ራሱን “የሊቢያ ብሔራዊ ጦር” (Libyan National Army – LNA) ብሎ የሰየመውና በፊልድ ማርሻል ከሊፋ ሃፍታር የሚመራው ጦር ትሪፖሊን ለመያዝ እንቅስቃሴ ካደረገበት ካለፉት ሁለት ሳምንት ጀምሮ በሊቢያ ያለው ቀውስ እየተባባሰ እንደመጣ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ ከቀናት በፊት ጀኔራል ከሊፋ ሃፍታር ወደ ግብፅ ተጉዘው በካይሮ ከፕሬዚዳንት አብደልፋታህ አል-ሲሲ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ፊልድ ማርሻል ሃፍታር ከፕሬዚዳንት አል- ሲሲ ጋር በተወያዩበት ቀን መቀመጫውን በትሪፖሊ ያደረገውና ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጠው “መንግሥት” ጦር በጀኔራል ሃፍታር ተዋጊ ኃይል የሚታዘዝ ነው የተባለ ተዋጊ ጀት መትቼ ጥያለሁ ብሏል፡፡
የአልጀዚራው ዘጋቢ መሐመድ አብደልዋሂድ ከፊልድ ማርሻል ሃፍታር ጦር አገኘሁት ብሎ ከትሪፖሊ ባሰራጨው ዘገባ በ”መንግሥት” ጦር ተመትቶ የወደቀው ተዋጊ ጀት በፊልድ ማርሻል ሃፍታር ተዋጊ ኃይል የሚታዘዝ እንደሆነ አመልክቷል፡፡
ተዋጊ ጀቱ ተመትቶ የወደቀው የሃፍታር ተዋጊ ኃይል በ”መንግሥት ጦር” ላይ የአየር ድብደባዎችን በላዩ በላዩ አከታትሎ ማዝነቡን በተያያዘበት ወቅት በመሆኑ በተፋላሚዎቹ መካከል የሚደረገው የማጥቃትና የመከላከል ውጊያ ወደለየለት የርስ በርስ ጦርነት ሊያመራ ይችላል የሚል ከባድ ስጋት ፈጥሯል፡፡
የፊልድ ማርሻል ሃፍታር ተዋጊ ኃይል የአገሪቱን ዋና ከተማ ትሪፖሊን ከ“መንግሥት” ነጥቆ ለመውሰድ የጀመረው ጥቃት የሊቢያውያንን ሕይወት ከድጡ ወደማጡ አድርጎታል።
የቀድሞው የሊቢያ መሪ መሀመድ ጋዳፊ በሕዝባዊ አመፅ ከስልጣን ከተወገዱ ወዲህ ሰላም የራቃቸው ሊቢያውያን የሰሞኑ የጀኔራል ሃፍታርና የ“መንግሥት” ኃይሎች ፍልሚያ ሕይወታቸውን የባሰ የከፋ አድርጎባቸዋል፡፡ ውጊያው ከተጀመረ ወዲህም መፈናቀል፤ ስደትና ሞት በሊቢያ ዳግም አገርሽተዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት (World Health Organization – WHO) ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው፤ የፊልድ ማርሻል ከሊፋ ሃፍታር ተዋጊ ኃይሎች ትሪፖሊን የመቆጣጠር ዘመቻቸውን ከጀመሩ ወዲህ ከ120 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከ560 የሚበልጡ ደግሞ ቆስለዋል፡፡ ሁለቱም ቡድኖች “ሰላማዊ ዜጎችን ኢላማ አድርገሃል”
እየተባባሉ እየተወነጃጀሉ ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ በግጭቱ ምክንያት ከ16 ሺህ የሚበልጡ ሰላማዊ ዜጎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንደተሰደዱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ክፍል ይፋ አድርጓል፡፡
የሊቢያ ተቀናቃኝ ኃይሎች ባለፈው ግንቦት ወር በፈረንሳይ ፓሪስ የሰላም ድርድር አካሂደው ነበር፡፡ ድርድሩም እ.ኤ.አ ከ2011 ጀምሮ በርስ በርስ ጦርነት ለምትታመሰው ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሰላም አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለው ተስፋ ያደረጉ ሰዎች ጥቂት አልነበሩም፡፡
ይሁን እንጂ፤ ድርድሩ እንዲደረግ የጋበዙት የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከፋይዘል አል- ሳራጅ እና ከሊቢያ ብሔራዊ ጦር መሪ ፊልድ ማርሻል ከሊፋ ሃፍታር ጋር በኤሊዜ ቤተ- መንግሥት እጃቸውን ሲጨባበጡ የነበረው ድባብ ድርድሩ ብዙም ተስፋ እንዳይጣልበት የሚያደርግ ነው ያሉ ወገኖች በበኩላቸው፤ ከድርድሩ ብዙ አትጠብቁ ብለው ስጋታቸውን ገልጸው ነበር፡፡
ድርድሩ ውጤታማ አይሆንም ብለው ስጋታቸውን የገለፁ ወገኖች የሚያነሱት መከራከሪያ ሃሳብ፤ በፓሪሱ የሰላም ጉባዔ ላይ ከተደራዳሪዎቹ ከሊቢያ ተቀናቃኝ ኃይሎችና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተጨማሪ የ20 አገራት ተወካዮች የተገኙ ቢሆንም፤ በምዕራባዊ ሊቢያ ጠንካራ ይዞታ ያላቸው ተዋጊዎች ግን በጉባዔው ላይ ያለመሳተፋቸውን ነው፡፡
እነዚህ ወገኖች በወቅቱ እንዳሉት፤ መሰረታቸውን በምዕራብ ሊቢያ ላይ ያደረጉት ታጣቂዎች ከፓሪሱ የሰላም ጉባዔ ራሳቸውን ማግለላቸው ትሪፖሊ ከሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዘል አል-ሲራጂ መንግሥት ጋር የነበራቸውን የላላ ጥምረት ጨርሰው ሊያቋርጡት ይችላሉ፡፡ በዚህም በምዕራባዊ ሊቢያ ጠንካራ ይዞታ ያላቸው ተዋጊዎች ከድርድር ውጭ መሆን ደግሞ የተፈለገውን ውጤት ያመጣል ብለው እንዳያምኑ አድርጓቸዋል፡፡
በምዕራብ ሊቢያ ጠንካራ ኃይል ያላቸውን 13 ታጣቂ ቡድኖችን ያሰባሰበውና ከጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዘል አል-ሲራጂ ጋር ደካማ ትብብር ፈጥሮ የነበረው ካውንስል፤ የፓሪሱ የሰላም ጉባዔ የቡድኖቹን ፍላጎት የሚወክል እንዳልሆነ ገልጾ ራሱን ከጉባዔው ማግለሉን አሳውቆ ነበር፡፡ ካውንስሉ ከጉባዔው በፊት ባወጣው መግለጫ “የርስ በርሱ ጦርነት መቋጫ ካገኘ በኋላ ሊቢያውያንን ያሳተፈና ፍላጎታቸውን የሚወክል ትክክለኛ ጉባዔ ለማዘጋጀት ዝግጁ
ነኝ” ብሎ ነበር። በእርግጥም እነዚህ ወገኖች የፈሩት አልቀረም፤ ድርድሩ ውጤታማ ሳይሆን ቀርቶ አሁን ሊቢያውያን በጭንቅ ውስጥ ናቸው። ፈረንሳይም የሊቢያን ተቀናቃኝ ኃይሎች ለማደራደር ከአንድም ሁለት ጊዜ ጥረት ብታደርግም ጥረቷ ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል፡፡
ለ42 ዓመታት ያህል የመሯት ኮሎኔል መሐመድ ጋዳፊ እ.ኤ.አ በ2011 በሕዝባዊ አመፅ ከስልጣን ተወግደው ከተገደሉ በኋላ ታጣቂ ቡድኖች እንደቅርጫ ስጋ የተከፋፈሏት ሰሜን አፍሪካዊቷ ሊቢያ፤ ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቃ ትገኛለች፡፡ በተለይ ደግሞ ምስራቃዊውና ምዕራባዊው የአገሪቱ ክፍሎች እርስ በእርስ በሚዋጉ ታጣቂ አንጃዎች ስር መውደቃቸው ጦርነቱን የከፋ አድርጎታል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውቅና የተሰጠውና በድርጅቱ ድጋፍ የሚደረግለት ቡድን በፋይዘል አል-ሲራጂ የሚመራው ሲሆን መቀመጫውን በትሪፖሊ አደርጎ “ገቨርመንት ኦፍ ናሽናል አኮርድ” (Government of National Accord) የተባለ “መንግሥት” መስርቶ ተቀምጧል፡፡
በፊልድ ማርሻል ከሊፋ ሃፍታር የሚመራውና ራሱን “የሊቢያ ብሔራዊ ጦር” ብሎ የሚጠራው ቡድን ደግሞ “የጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዘል አል-ሲራጂን መንግሥት አላውቅም” ብሎ በምስራቃዊ ሊቢያ በምትገኘው ቶብሩክ ከተማ ላይ ተሰይሟል፡፡ ይህ ቡድን የጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዘል አል-ሲራጂን መንግሥት ተፅዕኖ በትሪፖሊ ብቻ እንዲወሰን አስገድዶታል፡፡
የፊልድ ማርሻል ከሊፋ ሃፍታር ቡድን ለፋይዘል አል-ሳራጅ “መንግሥት” ያለውን ጥላቻ የአል-ሳራጂን “መንግሥት” “መንግሥትነትህን አላውቅም” ብሎ በመናገር ሳይገደብ የትሪፖሊውን መንግሥት ፈንግሎ በመጣል መንግሥት ለመሆን ወደ ዋና ከተማዋ እየገሰገሰ ነው፡፡ የአል-ሳራጂም መንግሥት “እጄን አጣጥፌ አልቀመጥም” ብሎ በሚወስደው የመከላከል እርምጃ ሊቢያውያን ፍዳቸውን እያዩ ነው፡፡
የሊቢያ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ቤንጋዚ በፊልድ ማርሻል ከሊፋ ሃፍታር ቡድን ቁጥጥሩ ስር ናት፡፡ ቡድኑ ቤንጋዚን ከታጣቂ ቡድኖች ነጥቆ በእጁ ያስገባው ሦስት ዓመታት ከፈጀ ዘመቻ በኋላ ነው፡፡ ፊልድ ማርሻል ከሊፋ ሃፍታር እ.ኤ.አ በግንቦት 2014 “ኦፕሬሽን ዲግኒቲ” (Operation Dignity) የተባለ ዘመቻ በማወጅ ቤንጋዚን ከታጣቂ ቡድኖች ነፃ ለማውጣት ቃል ገብተው ነበር፡፡
ሦስት ዓመታትን በፈጀው ዘመቻም የፊልድ ማርሻል ከሊፋ ሃፍታር ጦር ከበርካታ ታጣቂ ቡድኖች ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ እንደተዋጋም ይነገራል፡፡ ፊልድ ማርሻል ከሊፋ ሃፍታር፤ “ምስራቃዊ ሊቢያን በጦራቸው ቁጥጥር ስር ለማድረግ አካባቢውን ወደለየለት ጦርነት ቀጠና ከተውታል… የወደቀውን የኮሎኔል መሐመድ ጋዳፊ ስርዓት ለመመለስ ይፈልጋሉ” የሚሉ ተቃዋሚዎችም ይሰነዘሩባቸዋል፡፡
የሊቢያ ብሄራዊ ጦር የሚባለው ኃይላቸው ከግብፅ፤ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና ከሩስያ ድጋፍ እንደሚደረግለትና ቀስ በቀስ በጦር መሳሪያ እየደረጀ እንደመጣ ቢነገርም፤ አሁንም ድረስ ዘመቻዎቹ በአገሪቱ ልዩ ልዩ ጎሳዎች ትብብርና ድጋፍ ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው የሚሉ አካላት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡
የሊቢያ የርስ በርስ ጦርነት በተቀናቃኝ ኃይሎች ሽኩቻ ብቻ የሚመራ አይደለም። እንኳን እንዲህ ያለ ሰፊ ክፍተት ሲያገኙ ይቅርና ራሳቸው ችግር ፈጥረው ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚፈልጉት የምዕ ራባውያን አገራትም የሊቢያን ወቅታዊ ሁኔታ ለዓላማቸው ማሳኪያ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ይነገራል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2011
በአንተነህ ቸሬ