ለዛሬው መጣጥፌ መር መክፈቻ ይሆነኝ ዘንድ “ኢትዮጵያ ምን አጣች?” ስል በጥያቄ ጀምሬአለሁ። ይሄ ጥያቄ ደግሞ የጋራ ጥያቄችን ነው፤ የምንመልሰውም በጋራ ነው። ሆኖም እኔ የራሴን ምልከታ፤ የግሌን እይታ በሁላችንም ውስጥ ይኖራል ባልኩት ልክ ላነሳ ወደድኩ። እርግጥ ያጣነው ምንም የለም ተፈጥሮ ሙሉ አድርጋ ነው የፈጠረችን። እኛ ግን አንድ ነገር ግን ይጎለናል። እርሱም ተነጋግሮ መግባባት ነው። ተነጋግሮ ባለመግባባት ብዙ ነገሮቻችንን አጥተናል። የሰሜኑን ጦርነት ብናነሳ እንኳን ተነጋግሮ ባለመግባባት የመጣ ነው።
እርግጥ ነው ተነጋግሮ ለመግባባት የሁለት ሀይሎች ፍቃደኝነት ያስፈልጋል። ተነጋግሮ ለመግባባት የአንድ ወገን ፍቃደኝነት ብቻውን ዋጋ የለውም። አንዱ ሰላምን እየፈለገ አንዱ ጦርነትን በሚፈልግበት ሁኔታ ላይ ተነጋግሮ መግባባት አዳጋች ነው የሚሆነው። የሀገራችን ሁኔታም ይሄን እውነት የተላበሰ ሆኖ እናገኘዋለን። ሰላም በሚፈልጉና ነውጥ በሚፈልጉ ቡድኖች መካከል ሀገር ጸንታ መቆም አትችልም። የሀገር በጸንታ እንድትቆም ሰላም ፈላጊና የሰላምን ዋጋ የተረዳ ኃይል ያስፈልጋል፤ ይሄ ኃይል መሪንም ተመሪንም የሚመለከት ነው።
አበው ሲተርቱ ባለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል ይላሉ። እውነት ነው ባለመነጋገራችን ደጃዝማችነታችንን አጥተናል። ሰላማችንን አጥተናል። ክብራችንን፣ ከፍታችንን ተነጥቀናል። ባለመነጋገራችን ወደማይገባንና ወደማይመጥነን እልቂትና ትንቅንቅ ገብተናል። የሰላም አማራጮችን እየዘጋን የመገፋፋት መንገዶችን ስንጠርግ ነበር። ይሄ አስተሳሰብ ሀገር ከማጥፋትና ታሪክ ከማበላሸት ባለፈ ለማንም አልጠቀመም። ዓለም ላይ በጦርነት የከፋ ታሪክ ያላቸውን ሀገሮች ብንመለከት ሁሉም ታሪካቸውንና መሰረታቸውን ያበላሹ ሆነው ነው የምናገኛቸው።
ሰላም በመነጋገር ውስጥ፣ ጦርነት ደግሞ በእልህና ጠበኝነት ውስጥ የሚፈጠሩ ነገሮች ናቸው። በመነጋገር ሰላምን ማምጣት እየቻልን በእልህ ወደ ጦርነት የምንገባው ነገር አይገባኝም። እንደ ሀገር ብዙ ችግሮች አሉብን፤ ሁሉም ችግሮቻችን ግን በጠረጴዛ ዙሪያ መፈታት የሚችሉ ናቸው። ከሰላም የላቀም ሆነ፤ ከሰላም እጦት የገዘፈ ችግር በዓለም የለም። ችግሮቻችን ከሰላም ተልቀው ወደ ጦርነትና ወደ ሞት እንዲወስዱን እድል የምንሰጣቸው ራሳችን ነን።
የማንክደው ሀቅ ቢኖር ሀገራችን ኢትዮጵያ በሰሜኑ ጦርነት ብዙ ኪሳራ ደርሶባታል። በቆረቆር ላይ ቁምጥና ሆኖብን ብዙ ዋጋዎችን አስከፍሎናል። በተለይ በኢኮኖሚው ረገድ ይሄ ነው የማይባል ኪሳራን አስተናግደናል። በዋናነት ኢኮኖሚን እናንሳ እንጂ ጦርነት የማይደርስበት የማህበረሰብ ክፍል የለም። በነዚህ ሁለት አመት ውስጥ በሰሜኑ ጦርነት ያልታመመ የማህበረሰብ ክፍል የለም። እርግጥ የሰሜኑ ጦርነት እንዳይነሳ መንግስት ብዙ የለፋ ቢሆንም፤ ሰላም ግን በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሚሆን ባለመሆኑ በጦርነት ውስጥ ልናልፍ ተገድደናል። በዚህም ብዙ ነፍሶችን፣ ብዙ ጉስቁልናዎችን፣ ብዙ መፈናቅሎችን አስተናግደናል።
አሁን ልንረዳው የሚገባን ጉዳይ ቢኖር አንድ ነገር ብቻ ነው፤ እርሱም በጋራ ሀሳብ ሰላማዊ ሀገርን መፍጠር ነው። ሀሳቦቻችን ሰላምን እንዲወልዱ፣ አንድነትን እንዲጸንሱ እድል ልንሰጣቸው ይገባል። ሀሳቦቻችን ወደ እርቅ የሚወስዱ፣ ወደ ምክክር የሚያደርሱ መሆናቸውን ማጤን ይኖርብናል። ሀገራችን ሰላማዊ ሀሳብ አፍላቂነት ጎድሎባታል፤ ሀሳቦቻችን ሁሉ ነውጥ ፈጣሪዎች ናቸው። በተማሩትም ባልተማሩትም የሚፈበረኩ ሀሳቦች ለሀገራችን የሚበጁ ሳይሆኑ ለጥቂት ቡድኖች የሚበጁ ናቸው። ሀሳብ ስንፈጥር ሀገርና ህዝብን እያሰብን መሆን አለበት። ሀሳብ ስናስብ ወደ ማህበረሰቡ ደርሶ የሚፈጥረውን ነገር መረዳት መሆን መቻል አለበት። አሁን ላይ ሀሳቦቻችን ናቸው ወደ ጦርነትና ወዳልተፈለገ ነገር እየመሩን ያሉት።
ለሀገር በሚበጅ ሀሳብ ውስጥ ለውጥ እንጂ ነውጥ የለም። ሰላም እንጂ ጦርነት የማይታሰብ ነው። እናም በጋራ ሀሳብ ሰላማዊቷን ኢትዮጵያ እንድንፈጥር ሰላማዊ ሀሳብ ያስፈልገናል። በሰላም ውስጥ ካልሆነ በምንም ውስጥ ማትረፍ አንችልም። ዝም እንደሚነቅዝ በማሰብ፣ ካለመነጋገር ደጃዝማችነት እንደሌለ በማወቅ ልቦቻችን ለንግግርና ለተግባቦት እንክፈት።
ለዚህ ደግሞ ሀሳብ አላጣንም፤ ሀሳብ አጥተንም አናውቅም፤ ግን በሀሳቦቻችን መካከል ሰላማዊነት የለም። እርቅና ምክክር የለም። እኔ ብለን ጀምረን እኔ ብለን የምናበቃ ነን። በሀሳቦቻችን ውስጥ እኛነት ስለሌለ ነው ዛሬ ላይ ለጦርነት ቁርሾ የበቃነው። እኛ ብለን ጀምረን እኛ ብለን የምንጨርሰው ሀሳብና ታሪክ ከሌለን አብሮ መቆም አንችልም። አብሮ የሚያቆመን፣ አብሮ የሚያኖረን የጋራ ሀሳባችን ነው። እኛ ብለን ስንነሳ ያኔ ተነጋግሮ መግባባት እንችላለን። እኛ ብለን ስንነሳ ሰላማዊ ሀገር መፍጠር ይቻለናል። ሁልጊዜም ሀሳብ ስናነሳ ኢትዮጵያን እያሰብን መሆን አለበት።
ለእኛ የሚጠቅመውን ብቻ ሳይሆን ለብዙሃኑ የሚበጀውንም ማሰብ ያስፈልጋል። ለእኛ የሚበጀን ደግሞ የሚበጀን በጋራ ሀሳብ ሰላማዊ የሆነች ሀገርን መፍጠር ነው። ሀገራችን ሰላም እስካልሆነች ድረስ መጪው ጊዜ ሁላችንንም ነው የሚያስፈራን። መጪው ጊዜ ተምረን እንድንመረቅበት፣ ሰርተን እንድንከብርበት፣ ዘርተን እንድንቅምበት፣ ወግ ማዕረግ እንድናይበት ሰላም ሊሆን ይገባል። ሰላም የሚሆነው ደግሞ በጋራ ሀሳብ የጋራ ሀገር ስንፈጥር ነው። ዓለም ላይ በጦርነት ሰላም ያመጣ ሀገር የለም። ጦርነት ሰላም የሚታጣበት ስፍራ እንጂ የሰላም መገኛ ሆኖ አያውቅም። እኛም ሰላማችንን ትንሽ ዞር ብለን እስከዛሬ ባልሞከርንው የምክክር መንገድ ፈልገን ልናገኘው ይገባል።
ጦርነት ሁሌም አንድ አይነት ነው። በሀሳብ ልዩነት ይጀመርና ብዙዎችን ለሞትና ለአካል ጉዳት ይዳርጋል። ገዳይና ሟች እስኪበቃቸው እየገደሉ የሚሞቱበት ነው። መጨረሻው ግን በእርቅ ይቋጫል። እኔ የምለው ገዳይና ሟች ሳንሆን፣ ችግርና ጉስቁልና ሳይደርስብን ወደ ጦርነት የሚወስዱንን መንገዶች እንዝጋ ነው። እኔ የምለው ሳንገል እና ሳንሞት፣ ከብዙ እልቂት በኋላ ሳንጨባበጥ ልዩነታችንን አጥበን ወደ ሰላም እንምጣ ነው። እኔ የምለው በውይይትና በምክክር በጋራ ሀሳብ የጋራ ቤት እንስራ ነው። ሰላም እንጂ ጦርነት ለማንም ጠቅሞ አያውቅም። በተለይ እንደ እኛ ሀገር በድህነትና በኋላ ቀርነት በምትማቅቅ ሀገር ላይ ጦርነት ለምንም ነገር መፍትሄ ሆኖ አያውቅም። መፍትሄዎቻችንን መነጋገር ውስጥ መፈለግ ነው የሚኖርብን።
ከፍ ብዬ እንደገለጽኩት የሰሜኑ ጦርነት መልከ ብዙ ኪሳራን ነው ያደረሰብን። በምክክር ተፈትቶ ቢሆን፣ በሰላም ተቋጭቶ ቢሆን ይሄ ሁሉ ኪሳራ በሀገራችን ላይ ባልደረሰ ነበር። የሰሜኑን ጦርነት በኢኮኖሚ ላይ ምን ያክል ኪሳራ እንዳደረሰ አንድ እውነት ልንገራችሁ። ጦርነቱ ተጀምሮ የሕግ ማስከበር ዘመቻው እንደተጠናቀቀ ሰሞን መንግስት በትግራይ ክልል ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንዳደረገ በመግለጫው ነግሮናል። ልብ በሉ መቶ ሚሊዮን አይደለም መቶ ቢሊዮን ነው። መቶ ቢሊዮን ብር አይደለም ለአንዲት ድሀ ሀገር ቀርቶ በኢኮኖሚያቸው ለፈረጠሙ ባለጸጋ ሀገራትም ቢሆን ብዙ ብር ነው።
ይሄን በምሳሌ ለማስረዳት ልሞክር፤ የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ለስልሳ ሺ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ ተቋም ነው። ይሄ ለስልሳ ሺህ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረው ተቋም በአንድ ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር የተገነባ ነው። ልብ በሉ መንግስት በሰሜኑ ጦርነት ለዛውም በጥቂት ወራት ውስጥ መቶ ቢሊዮን ብር ወጪ አውጥቷል። የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በአንድ ቢሊዮን ብር ተገንብቶ ለስልሳ ሺህ ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል። በጦርነቱ የወጣው መቶ ቢሊዮን ብር መቶ ኢንዱስትሪያል ፓርክን ወይም ደግሞ ሌሎች ፋብሪካዎችን ገንብቶ ለበርካታ ስራ አጥ ዜጎች እንጀራ መሆን ይችል ነበር። ይሄን ሀሳብ ያነሳሁት ጦርነት ከኪሳራ በቀር ምንም እንደሌለው ለማሰረዳት ብዬ ነው።
ከዚህ እውነት በመነሳት ባለፉት ሁለት የጦርነት አመታት ውስጥ ኢኮኖሚያችን ምን ያክል እንደተጎዳ መረዳት እንችላለን። ጊዜው ከትላንት የምንማርበት ነው። ከሰላም ውጭ ምንም አማራጭ እንደሌለን የምንረዳበት ነው። ሀገራችን በምንም አይነት መልኩ ጦርነት የሚያስፈልጋት አይደለችም። ድህነት የቀደዳቸው፣ ማጣት ያጎበጣቸው ብዙ ቀዳዳዎች አሉብን። እነሱን መድፈን እንጂ በሆነ ባልሆነ ጦር መማዘዝ አሁን ላለንበት ሀገራዊ ሁኔታ የሚመች አይደለም። በሰላም ሀሳብ ወደፊት መሄድ ብቻ ነው የሚያዋጣን። ችግሮቻችን፣ ድህነቶቻችን፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ነውሮቻችን በሰላማዊ መንገድ ካልሆነ በሌላ በምንም እንዳይፈቱ ሆነው የተተበተቡ ናቸው።
ረጋ ካልን ዝግ ካልንና ከሰከንን የምንፈታቸው ብዙ ቋጠሮዎች አሉ። በሰላም የማይፈታ ቋጠሮ የለም። ጦርነት ቋጠሮ ያጠብቃል እንጂ ቋጠሮ አይፈታም። ዛሬ ላይ የምንገዳደልባቸው ችግሮቻችም በትላንት ፖለቲካ፣ በትላንት እኔነት የተቋጠሩ ናቸው። ቋጠሮዎቻችም እንዲላሉ የሰላም አማራጮችን መመልከት አለብን። ጦርነት ምን ያክል አስከፊ እንደሆነ ያለፉ ታሪኮቻችን ምስክሮቻችን ናቸው። እነሱን እማኝ አድርገን ወደ ሰላም እንጂ ወደ ነውጥ መመለስ አይኖርብንም።
በጋራ ሀሳብ የሰላም ሀገር መገንባት ቀጣዩ የቤት ስራችን ነው። በተጀመረው የሰላም ጥላ ስር ብዙ የኢትዮጵያ ህልሞች አሉ። የኢትዮጵያ ህልሞች የእኔና የእናንተ ህልሞች ናቸው። የእኔና የእናንተ ህልሞች ደግሞ የትውልዱ ህልሞች ናቸው። ሀገር የምትፈጠረው በዚህ እውነት ውስጥ ነው። ህልሞቻችን ሰላም ሲለብሱ የኔ ሀገር ትፈጠራለች። ያኔ ሁሉም ነገር መስተካከል ይጀምራል። ህልሞቻችን ነፍስ የሚዘሩት ደግሞ ኢትዮጵያ ሰላም ስትሆን ነው። በብቻ ሀሳብ ነውጥ ያነገበች ሀገር ፈጥረን ለራሳችንም ለሌሎችም መከራ ሆነን ሰንብተናል። አሁን ግን የይበቃል ጊዜ ላይ ነን። በጋራ ሀሳብ የሰላም ሀገር የምንፈጥርበት ጊዜ ላይ ነን። የኢትዮጵያ ህልሞቻ እውን ሊሆኑ ይገባል። ሰላምን ለብሰው፣ አንድነት ተዋህደው መሬት መንካት አለባቸው። ይሄ እንዲሆን እኛ የሰላም ሰዎች ልንሆን ይገባል። ስለ ሰላም እያወራን፣ በሰላም መኖርን ባህል ልናደርግ ይገባል።
ከፊታችን የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያረጋግጡ ብዙ ነገሮች እየመጡ ነው። ከዚህ ውስጥ አንዱ ስለሰላም የምናወራበት፣ ስለአንድነት የምንመካከርበት ሀገራዊ ምክክር ነው። እንዳየነው፣ እንደሰማነው፣ እንደደረሰብን፣ እንደተጎዳነው፣… ጥቂት ሰላም ሳይሆን ብዙ ሰላም ነው የሚያስፈልገን። ብዙ ሰላም እንዲመጣልን ደግሞ ሁላችንም የበኩላችንን መወጣት ይጠበቅብናል። በአንድ ሀገር ላይ አንድ አይነት ሀሳብ ብቻ ኖሮ አያውቅም። ሀገር በአንድ አይነት ሀሳብ ብቻ ተመርታ አታውቅም። ለሀገር የሚያስፈልጉ ሀሳቦች ከዚም ከዛም የተውጣጡ ዘርፈ ብዙ እና ሰላማዊ ሀሳቦች ናቸው። ሀሳብ ችግር የሚሆነው ነውጥ ሲቋጠር ነው። በሀገራችን ላይ እንደ ብዝሃነታችን ልዩ ልዩ ሀሳቦች መነሳታቸው ችግር የለውም። ችግር የሚሆነው እነዛ ልዩ ልዩ ሀሳቦች በምክክርና በውይይት አንድነትን መልበስ ካልቻሉ ነው። ሆኖም ህልሙን ሀገሩ ያደረገ ፖለቲከኛ በምንም ልዩነት ውስጥ መግባባት ይችላል። አላማውን ህዝብ ያደረገ ዜጋ በምንም የሀሳብ ልዩነት ውስጥ ወደ አንድነት የማይመጣበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ተነጋግረን የማንግባባው፣ አውረተን የማንስማማው ከሀገርና ህዝብ የተደበቀ ሌላ የኔነት አላማ ሲኖረን ነወ።
የኢትዮጵያ ህልሞች እንዲሰምሩ ልዩ ልዩ ሀሳቦችን የሚያስታርቅ የአንድነት ወግና ባህል ያስፈልገናል። ከነበርንበት የጦርነት ታሪክ ለመውጣት ተነጋግሮ የመግባባት፣ ተግባብቶ አብሮ የመኖር ስልጣኔ ያስፈልገናል። የሀገራችን ሰላም እኛ እጅ ላይ ነው ያለው። እጆቻችንን ለሰላም ስንዘረጋ፣ አንደበቶቻችንን ለእርቅና ለምክክር ስንከፍት ያኔ ሰላማችን ይፈጠራል። በአንድነት ከቆምን ከእኛ ርቆ ለሌሎች የተረፈ ብዙ ሰላም ያለን ሕዝቦች ነን። ብዙዎችን በሰላማችን አርቀንና አስታርቀን ቀን አውጥተናል። ያ ብዙ ሰላም ዛሬ ላይ ያስፈልገናል፤ እናም በሰላማዊ ሀሳብ ሰላማዊ ሀገር እንገንባ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 8/ 2015 ዓ.ም