በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በመተከልና ካማሺ ዞኖች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአሶሳ ዞን ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ሰላምን የሚያደፈርሱ ተግባራት ሲፈጽሙ እንደነበር ይታወሳል። የንብረት ውድመትም በተደጋጋሚ አድርሰዋል። በዚህም ሕዝቡ የጸጥታ ችግሩ በስጋት እንዲኖር አስገድዶታል። ከዚሁ የክልሉ ሁኔታ በመነሳት አሁን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል? ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሲባል በክልሉ በሚገኘው ኮማንድ ፖስት መሪነት፣ ከፌዴራል የጸጥታ አካላትና የተለያዩ ክልሎች ልዩ ኃይሎች ጋር በመሆን ኦፕሬሽን በማድረግ የተለያዩ ተግባራትን ከውኗል።
ከሁሉም የሚቀድመው ሰላማዊ ስምምነት በመሆኑም ታጣቂዎቹ እጅ እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርቧል። በተለይም በኮማንድ ፖስት ሲመሩ የቆዩትን መተከልና ካማሺ ዞኖችን ሰላማዊ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረቱን ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም በርካቶች እጅ ሰጥተው፣ሥልጠና ወስደውም ትጥቅ በመፍታት ወደ ልማት ፊታቸውን አዙረዋል። ስምምነት ሁሉን እንደሚፈታ አምነው ተቀብለውም ሰላማዊ ሕይወትም ጀምረዋል። ይህ ጉዳይ እንደክልል ምን አይነት መልክ ነበረው? አሁናዊ የክልሉ ሁኔታ ምን ይመስላል ስንል ከክልሉን የሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊውን አቶ አብዮት አልቦሮ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ክልሉ በተለያዩ ጸጥታ ችግሮች ሲፈተን እንደነበር ይታወሳል፤የችግሩ መሠረታዊ ምንጭ ምን ነበር ?
አቶ አብዮት፡- እንደተባለው ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በክልሉ ውስጥ በተለያዩ ዞኖች ላይ የተፈረራቀ ግጭቶችና ችግሮች ነበሩ። ለዚህ መንስኤው ደግሞ ግልጽ ነው። በወቅቱ የነበረውን ለውጡ እንቀለብሳለን የሚሉ አካላት ፍላጎት ነው። ስለዚህም እዚህም እዛም ችግሮችን በመፍጠር በለውጡ ሂደት ላይ እንቅፋት ለመሆን ሞክረዋል። ይህንን ችግር ከፈጠሩበት አካባቢ አንዱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነው።
በዋናነት ለውጡን የመቀልበስ ሂደት እንደ ሀገር ለተጀመረው የለውጥ ጉዞ እንቅፋት የመሆን ሁኔታዎች ናቸው። ይህ ተግባር ሲከናወን የቆየው ደግሞ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ነው። ክልሉ ላይ ትልቅ ዘመቻ ይደረግበት ነበር። ክልሉን የሚመሩ መሪዎች ጭምር በዘመቻ ለመጣል ትልቅ ጥረት ተደርጎ እንደነበር መውሰድ ይቻላል።
ክልሉ እንደሚታወቀው ብሔር ብሔረሰቦች ያሉበት ኅብረ ብሔራዊ ክልል ነው። የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ይኖሩበታል። ይህንን ኅብረብሔራዊ ክልል ለማተራመስ የሕዝቡን እሴት በመሸርሸር የብሔር ግጭት እናስነሳለን የሚል እኩይ የሆነ አስተሳሰብን ይዘው እንዲነሱ ሆነዋል። እነዚህ ኃይሎች ክልሉን የጦርነትና የግጭት አውድማ ለማድረግ ፍላጎት ነበራቸው። ሌላው የችግሩ ምንጭ ኅብረ ብሔራዊነትን የያዘውን ክልል ወደ ብሔርተኝነት በመቀየር ግጭት ውስጥ የማስገባት ዓላማን ያነገቡ አካላት ሴራ ነው።
የሁሉም ኢትዮጵያውያን የዓይን ብሌን የሆነው፣ መጠናቀቁን በጉጉት የሚጠብቁት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ጭምር ፕሮጀክት የሆነውን ታላቁ የህዳሴ ግድብን ለፍጻሜ እንዳይበቃ ለማድረግ ያለሙ አካላት ፍላጎት ነው። በተጨማሪም ክልሉ ከደቡብ ሱዳንና ከሰሜን ሱዳን ጋር ድንበር የሚዋሰን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በእነዚህ አካባቢዎች ላይ በረከት ያለ የፀረ-ሰላም ኃይል እንቅስቃሴ የሚታይበት መሆኑም የችግሩ መነሻ ምንጭ እንዲሆን አድርጎታል።
ክልሉ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ፋይዳ ያለው ትላልቅ የኢኮኖሚ ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናት ያሉበት፣ በእርሻ፣ ኢንቨስትመንት ላይ ትልቅ ሥራ መሥራት የሚቻልበት፣ የወርቅ ክምችት ያለበት፤ ዕምነበረድ፤ የከሰል ድንጋይ የመሳሰሉት ያሉበት በመሆኑ ሁሉም ይፈልገዋል። እናም ይህንን ሀብት ብቻቸውን መጠቀም ስለሚፈልጉ የተለያዩ ሰበቦችን በመፍጠር የክልሉ ሕዝብ ግጭት ውስጥ እንዲቆይ አድርገውታል። ክልሉ ሰፊ የአስተዳደር ወሰንን የሚጋራ መሆኑም
ሌላው የችግር መንስኤ ነበር። ከኦሮሚያ፣ ከአማራና ከጋምቤላ ክልል ጋር የሚጋራው ወሰን አለው። እናም ይህን እንደምቹ ሁኔታ እንጠቀማለን፤ አካባቢው ላይ ትርምስ እንፈጥራለን የሚሉ አካላት ችግር ውስጥ እንዲገባ ያደረጉበት ነው። አካባቢውን ማደፍረስ ከቻልን በሀገር ላይ ትልቅ ጫና እንፈጥራለን የሚል እሳቤ የነበራቸውም አካላት መነሳታቸው ችግሮች ለመቀስቀሳቸው ዋና ምንጭ ሆኗል። ስለዚህም ላለፉት ከሦስትና ከአራት ዓመታት በላይ መልካቸውንና ቦታዎችን እየቀያየሩ አንዴ ማኦ አኮቦ ልዩ ወረዳ ላይ፤ሌላ ጊዜ ደግሞ አሶሳ ዞን እንዲሁም ካማሽና መተከል ዞን ላይ እየተፈራረቁ ክልሉን ለፈተና ዳርገውታል። ምንጮቹ መልከ ብዙ ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- የጸጥታ ችግሮቹን ተከትሎ የተፈጠሩ ቁሳዊና ሰብዓዊ ጥፋቶች በምን ደረጃ ይገለጻሉ?
አቶ አብዮት፡- ጦርነትና ግጭት ሲኖር እንደ ክልል ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ቦታ በርካታ ሰብዓዊ ቀውሶች ይፈጠራሉ። በነበረው ግጭት ምክንያት በክልሉ በርከት ያሉ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመቶች ደርሰዋል። ምክንያቱም በጦርነት ውስጥ ማንኛውም አካል ሊያተርፍ አይችልም ውድመት ካልሆነ በስተቀር። ስለዚህ በክልሉ በነበሩ ግጭቶች በርከታ ዜጎቻችን ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። የገጠማቸው ማኅበራዊና ስናልቦናዊ ቀውስም ቀላል አይደለም። በርካታ የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋማት ወድመዋል። የሰው ሕይወትም ጠፍቷል።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን የወደመ ንብረት መልሶ ለማቋቋም ምን አደረጋችሁ፤ የተፈናቀሉ ወገኖችን ከመመለስ አኳያስ ምን እየተሠራ ነው ?
አቶ አብዮት፡- የቦታው ጉዳይና የደረሰው ጉዳት ኮሚቴ ተቋቁሞ በማጥናትና በመለየት የሥራ ጅማሮውን ማድረግ ተችሏል። ከዚህም አኳያ አንጻራዊና ዘላቂ ሰላም የተፈጠረባቸው አካባቢዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸዋል። የወረዳዎች ልየታ ተደርጎ በርካታ ተግባራትም ተከናውነዋል። ለአብነት በመተከል፣በከማሽና አሶሳ አካባቢዎች ላይ ወደቀያቸው ተመልሰው ወደልማት እንዲገቡ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል። በተመሳሳይ የወደሙና በከፊል የፈራረሱትን የመንግሥት ተቋማት መልሰው እንዲገነቡ አልያም እንዲጠገኑ የተደረገበት ሁኔታ አለ።
ግጭቱ ፈጥሮት ያለፈው ያለመተማመን ጉዳይ ከፍተኛ ነውና እርሱንም ወደነበረበት ለመመመለስም ብዙ ሥራዎች ተከናውነዋል። ለአብነት በቡድኖች መካከል፣ በግለሰቦች መካከል ቅራኔን ፈጥሮ ያለፈበት ሁኔታ ስለነበር ያንን ለመፍታት የማኅበራዊ እሴት ሀብቶቻችንን መጠቀም ተችሏል። እንደ እርቀሰላምና ይቅርባይነት የመሳሰሉ ባሕላዊ ሥነሥርዓቶችን በሰፊው ተጠቅመንባቸዋል። ምክንያቱም ማኅበረሰቡ መታከም የሚችለው በእነዚህ ባሕላዊ እሴቶቹ አማካኝነት ነው። እናም የስነልቦና ግንባታውን እነዚህን እሴቶች በመያዝ ማከናወን ተችሏል። አሁንም በዚህ መልኩ እየተሠራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- ሕዝብ ተረጋግቶ እንዲሠራ ችግር የሚፈጥሩ አካላትን አደብ ማስገዛት አስፈላጊ እንደሆነ ይታመናል። ከዚህ አኳያ እንደክልል ምን ተሠራ?
አቶ አብዮት፡– ልክ ነው። ለሰላም መኖር ሰላም ጠል አካላት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ወደ መስመር ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል። እናም እንደክልል ይህንን ከማረጋገጥ አኳያ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። ከሁሉም በላይ ትልቅ ነው ተብሎ የሚወሰደው ደግሞ መቀመጫቸውን ወደ ሱዳን አስገብቶ በህዳሴ ግድቡ አካባቢ ይንቀሳቀስ የነበረውን ታጣቂ ኃይል ወደ ሰላም ስምምነቱ ማስገባት መቻሉ ነው። ይህ አካል ከዚህ ቀደም የህዳሴ ግድቡ ግብዓት አቀራረብ ላይ ተግዳሮት ሲፈጥር የነበረ ነው። እናም ወደሰላማዊ ስምምነቱ እንዲገቡ በማድረግ ነገሮችን መቀየር ተችሏል።
ለአብነት የቤኒ ታጣቂዎች ማለትም ከዚያ በፊትም የጉሙዝ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (የጉህዴን) ታጣቂዎች ነን ብለው ራሳቸውን ያደራጁ አካላት እንዲሁ በመተከልም በካማሺም የነበሩ ታጣቂዎች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። እናም እነዚህን አካላት በሰላማዊ መንገድ ከክልሉ መንግሥት ጋር ተስማምተው በክልሉ ላይ በልማት ለመሠማራትና ክልሉን ለማሳደግ ዝግጁ ነን በሚል ወደሰላም ስምምነቱ እንዲገቡ የተደረገበት ሁኔታ አለ።
ሱዳን ጭምር የነበሩት የቤኒን ታጣቂዎችም መሣሪያቸውን ጥለው ወደ ተሐድሶ ማዕከል በመግባት ተሐድሶውን እንዲያጠናቅቁ ሆነዋል። ወደሰላምና ልማት ሥራ ለመግባትም ቁርጠኝነታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። አሁን ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ለመሥራት ተዘጋጅተዋል። ይህ ደግሞ ሰላሙን ከማረጋገጥ አኳያ ትልቅ ሚና ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን፡- ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በክልል ሆነ በፌደራል መንግሥት በኩል የተደረጉ ጥረቶች ምን ይመስላሉ?
አቶ አብዮት፡– ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ ክልሉን የጦርነት አውድማ ለማድረግ አንዳንድ አካላት ሲሠሩ ነበር። በተለይም ረዘም ያለ የግጭት ቀጠና ሆኖ እንዲቆይ ብዙ ለፍተዋል። በዚህም የመተከል ዞን በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዲቆይ አድርገውታል። በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመው የፌደራል ኮማንድ ፖስት በቂ ሥራ ሲከውን ከርሟል። ለአብነት የጸጥታ ሥራው በኦፕሬሽን እንዲሠራ ተደርጓል። በሰላማዊ መንገድ የሰላም ድርድር ሥራው እንዲከናወን የተደረገበት ሁኔታም አለ። ከታጣቂዎች ጋር የነበረውን የሰላም ስምምነት መሣሪያን እስከማስቀመጥ የደረሰ ሥራ መከናወን የቻለውም በጥሩ አመራር ተግባሩ በመከናወኑ ነው። ከፌደራሉ ሥራ ጋር የነበረው መስተጋብር እንዳለ
ሆኖ ክልሉ ብቻውን የሠራቸው ተግባራትም አሉ። ለአብነት ከአጎራባች ክልሎች ጋር አብሮ መሥራትና ሰላምና ጸጥታን ማስፈን ላይ ጥሩ የሚባሉ ውጤቶችን አምጥቷል። አብሮነትን የመገንባት ሥራዎችን ከክልሎቹ ጋር ሲከውን ቆይቷል፤ አሁንም እያከናወነ ይገኛል። የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደቀያቸው ለመመለስም እንዲሁ በአብሮነት ተሠርቷል። ከዚያ አለፍ ሲልም የጋራ የሰላም መገንባት ጽሕፈት ቤቶችን በማቋቋም የጸጥታ ሥራዎችን በመደጋገፍ መርሕ ለመሥራት የተሞከረበት ሁኔታ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም ፤ በተለይ ከአማራ ክልል ጋር። የሌሎች ክልሎች የጸጥታ አካላት የሰላምና ጸጥታ ሥራው ላይ ገብተው እንዲያግዙ በክልሉ ሲሠራ ነበር። በተለይም በኮማንድ ፖስት ውስጥ ተካተው በርካታ እገዛዎችን እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። አሁንም አብሮ የመሥራት እድሎችን አመቻችቶ እንደቀጠለ ነው።
ከኦሮሚያ ክልል ጋርም በተለይ ከወሰን ጋር በተያያዘ በካማሺና በአሶሳ በማኦ ኮሞ አስተዳደር የሚንቀሳቀሰውን አሸባሪው ሸኔን በተቀናጀ መልኩ በጋራ እንዲደመሰስ በማድረግ አካባቢ ቀጠናው ወደ ሰላም እንዲመጣ የማድረግ ሥራም ተከናውኗል። አሁንም በጋራ እየሠራን ነው። ለዚህ ደግሞ የተደራጀ ኮማንድ ፖስት አለ፤ መከላከያ ሠራዊትና የክልሉ ልዩ ኃይልም ያግዛል፤ ሚሊሽያው ተጨምሮ። ስለዚህም በቅንጅት ተግባሩን እየከወነ በመሆኑ ትልቅ ውጤት እየታየበት ይገኛል። እንደ አጠቃላይ እንደክልል በመልሶ ማቋቋሙ፣ በስነልቦና ግንባታ፣ ወደልማት ሥራ የሚገቡበትን ሥርዓት መፍጠሩ ላይ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። በፌደራልም ደረጃ ሰላምና ጸጥታ በክልሉ እንዲሰፍን የተቻለው ሁሉ እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን የተገኘውን ውጤት ዘላቂ ለማድረግስ ምን እየተሠራ ነው ?
አቶ አብዮት፡- ሁልጊዜ በጦርነትና በግጭት ዘላቂ ሰላምን ማምጣት አይቻልም። ሰላም ሊረጋገጥ አይችልም። እናም ችግሮችን በውይይትና በስምምነት ለመፍታት እየተሠራ ነው። ለዚህ ደግሞ ማሳያው የክልሉ መንግሥት ቁርጠኛ ሆኖ በርካታ ተግባራትን እየከወነ መሆኑ ነው። አንዱ ታጣቂዎችን ወደ ሰላም ስምምነት ማስገባቱ ነው። ከዚያ ባሻገር ደግሞ ለሰላም ተመላሾች እንደየፍላጎታቸው በተለያዩ የልማት ተግባራት ላይ እንዲሠማሩ ክልሉ ሁኔታዎችን አመቻችቷል።
ለምሳሌ፡- በእርሻ ሥራ ላይ እንሠማራለን ላሉት አካላት ለእርሻ ሥራቸው የሚያግዙ እንደ ትራክተር አይነት መሣሪያዎችን ገዝቶ በመስጠት ወደ ሥራ የሚገቡበትን ሁኔታ ፈጥሯል። ሌላው በማኅበር እንዲደራጁ በማድረግ ቦታና ገንዘብ አግኝተው ወደ ሥራ እንዲገቡ አመቻችቷል። የትምህርት ዝግጅት ያላቸውን ደግሞ ወደ መንግሥትና መሰል ሥራዎች እንዲገቡም እድል እየሰጠ ይገኛል።
ከሥራቸው የተፈናቀሉትም የቀደመውን ሕይወታቸውን እንዲመሩ ለማድረግ የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ነው። ወደ ንግድ ሥራ መግባት እፈልጋለሁ ያሉትንም እንደየፍላጎታቸው የማገዝ ተግባር እያከናወነ ነው። ይህ ደግሞ ማኅበረሰቡ የተረጋጋ ሕይወት እንዲኖረው በማድረግ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። የጦርነትን አስከፊነት አውቆ ዳግመኛ በዚህ ነገር ውስጥ እጁን እንዳያስገባም ያደርገዋል። ጦርነት አውዳሚ መሆኑን ተረድቶም ልማትን እንጂ ጦርነትን እንዳይመርጠው ያስችላል።
አዲስ ዘመን- በቅርቡ በክልሉ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ከመንግሥት ጋር በተደረሰ የሰላም ስምምነት መሠረት ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንደተመለሱ ገልጸውልናል። ይህ የሰላም ስምምነት ሂደቱ ምን ይመስል ነበር?
አቶ አብዮት፡– የሰላም ስምምነት ሂደቱ እጅግ አድካሚና ቀላል አይደለም። ምክንያቱም አንድም ስምምነት አልጋ በአልጋ የሚሆንበት አጋጣሚ አይኖርም። ስለዚህም ከታጣቂዎቹ ጋር የነበረው የሰላም ስምምነት ብዙ ሂደቶችን ያለፈ ነው። በርካታ መነጋገሮች የነበሩበት፣ በርካታ ግዴታዎች የተጣሉበት ነው። ለአብነት በመንግሥት በኩል ከስምምነቱ በኋላ እነዚህ አካላት በልማት ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ፤ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥና ተሳትፏቸው እንዲያድግ ማድረግ፤ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸው ወደ ቀያቸው እንዲመለሱና እንዲሠሩ ማስቻል፤ አስተሳሰባቸው ወደልማት የሚዞርበትን ሥራ መሥራት የሚሉት ዋናዋና ግዴታዎች ናቸው።
ከታጣቂዎቹ ደግሞ የገቡትን ቃል ማክበር ሲሆን፤ በተለይም ትጥቃቸውን ፈተው በሰላማዊ መንገድ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን ማገልገል አለባቸው የሚል ነው። የተሰጣቸውን እድል እየተጠቀሙ መቀጠል እንጂ ተመልሰው ወደግጭት መግባት የለባቸውም የሚለው ግዴታ ተጥሎባቸዋል። እነርሱም ተቀብለውት ወደ ሥልጠና ገብተው ለመመረቅ በቅተዋል። ወደ ሥራ እየገቡም ይገኛሉ። ለዚህ ሂደት ስኬት ደግሞ ብዙ አካላት ለፍተዋል። ለአብነት የንቅናቄው አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች ሰፊ ውይይት በማድረግ የማግባባት ሥራ ከውነዋል። በዚህም ‹‹እስካሁን የተከፈለው ዋጋ ይበቃል›› የሚል አቋም የተያዘበት ውጤት ታይቷል።
ስምምነቱ ችግሮችን ወደጫካ ገብቶ በመሣሪያ በመታገል ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ በመነጋገር መፍትሔ መስጠት እና በመተከልና ከማሺ ዞኖች ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ አስተማማኝ ሰላም በማስፈን የክልሉን ሕዝብ የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥን ማዕከል ያደረገ እንዲሆንም አስችሏል። አሁንም ቢሆን ይህ ውጤት በትክክል እስከታች ወርዶ ለክልሉ ሠላም ተጨባጭ እንዲሆን እየተሠራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለታጣቂዎቹ የተሐድሶ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል ፤ሥልጠናው ታሳቢ የሚያደርገው ምንድን ነው ? ሠልጣኞቹ የሚያነሱት ጥያቄ ይኖር ይሆን?
አቶ አብዮት፡– ታጣቂዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተጠቃሚ አልሆንም፣ ሥርዓቱ የተሻለ እድሎችን እየሰጠን አይደለም፤ ማኅበረሰባችንም ተጠቃሚነቱ አልተረጋገጠለትም የሚሉና መሰል ነገሮች ናቸው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከለውጡ ጋር ተያይዞ ያለው የግንዛቤ እጥረት ሲሆን፤ ይህንን ከመፍታት አኳያም ታሳቢ ተደርጎ ሥልጠናውን እንዲወስዱ ተደርጓል። ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ የሚሰጡ ነገሮችን በማካተትም ሥልጠናውን የሚወስዱበት ሁኔታ ነው የተመቻቸው። ለምሳሌ፡- የኢትዮጵያና የክልሉ የፖለቲካ ዳራ ምን ይመስላል፣ ሕገመንግሥታዊ መርሆች ምን ምን ናቸው፣ ብሔራዊ የደህንነት ጉዳዮች በምን መልኩ ይታያሉ የሚሉት ፖለቲካዊ አስተሳሰባቸውን ሊለውጡ ይችላሉ ተብለው ከተሰጡት መካከል ናቸው። እነዚህ አካላት ግጭት ውስጥ የቆዩ በመሆናቸው የስነልቦና ሥልጠናዎች እንደሚያስፈልጓቸው ይጠበቃል። ስለዚህ ይህንን ታሳቢ ያደረጉ ስልጠናዎችን በማካተት የሚሰለጥኑበት ሁኔታ አለ ።
በተጨማሪም ከተሐድሶ በኋላ ለሚኖራቸው ቆይታ አጋዥ የሆኑ ስልጠናዎችን ወስደዋል። ምን ሊገጥማቸው ይችላል ፤ ምንስ መልካም አጋጣሚዎች አሏቸው፤ ክልሉ ላይ ያሉ ምቹ ሁኔታዎች ምን ይመስላሉ የሚለውንና የሥራን ክህሎት ስልጠናዎችን እንዲወስዱ ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፡- ከታጣቂ ቡድኑ ጋር የተደረሰው የሰላም ስምምነት በድንበር አካባቢና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ፋይዳው ምን ድረስ ነው ?
አቶ አብዮት፡– ድንበር አካባቢዎች ላይ ብዙ የምንዋሰናቸው አሉ። ለምሳሌ፡- የሱዳን ድንበር አንዱ ነው። እናም የእነዚህ አካላት ወደ ስምምነቱ መግባት በተለይም በቀጠናው አካባቢ ለሚፈጠረው ዘላቂ ሰላም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። በየቦታው የሚፈጠሩትን አለመተማመኖች የሚፈታም ነው። ምክንያቱም በዚያ ተሸሽጎ ጥቃት ሊያደርስ የሚችል አካል አይኖርም። በዚያ ላይ ሰላማዊ ስምምነት በራሱ የሚያመጣው ውጤት አለ። ከአዕምሮ እረፍት ጀምሮ ብዙ ለውጥን ያጎናጽፋል። ስጋትንና ፍርሃትን አቅልሎ የሰላም አየር ለመተንፈስም ያስችላል። ስለዚህም ከእነዚህ አካላት ጋር ሰላማዊ ስምምነት ማድረጉ ብዙ ነገሮችን እንደሀገር ያስገኛል።
ታጣቂዎቹ ከዚህ በፊት በነበራቸው አቋም ትጥቅ ታጥቀው በየጫካው እየሄዱ ንጹሐን ዜጎች ላይ ጉዳት ያደርሳሉ፤ በንብረት ላይም እንዲሁ ውድመት የሚፈጥሩ ነበሩ። ጉዳቱ ቀላል አይደለም። ሆኖም ከዚህ የባሰ አደጋ እንዳይደርስ ስምምነቱ በብዙ መንገድ አግዟል ብሎ መውሰድ ይቻላል። ምክንያቱም በተለይ ክልሉ እንደሀገር ሁሉም የተረባረበበት ትልቁ የሀገር ተስፋ የህዳሴ ግድብ መገኛ በመሆኑ አደጋ እንዳይከሰትበት ለማድረግ ተችሏል። በስምምነቱ ዛሬ ላይ የሚታሰበው ግጭት ፤ ፍርሃትና ስጋት ሳይሆን ልማት ነው። ለዜጎችም መንግሥት መስጠት የሚችለው ይህንን ነው። ስለዚህም ስምምነቱ መንግሥትን ከጸጥታ ሥራ ወደ ልማታዊ አስተሳሰብ አስገብቶታል ብሎ መውሰድ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ በሚኖሩ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች መካከል አልፎ አልፎ የሚታይን አለመግባባት ለማስወገድና አዲስ የወንድማማችነት የታሪክ ምዕራፍ ለመክፈት ምን እየተሠራ ነው?
አቶ አብዮት፡– ክልሉ ኅብረ ብሔራዊ ክልል ነው። ነገር ግን በብሔረሰቦች መካከል አለመግባባት አለ ተብሎ መወሰድ የለበትም። ምክንያቱም መቃቃርንና ግጭቶችን የሚፈጥሩት ጥቂት ግለሰቦች ናቸው። ጥቂት ቡድኖች የብሔር ሽፋንን ይዘው አለመግባባትን ሊፈጥሩ ይችላሉ። ተከታዮችንም የሚያፈሩበት ሁኔታ ይፈጠራል። ምክንያቱም ሀሳባቸውን ሲያቀርቡ ለብሔራቸው ተቆርቋሪ በመምሰል ሌላው ብሔረሰብ ላይ ጥቃት ለማድረስ ይንደረደራሉ። በዚህ ዙሪያ የሄዱበት ርቀት ነበር። ነገር ግን እነዚህ አካላት ሙሉ ብሔረሰቡን ይወክላሉ ብሎ መውሰድ አይቻልም። ይህ ሲባል ግን የደረሰው ጉዳት ቀላል ነው አያስብልም። በእነዚህ አካላት ምክንያት የሥነልቦና፣ የኢኮኖሚ፣ማኅበራዊ ጉዳት ደርሷል። በመንግሥትና በሕዝብ መካከልም አለመተማመን ተፈጥሯል። በማኅበረሰብ መካከልም እንዲሁ። ስለዚህም በሕዝቦች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር ለማድረግ እንደክልል በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።
በመጀመሪያ የተደረገው በማኅበረሰብ ውይይት፣ በሀገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች አማካኝነት ወንድማማችነትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ሥራዎች እንዲከናወኑ ሆነዋል። በሁለተኛ ደረጃ መልካም እሴቶቻችንን አጉልቶ በማውጣት ወንድማማችነትን የማጎልበት ሥራ እየተሠራ ነው። ባሕላዊ የችግር መፍቻ መንገዶችን እንደ እርቅ ሥርዓት ዓይነቶችን በመጠቀም መልካም ግንኙቶችን ወደማጠናከሩ ሥራ ተገብቷል። ይህ ደግሞ ቁርሾዎች የሚታከሙበት፤ ጠባሳዎች የሚድኑበትን መንገድ አሳይቷል። ማኅበረሰቡ በራሱ ወግና ባሕል እንዲቀራረብ አስችሎታል።
አዲስ ዘመን፡- ችግሮች በሰላማዊ መንገድ በድርድር እንዲያልቁ በክልሉ የተደረገው ጥረትና የተገኛው ስኬት እንደ አንድ ሀገራዊ ተሞክሮ የሚኖረው ፋይዳ እንዴት ይገለጻል?
አቶ አብዮት፡- ችግሮች በጦርነት ሊፈቱ አይችሉም። ለመነጋገር እድል የማይሰጡ ሲሆኑ ብቻ ነው እንደአማራጭ ጦርነት መፍትሔ የሚሆነው። እናም ግጭትን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ከምንም በላይ አስፈላጊና ዘላቂ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ነው። እንደ ክልል የተወሰደው እርምጃም ከክልል አልፎ ለሀገር ያለው ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ ነው።
በግጭትና በጦርነት ማንም አካል አትራፊ አይደለም። ሕዝብም እንደሕዝብ ያረጋገጠው ነው። ምክንያቱም በግጭቱ ምክንያት ብዙዎች ቤተሰባቸውን አጥተዋል፤ ሀብት ንብረታቸው ወድሟል፤ የአዕምሮ እረፍት አጥተዋል፤ተረጋግቶ ለመኖር እንኳን አልተቻለም። ስለዚህም ምርጫ የሌለው ጉዳይ ሰላምን ለማምጣት መነጋገሮችና ሰላማዊ ድርድሮችን ማድረግ ነው። ከዚህ አንጻርም ክልሉ ተጠቅሞበት ችግሮቹን እያለፈበት ይገኛል። ይህ በመሆኑ ዳግመኛ ለሚጠፋው ነገር ዋጋ አትከፍልም። ዜጎቿ ወደልማት ገብተውም የተሻለ ነገር እንዲመጣ ያስችሉታል። ይህ ደግሞ ለሀገርም የሚሆን ነገር ነው። ምክንያቱም አንድ ክልል ሰላም አላገኘም ማለት ሀገር እንደሀገር የምትከፍለው ዋጋ ከፍ ያለ ነው። እናም ጥቅሙ የሀገርም የክልልም ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን በክልሉ ያለው ሰላምና መረጋጋት እንዴት ይገለጻል ?
አቶ አብዮት፡– ክልሉ በአሁኑ ሰዓት በተሠሩ ሥራዎች ወደ ሰላምና መረጋጋት ውስጥ እየገባ ይገኛል። ከእለት እለት መሻሻሎች እየታዩበትም ነው። አልፎ አልፎ በተለይም መተከል አካባቢ ላይ ጉባ ወረዳ ወንበራ ውስጥ ፤ ድባጤ አካባቢ አንዳንዴ የሚታዩ ቡድን እየፈጠሩ የሚንቀሳቀሱ አካላት ከሚያጋጥም ችግር ካልሆነ በስተቀር ሰላም መጥቷል ብሎ መውሰድ ይቻላል። እነዚህ አካላትም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ ተደርጓል። ያ ካልሆነ ደግሞ ለዘላቂ ሰላም ሲባል የሚወሰዱ እርምጃዎች ይኖራሉ። ሆኖም የክልሉ መንግሥት እዚህ ውስጥ እንዳይገባ እየሠራ ነው። ምክንያቱም ሰላምን የሚተካ ነገር የለም።
እንደክልል ከግጭት ይልቅ መልሶ መገንባትና ልማት ላይ አተኩሮ እየሠራ ይገኛል። ይህም ሆኖ ሌሎች ተጨማሪ ፈተናዎች እያጋጠሙ መሆኑን ሳላነሳ አላልፍም። ችግሩ ከክልሉ ውጪ በሆኑ ምክንያቶች የተፈጠረ ነው። አሁንም ክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖረው እየተፈተነ ይገኛል። በምዕራብና ምስራቅ ወለጋ አካባቢ በሚንቀሳቀሰው የሸኔ ቡድን አማካኝነት አዋሳኝ የክልሉ ቀጠናዎች ችግር እያጋጠማቸው ነው። በተለይ እንደ ከማሺና አሶሳ ባሉ ዞኖች ክልሉ ትልቅ ጫና ውስጥ ገብቷል። እንደልብ የክልሉ ሕዝብ መንቀሳቀስ አልቻለም። መንገዶች ተዘግተዋል። በተጨማሪም ማኅበረሰቡ ላይ የሥነልቦና ጫና፤ የኑሮ ውድነትና የትራንስፖርት ችግርም ፈጥሯል።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ እነዚህ ችግሮችን ለመፍታት በክልሉ መንግሥት ምን ታስቧል?
አቶ አብዮት፡– የመጀመሪያው ሰላምና ጸጥታውን ከማረጋገጥ አኳያ ይተገበራል ተብሎ የታሰበው ጉዳይ ሲሆን፤ ይህም መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ናቸው። የሰላም ተመላሾችን ወደ ሥራ በማስገባት የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥና የክልሉን ልማት ማፋጠን ላይ ይሰራል። የመልካም አስተዳደር ችግር ናቸው ተብለው የተለዩ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ሌላው ሥራ ይሆናል። ከአጎራባች ክልሎች ጋር በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም በልማት ሥራ ላይ የተጀመረውን አጠናክሮ ማስቀጠልም አንዱ የቀጣይ እቅድ ነው።
በድንበሮች አካባቢም ያለውን ሰላም ማስፈን ላይ በተለይም በሱዳን አካባቢ በሰላማዊ መንገድ የጋራ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል። ይህም እንደ ቀጣይ እቅድ የተያዘ ነው። የሰላም አማራጭን የማይቀበልና በጦርነት እኖራለሁ የሚል አካል ካለም ለዚያ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠትም በቂ የኃይል ዝግጅት ያስፈልጋል። ይሄ በቀጣይ ይሠራል ተብሎ የታሰበ ተግባር ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ እናመሰግናለን።
አቶ አብዮት፡- እኔም እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥር 10 ቀን 2015 ዓ.ም