ኢትዮጵያውያን ለስደት ከሚወጡባቸው አገራት አንዷ ወደሆነችው ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚያደርጉት ጉዞ እጅግ አደገኛ ከሚባሉ ስደት ኮሪደሮች መካከል ተጠቃሽ ነው።ደቡብ አፍሪካ ለመግባት የስድስት ሀገራትን ድንበር መሻገር ይጠበቅባቸዋል።ደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵያ በስተደቡብ 4 ሺህ 777 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን ይህ የስደት ኮሪደር በዓለም ውስጥ ከሚገኙ ረጅም የስደት ኮሪደሮች መካከል አንዱ ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡
ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረገው ስደት የተለያዩ የመጓጓዣ ዘዴዎችን በመጠቀም የሚደረግ ሲሆን፤ የአየር ትራንስፖርት፣ የውሃ ላይ ትራንስፖርት፣ እና የየብስ ትራንስፖርትን በመጠቀም በርካታ የአፍሪካ ሀገራትን በማቋረጥ የሚደረግ ነው።አንዳንዶቹ ከአዲስ አበባ ወደ ጆሃንስበርግ ቀጥታ በረራ የሚያደርጉ ሲሆን፤ አብዛኛው ስደተኛ ግን የአውቶብስ ትራንስፖርት እና የእግር ጉዞንን በማጣመር የመተላለፊያ አገሮችን ያቋርጣሉ። አንዳንዶች ደግሞ በህንድ ውቅያኖስ ላይ በጀልባ ይጓዛሉ።
በተለምዶ ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረገው የየብስ ትራንስፖርት ከኬንያ የሚጀምር ሲሆን፤ ከዚያም በታንዛኒያ፣ በማላዊ፣ በሞዛምቢክ/ዚምባብዌ ወደ ደቡብ አፍሪካ ይዘልቃል። ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት እ.አ.አ በ2021 ባወጠው ሪፖርት ከ2016 እስከ 2018 ድረስ ብቻ ወደ ደቡብ አፍሪካ የገቡ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ቁጥር ከ200 ሺህ እስከ 300 ሺህ ይገመታል፡፡
ይህ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረገው ረጅም የስደት ጉዞ በአደጋዎች የተሞላ ነው። በመሸጋገሪያ አገሮች ውስጥ ብዙ ስደተኞች እንደወጡ ቀርተዋል። ዓለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት ባካሄደው ጥናት መሰረት እ.አ.አ ከ2012 እስከ 2020 ድረስ ባሉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ቅርብ ጊዜ ከሰባት ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ከኢትዮጵያ ተነስተው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ ከቤታቸው ወጥተው የደረሱበት አይታወቅም ወይም ሞተዋል፡፡
በዚህ መልኩ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረገው ጉዞ በተግዳሮቶች የተከበበ እና ለአደጋ የሚያጋልጥ ቢሆንም፤ በደቡብ አፍሪካ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች አሉ። ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ አንዳንድ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ገንዘብ በመላክ በሀገር ቤት የሚኖር ቤተሰባቸውን የሚደግፉ ሲሆን፤ በሀገራቸው የሚያፈሱት የኢንቨስትመንት መጠንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው።አንዳንዶቹም እምነት ተቋማትን ጭምር ለመደገፍ ገንዘብ ይልካሉ።በተጨማሪም በትውልድ ቦታቸው የሚገኙ አካባቢያዊ እና ብሄራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን በገንዘብ ይደግፋሉ፡፡
እናም በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም። በተለያየ መልኩ ተሰድደው በተለያዩ አገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ኢትዮጵያ በዓመት ከአምስት ቢሊየን ዶላሮች በሪሚተንስ ታገኛለች።በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም ኢትዮጵያ ለምታገኘው ሪሚታንስ የራሳቸውን ድርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከመላው ሀገሪቱ የሄዱ ቢሆኑም፤ አብዛኞቹ ግን ከሀዲያ ዞን እና ከከምባታ ጠምባሮ ዞን የሄዱ ናቸው። የሀዲያ ዞን የሰው ሀብት እና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያን ጠቅሶ፣ ደረጃ ፈይሳ የተሰኘ ተመራማሪ በጥናታዊ ጽሁፉ ላይ እንዳስቀመጠው፤ እ.አ.አ ከ2013 እስከ 2018 ባሉት አምስት ዓመታት 61 ሺህ 148 ወጣቶች ወደ ደቡብ አፍሪካ ተሰደዋል።ይሄው ተመራማሪ ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት መሰረት ከሀዲያ እና ከከምባታ ጠምባሮ ዞኖች ውስጥ ከሚኖሩ ቤተሰቦች ውስጥ 40 ከመቶ የሚጠጋ ቤተሰብ ቢያንስ አንድ ዓለም አቀፍ ስደተኛ አለው።
ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለሚደረገው ስደት ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል።በእርሻ መሬት ላይ ያለው ጫና መጨመር ደግሞ ከሀዲያ እና ከምባታ አካባቢዎች ወደ ደቡብ አፍሪካ ለሚደረገው ስደት ቁልፍ ከሆኑ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች አንዱ ነው። መረጃዎች እንደሚያሳዩት የሀዲያ ዞን ከፍተኛ የህዝብ ጥግግት ካለባቸው የሀገራችን አካባቢዎች አንዱ ነው።በካሬ ኪሎ ሜትር 342 ነጥብ 64 ሰው ይኖራል። ሀገራዊ የህዝብ ጥግግት በካሬ ኪሎ ሜትር 109 ነጥብ 22 አንጻር ሲታይ እጅግ የላቀ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።ይህ የህዝብ ጥግግት በእርሻ መሬት ላይ የበለጠ ጫና ፈጥሯል።ምርታማነት እያሽቆለቆለ እንዲሄድም ምክንያት ሆኗል፡፡
የአቶ ደረጀ ጥናት እንደሚያሳየው የሀዲያ አካባቢ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚከሰተው ድርቅ በተደጋጋሚ ከሚጠቁ አካባቢዎች አንዱ ነው።ይህም የግብርና ስራ ላይ አደጋ ፈጥሯል።ይሁን እንጂ እነዚህ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በሀዲያ ዞን ብቻ ያሉ ችግሮች አይደሉም።ችግሮቹ ሀዲያ ከጎረቤቶቹ ጋር የሚጋራቸው ናቸው።በአካባቢው ያሉ አንዳንዶቹ ዞኖች እንዲያውም ከሀዲያ ከፍ ያለ የህዝብ ጥግግት አላቸው። ይሄም “ታዲያ ከሀዲያ አካባቢ እንዴት ከፍተኛ ስደተኛ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊሰደድ ቻለ?” የሚል ጥያቄ የሚያጭር ይሆናል፡፡
አንዳንድ ሰዎች የሀዲያ አካባቢ ወደ ደቡብ አፍሪካ እየተሰደዱ ያሉት ለመሰደድ የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ አቅም ስላላቸው ነው የሚል መከራከሪያ ሲያቀርቡ ይታያል።ሆኖም ይሄ እጅግ የተሳሳተ መከራከሪያ ነው። የሀዲያ ወጣት ወደ ደቡብ አፍሪካ እየተሰደደ ያለው ለመሰደድ የሚያስችል የኢኮኖሚ አቅም ስላለው አይደለም።የኢኮኖሚ አቅም ጉዳይ ቢሆን ኖሮ ከጎረቤት ዞኖች ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚሰደዱ በርካታ ስደተኞችን እናይ ነበር። አጎራባች ዞኖች የሚኖሩ ህዝቦች ከሀዲያ ያነሰ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው አይደሉም።አንዳንዶቹ ከሀዲያ አካባቢ የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ያደረጁ ናቸው፡፡
ከሀዲያ እና ከምባታ ዞኖች አካባቢ የሚደረገውን ስደት ለማብራራት ከኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ባሻገር ያሉ ምክንያቶችን ማብራራት አስፈላጊ ነው።ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ምክንያቶች በተለይም “የዳርፍሪማ’’ የሚባለው የማህበረሰቡ እሳቤ፣ ለስደት የሚሰጠው መንፈሳዊ ትርጉም፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ኔትወርክ እየተጫወቱ ያለውን ሚና መመርመር አስፈላጊ ነው።ምክንያቱም እነዚህ ለስደት የበኩላቸውን እየተወጡ ቢሆንም፤ ምሑራን በጥናታቸው፣ መንግስትም በመከላከል ትኩረቱ ውስጥ ተገቢው ትኩረት ያልተሰጣቸው በመሆናቸው ነው፡፡
ቀደም ብዬ ባነሳሁት የአቶ ደረጃ ጥናት፣ በተለይም ከሀዲያ አካባቢ የሚደረገው ስደት እንቅስቃሴ በእጦት ምክንያት ብቻ ሳይሆን የአካባቢው ማህበረሰብ ስደትን እንደ መብት ይመለከተዋል።የተሻለ እድል ወዳለበት አካባቢ ሄዶ መስራትን እና መለወጥ በአካባቢው እንደ ባህል ሆኗል።ቀደም ባሉ ጊዜያት በሀገር ውስጥ የተሻለ እድል ወዳለባቸው አካባቢዎች ሄዶ የመስራት ባህል የነበረው ህዝብ ሲሆን፤ ይሄ የተሻለ እድል ወዳለበት ሄዶ መስራት በሀዲይሳ “ዳርፍሪማ” ይሰኛል።ጋምቤላ፣ ወንጂ እና ድሬዳዋ አካባቢ የሀዲያ ማህበረሰብ በብዛት መኖሩ በአካባቢው ስር የሰደደ የዳርፍሪማ ባህል እንዳለው ማሳያ ነው።ከዚህ በተጓዳኝ መንፈሳዊ እይታው ሲሆን፤ ለምሳሌ፣ አንድ ስደተኛ በመንገድ ላይ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች ተሻግሮ ካሰበበት ቦታ ሲደርስ እና ተሳክቶለትም ከተገኘ፣ ቀድሞውኑ ፈጣሪ ያዘዘለት እድል እንደሆነ ይነገርለታል፤ በአንጻሩ ካሰበበት ሳይደርስ ቢቀር የፈጣሪ ፈቃድ ስላልሆነ ነው የሚል እሳቤ በመያዙ ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሰው ጥናት ባለቤት አቶ ደረጀ እንደሚሉትም፤ ከኢኮኖሚያዊ አቅሙ ባሻገር ፖለቲካዊ ኔት ወርክ እና ማህበራዊ ኔት ወርክ የበኩሉን ሚና ሲጫወት ቆይቷል።ቀደም ባሉ ጊዜያት የመንግስት ባለስልጣናት ስደትን ማበረታታቸው እና በኢትዮጵያ ደቡብ አፍሪካ ኮሪደር የሚንቀሳቀሱ ደላሎች ጋር የመገናኘት እድል በራሱ በአካባቢው ለስደት ምክንያት ነው።በመሆኑም ዛሬ ላይ ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረገውን ስደት ለማስቆም በሚደረገው ጥረት ከኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ባሻገር የቆየውን ስደት ባህል፣ የመንፈሳዊ ፈቃድ እሳቤ እንዲሁም ፖለቲካዊና ማህበራዊ ኔትወርኮችን ከግምት ያስገባ መሆን ይኖርበታል፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ጥር 8/ 2015 ዓ.ም