በኢትዮጵያ የምርትና ምርታማነት ጉዳይ ሲነሳ ግብርናን ማዘመን ቀዳሚ ጉዳይ ሆኖ ሲጠቀስ ቆይቷል። ለዚህም ምክንያቱ በበሬ ጫንቃ አርሶ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንዲሁም በአጠቃላይ ሀገር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ልታገኝ ስለማትችል ነው። ከግብርናው የሚጠበቀውን ለማግኘት ሜካናይዜሽን ላይ መሥራት አንዱ አማራጭ ስለመሆኑም የዘርፉ ባለሙያዎች ሲመክሩ ኖረዋል።
ይህን ሀሳብ መሬት ለማውረድ፤ መንግሥት ለምርትና ምርታማነት እድገት ወሳኝ በሆኑት ግብርናውን በማዘመን፣ ዝናብ ጠብቆ ግብርናን ከማካሄድ በተጓዳኝ እንደ መስኖ ባሉት አማራጮች ላይ አተኩሮ መሥራት ውስጥ ገብቷል፤ በዚህም ውጤቶች እየታዩ ናቸው። በመንግስት በኩል የግብርና ሜካናይዜሽን ማሽነሪዎችን በስፋት መጠቀም የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ናቸው።
በአሁኑ ወቅትም ብርቱ አርሶ አደሮች በግላቸው፣ ሌሎች ደግሞ በአርሶ አደሮች የህብረት ሥራ ማህበሮቻቸው ትራክተሮችንና ኮምባይነሮችን እየገዙ ለግብርና ሥራቸው እያዋሉ ናቸው። የአርሶ አደሩ የማሽነሪ ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ የማሸነሪ አከራዮችም መፈጠር ጀምረዋል።
የሜካናይዜሽን ማሸነሪ አከራዮች አርሶ አደሮች በቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረጉ ናቸው፤ እነርሱም በሚሰጡት የኪራይ አገልግሎት ገቢ በማግኘት የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ችለዋል።
የግብርና ቴክኖሎጂ የሰው ድካምን ከመቀነስና ጊዜን ከመቆጠብ በተጨማሪ በግብርና ሥራ ወቅት መሬትን በደንብ በመገልበጥ፣ በአጨዳ፣ በዘር መሰብሰብና በውቂያ የሚባክን ምርትን በመቀነስ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
እንዲህ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያስገኘ ያለው የግብርና ቴክኖሎጂ በማህበር በተደራጁ ወይንም የገንዘብ አቅም በፈጠሩ አርሶ አደሮች ካልሆነ በስተቀር በአርሶ አደር አቅም ለመግዛት የሚቻል እንዳልሆነ ይታወቃል። በኪራይ አገልግሎቱን የማግኘት አማራጭ በመኖሩ እያንዳንዱ አርሶ አደር ቴክኖሎጂውን መግዛት አይጠበቅበትም።
በዚህ ወቅትም ቴክኖሎጂው በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው ወይንም እየቀረበ ያለው በኪራይ አገልግሎት በሚሰጡ አካላት ነው። የኪራይ አገልግሎቱ የሚሰጠውም በማህበር በተደራጁ አካላትና በግለሰብ አቅራቢዎች በመሆኑ አርሶ አደሩ ተመጣጣኝ ኪራይ አቅራቢዎችን ለመምረጥ አማራጭ ተፈጥሮለታል። የቴክኖሎጂ አቅርቦቱ እየጨመረ ሲሄድ ደግሞ የአገልግሎት ተመጣጣኝነት እየተሻሻለ ይሄዳል።
በግብርና ቴክኖሎጂ የመጠቀም የፍላጎት ማደግን መሠረት በማድረግ ግብርና ሚኒስቴር በየግላቸው እንደ ትራክተር፣ ኮንባይነር ሀርቨስት (ሰብል አጭዶ የሚወቃ መሣሪያ)፣ ሌሎችም የግብርና ቴክኖሎጂ ገዝተው የኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችና ግለሰቦች በማህበር ተደራጅተው በጋራ አቅም ፈጥረው አገልግሎቱን እንዲሰጡ የማስተባበር ሥራ እየሰራ ይገኛል። ከ270 በላይ የሆኑ አባላትን የያዘ ኢትዮጵያ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ሰጭዎች ማህበር ተመስርቶ የተናበበ ሥራ ለመሥራት እንዲሁም ድጋፍና ክትትል ለማድረግ መቻሉን፣ አገልግሎት አቅራቢዎችም በየግላቸው አገልግሎት ሲሰጡ ያጋጥማቸው የነበረውን ችግርና ከመንግሥትም የሚፈልጉትን ድጋፍ ለማግኘት እንዳስቻላቸው እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደተቻለ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ፍላጎትን ለማሟላት ደግሞ አገልግሎት ሰጭዎች ቴክኖሎጂውን በብድር መግዛት እንዲችሉና ከቀረጥም ነፃ እንዲሆን መንግሥት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። እንዲህ ያሉ የመንግሥት ድጋፎች ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ቴክኖሎጂ አስፈላጊነት ታምኖበት ትኩረት እንደተሰጠው አንዱ ማሳያ ነው።
ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ በግዥ በስፋት ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ መሆኑን፣ የቴክኖሎጂ አገልግሎት በሚያቀርቡ አካላት ያለው የግዥ ፍላጎትም ሆነ በአርሶ አደሩ በኩልም በቴክኖሎጂ ለመጠቀም ያለው ተነሳሽነት እየጨመረ መምጣቱን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሰሞኑን ለሊዝ ፋይናንስ ደንበኞች ያቀረባቸውን የአጭዶ መውቂያ የግብርና ማሽኖች ርክክብ በተደረገበት ወቅት ለመገንዘብ ችለናል። ባንኩም ሆነ የባንኩ አምስተኛ ዙር ተረካቢ ደንበኞችም በወቅቱ ይህንኑ አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ የዋሉት ትራክተሮች 12ሺ ብቻ እንደነበሩ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝደንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው በዚሁ የርክክብ ሥነስርአት ላይ አስታውሰዋል። መንግሥት የግብርና ሜካናይዜሽን ፕሮግራም መተግብር ከጀመረ ከሁለት አመታት ወዲህ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ትራክተሮች ሥራ ላይ እንዲውሉ መደረጉን ገልጸዋል። ፕሮግራሙ መተግበር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ 13 ሚሊዮን ዩሮ ተመድቦ ቁጥራቸው 89 የሚደርስ የተለያዩ የግብርና መሣሪያዎች ተገዝተው መቅረባቸውንም አመልክተዋል።
ዶክተር ዮሐንስ እንዳሉት፤ በዚህ ጥቂት ጊዜ ውስጥም የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ለማቅረብ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ሆኗል። እስካሁንም 530 ያህል ጥያቄዎች ለባንኩ ቀርቧል። የቀረበው ጥያቄም በገንዘብ ወደ 82 ሚሊየን ዩሮ የሚያወጣ ነው። ይህም 13 ሚሊየን ዩሮ የጀርመን መንግሥት፣ ሁለት ሚሊየን ዩሮ ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን እንደሆነና ቀሪውን ለማሟላት የተለያዩ መንገዶች እየተሞከሩ እንደሆነና ተስፋ መኖሩን አስረድተዋል።
እንደ ዶክተር ዮሐንስ ገለጻ፤ በአነስተኛ አርሶ አደሮች የተያዘ መሬት ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። እነዚህ አነስተኛ የእርሻ መሬት የያዙ አርሶ አደሮች ከመሬታቸው ሳይፈናቀሉ ግብርናውን ማዘመን (ትራንስፎርም) ማድረግ ካስፈለገ አማራጩና መፍትሄው የግብርና ሜካናይዝሽንን ጥቅም ላይ ማዋል ነው። በተለይም በኩታ ገጠም (ክላስተር) የተጀመረውን የግብርና ዘዴ በሜካናይዝሽን እንዲታገዝ ማድረግ ውጤታማ ያደርጋል። ውጤቱም ከወዲሁ መታየት እንደጀመረም ዶክተር ዮሐንስ ይገልጻሉ። ጥቅም ላይ እየዋሉ ባሉ የእርሻ ትራክተር፣ አጭዶ በሚወቃ ማሽን እየተከናወነ ያለው ልማት ለግብርናው መዘመን አስተዋጽኦ በማበርከት ክፍተቶችን መቅረፍ እንደተቻለ ባንኩ ማረጋገጥ መቻሉንም አመልክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ መዋሉ በግብርናው ሥራ ላይ የሚሰማራውን ሰፊ የሰው ኃይል ለሌላ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማዋል የሚቻልበትን እድል ይፈጥራል፤ በተለይም አርሶ አደሩ በሚያገኘው ትርፍ ጊዜ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝለት ሥራ ላይ ለመሰማራት ምቹ ሁኔታን ይፈጥርለታል።
በግብርና ሥራ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው የሚስተጓጎሉ ተማሪዎችንም ችግር ይፈታል። ጊዜና ጉልበት ተቆጥቦ ለሌላ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሲውል በምጣኔ ሀብት እድገት ከፍ ያለ ሚና ይኖረዋል።
እነዚህን ውጤቶች ለማስመዝገብ የተጀመረው የግብርና ሜካናይዜሽን አቅርቦት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና ሰፊ የቤት ሥራም እንደሚጠበቅ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክም ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን ሰፊ ሥራ ለመሥራት የተለያዩ ጥረቶች በማድረግ ላይ እንደሆነም ተናግረዋል።
በእለቱ የአጭዶ መውቂያ የግብርና ሜካናይዜሽን ከተረከቡት በግላቸው የኪራይ አገልግሎት ሰጭዎች መካከል አንዱ አቶ አሳዬ ከበደ ናቸው። ነዋሪነታቸው ባሌ እንደሆነና የኪራይ አገልግሎቱንም በአካባቢያቸው ለመስጠት እንደተዘጋጁ ነው የነገሩን። አቶ አሳዬ እንደገለጹልን፤20 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ፈጽመው፣ ቀሪውን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባመቻቸላቸው በአምስት አመት የጊዜ ገደብ ተከፍሎ በሚመለስ ብድር መሠረት GC 590 ጉልበት ያለው ኮንባይነር ነው የተረከቡት። ዋጋውም 11 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ነግረውናል።
አቶ አሳዬ ልማት ባንኩ ባመቻቸው ብድር የግብርና ሜካናይዜሽን ማሽን ግዥ ሲፈጽሙ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ማሽኑ እንደየሰብሉ አይነት መሳሪያዎችን በማቀያየር አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው። በዚህ ዘዴ የተለያዩ ሰብሎችን አጭዶ ሰብስቦ ማጓጓዝ ይቻላል። ቀደም ሲል የገዙት ማሽን ዋጋ አራት ሚሊዮን ነበር። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ከእጥፍ በላይ ጨምሯል። አዲስ የተረከቡት ማሽን ግን በፈረስ ጉልበቱ እንዲሁም ፍጥነቱና በቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ ቀድሞ ከገዙት ማሽን የተሻለ ሆኖ ነው ያገኙት።
የፈረስ ጉልበቱ ሲጨምር በብዛት እህል ለመሰብሰብ ያስችላል። ካሜራም የተገጠመለት መሆኑ ደግሞ እይታን ከሚጋርዱ ነገሮች ነጻ በሆነ ማሽኑን እንደልብ በማሣ ውስጥ ለማንቀሳቀስ ያስችላል። ለደህንነት የሚጠቅም ነገርም የያዘ በመሆኑ በቴክኖሎጂ የተሻለ ነው ሲሉ አቶ አሳዬ ያብራራሉ።
ቀደም ሲል የገዙት ማሽን ግን GC 580 ነበር። አዲሱን ማሽን በፈለጉት ወቅት አላገኙም። መክፈል የሚጠበቅባቸውን ክፍያ እንደፈጸሙ በአጭር ጊዜ በተለይም የመኸር ሰብል ለመሰብሰብ ይደርሳል ብለው ጠብቀው ነበር። የደረሳቸው ታኅሣሥ መጨረሻ ላይ ነው። ሥራ የተገባደደበት ጊዜ መሆኑን ነው የገለጹት።
ማሽኑ የዋጋ ጭማሪ ሲኖረው ለአርሶ አደሩ የሚሰጠው የኪራይ አገልግሎት ላይም የዋጋ ጭማሪ እንደሚኖረው ይገመታል። ከዚህ አንጻርም ስላለው ሁኔታ አቶ አሳዬ እንደነገሩን እስካሁን በተለያየ ዋጋ የኪራይ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ቢሆኑም በ2014-2015 የምርት ዘመን በአንድ ኩንታል 150 (አንድ መቶ ሃምሣ) ብር ሂሣብ ነው አገልግሎት የሰጡት። የነዳጅና የተለያዩ ወጪዎች ስላሉ ወደፊት የሚሆነውን ለመገመት ያስቸግራል ነው ያሉት።
አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂው የምርት ብክነትን እያስቀረላቸውና የተለያየ ጥቅምም በማየቱ አገልግሎቱ እንዲቀርብለት ፍላጎት እንዳለው አቶ አሳዬ ጠቅሰው፣ እስካሁን ባለው አገልግሎትም በግላቸው መልካም ሆኖ እንዳገኙት ይናገራሉ።
አቶ አሳዬ ከአርሶ አደሩ ጋር በአገልግሎት መልካም ግንኙነት እንዳላቸው ቢገልጹም ለገበያ ሽሚያ ሲባልና ለነዳጅ ቁጠባ የግብርናው ሥራ በሚጠይቀው አግባብ በተለይ በአጨዳ ወቅት በትክክል ካለመፈጸም ጋር በተያያዘ አርሶ አደሩ በአገልግሎት ሰጭዎች ላይ ቅሬታ ይቀርባል። እርሳቸው አገልግሎት በሚሰጡበት ባሌ አካባቢ በአመት ሁለት ጊዜ ምርት በሚሰበሰብበት ጊዜ አገልግሎት ሲሰጡ በመጀመሪያ ቢያበላሹ በሁለተኛው አገልግሎታቸውን ፈልጎ የሚመጣ አርሶ አደር እንደማይኖር ስለሚገነዘቡ ተገቢውን አገልግሎት ለመሰጠት ነው ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ይገልጻሉ። በእዚህ በኩል እስካሁንም ችግር ያልገጠማቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የኪራይ አገልግሎቱን በባሌና አርሲ አካባቢዎች ነው እየሰጡ ያሉት። ወደሌላ አካባቢ በመሄድ አገልግሎት ለመስጠት የማሽኑ አካላት መፍታት እንደሚያስፈልግና ሌላ ማጓጓዣ መጠቀም እንደሚገባ ይናገራሉ፤ ለመጫኛ የሚወጣው ወጪም ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ግብርናውን ለማዘመን የተያዘውን እንቅስቃሴ ለማጠናከር ማሽኖችን በስፋት ማቅረብ ይጠበቃል። በአቅርቦት በኩል መዘግየት ከተፈጠረ ምርታማነትን በሚፈለገው ፍጥነት ለማሳደግ ካለማስቻሉ በተጨማሪ የማሽን ዋጋ እንዲጨምር ያደርጋል። የማሽን ዋጋ ሲጨምር ደግሞ በሚሰጠው በግብርና ሥራ የኪራይ አገልግሎት ላይ የዋጋ ጭማሪ ወይም መናር በማስከተል የአርሶ አደሩን የመክፈል አቅም ሊፈታተን ይችላል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝደንት ዶክተር ዮሐንስ በሰጡት ማብራሪያ፤ መዘግየትን ከእርሻና የሰብል መሰብሰብ ወቅቶች ጋር በማያያዝ ካልሆነ በስተቀር መዘግየት አልተፈጠረም። ኤልሲ ከተከፈተ በኋላ ከሶስት ወር በላይ አይቆይም። አምስት ዙሮች መድረስ የተቻለው በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ነው።
ስድስተኛውም ዙር ተጀምሯል። ግዥው የሚፈጸመው ገዥው በሚያመለክተውና ባንኩ በሚያመቻቸው ነው። የገንዘብ ድጋፍ (ፈንድ) የሚለቀቀው ለመግዛት የሚያስፈልገው ሂደት እንደተጠናቀቀ ነው።
በዚህ የግብርና ሜካናይዜሽን ድጋፍ እስካሁን ከጀርመን መንግሥት ጋር ባለው ስምምነት እየተፈጸመ እንደሆነና ከሌሎች አጋሮች ጋርም በጋራ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ መሆኑንና ተስፋ ሰጭ ነገሮች መኖራቸውንም አመልክተዋል። እስካሁን በተገዙት ማሽኖች በተሰራው ሥራም ለጋሾች ደስተኞች መሆናቸውንና ይህም ለቀጣይ ድጋፍ በጎ ምላሽ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
በግዥ እየገቡ ስላሉት ማሽኖች ዘመናዊነትም እንዳስረዱት፤ ማሽኖቹ በዓለም ላይ የተሻሉ፣ ለረጅም ጊዜም አገልግሎት የሚሰጡ ለኢትዮጵያ መሬት ተስማሚ ናቸው። ግዥ ከመፈጸሙ በፊት ማሽኑ ለኢትዮጵያ መሬት ተስማሚ መሆኑ ጥናት ይደረጋል። በጥናት ሥራው ግብርና ሚኒስቴርም ተሳታፊ ነው። ግዥው የሚፈጸመውም አቅራቢዎች ተወዳድረው በመሆኑ በጣም የተሻለው ተመርጦ ነው የተገዛው።
በልማት ባንኩ የብድር አመቻችነት ወደ ሀገር ገብተው ለአገልግሎት የበቁት የግብርና ሜካናይዜሽን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በባሌ፣ አርሲ፣ ሻሸመኔ፣ ቡሬ፣ አላባ ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆናቸውንም ከልማት ባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ጥር 8/ 2015 ዓ.ም