እኛ ሀገር ብዙ ተናጋሪዎች አሉ..ስለሀገራቸው ሲጠየቁ ከወርቅ ባማረ ከማር በጣፈጠ ቋንቋ የሚናገሩ። እኛ ሀገር ብዙ ፖለቲከኞች አሉ ስለ ሀገራቸው ሲጠየቁ ከቅዱስ ጳውሎስ ስብከት ባልተናነሰ የሚሰብኩ። እኚህ ሰዎች ተግባራቸው ሲታይ ግን ምንም ሆኑ ሰዎች ናቸው። ሀገር በቃል ሳይሆን በተግባር ነው የምትገለጸው። በወሬ ሳይሆን በስራ ነው የምትገለጸው።
ማንም ሰው ከመሬት ተነስቶ ሀገሬ እንዲህ ናት እያለ ባማረና በተዋበ ቃል ቢያወራ በጎ ተግባር ካልሰራ እንደ ይሁዳ ነው። ይሁዳ ማለት ጌታን ከሚወዱና ጌታን ከሚያፈቅሩ ደቀ መዝሙሮቹ አንዱ ነበር። መጨረሻው ግን አላማረም። ይሁዳ ጌታን ሲሸጠው ወዳጁ ሆኖ ነበር። ይሁዳ ጌታን አሳልፎ ሲሰጠው ስሞና አቅፎ ነበር። ከተግባር ርቀን ስለ ሀገራችን ወሬ ብቻ ከሆንን እንደ ይሁዳ ስመን እየሸጥናት ነው። ከበጎ ሀሳብ ርቀን ተናጋሪዎች ብቻ ከሆንን እንደ አስቆሪቱ ይሁዳ እየከዳናት ነው።
የሀገር ፍቅር ጥሩ በመናገር ሳይሆን ጥሩ በመስራት የሚገለጽ ነው። ሀገር መውደድ ለሀገር ምርጡን ነገር በማድረግ የሚጀምር ነው። ተግባር የሌለው በጎ ቃላት፣ ሀሳብ የሌለው በጎ ፍቅር ከማስመሰል እኩል ነው። እናም ሀገራችንን ሀሳብና እርቅ፣ ፍቅርና አንድነት በሌለው የቃላት ጋጋታ እንወድሻለን ብንላት፣ ብንስማት፣ ብናቅፋት፣ ብናሞካሻት፣ ብናቆለጳጵሳት እንደ ይሁዳ ነን። አለም በውድድር ውስጥ ናት። የውድድሩ መድረክ ደግሞ ወሬ ሳይሆን ተግባር ነው።
ጠንክሮ በመስራት ውስጥ ብቻ ነው ድህነት ታሪክ ሊሆን የሚችለው። ጠንክሮ በማውራት ውስጥ ታሪክ የለም። የስልጣኔ ታሪካችንን፣ የልማት ታሪካችንን ተግባራችን ውስጥ እንፈልገው። እንደ ሀገር የማደግና የመበልጸግ ምኞታችንን ከወሬ በዘለለ ትጋትና ልፋት እንመዝነው። ፖለቲከኞቻችን እያወሩ ህዝቡን ወሬኛ እያደረጉት ነው።
በዝምታ በመቆም ውስጥ ያለውን ሀይል ያለውን ልዕልና መለማመድ አለብን። እንደ ፖለቲከኛ ምን መናገር እንዳለብን ሳይሆን ምን መስራት እንዳለብን ነው ለህዝቡ ልናስተምረው የሚገባን። ምን መስራት እንዳለበት የተለማመደ ትውልድ ሀገር የመፍጠር ስብዕናው የተገነባ ነው።
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ሀገራችን ከእኔና ከእናንተ ከሌላውም ሰው የምትፈልገው ነገር እጆቻችንን ለስራ፣ አንደበቶቻችንን ለምርቃት፣ ልቦቻችንን ለፍቅር መክፈት ነው። ለእርግማን እና ለትችት የተከፈቱ አንደበቶቻችን እንዲመርቁና እንዲያመሰግኑ ልናስተምራቸው ይገባል።
ስራ ፈተው የእንጀራ ጠርዝ የሚያደማቸውን እጆቻችንን ስራ ማስለመድ ሀገር የመውደድ አንዱ መገለጫ ነው ። በመነጋገር ልዩነቶቻችንን እየፈታን የምንሄደው ፖለቲካዊና ማህበራዊ ልምድ አዲሲቷን ኢትዮጵያ የሚፈጥር የመጀመሪያው የለውጥ ምዕራፍ ነው፡፡ በአጉል እምነት የዳበሩ፣ ሳይንሳዊ ማስረጃ የሌላቸውን እንዲህና የመሳሰሉ ወደፊት የማያራምዱ አመሎቻችንን ጥለን አዲስ ስብዕናን መላበስ ከራስ አልፎ ለሀገር የሚትርፍ ማንነት ነውና ልንለማመደው ይገባል።
አበው ሲተርቱ ‹ወሬ የለውም ፍሬ› ይላሉ። ታላቁ መጽሀፍም በምሳሌ መልዕክቱ ‹አስተዋይ ግን ዝም ይላል› ይለናል። እውነት ነው ወሬ የለውም ፍሬ። ወደ ጦርነት ስንገባ ብዙ አውርተን፣ ብዙ ተዛዝተን ነበር። እነዛን ጊዜያቶች ስለሰላም ብናወራባቸው፣ ስለፍቅርና ወንድማማችነት ብንነጋገርባቸው ዛሬ መልካችን ሌላ በሆነ ነበር።
አንዳንዶቻችን በጣም አስገራሚዎች ነን..ስለጦርነት ሲሆን ብዙ አውርተን ስለሰላም ሲሆን አንደበት የሚያጥረን ነን። ስለ ጥላቻ ብዙ ሀሳብ እያለን ስለአንድነት እውነት የሚጎድለን ነን። ካወራን ስለሰላም እናውራ። ካወራን ሀገራችን ከፍ ስለምትልበት፣ ህዝባችን ከድህነት ስለሚወጣበት እንናገር። ካወራን አንድ ስለሚያደርጉን የጋራ እሴቶቻችን እናውራ። ሀገር የምትቆመው በአስተውሎት ነው። አስተዋይ ሰው ዝም ይላል እንደተባለው ስለ ክፉ ዝም እያልን ስለበጎ የሚበረታ አንደበት ሊኖረን ይገባል።
ኢትዮጵያ በእኛ የውሸት ወሬ ታክቷታል..ነፍስ ቢኖራት ኖሮ እባካችሁ በማይሆን ወሬ አትሸንግሉኝ። እኔ የሚያስፈልገኝ እውነት፣ ሰላምና ፍቅር ነው› ትለን ነበር። እውነት ነው የሚጠቅመንን እስክናገኝ ድረስ ሀገራችንን በብዙ ቃል ሸንግለናታል። እውነት ነው ሆዳችንን ለመሙላት፣ ቀዳዳችንን ለመድፈን ነውር በሆነ በብዙ የማስመሰል ወሬ አሽሞንሙነናታል።
ይሄ በሀገርና በህዝብ፣ በፖለቲካና በፖለቲከኛ፣ በመሪና በተመሪ መካከል የተፈጠረ ያልተጣጣመ ወሬ ነው ከከፍታችን አውርዶ ጠባቂዎች ያደረገን። ሀገር ቃል አትፈልግም ሀገር ትንሽ እያወራ ብዙ የሚሰራላት ሰው ነው የምትፈልገው። ሀገር ወሬ አትፈልግም ለአመል እያወራ ብዙ የሚተጋላትን ነው የምትፈልገው። ሀገር ተናጋሪ አትፈልግም ሙያ በልብ ብሎ ስለሰላሟ፣ ስለአንድነቷ የሚደክምላትን ነው የምትሻው። ውጥንቅጣችን የወጣው ውጥንቅጡ በወጣ የህይወት ልምድ ነው።
አስገራሚዎች እኮ ነን። ብዙ ማውራት ስንወድ ብዙ መስራት ግን አንወድም። ብዙ መናገር ስንለምድ ብዙ መስራት ግን አለመድንም። ለዚህ ነው ድሀ የሆንነው። ለዚህ ነው እልፍ የሆነውን ተፈጥሮ ሀብታችንን መጠቀም ያልቻልነው። ለዚህ ነው ብዙሀነታችንን መጠቀም ያልቻልነው። ለድህነታችን፣ ለኋለ ቀርነታችን ከዚህ የተሻለ አስተማማኝ ምክንያት አናገኝለትም።
ሰላም ለማጣታችን፣ ተነጋግሮ ላለመግባባታችን ከዚህ የላቀ ምክንያት አናመጣም። ሀገራችን እንድትቀየር እኛ መቀየር አለብን። የእኛ ለውጥ ነው የሀገራችንን ለውጥ የሚሰጠን። ራሳችንንም ሆነ ሀገራችንን ለመቀየር ተዐምር መጠበቅ የለብንም። ለውጣችን በውስጣችን ነው ያለው። ውስጣችንን በስንፍና፣ በጦርነት፣ በጥላቻ ካደከምንው ለለውጥ የሚሆን ሀይል አናገኝም። ውስጣችንን በወሬ፣ በውሸት፣ በማስመሰል ካደከምነው ለማሸነፍ የሚሆን አቅም አናገኝም።
ሀገራችን ሰፊ ናት..እኛም ልጆቿ ሰፊዎች ነን። ይሄን ስፋታችንን ለመጠቀም ከጥበት መውጣት አለብን። ጠባብነት ሰፊነትን የሚሰውር የነውር ቋት ነው። ጠባብነት አንደነበረ የሚያኖር፣ ከዘመኑ የሚያርቅ የኋላቀርነት አለቃ ነው። ጠባብነት ከወሬኝነት የሚፈልቅ፣ ለጥላቻና ለጦርነት በር የሚከፍት የውንብድና መንገድ ነው። ጠባብነት ሀገርን ከሙላት፣ ህዝብን ከስልጣኔ፣ ትውልድን ደግሞ ከመልካም መንፈስ የሚያጎል የሰይጣን ቁራጭ ነው።
እንደ ሀገራችን መስፋት አለብን። እንደ ብዙሀነታችን በሀሳብና በተግባር መላቅ አለብን። እንደ ታሪካችን፣ እንደ ባህላችን በሰውነታችንም ወንዝ መሻገር አለብን። አለምን እንደ ቀለመ፣ አፍሪካን እንዳሳመረ ስማችን ከዚህም በላይ ከፍ ማለት አለብን። እንደ ወንድማማችነታችን፣ ዘመን እንዳስቆጠረው አብሮነታችን ከፍ ማለት አለብን። ከፍ ካላልን ከፍ ላሉት መወጣጫ ነው የምንሆነው። ከፍ ካላልን ከፍ ላሉ ሀገራት ማላገጫ ነው የምንሆነው። በላቀ ሀሳብና በላቀ ምግባር ሀገራችንን ከዝቅታ ማውጣት አለብን። ጦርነት ባልገባበት ሰላም፣ ጥላቻ ባልነካው ፍቅር ትውልዱን ከፍ ማድረግ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል።
ሰፊዋ ሀገራችን፣ ከዚህ እስከዛ የሌላት ምህዳረ ሰፊዋ ኢትዮጵያ ምግባር በሌለው ወሬ መጥበብ የለባትም። ለድህነቷ ምክንያት ሆነን እስከመች እንራመዳለን? እርምጃችንን ማስተካከል አለብን..ከወሬ የበረታ ተግባር፣ ከጥላቻ የራቀ ፍቅር ያስፈልገናል። ከማስመሰል የራቀ እውነት፣ ከውሸት የተለየ የሀገር ፍቅር ያስፈልገናል። ኮሽ ባለ ቁጥር ጎራዴአችንን ከአፎቱ መምዘዝ፣ መትረየሳችንን ከመስቀያ ማውረድ ሳይሆን በመነጋገር መስማማትን መልመድ አለብን።
ኮሽ ባለ ቁጥር ውረድ እንውረድ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ መቀመጥን ባህል ማድረግ አለብን። ኮሽ ባለ ቁጥር ይዋጣልን ሳይሆን ስለድሀ ሀገራችን ስንል ልዩነቶቻችንን ማጥበብን ልንማር ይገባል። ሰው ወሬ ካበዛ እየጠበበ ነው። ፖለቲከኛ የህዝብን ጉዳይ ቸል ካለ እየጠበበ ነው። ከጥበት ለመውጣት አገልጋይነትን መለማመድ አለብን። ከጥበት ለመውጣት ከዛሬ የራቀ ነገን ማለም አለብን።
ከጥበት ለመውጣት የመስፋትን ሚስጢር ማወቅ ግድ ይለናል። ዛሬም እኛ ነን.. ነገም በእኛ በኩል የሚመጡ ልጆቻችን ናቸው ኢትዮጵያን የሚወርሷት። የዛሬ ጠባብነታችን የነገውን የልጆቻችንን እድል ከማጥበብ ባለፈ የሚጠቅመን የለም። እናም መስፋት አለብን። በሀሳብ በፍቅር መትረፍረፍ አለብን።
ኢትዮጵያ የእኛን አንድ መሆን፣ የእኛን በፍቅር መተቃቀፍ እየጠበቀች ነው። በአንድነት በቆሙና በፍቅር በተቃቀፉ ነፍሶች መካከል የሚገባ ምንም ሀይል የለም። ፍቅር የሰላም የብረት በር ነው..ይሄን የብረት በር አልፎ የሚገባ ምንም ምድራዊ ሀይል የለም። ሰላማችንን መጠበቅ የሀገራችንን መጻኢ እድል ማስጠበቅ ነው። ሰላማችንን ማስጠበቅ ተስፋዎቻችንን ማስጠበቅ ነው።
ይቺን ድንግል ሀገር በሰላም ካልሆነ፣ በበጎ ተግባር ካልሆነ በምንም ከፍ አናደረጋትም። አንድ ቦታ እየረገጠች የባከነችባቸው ብዙ ዘመናት አሉ..እነዛ ዘመናት የሚታከሙት ዛሬ ባለን የሀገር ፍቅር ስሜት ልክ ነው። ከመናገር ወጥተን ወደ ስራ መግባት አለብን። ከመተቸት ወጥተን ወደ ተግባር መሰማራት አለብን።
እስከዛሬ ድረስ ስለሀገራችን ብዙ ተናግረናል፣ ብዙ ጽፈናል። የንግግራችንን ሩቡን ግን አልሰራንም። የወሬአችንን ግማሹን ግን አለፋንም። ከወሬአችን እኩል ብንለፋ ወይም ደግሞ እያወራን ብንሰራ ለሀገራቸው ውለታ ከዋሉ ጥቂት ሰዎች ውስጥ እንመደብ ነበር።
ስለኢትዮጵያ በተነገሩ መልካም ንግግሮች ልክ ሰርተን ቢሆን ኖሮ፣ ማይክ ስንጨብጥ በምንናገራቸው የተመረጡ ወሬዎች ልክ የተመረጡ ስራዎችን ሰርተን ቢሆን ኖሮ ዛሬ አለምን በኢኮኖሚያቸው ከሚመሩት ሀገራት ጎን እንቆም ነበር። እስኪ እንማር ሀገር መውደድ ማለት ተግባር እንደሆነ ይግባን። ሀገር ማፍቀር ማለት ለሀገር መልፋት እንደሆነ ይገለጥልን።
የሀገር ፍቅር ማለት ከሀገሬ በፊት እኔን ማለት እንደሆነ እንወቅ። አሁን ላይ ሀገራችን ለእኛ የምትከፍለን ነገር የላትም። እኛ ነን ለሀገራችን መክፈል ያለብን። የሀገር ክፍያ ከኪስ የሚወጣ ሳይሆን ከልብ የሚወጣ ነው። የሀገር ክፍያ ከካዝና የሚመነዘር ሳይሆን ከጭንቅላት የሚፈልቅ ነው። የሀገር ክፍያ በጎ ሀሳብን፣ መልካም ምኞትን መስጠት ነው። እውቀትን፣ ጉልበትን፣ ገንዘብን መስጠት ነው።
የሀገር ክፍያ በተሰማራንበት ማናቸውም ቦታ ላይ በታማኝነት ማገልገል ነው። ሳንሰርቅና ሳንዘርፍ ሳናጭበረብርም መቆም ነው። የሀገር ክፍያ ኮሽ ባለ ቁጥር ወደጦርነት መግባት ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን መቅረፍ ነው። የሀገር ክፍያ ሰላም ያለበትን ሀሳብ፣ ፍቅር ያለበትን ተግባር፣ እውነትና ፍትህ የበዙበትን ማዋጣት ነው።
ለሀገራችን ይሄን ስንሰጣት ነው ከሰጠችን አብልጣ የምትሰጠን። ለሀገራችን ይሄን ስንከፍላት ነው ከከፈለችን የሚበልጥ ብዙ ነገር የምትከፍለን። ምንም ባልሰጠንበት ሁኔታ ከሀገራችን ለመቀበል እጃችንን መዘርጋት አይጠበቅብንም። ምንም ባለፋንበት ሁኔታ ሀገራችን እንድትለፋልን ማስገደዳችን ፤ ምንም ባልከፈልንበት ሁኔታ እንድትከፍለን መጠበቃችን አሳዛኝ ነው። መች ሰጠናትና እንቀበላለን? መች አገለገልናትና እንድታገለግለን እንፈልጋለን? መጀመሪያ የሚጠበቅብንን እናድርግ።
መጀመሪያ እንደ ዜጋ ሀላፊነታችንን እንወጣ። ዜግነት አገልግሎ መገልገል ነው። ዜጋ የሆንው ሀገራችንን አገልግለን ለመገልገል ነው። ዜጋ የሆነው ሰጥተን ለመቀበል ነው። ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ ላይ የምንፈጥረው አዲስ ነገር የለም። አዲስ ነገር ለመፍጠር የሀገርና ህዝብን እውነተኛ ቁርኝት መረዳት ይኖርብናል። ሀገር በዜጎች የምትፈጠር ናት..ዜጎች በሀገር የሚደምቁ ናቸው..የምንቀበለው ለሀገራችን የሰጠነውን ነው..ቁርኝቱ ይሄ ነው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 12 /2015