በጃፓን ኤምባሲ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን አስተባባሪነት ከጥር 5/2015 ጀምሮ በምሥራቅ ድል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የካራቴ ስፖርት ትዕይንት የተካሄደ ሲሆን በትናንትናው እለትም መርሐግብሩ መጠናቀቁ ታውቋል። የካራቴ ትዕይንቱን ያሳዩት አራት የካራቴ አሰልጣኞችና የጄኬስ ኢትዮጵያ የካራቴ ስፖርት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ናቸው።
ካራቴን በትምህርት ቤት ደረጃ ማሳየት የተፈለገው የካራቴ ስፖርትን በኢትዮጵያ በስፋት ለማስተዋወቅ መሆኑን የጃፓን ኤምባሲና የኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን በዝግጅቱ መክፈቻ ወቅት ገልጸዋል። ተማሪዎችና ወጣቶች በካራቴ ስፖርት ፍላጎት እንዲኖራቸውና ብዙ የካራቴ ማስተር(አሰልጣኞችን) ለማፍራት እንደሆነም ተጠቁሟል።
ትዕይንቱን በግልና በጣምራ በመሆን ማስተር አድርያኖ ፒቶኒ፣ማስተር ገነት አበጋዝና ማስተር ሰለሞን ከበደ የተለያዩ የካራቴ እንቅስቃሴዎችን (ካታዎችን) ለተመልካች ማሳየት ችለዋል። ካራቴ በዓለም አቀፍ ደረጃ 128 ካታዎች ሲኖሩት ካታ ጆን፣ ካታ ፑንቴ፣ ካታ ባሳሼየርና ኢፕርየም ፕሩቴ ትዕይንቱን ባቀረቡት አሰልጣኞች አማካኝነት ለተማሪዎች ለዕይታ የቀረቡ ናቸው። በዚህ ትዕይንት በካራቴ ካታዎች እንዴት እራስን መከላከልና ማጥቃት እንደሚቻል ለተመልካች ማሳየት ተችሏል።
ትይንቱን ካቀረቡ አሰልጣኞች አንዱ የሆነው ማስተር ሰለሞን ከበደ፣ በካራቴ ስድስት ዳን ያለውና ለሃምሳ ሦስት ዓመታት ካራቴን፣ ፖኪዶን፣ ጂዶን፣ ጂዶት ሱን፣ ኡሹንና ቴኳንዶን መሥራት እንደቻለ ይናገራል። ማስተር ሰለሞን ካራቴ ከስር ጀምሮ በታዳጊዎች ላይ ቢሠራ ልጆች የያዙትን ስለማይረሱ ስፖርቱን በኢትዮጵያ ትልቅ ደረጃ ማድረስ እንደሚቻል ተናግሯል።
ማስተር ኃይለሚካኤል አሰፋ የጄኬስ ኢትዮጵያ ካራቴ ትምህርት ቤት አሰልጣኝ ሲሆን የካራቴን ስፖርት እንደ ቅርጫት ኳስና መረብ ኳስ በትምህርት ቤቶች እንዳልተሠራበት ይናገራል። በካራቴ ስፖርት ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ የሩቅ ምሥራቅ ሀገሮች በስፖርቱ አሁን ለደረሱበት ትልቅ ደረጃ በትምህርት ቤቶችና ተማሪዎች ላይ ትኩረት አድርገው በመሥራታቸው በመሆኑ በኢትዮጵያም በተመሳሳይ መልኩ ሊሠራበት እንደሚገባ ጠቁሟል። ለዚህም እሱን የመሳሰሉ ባለሙያዎች በቀጣይ ስፖርቱን በደንብ ለማስተዋወቅ በተለያዩ ትምህርት ቤት እየዞሩ ትዕይንቶችን ለማሳየት እቅድ እንዳላቸው ተናግሯል።
ማስተር ገነት አበጋዝ ከኢትዮጵያ በካራቴ ስፖርት ብቸኛ አምስት ዳን ያላት ሴት ስትሆን ኢትዮጵያን ወክላ ለሁለት ጊዜያት ያክል በመላው አፍሪካ ውድድር በካራቴ ስፖርት መሳተፍ የቻለች ሲሆን ለተማሪዎችም ትዕይንት አቅርባለች።
የኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢትዮጵያ በዴቻ፣ ለተማሪዎች ትዕይንት የቀረበበት መድረክ በካራቴ ፌዴሬሽን ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ገልጸው፣ልጆች የካራቴ ስፖርትን በሚመለከቱበት ወቅት ተሰጥዋቸው ምን እንደሆነ ለመረዳት እንደሚያግዛቸው አብራርተዋል። ይህም በካራቴ ስፖርት በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትላልቅ ስፖርተኞችን ለማፍራት እድል ይፈጥራል ሲሉ ተናግረዋል። “የጃፓን ኤምባሲ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፤ ይህ በስፖርቱ የምናደርገው ቅንጅትና የሁለቱን ሀገራት በዘርፉ ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር ስለሆነ እንደ ካራቴ ፌዴሬሽን የጃፓን ኤምባሲን ላመሰግን እፈልጋለሁ” ሲሉም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
የጃፓን ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር ፋሚኦ ኢዳ በበኩላቸው፣ ትዕይንቱን ላቀረቡት አራት የካራቴ አሰልጣኞች ምስጋና ማቅረብ እንደሚፈልጉ ገልጸው፤ ካራቴ የጃፓን ማርሻል አርትና ረጅም ታሪክ ያለው ስፖርት መሆኑን አስታውሰዋል። ካራቴ ሰዎች ነፍሳቸውን በልምምድ የሚያንጹበት የስፖርት ዓይነት እንደሆነም ገልጸዋል። ምክትል አምባሳደሩ አያይዘውም ካራቴ መተባበርን፣ የሰዎች ስብዕናን፣ ድፍረትን፣ ትዕግስትን እራስን ማወቅንና መልካምነትን ማጎልበቻ መሆኑን አብራርተዋል። ዝግጅቱን በጣምራ ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን ስፖርቱን ለሃያ ዓመታት ሲያስፋፋ መቆየቱንና በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ስፖርቱን የሚሠሩ ሰዎች ከአስር ሺ እንደሚልቁም ተናግረዋል።
በትዕይንቱ የጃፓን ኤምባሲ፣ የኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን፣ የምሥራቅ ድል ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ታድመዋል። በአራቱ አሰልጣኞችና በጄኬስ ኢትዮጵያ ካራቴ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የቀረበውን ትዕይንት ለመመልከት በዝግጅቱ የታደሙ ተማሪዎችም በተመለከቱት ነገር ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የካራቴ ስፖርት በተለይም የጃፓን ባሕላዊ ስፖርት ሲሆን በሩቅ ምሥራቅ ሀገሮች በስፋት ይዘወተራል። በቅርቡም ካራቴ የበጋ ኦሊምፒክ ስፖርት ሆኖ በታላቁ መድረክ የተለያዩ አገራት እየተፎካከሩበት ይገኛል። ስፖርቱ በኢትዮጵያም እንዲስፋፋና ባሕል እንዲሆን የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ የሚያመለክት ሲሆን መሰል ትዕይንቶችና ዝግጅቶችም ስፖርቱን የማስተዋወቅ አካል መሆናቸው ተጠቁሟል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጥር 10 ቀን 2015 ዓ.ም