ሚስቱ ኩርፊያቸውን በጊዜያዊነት አቁመው ሰላማዊ መስለው ለመታየት የሚሞክሩት እንግዳ ቤታቸው ሲመጣ ብቻ ነበር።እንግዳው ቤታቸው ከገባበት ሰዓት ጀምሮ ትዝብት ላይ እንዳይወድቁ በመስጋት ወዳጃቸውን የሚያስተናግዱትና እርስ በእርስ የሚጠራሩት “ፍቅሬ ያን ነገር ታመጭልኝ? ውዴ ይህ ጎደለ፣ ያ አነሰ ወዘተ.” በመባባል ሲሆን እንግዳው መስተንግዶውን ጨርሶ ከቤታቸው እንደወጣ ወዲያው የለመዱት የኩርፊያ በሽታ አገርሽቶባቸው ወደ ዝምታ ዋሻቸው ይመሽጋሉ – ይባላል፡፡
ታዲያ እንደለመዱት አንድ ዕለት በኩርፊያ ውስጥ እንዳሉ ድንገት እንግዳ ስለመጣባቸው ዝምታቸውን ለጥቂት ሰዓታት አቁመው ወዳጃቸውን በአግባቡና በፈገግታ በማስተናገድ ከሸኙት በኋላ እንደ ለመደችው ሚስት ወደ ኩርፊያዋ መሸጋገሩን ዘንግታና ረስታ ባሏን “ፍቅሬ እንዲህና እንዲህ ሆነ እኮ! እንዲህ ብናደርግስ?” በማለት በባሏ ፊት ፍልቅል እያለች ገና ንግግሯን እንደጀመረች ያገነገነው ባል ፈጠን ብሎ “የምን ማስመሰል ነው! ቀልዱን ትተሸ ኩርፊያችንን ካቆምንበት እንጀመር” አላት ይባላል – “ይባላል” መባሉ አጽንኦት ይሰጠው፡፡
በምሳሌነት የጠቀስናቸው ባለትዳሮቹ አደረጉ እንደተባለው በዓላትን እየተፍለቀለቅን አክብረን፣ በአምልኮ መልክ ተለብጠንና በርካታ ፋይዳዎችን ገብይተን ስናበቃ በማግሥቱ ወደ ወትሮው የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ስንገባ በጊዜያዊነት ካቆምንበትና ከማይበጀን ከትናንት ተሞክሮ እስካልተላቀቅን ድረስ በዓላትን ዓመት እየጠበቅን ማክበርና መዘከሩ በራሱ ከከበር ቻቻ ያለፈ ፋይዳ ይኖረዋል የሚል ግምት የለንም።
የተበላባቸውን ዕቃዎች አጣጥበንና የተጎዘጎዘውን ደረቅ ቄጤማ ጠራርገን በጣልን ቅጽበት ውስጣችንን ያሳደፈውን መራራ ስሜት እንደ አዲስ ቀስቅሰን ወደ ተለማመድነው ጥላቻና መገፋፋት፣ መናናቅና መቆራቆዝ፣ መገዳደልና መፈናቀል ፊታችንን አዙረን በመዘፈቅ እንደ እሪያ ወደምንትሳችን የምንመለስ ከሆነ በዓላትን ማክበር ምን ምን ትርጉም ይኖረዋል? የእኔ የምንለው የትምክህት “ቅርስ” የሚነካብን እየመሰለን የሰቀልነውን ሻምላ በመምዘዝ ይዋጣልን እየተባባልን የመፋለሚያውን የደም ሸማ በመጣጣል በበዓላት ማግሥት ወደ ቀደመው ጥላቻና ቂም መመለሱስ ምን ይረባናል?
አንድ የንባብ ማዋዣ በእግረ መንገድ ጣል አድርገን እንለፍ።ነፍሰ ሄሩ ጎምቱው ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ሁለት ወዳጆቼ ባሳተሙት አንዲት ብጥሌ መጽሐፍ ጀርባ የሰጠው አስተያየት ሁሌም እንዳስገረመኝ አለ።ጋሽ ጳውሎስን የመጽሐፉ ይዘት አልጣመው ኖሮ በለመደው ምጸታዊ ተረቡ የሰጠው የስላቅ አስተያየት እንዲህ የሚል ነበር።“ሰውዬው የበግ ቅልጥም ቀርቦለት ሥጋውን ግጦ ከጨረሰ በኋላ መቅኒውን ለመምጠጥ ትንፋሹን አስተባብሮ አንዴ ወደ ውስጥ ሳብ ሲያደርግ የተጥመለመለው መቅኒ ሳያጣጥመው ዘው ብሎ ሆዱ ውስጥ መግባቱ ቆጭቶት ‹አይ ከንቱ ድካም!› አለ ይባላል።”
የሞራል ትምህርቱ፡- መቅኒ የሚመጠጠው ለጥጋብ ሳይሆን በአፍ ውስጣ እየተጣጣመ እንዲጣፍጥ ነው።ሳያጣጥሙት ወደ ሆድ ውስጥ ዘው ብሎ የሚገባ ከሆነ የመቅኒ ጥቅሙ እጅግም ነው – ለማለት ነው።ይህን ምሳሌ ከኮልስትሮ ጣጣ ጋር አያይዘው የሕክምና ባለሙያዎቹ እንደማይገስጹን ተስፋ እናደርጋለን።
በዓላትም እንዲሁ በአንድ ዕለት ብቻ “ሽው” ብለው ተከብረው ካለቁና ለነገ የለውጥ፣ የሰላም፣ የእርቅ፣ የመቀባበል፣ የመከባበር ስንቅ፣ እሴትና ማጣፈጫ ቅመም እስካልሆኑ ድረስ ሽር ጉዱም ሆነ ዝግጅቱ፣ ድምቀቱና መሰባሰቡ፣ መገባበዙ፣ መዘመሩም ሆነ መዘየሩ ትርፉ ድካም፣ ውጤቱም ከንቱ ከመሆን ውጭ ምን የተለየ ፋይዳ ይኖራቸዋል? እውነታው ለበዓላት ሁሉ የሚሰራ ቢሆንም በተለየ ትኩረት ግን የሃይማኖት በዓላት በጎ ተጽእኖ የማምጣት አቅማቸው ከፍ እንደሚል ማናችንም እንረዳለን።
ሰሞኑን ባከበርናቸው በዓላት ላይ እንደተስተ ዋለው ጥሞናና እርጋታ፣ ዝማሬና እልልታ፣ መተሳሰብና ፍቅር በእለት ተእለቱ ሕይወታችን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሀገራችን እንደ ዋና ባህል ሆኖ ለሰላማችንና ለእረፍታችን መደላድል ቢሆን ዛሬ የወየበው የኢትዮጵያችን መልክ ፈክቶና ተውቦ ምን ልትመስል እንደምትችል በዐይነ ኅሊናችን እየቃኘን መገመት የሚሳነን አይመስለንም።
በበዓላት ዋዜማ ከሹም እስከ ተራ ዜጋ የሚተገበረው የአደባባይና የጎዳና ላይ የጽዳት ዘመቻዎች የየዕለቱ ባህላችን ቢሆኑ ከተሞቻችንና የገጠሩ ክፍል ምን ሊመስል ይችል ይሆን? በግለሰቦችና በተቋማት የሚደረገው የማዕድ ማጋራትና የታረዙትን የማልበሱ የበጎነት እሽቅድምድምም ከሰኞ እስከ እስከ ሰኞ፣ ከመስከረም እስከ መስከረም ፍጥነቱ ሳይቀንስና ስሜቱ ሳይደበዝዝ ቢከወን በኢትዮጵያ ምድር የተራቡና የታረዙ ዜጎች ቁጥር ከምንገምተው በላይ በቀነሰና ጎዳናዎቻችን ከተዘረጉ የታዳጊዎቻችን የልመና እጆች ነፃ በወጡ ነበር።
ቋንቋ፣ ሃይማኖትና “የትመጣችን” መስፈርት ሳይሆን ጎረቤታማቾችና ዘመዳማቾች በየበዓላቱ እየተገናኘን በመገባበዝና “በሞቴ” እየተባባልን በመጎራረስ እንደምናሳልፈው ሁሉ ከበዓላት ማግሥትም የአዘቦት ቀን ተግባር ብናደርገው ኖሮ የዛሬ አበሳችንና ፍዳችን መልኩ በተቀየረ ነበር አሰኝቶ ያስመኛል።
የሃይማኖት አባቶች በዓላትን አስታከው የሚሰጡት ምክርና መንፈሳዊ ትምህርት ለዘመን መለወጫ፣ ለመስቀል፣ ለኢየሱስ ክርስቶስና ለነብዩ መሐመድ ልደት፣ ለጥምቀት፣ ለኢድ አል ፈጢርና ኢድ አል አድሃ፣ ለስቅለትና ለትንሣኤ ብቻ ሳይሆን የየዕለቱ ትኩረታቸውና ተግባራቸው ቢሆን ጠብና ንትርክ፣ መጋደልና መፈናቀል፣ መካሰስና መወቃቀስ በሀገራችን ሥርና ቅርንጫፋቸው ደርቆ ኢትዮጵያችን ለዓለም ተምሳሌት በሆነች ነበር።
ይህ ምኞት በተግባር ተተርጉሞ ውጤቱን ለማየት እንዲቻል እያንዳንዱ ዜጋ፣ የሃይማኖት መሪዎቻችንና አስተማሪዎቻችን፣ መሪዎቻችንና አስተዳዳሪዎቻችን ልብ ተቀልብ ሆነው ሊያስቡበት፤ አስበውም ሊተገብሩት ይገባል።ይህ ነው የበዓል ማግሥት ምኞታችን።
ሰላም ይሁን።
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም