ኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላትን በአደባባይ በድምቀት ከሚያከብሩ አገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች፡፡ በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት ደግሞ ጥምቀት አንዱና ዋነኛው ነው።
ጥምቀት ማለት ‹‹አጥመቀ-አጠመቀ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ‹‹መነከር፣ መድፈቅ፣ በተባረከው ውሃ ጸበል ውስጥ ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ›› ማለት እንደሆነ የተለያዩ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
በየዓመቱ በመላ ኢትዮጵያ የሚከበረው የጥም ቀት በዓል፣ ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው፣ በየጥምቀተ ባሕሩ የሚከበሩ በመሆናቸው፣ ይህም በዓሉ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መስህብ በመፍጠሩ፣ ቱሪስቶችን መሳቡ አልቀረም። ከአዲስ አበባ እስከ ጎንደር፣ ከላሊበለ እስከ አክሱም በሁሉም ስፍራዎች ደምቆ የሚከበረው የጥምቀት በዓል፤ ምእመናኑም ሆነ የካህናትና ዲያቆናት አለባበስ ፍፁም በሚማርክ ባህላዊ አልባሳት የተዋበ በመሆኑ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ለሚመጡ ጎብኚዎች ሁል ጊዜ አዲስ ነው፡፡
ሊቃውንት እንደሚናገሩት፣ ዘመነ አስተርእዮ የሚባለው ከጥር 11 ቀን ጀምሮ እስከ ጾመ ነነዌ ጥር 17 ቀን ያለውን ወቅት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ አምላክ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡ፣ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ አንድነትና የሦስትነት ምሥጢር መታወቁ፣ በቃና ዘገሊላ በተደረገው ሠርግ ላይ የመጀመሪያው ተአምር በመፈጸሙ፣ አምላካዊ ኃይሉ እና መገለጡ፣ እየታሰበ ምስጋና ይቀርባል፡፡ ይህ ሁነት ኢትዮጵያ ብሂልን ከባህል ጋር አዛምዳ ከሌላው የክርስቲያን ዓለም በተለየ አከባበር በዓሉን ማክበሯ፣ አያሌ ቱሪስቶችን ለመሳብ አስችሏታል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ዘጠኝ ዓበይት በዓላት ውስጥ በየዓመቱ ጥር 11 ቀን በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ፣ በገጠርም በከተማም በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መምህር ሊቀ ብርሃናት ኢሳይያስ ወንድምአገኘሁ በአንድ ፅሁፋቸው ላይ ሲገልጹ፣ ‹‹የጥምቀት በዓል አከባበር ከሁሉም በዓላት ለየት ከሚያደርጉት ምክንያቶችና ሁኔታዎች አንዱ ጥር 10 ቀን በዋዜማው ‹‹ከተራ›› በሚል ስያሜ በሚታወቀው በዚሁ ዕለት ባሕረ ጥምቀት ከተዘጋጀ በኋለ በመላው ኢትዮጵያ በከተማም በገጠርም በመሐል አገርና በጠረፍ ጭምር ባሉት አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ታቦታት ሁሉ ከመንበራቸው ተነሥተው ወደተዘጋጀው ባሕረ ጥምቀት በመውረድ እና በተዘጋጀላቸው ድንኳን ውስጥ በማደር በዚያው ባደሩበት ድንኳን ማኅሌቱና ሥርዓተ ቅዳሴው ከተከነወነ በኋላ ባሕረ ጥምቀቱ ተባርኮ ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ የበረከቱ ተሳታፊ ከመሆኑም በላይ በዓሉ ከዋዜማው ማለትም ከከተራው ቀን ጀምሮ ታቦታቱ ወደየአብያተ ክርስቲያናቱ ተመልሰው በመንበራቸው ላይ እስኪያርፉ ድረስ ሁለት ቀን ሙሉ በየባሕረ ጥምቀቱና በየመንገዱ ሁሉ በድምቀት የሚከበር በዓል በመሆኑ ነው፡፡
ሌላው የጥምቀት በዓል ካህናቱ በማኅሌትና በመዝሙር፣ በቅዳሴና በልዩ ልዩ ውዳሴ፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በተለያዩ መዝሙራትና ሽብሸባዎች ሕዝበ ክርስቲያኑ ደግሞ ወንድ ሴት ሽማግሌና ወጣት ሕፃናትም ሳይቀሩ ሀብት ያለው አዲስ ልብስ ገዝቶ፣ አቅም የሌለው ደግሞ በቤት ውስጥ ያለውን አጥቦና አጽድቶ፤ ነጭ በነጭ ለብሶና አሸብርቆ እጅግ በደመቀና ባማረ ሁኔታ ታቦታቱን በማጀብ በዝማሬ፣ በሆታና በእልልታ፣ በከበሮ፣ በበገናና በእምቢልታ በታላቅ ዝግጅትና ሰልፍ በባሕረ ጥምቀቱ አካባቢና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ሁሉ በታላቅ ድምቀት የሚያከብረው በዓል በመሆኑ ነው›› ብለው ሊቀ ብርሃናት ኢሳይያስ ወንድምአገኘሁ ያስቀምጣሉ፡፡
‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› የሚለው ዘይቤም የሚያመለክተው ይህንኑ የጥምቀቱን በዓል ታላቅነት ነው፡፡ ነጭ በነጭ ተለብሶ የሚከበር በዓል መሆኑም በጥምቀት የሚገኘውን አዲስ ልደትና ከሐጢአት ቁራኛነት የመንፃትን ምሥጢር የሚያመለክት ስለመሆኑም በመግለፅ ከሃይማኖታዊ ፋይዳው ባሻገር በርካታ ማህበራዊ መስተጋብሮች የሚስተዋሉበት በዓል ነው፡፡
ይህ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበ በዓል በመሆኑ በቱሪዝሙ ዘርፍ ለኢትዮጵያ ያለው ፋይዳ እጅግ የጎላ ነው። ታዲያ ከዘመን ዘመን እሴቱን ጠብቆ ዛሬ ላይ የደረሰው ይህ አኩሪ የሁሉም ኢትዮጵያውያን በዓል ሥርዓቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር መስራት የሁሉም ኃላፊነት መሆኑ እሙን ነው፡፡
በአጠቃላይ የሀገር አንድነትና ሕዝባዊ ትስስር ተጠብቆ እንዲቆይ፣ እንዳይሸረሸር የኢትዮጵያውያን አብሮነት፣ ሰላም፣ ፍቅርና መተሳሰብ ጎልቶ እንዲወጣ ይህንና መሰል ሕዝባዊና የአዳባባይ በዓላትን ከሁከትና ብጥብጥ መጠበቅና የማንም መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ማድረግ ከሁሉም የበዓሉ ታዳሚ ይጠበቃል፡፡
ከመጥምቁ
አዲስ ዘመን ጥር 12 /2015