የአለም የከተማ ነዋሪዎች ብዛት እየጨመረ መምጣቱንና ከዚህ ሕዝብ ግማሽ ያህሉ በከተማ እንደሚኖር መረጃዎች ይጠቁማሉ። በኢትዮጵያ 20 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በከተማ እንደሚኖር እና እስከ 2040 ዓ.ም ድረስ የከተማ ሕዝብ ብዛት በሦስት እጥፍ ሊያድግ እንደሚችል መረጃዎች ያሳያሉ። እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ደግሞ የሕዝብ ቁጥሩ ከዚህም በላይ እንደሚጨምር ይገመታል።
በእዚሁ ልክ መንግስታዊና ሌሎች አገልግሎቶች መስጠት እንደሚያስፈልግ ይታመናል። ይሁንና የሀገራችንን ከተሞች ሁኔታ ብንመለከት በእዚህ በኩል ሰፊ ክፍተት ይታያል። ፈጣንና የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት በኩል ሰፊ ክፍተት ይስተዋላል። ሁኔታው በአግልግሎት አሰጣጥ፣ በአቅርቦትና ፍላጎት አማመጣጠን፣ ወዘተ ላይ በቴክኖሎጂ ታግዞ በትኩረት መስራትን ይጠይቃል። በዚህም ከተሞች ጫናዎችን እንዲቋቋሙ፣ ለኑሮ ምቹና ተስማሚ እንዲሆኑ በማድረግ የሚፈለገውን ለውጥ እንዲያመጡ መስራት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ሆኗል። ለእዚህ ደግሞ ስማርት ሲቲ መገንባት ወሳኝ መሆኑ ታምኖበት እየተሰራ ነው፡፡
በሀገራችንም በአሁኑ ወቅት የዘመናዊ ከተማ /ስማርት ሲቲ/ ጉዳይ በስፋት እየተነሳ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባና አደማ ከተሞች ስማርት ሲቲ የመገንባት ፍላጎት እና እንቅስቀሴዎች ይስተዋላሉ። ለመሆኑ ስማርት ሲቲ መገንባት ለምን አስፈለገ? እንዴትስ እውን ሊሆን ይችላል?
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ስማርት ሲቲ የመገንባት ጽንስ ሀሳብ ዘመኑ የሚጠይቀውንና ከዘመኑ ጋር አብሮ የሚሄደውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓትን መዘርጋትን ይጠይቃል። በከተሞች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ መረጃዎች (ዳታ) ላይ ተመሠርቶ በመተንተን የሞባይል መተግበሪያዎች በመጠቀም የከተማ ኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች፣ የከተማ የመሬት አስተዳደር እንዲሁም በቴክኖሎጂ የታገዘ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋትንም ይፈልጋል። ከተሞች ሲዘመኑ ለነዋሪዎቻቸው ምቹ ፤ ለኢንቪስትመንት ተመራጭና እድገታቸው ፈጣን ስለሚሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ተመራጭ ይሆናሉ ።
በአዲስ አበባ ከተማ የስማርት ሲቲ ትግበራ ወሳኝ መሆኑ እየተገለጸ ነው። ከተማዋ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ መዲና ከመሆኗም ባሻገር የዓለም አቀፍ ተቋማት የአፍሪካ ቅርንጫፎችና የሀገራት አምባሲዎች መቀመጫ እንደ መሆኗ ነዋሪዎቿን፣ እንግዶቿን፣ እድገቷን፣ ወዘተ. ታሳቢ ያደረገ ከተማዋን የማዘመን ስራ ውስጥ መግባት ያስፈልጋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ በሚተገበረው የስማርት ሲቲ ፕሮጀክት ላይ እንዳሉት ፤ በአዲስ አበባ ከተማ የስማርቲ ሲቲ ግንባታ እንደሚያስፈልግ ታምኖበት እየተሰራ ነው። እየጨመረ የሚመጣውን የከተማዋን ነዋሪዎች ብዛትና ፍላጎት ለማሟላት ውብ፣ ሳቢና ለሰው ልጆች ቀላል የሆነ ዘመናዊ ከተማ ለመገንባት የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል። አዲስ አበባ ከተማን በማዘመን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለኢንቨስትመንት ተስማሚና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ከተማ ለማድረግ የሚያስችል የቅድመ ትግበራ ስራ ሲሰራ ቆይቷል። አዲስ አበባን ዘመናዊ ከተማ /ስማርት ሲቲ / በማድረግ የከተማዋን ነዋሪዎች እንግልት በማስቀረት ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎት መስጠት ቅድሚያ የተሰጠው ተግባር ነው።
እሳቸው እንደሚሉት፤ በከተሞች በከፍተኛ ፍጥነት ቁጥሩ እየጨመረ ያለውን ነዋሪ ፍላጎት ለማርካት ውብ፣ ሳቢ እንዲሁም ለሰው ልጆች ቀላልና ምቹ የሆኑ ዘመናዊ ከተሞችን ለመገንባት የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ጊዜ ሊሰጠው አይገባም። በዚህ ረገድ በአዲስ አበባም ዘመናዊ ከተማን / ስማርት ሲቲ/ የመገንባት ጽንስ ሀሳብ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት አስፈላጊ በጀትም ተመድቦለት በጥናት ተደግፎ፣ ለስኬቱ ተቋማዊ አደረጃጀቶችን በማዋቀር አስፈላጊውን የሰው ኃይል በማደራጀት ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።
ቴክኖሎጂዎች ከፈጠራና ከሰዎች ጋር የተቆራኙ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ቴክኖሎጂ ልናሳካ የሰብነውን ራዕይ መተግበሪያ መሳሪያ፣ ከተሞች ደግሞ የመተግበሪያ ስፍራዎች ናቸው ሲሉ አብራርተዋል። ቴክኖሎጂ ለአንድ ሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት አይነተኛ ሚና ሊጫወት የሚችለው ህብረተሰቡ ዘንድ ሲሰርጽና በፈጠራ ሲታገዝ ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ ከቴክኖሎጂ አኳያ ያሉት መሰረተ ልማቶች ወይም ቴክኖሎጂዎች በግዥም ሆነ በምርምር የሚገኝ የቴክኖሎጂ እውቀትን ለማሰባሰብ ፣ ለማከማቸትና ለማስራጨት የሚያስችሉ ካለመሆነባቸው ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ የቴክኖሎጂ እውቀት ለማከማቸትም ሆነ የተከማቸውን እውቀት በሚገባ ጥቅም ላይ መዋል የሚያስችል ሁኔታ እንደሌለ ይገልጻሉ። በስራ ላይ ያሉት ቴክኖሎጂዎችም ቢሆኑ የተመቻቹ ናቸው የሚባሉ አይነቶች አንዳልሆኑ ጠቁመዋል።
ከንቲባዋ እንዳብራሩት፤ ከተሞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች አገልግሎታቸውን ማሳለጥ እንዲችሉ በቅድሚያ ከአካበቢው ጋር የተጣጠመና የተቀናጀ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት መዘርጋትና ለዚህ የሚመጥን ቴክኖሎጂን መመረጥ ያስፈልጋል። በተለይም ውብ ከተሞች በመፍጠር ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ ቴክኖሎጂ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው።
የሰማርት ሲቲ ለሕዝቡ አዳዲስ እድሎችን፣ የተሻለና ቀልጣፋ አገልግሎት፣ የነዋሪዎችን የደህንነት ሁኔታ ለማረጋገጥ ያስችላል ያሉት ከንቲባዋ፣ ወጪንም ይቀንሳል፣ በመንግሥትና በከተማ ነዋሪዎች መካከል ያለውን እምነት ብሎም ትብብርን ያሳድጋል ይላሉ።
ከንቲባዋ የሕዝብ እንግልትን ለማቅለል ያስችል ዘንድ አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን እየተሰራ ነው ብለዋል። ከተማን ማዘመን ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ከታች ለመጀመር ሳይሆን ያሉንን መሠረተ ልማቶች መነሻ በማድረግ መሻሻል ያለባቸውን ማሻሻል እንዲሁም በአዲስ መልክ መገንባት ያለባቸውን መገንባት ውጤታማ ሥራ መሥራት የሚያስችል መነሻ ሀሳብ ነው ሲሉ ከንቲባዋ አመልክተዋል። በስራ ላይ ያሉ የቴክኖሎጂ አገልግሎቶች ሳይቋረጡ አዳዲስ አሠራሮችን በመዘርጋት የማሸጋገር ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ከተማን የማዘመን አሠራር ጊዜ የሚፈልግና በሂደት የሚፈጸም መሆኑንም ተናግረው፣ ሁሉንም ዘርፎች በአንድ ጊዜ ወደ ዘመናዊ አሠራር ማስገባት እንደሚቻል አስታውቀዋል።
አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹና ተስማሚ ለማድረግ የተጀመረው ዘመናዊ ከተማን የመገንባት /የስማርት ሲቲ/ ፕሮጀክትን ተቋማት ወይም አመራሮች ብቻቸውን የሚፈጽሙት እንዳልሆነም ጠቁመው፣ የሁሉንም ቅንጅት እንደሚጠይቅ አስታውቀዋል። እንደ ስሟ አበባ የሆነች ዘመናዊ አዲስ አበባን የመገንባት ሥራዎችን በማቀላጠፍ ቀላልና ምቹ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር የተጀመረውን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ እንዳሉት ከተማዋን ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ ያለባት፣ በኢኮኖሚ የዳበረች፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የበለፀገችና ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነች ለማድረግ ይሰራል። በከተማዋ የዲጂታል አገልግሎት ለመዘርጋት ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ ለኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ /አይሲቲ/ግንባታ፣ የተቀናጀ የሶፍትዌርና ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለመገንባት እየተሰራ ነው።
የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዲጅታል ኢኮኖሚውን የሚመራ መሳሪያ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የሚገልጹት ወይዘሮ ሀቢባ፤ ባለፉት ዓመታት የሶፍት ዌር ፕሮጀክቶችን በልማትና የተቀናጀ የኔትወርክ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናከር ተቋማት የቴክኖሎጂ ልማት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል። ዘንድሮም የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግና አገልግሎቶችን ለማዘመን ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ በትምህርት ቤቶች፣ በወሳኝ ኩነት ቢሮዎች፣ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ በትራፊክ ማኔጅመንት ፣ በጤናና በሌሎች ተቋማት ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎትን በማቀላጠፍ የተጀመረውን ዘመናዊ ከተማ ግንባታ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው። በአዲስ አበባ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ በኢትዮ ቴሌኮም ዘርፍ ከተማዋን ስማርት ለማድረግ ጥናቶች ቀርበው ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎባቸዋል።በዚህም የቴክኖሎጂ ፈላጊ ተቋማትና የቴክኖሎጂ አመንጪ ተቋማት ተገናኝተዋል። ለከተማዋ የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎች በመምረጥ በመለየት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የከተማ መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኢትዮጵያ በዴቻ በበኩላቸው ከተሞችን የማዘመን ስራ በከተሞች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች እና አሠራሮችን ተግባራዊ በማድረግ የተሻሉ አገልግሎቶች መስጠትን ታሳቢ እንደሚያደርግ ይገልጻሉ፡፡
አቶ ኢትዮጵያ እንዳሉት፤ ዘመናዊ ከተማን/ስማርት ሲቲ/ የመገንባት ጽንሰ ሀሳብ በዓለም ሀገራት በተሻለ ቴክኖሎጂ በተሻለ አሠራር ከተሞችን በማዘመን ከተሞችን ለነዋሪዎቹ የተሻለ አድርጎ ማቅረብ የሚሉትን ያካትታል። ይሄም ከተሞች በሚፈለገው ስታንዳርድ መሠረት በፕላን እንዲመሩ ማድረግ ያስችላል። በፕላን የሚመሩ ከተሞች ደግሞ በከተማ ለሚኖረው ሕዝብ የሚፈለገውን አገልግሎት በተቀላጠፈ መንገድ፣ በተሻለ አረዳድ ለመስጠት ያስችላል፡፡
ከተሞችን በፕላን መምራት ዘመናዊ ከተማን ለመገንባት ትልቅ እድል እንደሚፈጥር አቶ ኢትዮጵያ ጠቅሰው፣ ከተሞችን ማራኪ ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት ዘርግቶ፣ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ፣ ባለው የሰው ኃይል ተጠቅሞ አገልግሎትን ማዘመን እንደሚቻል ይገልጻሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ከተሞችን በቴክኖሎጂ ማበልጸግ የትራንስፖርት አገልግሎትን ማሳለጥ፣ ኢንተርኔትን ተደራሽ ማድረግ እና የኤሌክትሮኒክስ ዘዴዎችን ተጠቅሞ አገልግሎቶችን ማቀላጠፍ እና የመሳሰሉት ሂደቶች ከተማን ለማዘመን ወይም ዘመናዊ ከተማን/ስማርት ሲቲ/ ለመገንባት ለሚደረገው ጉዞ እንደ መነሻ ናቸው። የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር ማድረግ፣ የአካባቢውን አየር ለመቆጣጠር የራስን ድርሻ ማበርከት፣ ሕብረተሰቡ በቀላሉ አገልግሎቱን ማግኘት እና ፈጣንና ጊዜ ቆጣቢ ዘዴዎች መጠቀም የሚችልበት ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ነው ።
አቶ ኢትዮጵያ እንዳሉት፤ ዘመናዊ ከተማ/ስማርት ሲቲ/ መገንባትን በተመለከተ ትኩረት በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። ለተግባራዊነቱም ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ በማድረግ የሕግ ማዕቀፎች እንዲዘጋጁ ፣የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮዎች የመቀመር እና የመሳሰሉት በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
ከተሞችን በማዘመኑ ሂደት ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲና አዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ሌሎች የትምህርት ተቋማትም ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ጠቅሰው፤ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከተቋማቱ ጋር በትብብርና በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡
የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያው አቶ ሀብታሙ ዳምጤ እንደሚሉት፤ ከተሞችን ዘመናዊ ማድረግ/ የስማርት ሲቲ/ ጽንስ ሀሳብ ለኢትዮጵያ ከተሞች ያስፈልጋል። ከተማ ሲዘመን እንደ ሀገር በቴክኖሎጂ ወደኋላ ለተቀረበት ምክንያት የሆኑ ችግሮች መቅረፍ ይቻላል። ከዓለም ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን ይጠቅማል፡፡
አሁን ላይ አለምን እየተቆጣጠሩ ያሉት እንደ ፌስ ቡክ፣ ዩቲዩብ ያሉት የሶሻል ሚዲያዎችን በመጠቀም የውጭ ምንዛሬን ማግኘት ያስችላል። ለአብነት ሕንድ 30 በመቶ የሚሆነውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ የምታገኘው ከዩቲዩብ ነው። በዚህ ላይ ከሶፍትዌር ሽያጭ የምታገኘው ሲጨመር 40 በመቶ ያህል ይሆናል።
እኛ እንደ ሀገር የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማግኘት ከምንልካቸው ምርቶች ባሻገር ባለው የሰው ኃይል ላይ ብንሰራ በቀላሉ ተጠቃሚ መሆን እንችላለን ያሉት ባለሙያው፣ ይህ ዘመናዊ ከተማን /የስማርት ሲቲን/ የመገንባቱ ሀሳብ አንድ እርምጃ ከፍ የሚያደርግ ነው ይላሉ፡፡
እንደ አቶ ሀብታሙ ገለጻ፤ ዘመናዊ ከተማ የመገንባት ጽንሰ ሀሳብ ኢንፎርሜሽን ፣ቴክኖሎጂና ኮሙኒኬሽን አንድ ላይ አጣምሮ በመያዝ መንግሥትና ሕዝብ ይበልጥ የሚግባቡትን ሁኔታ ለመፍጠር ይጠቅማል። በአጠቃላይ ዘመናዊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች መጠቀም ያስችላል ።
በሀገሪቱ ተግባራዊ እየሆነ ያለው በብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያም የከተማን ማዘመን አንድ አካል ነው ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ አስፈላጊዎቹ መረጃዎች አንድ ቦታ ላይ ተሰብሰበው ከተቀመጡ ነገ ዘመናዊ ከተማ ሲገነባ ከዜሮ እንደማይጀመርና መረጃው ከዚያ የሚወሰድበት ሁኔታ እንደሚኖር አመላክተዋል። እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በዲጅታል ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም አገልግሎትን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የህብረተሰቡን እንግልት በመቀነስ ትልቅ ሚና እንዳላቸው አስታውቀዋል። በአዲስ አበባ እየተተገበረ ያለው የዘመናዊ ከተማ/ ስማርት ሲቲ ግንባታ ዘመናዊ ከተማ የመገንባቱን ሂደት አንድ እርምጃ ወደፊት ያስኬዳል ይላሉ።
ዘመናዊ ከተማ ለመገንባት የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶችን የማሟላቱ ሥራ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የሚገልጹት አቶ ሀብታሙ፤ አሁን ላይ ያለን አቅም ተጠቅሞ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ከተሰራ ዘመናዊ ከተማ የመገንባቱን ስራ ቀላል እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ጥር 9 /2015