የጥበብ ዋነኛውና ትልቁ አላማ የአንድን ማህበረሰብ መልካም እሴት መገንባት ነው። የነበረና የኖረን የማህበረሰብ መልካም እሴት እንዳይናድና ወደ መጥፎ አቅጣጫ እንዳያመራ መጠበቅም የጥበብ አንዱ ኃይል ነው። ያው ጥበብ ሲባል አንዱና ዋነኛው ሙዚቃ ነውና በኢትዮጵያ ሙዚቃዎች ውስጥ ከዚህ አኳያ የሚስተዋሉ የሀሳብ ተቃርኖዎች አስገራሚ ናቸው።
ለዚህ እንደመነሻ እንዲሆን ለዛሬ ብዙዎችን የሚያከራክር አንድ ሀሳብ እናንሳ። በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ በታላላቅና አንጋፋ ሙዚቀኞች ጭምር የተዜሙ ራስ ወዳድነትን ወይም ከምንም በላይ ለገንዘብ ዋጋ መስጠትን የሚሰብኩ ዘፈኖች ጥቂት አይደሉም። እነዚህ ዘፈኖች በብዙ ሰዎች ዘንድ እጅግ ተወዳጅና ሙዚቃዎቹን ያዜሙትም አርቲስቶች ልዩ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው። ለምሳሌ ያህል በዚሁ ሀሳብ ዙሪያ በተወዳጅ አርቲስቶች የተዜሙ ተወዳጅ ዘፈኖች የመልእክታቸውን ጭብጥ በጥቂቱ እንመልከት:-
“እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም” ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ፣
“ኪስህ ነው የቅርብ ወዳጅህ” ኤፍሬም ታምሩ፣
“ አብሮ መብላት ተሳስቦ ኑሮ ገዳም ሰፈር ቀረ ድሮ” አብዱ ኪያር፣
ተመሳሳይ መልእክትና ጭብጥ ያላቸው ሙዚቃዎቻችን እነዚህ ብቻ አይደሉም። ትዝብቴ ሙዚቃዎቹ ላይ ትችት መሰንዘር ሳይሆን ሙዚቃዎቹ የሚያስተላልፉት መልእክት ላይ በመሆኑ እነዚህን ዝነኛና ተወዳጅ ዘፈኖች ለአብነት ከጠቀስኩ በቂ ነውና ወደ ዋናው ሃሳብ ልለፍ።
እውነት ለመናገር እንደዚህ አይነት ጭብጥ ያላቸው ሙዚቃዎች መረዳዳት የኢትዮጵያውያን ባህል ነው በሚባልበት ማህበረሰብ ውስጥ መልካም የተባለውን እሴት የሚቃረኑ ናቸው። ከዚያም በላይ እንደዚህ አይነት መልእክቶችን ያዘሉ ሙዚቃዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የካፒታሊዝም አስተሳሰብን የሚሰብኩ ናቸው ማለት ይቻላል። እርግጥ ነው የእነዚህ ዘፈኖች ጭብጥ በገሃዱ ዓለም ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በትክክል የሚገልጽ ሊሆን ይችላል። ጥበብ ደግሞ የገሃዱ ዓለም ነጸብራቅ ነው የሚል ክርክርም ከዚህ አኳያ ሊያስነሳ ይችላል። ጥያቄው ግን ጥበብ የገሃዱ ዓለም ነጸብራቅ ቢሆንም ሁሉንም የገሃዱ ዓለም እውነታዎች ገሃድ ማውጣት ወይም “ፕሮሞት” ማድረግ አለበት ወይ ነው?። እዚህ ጋር ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር የተያያዘ አንድ ምሳሌ የበለጠ ይህን ሃሳብ ሊያብራራ ይችላል። በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ዜና የሆነ ነገር ሁሉ አይዘገብም፣ የሙያ ስነምግባር የሚባል ነገር አለ፣ አንድ ጋዜጠኛ የሆነ ትልቅ ዜና መሆን የሚችል ክስተት ቢገጥመው ከመዘገቡ አስቀድሞ በህዝብ ዘንድ የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽእኖ መኖር አለመኖሩን ማሰብ አለበት። ዜናው ምንም ያህል ትልቅ ቢሆን ህዝብ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ ካለ ሊሰራው አይገባም ተብሎ ይታመናል። ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን ከሆነ ይተወዋል ማለት ነው። ጥበብም ተመሳሳይ ባህሪ አለው፣ ምንም ያህል የገሃዱ ዓለም ፈጦ የወጣ እውነት ቢኖር ጥበብ እሱን ከማራገብ መቆጠብ እንጂ ማስተዋወቅ አይገባትም። አንድ የገሃዱ ዓለምን እውነታ ጥበብ በይፋ አደባባይ ላይ ባታወጣውም ቀድሞውንም ህዝብ የሚያውቀውና ጸሃይ የሞቀው ሊሆን ይችላል ብለን እናስብ ይሆናል። ነገር ግን አንድ እውነት በጥበብና ጥበበኞች ሲገለጽ የሚፈጥረው ተጽእኖ ቀድሞም ዓለም ያወቀው ቢሆን እንኳን ቀላል አይደለም። ጥበብ የህዝብ መሪ ናት፣ የጥበበኞችን ሃሳብም ህዝብ ገዝቶት የመከተል እድሉ በጣም ሰፊ ነው። ከዚህ አንጻር ጥበብ የገሃዱን ዓለም እውነታ እያየች እንዳላየች ሆና ትለፍ ሳይሆን አካሄዷን መምረጥ አለባት የሚለው ሃሳብ የበለጠ ገዢ ይሆናል።
ይህን የምንለው ያለምክንያት አይደለም። ዘፈኖቹ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ስላለ ነው። እስኪ ልብ ብላችሁ አስተውሉ! አንዳንድ ሰዎች ግደለሽ ወይም ብኩን መሆን ሲፈልጉ የአንዱን ዘፈን ይጠቅሱና ‹‹… አለ እገሌ›› ይላሉ። ይሄ ማለት ዘፋኙ ያለውን ነገር ለማድረግ አስበዋል ማለት ነው። ‹‹ስለነገ ምንም አታስብ›› የሚል ይዘት ያለው መልዕክት የሚያስተላልፉ ዘፈኖች አሉ። ይህን የሚሰማ ወጣት ግደለሽ ለመሆን ይበረታታል ማለት ነው። ይሄ ደግሞ ከነገ የሕይወት መርህ ጋር ይጣረሳል። የሰው ልጅ ትውልድን የሚያስቀጥል ስለነገ በማሰብ ነው።
በምሳሌነት የተጠቀሱት ሙዚቃዎች ዜማና ግጥማቸው ግሩም ነው። ከሚያስተላልፍለት ጭብጥ ሃሳብ አንጻር አንዳንዶቹ የተሻሉ ሆነውም እናገኛቸዋለን። ለምሳሌ ያህል የክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን “ከሌለህ የለህም” የተሰኘ ሙዚቃ አጠቃላይ ጭብጥ ስንመለከት ለሌሎች አታስብ፣ ከሰው ይልቅ ለገንዘብ ብቻ ተጨነቅ የሚል አጠቃላይ መልእክት የለውም። እንዲያውም ይኑርህ ነው የሚለን። ይህ ደግሞ ክፋት የለውም፣ ማንኛውም ሰው ይኖረውና ሀብት ንብረት ያፈራ ዘንድ የሚቃወም አለ ተብሎ አይታሰብም። የዘፈኑ አጠቃላይ መንፈስ ግን ሰው ሁሉ ጥሪት እንዲኖረው እንጂ ኖሮት የሌላቸውን እንዲረዳና እንዲደግፍ የሚያነሳሳ አይደለም። ከዚያም በላይ ከሌለህ የለህም የሚለው አሻሚ ትርጉም ሰፊው ህዝብ ሁሉ ኖሮት ነው እንዴ የሚኖረው? ወደሚል ጥያቄ ይገፋናል።
ሌላው የኤፍሬም ታምሩ “ኪስህ ነው የቅርብ ወዳጅህ” የሚል ዜማ አጠቃላይ ጭብጥ ለጉምቱው የግጥምና ዜማ ደራሲ ይልማ ገብረአብ ከፍ ያለ አክብሮት ቢኖረኝም በዚህ ሃሳቡ ግን እንዳልስማማ አድርጎኛል። ገንዘብ የቱንም ያህል ቢከመር በርካቶችን ከሞት ማዳን እንደማይችል በብዙ አጋጣሚዎች ታዝበናል። ከዚያ ይልቅ ሰው የሰው የቅርብ ወዳጅ ሲሆን ከብዙ ነገሮች የሰውን ሕይወት ሲታደግ ሁሌም እያስተዋልን ነው። ሰው ኪሱ ሞልቶ ነገር ግን ሰው ርቦት ሲሰቃይ በአንጻሩ ሰው ሰውን ከገንዘብ በላይ ሲያድን ብዙ ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል። ሰው ከምንም በላይ ወዳጁ ኪሱ ቢሆን ኖሮ ዛሬ መቄዶንያን የመሳሰሉ የረድኤት ድርጅቶች ባልተፈጠሩ ነበር።
በተወዳጁ ድምጻዊ አብዱ ኪያር የተዜመው “አራዳ” የተሰኘ ተወዳጅ ዘፈንም ቀደም ሲል ከተጠቀሱት ምሳሌዎች የባሰ እንጂ የተሻለ መልእክት የሚያስተላልፍ አይደለም። “አብሮ መብላት ቀረ ድሮ”፣ በኪስህ ተማመን ጎበዝ ፍቅር ጠፍቷል” የሚሉ ስንኞች የዚህ ሙዚቃ ጭብጥ ሃሳቦች ናቸው። ትክክል ነው ሃሳቡ የገሃዱ ዓለም እውነታ ነው። ነገር ግን ፍቅርና መተሳሰብ ጠፍቷል ወይም እየጠፋ ነውና ሰው ሁሉ ግለኝነትን እንዲከተል ከማነሳሳት ይልቅ ለምን መተሳሰብና ፍቅር ይጠፋል? የሚል ጭብጥ የዘፈኖቹ ዋነኛ መልእክት ቢሆን ማህበረሰብን በመልካም እሴት ከመገንባት አኳያ የተሻለ ጥቅም ይኖረዋል። መቼም መተሳሰብና ፍቅር መጥፋቱ ጥሩ ነገር ሊሆን አይችልም፣ ስለዚህ ጥበብ ወደ ጠፋው መልካም እሴት ማህበረሰቡን የመመለስ ሚና ሊኖረው ይገባል እንጂ ከጠፋው ጋር አብሮ መጥፋትን የሚሰብክ አይነት መልእክት(negative energy) መፍጠር የለበትም።
እዚህ ላይ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሚሉትን አንድ ነገር እንጥቀስ። ደረጃ እና ተፈላጊነት (Standardization and Popularization) የሚባል ነገር አለ። ደረጃ (Standard) የሚባለው ከያኒው የመጣለትን ነገር እንደ ወረደ ሲያቀርበው ነው። ትክክለኛ የተሰማው ስሜት ሳይጨመር ሳይቀነስ የሚቀርብ ማለት ነው። ሥራው ይወደድም አይወደድም ከያኒው የሚያቀርበው የውስጡ ስሜት ያዘዘውን ነው።
ተፈላጊ (Popular) የሚባለው ደግሞ፤ ማህበረሰቡ ምን ያስፈልገዋል? ምን ቢቀርብለት ነው የሚወድ? የሚለውን ታሳቢ በማድረግ የሚሰራ ነው። ይህም የሚሰራው በመልዕክቱ ትውልድ ለመቅረጽና ለማነጽ ነው።
በኢትዮጵያ ደረጃ የትኛው ነው የሚያስፈልገን የሚለውን ማሰብ ነው። በሬዲዮና ቴሌቭዥን የሚታይና የሚሰማ ነገር ሁሉ ትክክለኛ ነው ብሎ በሚያምን ማህበረሰብ ውስጥ ሊገነባ የሚችል ነገር ነው መተላለፍ ያለበት። ምክንያቱም ገና ማህበረሰብ የማስተማር ደረጃ ላይ ነን። ለዚህ ደግሞ ኪነ ጥበብ ኃላፊነት አለበት!
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 8/ 2015 ዓ.ም