በአሁን ወቅት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው የሚወጡና ስራ አጥተው የተቀመጡ በርካታ ወጣቶች በሀገሪቷ ይገኛሉ። እነዚህን ወጣቶች የስራ ባለቤት ለማድረግ መንግስት ቀዳሚ ቢሆንም አምራች ኢንዱስትሪዎችም ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ይታወቃል።
ይሁን እንጂ፤ በሀገሪቱ የሚገኙ በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች በሚያጋጥማቸው ተመሳሳይ ችግር ምክንያት በርካታ ፋብሪካዎቹ ስራቸውን ሲያቆሙ ይስተዋላል። ከሚገጥማቸው ችግሮች መካከልም ብድር በበቂ መጠን ያለማግኘት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የፀጥታ ችግር ማጋጠሙ ይጠቀሳል።
በቤንሻንጉል ክልል የሚገኘው ብቸኛ ፋብሪካ የቀርከሃ አግሮ ኢንዱስትሪ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ነው። የፋብሪካው ባለቤት አቶ ሚካኤል ገብሩ ከሀገረ ከአሜሪካ የመጡ ባለሀብት ናቸው። ባለሀብቱ በቤንሻንጉል ክልል አካባቢ የቀርከሃ ምርት ለማምረት ትልቅ ፋብሪካ ገንብተው ስራ የጀመሩት በ66 ሚሊዮን ብር ሲሆን፤ የፋብሪካው ካፒታል አሁን 100 ሚሊዮን ደርሷል። ይሁን እንጂ፤ በገጠማቸው የስራ ማስኬጃ ገንዘብና የውጭ ምንዛሬ እጥረት፤ እንዲሁም ባለፉት ዓመታት ሀገሪቱ በገጠማት የፀጥታ ችግር ምክንያት ፋብሪካው በአሁን ወቅት ስራ አቁሟል።
የፋብሪካው ጭስ ናፍቆኛል የሚሉት ባለሀብቱ፤ ፋብሪካውን ሙሉ በሙሉ በራሳቸው ወጪ የገነቡና ለስራ ማስኬጃ የጠየቁት የብድር መጠንና በወቅቱ የተሰጣቸው ብድር በቂ እንዳልነበር ይናገራሉ። ይህም ሆኖ ወደስራው ለመግባት በነበራቸው ከፍተኛ ጉጉት ወደስራው የገቡ ቢሆንም፤ በአካባቢው ባሉ የተለያዩ ችግሮች፤ እንዲሁም ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ፋብሪካው ያሰብነውን ያህልና በሙሉ አቅሙ ማምረት አልቻለም። ከዚህም በላይ በአሁን ወቅት ፋብሪካው ሙሉ ለሙሉ ተዘግቶ ሰራተኞችን ለመበተን መገደዳቸውን ይናገራሉ።
ፋብሪካው ከሚያመርታቸው ምርቶች መካከል፤ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች፣ የመሬት ምንጣፍ፣ ኮርኒስና ስቲኪኒ የሚገኙበት ሲሆን፤ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ለምርቱ የሚያስፈልገው ግብዓትም በአካባቢው በሚገኝ የቀርከሃ ክምችት የሚሸፈን መሆኑን ባለሀብቱ ተናግረዋል። ይህ የቀርከሃ ምርት በአካባቢው በስፋት መገኘቱ ትልቅ ጥቅም ነው። ከዚህ ጎን ለጎን መንግስት የጸጥታውን፤ የብድር አቅርቦቱንና ሌሎች ችግሮችን ቢቀርፍልን ደግሞ ምርታማነቱን በማሳደግና ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ሚና መጫወት ይቻላል ብለዋል።
ፋብሪካው ከመዘጋቱ በፊት ጫካ ውስጥ የሚተክሉና ችግኝ ጣቢያ ላይ የሚሰሩ ከ500 በላይ ሰራተኞች እንዲሁም፤ 600 የሰለጠኑ ሰራተኞች ደግሞ በፋብሪካ ውስጥ በድምሩ ከ1‚100 በላይ ለሆኑ የአካባቢው
ማህበረሰብ የሥራ ዕድል በመፍጠር የሚንቀሳቀስ ፋብሪካ ነበር። ፋብሪካው ከተዘጋ በኋላም ጥበቃዎችን ጨምሮ ስልጠና የወሰዱ ፋብሪካው ተመልሶ ቢንቀሳቀስ ሙያው ያላቸውና በቀላሉ ወደ ስራው ሊቀላቀሉ የሚችሉትን 50 ሰራተኞች ለሶስት ዓመታት ባለሀብቱ፤ ከኪሳቸው ደሞዝ እየከፈሉ ይገኛሉ።
ይሁንና፤ ከፍተኛ የሆነ የስራ ዕድል እጥረት ባለበት ሀገር በተለይም ከፍተኛ የሆነ የስራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ ፋብሪካዎች ሲዘጉ ለምን የሚል አካል ሊኖር ይገባል። ከዚህም ባለፈ መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ያሉትን ችግሮች በመፍታት ፋብሪካዎች ወደ ስራ እንዲገቡ ቢደረግ መልካም ነው የሚሉት ባለሀብቱ፤ ይህ የቀርከሃ ማቀነባበሪያ ፋብሪካም የገጠመው የገንዘብ እጥረት ተቀርፎለት ወደ ስራ ቢገባ እኔ እንደ ግለሰብ ህዝብንና ሀገርን ለመርዳትም ሆነ ለማገዝ ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ ብለዋል።
ሌላው፤ አምራች ኢንዱስትሪ ዱከም የሚገኘውና አሮጌ ጎማዎችን በመጠገን መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያደርግ እጥፍ ጎማ ቁጠባ የተባለ አምራች ኢንዱስትሪ ነው። ኢንዱስትሪው አሮጌ ጎማዎችን ከጥቂት ደንበኞቹና ከየአካባቢው ተዘዋውሮ በመግዛት እያደሰ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ የሚሸጥ ድርጅት ነው።
አቶ አየለ አስፋ ወሰን የእጥፍ ጎማ ቁጠባ ባለቤትና ስራአስኪያጅ እንደገለፁት፤ የከባድና የመለስተኛ መኪና አሮጌ ጎማዎችን ሶስት ጊዜ ያህል በመጠቀም መልሰው ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማድረግ ስራ የሚሰራ በመሆኑ የውጭ ምንዛሪን በማዳን በኩል በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የጎላ አስተዋፅዖ ማበርከት ይችላል። ጎማ፤ ለተሽከርካሪና ለትራንስፖርት ድርጅቶች ከነዳጅ ቀጥሎ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ነው የሚሉት አቶ አየለ፤ ህብረተሰቡ ጎማን መልሶ የመጠቀም ግንዛቤ የለውም። ግንዛቤውን ለመፍጠር ድርጅቱ የተቻለውን እያደረገ ቢሆንም ስራው በስፋት እንዲተዋወቅ መንግስትም ሊያግዘን ይገባል ይላሉ።
ቴክኖሎጂው እንዳለ እንኳን ብዙ የትራንስፖርት ድርጅቶች አያውቁም። እንዲያውቁትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እጥፍ ጎማ ቁጠባ፤ በተለያዩ የኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያዎች ላይ በመቅረብ የማስተዋወቅ ስራ መስራታቸውን አስታውሰው፤ ከዚህም በላይ መንግስት እንደ ጎማ አይነት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጥቶባቸው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎችን መልሰው ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማስተዋወቅ እንዲሁም የወጣባቸውን የውጭ ምንዛሬ ያህል አገልግሎት ሰጥተው ነው ወይ እየወደቁ ያሉት የሚለውን መንግስት ቢሰራበት ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬን ማዳን እንደሚቻል ተናግረዋል።
አንድ ጎማ በ13 ሺህ ብር ተገዝቶ ተሽከርካሪው ላይ ተገጥሞ ከ45 ሺህ እስከ 50 ሺህ ኪሎሜትር የሚያገለግል ሲሆን፤ ተሳቢ ላይ በመግጠም ደግሞ 20 ሺህ ኪሎሜትር በድምሩ 70 ሺህ ኪሎሜትር አገልግሎ ጎማው ይጣላል። ነገር ግን እጥፍ ጎማ እየሰራ ያለው መኪናው ላይ 45 ሺህ ኪሎሜትር ተጠቅመው ቢያወጡትና በአራት ሺህ በአራት ሺህ ብር ለሶስት ጊዜ ያህል ቢጠገን በ12 ሺህ ብር ተሳቢ ላይ 300‚000 ሺህ ኪሎ ሜትር ማገልገል ይችላል።
አሁን ግን አንድ ጎማ በ13 ሺህ ብር ተገዝቶ 70 ሺህ ኪሎሜትር ብቻ አገልግሎ ይወድቃል። እጥፍ ጎማ ይህን 70 ሺህ ኪሎሜትር ያገለገለ ጎማ ቢያገኝ የተጎዳውን ፓርት አውጥቶ በመጣል መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ እንደ አዲስ በማድረግ የሚሰራ ቢሆንም ህብረተሰቡ ግንዛቤውን አግኝቶ ጎማዎቹን በብዛት እያቀረበልን አይደለም። በመሆኑም በአሁን ወቅት እጥፍ ጎማ 25 ሰራተኞችን ይዞ በቀን እስከ 160 ጎማዎችን ማደስ የሚችል አቅም ያለው ድርጅት ነው። ይሁን እንጂ፤ ማህበረሰቡ ቴክኖሊጂውን አውቆ ጎማዎችን በብዛት ቢያቀርብልን ከመቶ በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠርና ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ንም ማዳን ይቻላል።
በአሁን ወቅት በዓለም ላይ የትራንስፖርት ሴክተሩን በከፍተኛ ሁኔታ ተቆጣጥሮት ያለው አዲስ ጎማ ሳይሆን የታደሱ ጎማዎች ናቸው የሚሉት አቶ አየለ፤ በቴክኖሎጂው እንኳን የመኪና የአውሮፕላን ጎማም እንደሚጠገን አብራርተዋል። እጥፍ ጎማም ቁጠባ፤ የመኪና ጎማዎችን መልሶ በመጠቀም እየጠገነ ይገኛል። ስለ አስተማማኝነቱም ለደንበኞች ለማረጋገጥ የተጠገነውን ጎማው ከክፍያ በፊት በመውሰድ የተወሰኑ ኪሎሜትሮችን እንዲጠቀሙና አምነውበት እንዲከፍሉ በማድረግ ደንበኞችን እያፈሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለያዩ የውጭ ሀገራት አዳዲስ ጎማዎችን ኤክስፖርት ሲያደርጉ እንጂ ለመኪናዎቻቸው ሲጠቀሙ አይታዩም። አዳዲስ ጎማቀዎችን የሚጠቀሙት የፊት እግሩን ብቻ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ጎማዎች በሙሉ መልሰው ጥቅም ላይ የዋሉ ወይም የታደሱ ጎማዎችን ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለማወቅ በ13 ሺህ ብር የተገዛ ጎማ 70 ሺህ ኪሎሜትር ብቻ አገልግሎ ይጣላል ያሉት ስራአስኪያጁ፤ ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሬውን ቀዶ እንደመጣል ይቆጠራልም ብለዋል።
እያንዳንዱ የትራንስፖርት ድርጅት አራት አዳዲስ ጎማዎችን በአንድ መኪና ላይ ገጥሞ በመጠቀም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ብክነትን እያስከተለ ነው። ስለዚህ እጥፍ ጎማ ቁጠባ ገበያውን ሰብሮ ለመግባትና የውጭ ምንዛሪ ብክነትን ለመቀነስ በየጎሚስታው አሮጌ ጎማዎችን በማፈላለግ ጠግኖ በመሸጥ ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ፤ ህበረተሰቡ ግንዛቤ አግኝቶ ጎማዎችን ከመጣሉ በፊት እስከ 45 ሺህ ኪሎሜትር ብቻ
ተጠቅሞ ቢያቀርብልን በአራት ሺህ ብር ተጠግኖ እሰከ 100 ሺህ ኪሎ ሜትሮችን መገልገል ይችላል። ስለዚህ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ በሚዲያ የማስተዋወቅ ስራን በጋራ ብንሰራ ህብረተሰቡን የበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋል። እንዲሁም ለጎማ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ መጠን በመቀነስ በሀገርን ኢኮኖሚ ለይ አሉታዊ አስተዋፅዖ ያበረክታል።
የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በኮንስትራክሽን ዘርፍ አራት፤ በኬሚካል ዘርፍ ደግሞ አምስት በድምሩ ዘጠኝ ትላልቅ ንዑስ ዘርፎችን የሚመራና በተቋሙ የሚታወቁ ከ600 በላይ የሚሆኑ በመካከለኛና በከፍተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ ተቋም ነው።
ተቋሙ በኬሚካልና በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ኢንዱስትሪዎቹ በሙሉ አቅማቸው ማምረት እንዲችሉ እገዛ ያደርጋል። ይሁን እንጂ፤ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ሀገሪቷ በገጠማት የፀጥታ ችግር እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች መዘጋታቸውንና እንደ ሀገር ኢኮኖሚው መቀዛቀዙን የዘጠኝ ወር ግምገማ ባደረገበት ወቅት አሳውቋል። በመሆኑም ባለፉት ዘጠኝ ወራትም በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ የኢንዱስትሪው የኢኮኖሚ ድርሻ 68 ነጥብ 65 ሆኗል።
አቶ ሀዱሾም ጥዑሙ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር፤ እንደገለፁት አጠቃላይ በኬሚካልና በኮንስትራክሽን ዘርፍ የውጭ ንግድ አፈፃጸሙ ከ50 በመቶ በታች መሆኑን ተናግረዋል። የውጭ ንግድ ላኪ ኢንዱስትሪዎችም ባጋጠማቸው የግብዓት እጥረትና የገበያ መዳረሻዎች ችግር ተወዳዳሪነታቸው እየቀነሰ መምጣቱን አብራርተዋል። ለገበያው መቀዛቀዝ በተለይም የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትና ብድር በሚፈለገው መጠንና ወቅት ያለመገኘት እንዲሁም የግብዓት አቅርቦትና በሀገሪቷ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በዋናነት ይጠቀሳል ብለዋል።
በተመሳሳይ ባለሀብቱ የአመለካከት ችግር እንዳለበት የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ብዙ ልፋትና ትዕግስት የሚጠይቅ አድካሚ በመሆኑ አብዛኛው ባለሀብት በቁርጠኝነት ዘርፉን ለመቀላቀል አለመድፈሩንም ተናግረዋል። ይሁን እንጂ፤ ኢንስቲትዩቱ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ያልተቻለባቸውንና ፋብሪካዎች የተዘጉበትን አጠቃላይ ችግሮች ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር ባደረገው ውይይት ችግሮቹን ለይቶ በቀጣይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ችግሮቹን ለመፍታት እንደሚሰራ ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2011
በፍሬህይወት አወቀ