የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ከታላላቆቹ በዓላት አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ይህ በዓል በየዓመቱ የሚከበር ሲሆን ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ፣ በመጥምቁ ዮሃንስ የተጠመቀበትን ለማስታወስ የሚከናወን ታላቅ መንፈሳዊ በዓል ነው። ጥምቀት በአክሱም ዘመነ መንግሥት በስድስተኛው ክፍለ ዘመን መከበር መጀመሩን ታሪክ ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም በዓሉ በንጉሥ ላልይበላ እና በአፄ ገብረ መስቀል ጊዜ ይከበር እንደነበርና ለረዥም ዘመናት በዓሉ ይከበር የነበረው ግን በአብያተክርስቲያናት አጥር ግቢ ውስጥ ብቻ ተወስኖ እንደነበር ነው በበዓሉ ዙሪያ የተፃፉ ሰነዶች የሚገልፁት፡፡ በኋላ ግን ነገሮች እየተቀየሩ ሄደው በየኩኑ ዓምላክ ዘመነ መንግሥት ታላቁ መንፈሳዊ አባት አቡነ ተክለ ኃይማኖት በፈቀዱት መሠረት ታቦታቱ በጥምቀተ ባሕር ውለው እንዲያድሩ ተደረገ፡፡ እናም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በዓሉ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በአደባባይ ደምቆ የሚከበር ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትዕይንት ሆኖ ቀጥሏል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኒስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የጥምቀት በዓል ዛሬም እንደጥንቱ በተለያዩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክዋኔዎች ታጅቦ ነው የሚከበረው። በዓሉ በድምቀት ከሚከበርባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች መካከል ደግሞ ጎንደር ከተማ ቀዳሚዋ ናት። ጥምቀትን በጎንደር መታደም ልዩ ስሜት እንደሚፈጥር የብዙሃኑ የእምነቱ ተከታዮች ይመሰክራሉ፡፡ ጥምቀትና ጎንደር የገጠሙ እለት እንኳንስ ለጎብኚዎች ለነዋሪዎችም ጭምር ሁሌም አዲስ ነው የሚሆኑት፡፡
የጎንደር ጥምቀት በዓል ከመላ ኢትዮጵያ አከባበር የሚለይባቸው በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም በዋናነት ግን ከቀድመው የመሳፍንት እና የአፄው ሥርዓት ጋር በተያያዘ ከተማዋ ለረዥም ዓመታት መናገሻ ከተማ ሆና መቆየቷ፣ በጊዜው የነበረው ኃይማኖታዊ መንግሥት በመሆኑ አብዛኛው ነዋሪ ጥብቅ የኦርቶዶክስ ክርስትና ኃይማኖት ተከታይ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ከሌላው አካባቢ (ከተማ) በተለየ መልኩ “የአርባ አራቱ ታቦታት” መገኛ መሆኗ እንደሆነ አንዳንድ ፃህፍት ያስረዳሉ፡፡
በተጨማሪም ደግሞ በ 17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ከአፄ ፋሲል ቤተ-መንግሥት ምስረታ በኋላ ከቤተ- መንግሥቱ በስተ ምዕራብ በኩል አራት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በ18 ሺ ካሬ ሜትር ምድረ ግቢ ውስጥ በግሩም የሥነ ሕንፃ ውበት ለጥምቀተ ባህር መዋኛና ታቦታት ማደሪያ ተብሎ በአፄ ፋሲል የተሰራው የፋሲለደስ መዋኛ መገኘቱና ለበዓሉ ድምቀት የጎላ ተፅዕኖ ማሳደሩ የጎንደርን የጥምቀት በዓል የተለየ ያደርገዋል ባይ ናቸው፡፡ የፋሲለደስ መዋኛ ስፋት 50 ሜትር በ30 ሜትር ሲሆን፣ ጥልቀቱ ደግሞ 2 ነጥብ 5 ሜትር ይሆናል፡፡ በእርግጥም እንደዚህ አይነት ስፋት ያለው መዋኛ ገንዳ በዚያ ዘመን መገንባቱ በራሱ ድንቅ ያደርገዋል፡፡
ከዛሬ አራት ከፍለ ዘመን (400 አመት ) በፊት የተሰሩት የጎንደር ቤተ መንግሥቶች አስገራሚ ጥበብ ዛሬ ድረስ ውበትና ግርማ ሞገስ ይታይባቸዋል፡፡ የዚያን ዘመን ሰማይ ጠቀስ ቤተ መንግሥቶችን አስገንብተው የጎንደርን ከተማ በመቆርቆራቸው የሚታወቁት አጼ ፋሲል አገሬው በዓሉን የሚያከብርበትን የመዋኛ ቅጥር ግቢ ከልለው ያሰሩ ብልህ መሪ ነበሩ፡፡ ይህም የያኔው ብልህ መሪ ለጥምቀት የሰጠውን ልዩ ክብር አመልካች እንደሆነ ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡ አጼ ፋሲል በቀሃ ወንዝ ዳርቻ ያሰሩት የመዋኛ ገንዳ ዛሬ ድረስ ለጎንደር ጥምቀት መድመቅ ፈርጥ ሆኖ ዘመን ሲነጉድ የዚያ ዘመን የሥልጣኔ አሻራ ያስቃኘናል፡፡
አፄ ፋሲል ከመዋኛው አንድ ጫፍ ታቦተ ጽላቱ በክብር የሚያርፍበት መቅደስ አሰርተዋል፡፡ በዚያ የጸሎት ቤት ሥርዓተ ቅዳሴ ፤ ማህሌት ሽብሸባው ጥምቀት በመጣ በሄደ ቁጥር ይከወንበታል። ግርማ የተላበሰውን ይህን መዋኛ ሶስት ፎቅ ህንጻ አስገራሚ ጥበብ ይታይበታል። ጥምቀት በጥንታዊዋ መዲና በጎንደር ሲከበር የጥበብና የሥልጣኔ አሻራ ሲከበር ለበአል አክባሪዎቹ ብዙ መልዕክትን ማጫሩ አይቀርም። የአጼ ፋሲል የቀደመ ሥልጣኔ ቅሪት ውብ ህንጻዎች የጥንቱን ማንነታችን ከማውሳት ባሻገር የቀደሙትን አባቶቻችን የሥልጣኔ ፈርቀዳጅነት ይመሰክሩልናል፡፡
በዓሉን በከተማዋ ለማሳለፍ ብዛት ያላቸው የአገር ውስጥና የባህር ማዶ ጎብኚዎች በበዓለ ጥምቀቱ ላይ መታደማቸው ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች በተጨማሪነት የጎንደርን ጥምቀት ከሌላው አካባቢ አከባበር የተለየ ያደርገዋል የሚሉም አሉ፡፡ በተለይም ይህች እድሜ ጠገብ በርካታ የታሪክና የባህል ሀብት ያላት ከተማ በድንቁና በደማቁ የጥምቀት አካባበሯ ምክንያት በወርሃ ጥር በርካታ እንግዶችን ታስተናግዳለች። የአብሮነት መገለጫ የሆነች ከተማ ዘወትር በወርሃ ጥር ትደምቃለች፤ ትዋባለች፡፡ በነዋሪዎቿ ማራኪ መስተንግዶ እንግዶቿንም በሃሴትና በምቾት እንዲቆዩ ታደርጋለች፡፡
የጎንደር አባቶችና እናቶች ባማረ የባህል ልብሶቻቸው ተውበውና ደምቀው ጎንደርና ጥምቀትን ያደምቋታል። ጥምቀት ገና ከጥንት ከጠዋቱ የውጭ አገር ጎብኚዎችን ቀልብ ከሚስቡት በዓላት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። አባቶች ጥንግ ድርብ እና አልፎ አልፎም ቀደምቱን ያማራ በርኖስ የባህል ልብሳቸውን ለብሰው ጥምቀትን ደምቀው ሲያደምቁት ፣ የቀረው ነዋሪም አቅሙ በፈቀደ መጠን አዲስ ልብስ ገዝቶ ይለብሳል። በጥምቀት የጎንደር ስመ ጥሩ የአርባ አራቱ ታቦት ፣ ሊቃውንት፤ ስመጥር የደብር አለቆችና ካህናት በሚያምረው ልብሰ ተክህኖ አምረውና ደምቀው ይታያሉ፡፡ በነጭ የባህል ልብሳቸው ላይ ጣል ከሚያደርጉት ጥቁር ካባቸውንና በራሳቸው ጥምጣም የሚታወቁት በጎንደር የቅኔ ፤ የመወድስና የአቋቋም ዝማሬ ሊቃውንት ባማረው አንደበታቸው የውዳሴ መዝሙር ጣዕመ ዜማ፣ ወረብና ሽብሸባውን በአደባባይ የሚያሰሙበት ልዩ አጋጣሚ ቢኖር ይህ የጥምቀት በአል ነው፡፡
በተለይም ደግሞ ኃይማኖት ያዛመዳቸው አማኞች ከከተራ በዓል እስከ ጥምቀት ባህር መልስ (የሚካኤል ንግስ) ድረስ ታቦቱን አጅበው ይጓዛሉ፡፡ በያሬዳዊ ዜማም አምላካቸውን ያመሰግናሉ፡፡ እነዚህ አማኞች በቡድንና በተናጠል ጧፍ፣ ዘቢብና መሰል ስጦታዎችን በታቦቱ ፊት ይጥላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በልጃገረዶች ደረት ላይ ሎሚ ለመወርወር ይጣጣራሉ፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ የባህር ማዶ ጎብኚዎች ደግሞ ትዕይንቱን እየተከታተሉ በካሜራና በብርሃን አሰናስለው ይቀርፃሉ።በግል ማስታወሻቸውም ይከትባሉ፡፡
የጎንደርን ጥምቀት በልዩ ድምቀት ከሚያከብሩ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ውስጥ የሚመደቡት ያለም አጫዋቾች (አዝማሪዎች) ሲሆኑ፣ የበዓሉ ቀን ፈጣሪን የሚያመሰግኑ ዘለሰኛ ግጥሞችን ቢጫወቱም የማታ ማታ የማህበራዊ ሞገድ ሰለባ ናቸውና ፈጣሪን ባመሰገኑበት መሰንቆ ለዓለማዊ ጉዳዮች ሲገጥሙ ሌሊቱን ያጋምሳሉ፡፡ በጥቅሉ ጥምቀት ለኃይማኖቱ ተከታዮች ከኃጢያታቸው የሚነፁበትና አምላካቸውን የሚያመሰግኑበት ኃይማኖታዊ በዓል፣ ለባህር ማዶ ጎብኚዎች ታይቶ የማይጠገብ ልዩ ባህለ- ኃይማኖታዊ የትዕይንት መድረክ ሆኖ ነው የሚያልፈው፡፡
ጥምቀት በጎንደር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ታዳሚ ለመሆን የሚጓጓለት ትልቅ ኹነት ነው። ጥምቀት ጎንደርን በጥር ወር ከሚያደምቋት በዓላት ዋነኛው ነው። ለጥምቀት ብዙዎች ወደ ጎንደር ለመሄድ ልባቸው ይሻል። የቻሉት በቦታው ተገኝተው በሚያዩት ነገር ሁሉ ተገርመው ሀሴትን ይሸምቱበታል። እድሉን ያላገኙት ደግሞ በሩቅ ሆነው ይናፍቁታል። በዚህ ረገድ የነገሥታቱ ከተማ ጎንደር የዘንድሮውንም በዓል በተለየ ድምቀት ለማክበር ዝግጅቷን ያጠናቀቀችው ከሳምንታት ቀደም ብላ ነው፡፡ በተለይም ይህንን የዓለም ሀብት የሆነው የጥምቀት በዓል ለከተማ አማራጭ የገቢ ምንጭ እንዲፈጥር ታስቦም ከተማ አስተዳደሩ ከጥር እስከ ጥር በሚል መርሃግብር ባለሀብቶችን ለመሳብ ሰፊ ስራ አከናውኗል፡፡
ይህንን ሃይማኖታዊ በዓል ምክንያት በማድረግ ከተማዋን መዳረሻቸው ለሚያደርጉ እንግዶች የቆይታቸውን ጊዜ ለማራዘም የተለያዩ ሁነቶችን ከተማ አስተዳደሩ አዘጋጅቶም ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል ከጥር 6 ጀምሮ የተለያዩ የአፄ ቴዎድሮስ የልደት በዓል፤ ለፋሲል ከነማ እንሮጣለን በሚል በርካታ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎችና ሕብረተሰቡ የሚሳተፉበት ታላቅ ሩጫ ተካሂዷል፡፡
የታላቁን ንጉሥ የአጼ ቴዎድሮስን የልደት በዓል ከማክበር እስከ አዝማሪዎች ፌስቲቫል እና የባሕል ፌስቲቫል፣ ከባዛርና ኤግዚቢሽን እስከ ወይዘሪት ቱሪዝም የሳምንቱ የጎንደር ድምቀት ሁነቶች ናቸው። በጥር 9 ደግሞ ታዋቂ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን ያሳተፈው “ግጥም በማሲንቆ” የኪነ-ጥበብ መድረክ በታሪካዊቷ ጎንደር ተደግሷል። ግጥምን በማሲንቆ የኪነ-ጥበብ ምሽት በጎንደር ከተማ አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆ ፣ የአምባሰሏ ንግሥት ማሪቱ ለገሰ ፣ ገጣሚ አበባው መላኩ እና በርካታ ታዋቂ የኪነ -ጥበብ ሰዎች፣ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችና የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ተግኝተውም ነበር። ከእነዚህም መካከከል የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዘውዱ ማለደ አንዱ ሲሆኑ ኪነ-ጥበብ የባሕል፣ የሥልጣኔ ፣ የአመለካከትና የማንነት መግለጫ ነውና እንዲህ አይነት ሁነቶችን ለሚያዘጋጁ አካላት ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም ነው በእለቱ ያበሰሩት፡፡
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዘውዱ የግጥም በማሲንቆ ፕሮግራም በጎንደር አዘጋጆች ለአምባሰሏ ንግሥት ለክብርት ዶክተር ማሪቱ ለገሰ ፣ለአርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆ በኪነ ጥበብ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርክተዋል። በተጨማሪም በዚህች እድሜ ጠገብና የታሪክ ማማ በሆነችው ጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓልን ለማክበር የመጡ እንግዶችን ምቾት ለመጠበቅ አማራጭ ማረፊያዎችንና መሰል ማህበራዊ አገልግሎቶችን ቀደም ብሎ በማሟላትም ነው የበዓሉን ታዳሚዎች ሲጠባበቁ የቆዩት፡፡ በፀጥታ ረገድም የከተማዋን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ ከፀጥታ አካላትና ክህብረተሰቡ ጋር ተሰርቷል። በዚህም ከወትሮ በላቀ ቁጥር ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል ለመታደም የመጡ የከተማዋ እንግዶች ምንም አይነት ስጋት ሳይገባቸው ማክበር ችለዋል፡፡
የከተማዋ የሆቴልና ሬስቶራንት ባለሀብቶችም ከሌላ ጊዜው በተሻለ ዝግጅትና መስተንግዶ እንግዶቻቸውን የተቀበሉ ሲሆን በተለይም ከተለ መደው አገልግሎታቸው ባሻገር ባህላዊ ይዘታቸውን የጠበቁ ክዋኔዎችን በማዘጋጀት የበርካታ ቱሪስቶችን ቀልብ መሳብ ችለዋል፡፡ የባህል ምሽት ቤቶችም እንደተለመደው ሁሉ የከተማዋ ሌላኛው ድምቀት ሆነው የሰነበቱት፡፡ አስጎቢኚ ድርጅቶችና የከተማዋ ወጣቶች እንግዶቹም በበኩላቸው በከተማዋ ባይተዋርነት እንዳይሰማቸውና በነፃነት እንዲቀሳቀሱ የበጎ ፍቃድ ስራዎችን በመስራት አኩሪ ተግባር ፈፅመዋል፡፡
በሌላ በኩልም ከተማ አስተዳደሩ የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል ምክንያት በማድረግ ማልማት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች 100 ሄክተር መሬት ማዘጋጀቱንና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩን ሰምተናል፡፡ ይህና መሰል የከተማ አስተዳደሩ ጥረት ታካዊቷ ከተማ ጎንደር በቱሪዝም ኢኮኖሚያዋን እንድታሳድግ፤ ለነዎሪዎቿ የምትመች ከመሆኑም ባሻገር ዳግም እንደጥንቱ ገናና የሥልጣኔ ፊትመሪነቷን ይዛ እንድትቀጥል በር ከፋች ነው ባይ ነኝ፡፡ የከርሞ ሰው ይበለን እያልኩ ለዛሬ ያሰናዳሁትን በዚሁ ላብቃ፤ ቸር እንሰንብት፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥር 12 /2015