አቶ ባህሩ ሻፊ በቡታጅራ ከተማ የሚኖሩ የ65 ዓመት አዛውንት ናቸው:: ኑሯቸውን የሚገፉት በቀን ሥራ ማለትም በጭቃ አቡኪነትና ቤት ምረጋ ነው:: አንድ አጋጣሚ ግን ስራቸውን ሰርተው ጉሮሯቸውን እንዳይደፍኑበት አደረጋቸው:: በዚህም ቤታቸው እንዲውሉ ተገደዱ:: አጋጣሚው አፈሩን ረግጠው ወደ ጭቃ እየቀየሩ ባለበት ጊዜ የተከሰተ ነው:: እንደተለመደው አንድ ማለዳ ሥራቸውን ለማከናወን ከቤት ይወጣሉ:: ስራ ቦታቸው ላይ እንደደረሱም ልብሳቸውን ቀይረው ጭቃውን መርገጥ ይጀምራሉ፤ የሆነው ነገር ግን ለማመን የሚከብድ ነበር:: እግራቸውን ክፉኛ የማያውቁት ነገር ሲወጋቸው ተሰማቸው:: ሆኖም የተለመደው ክስተት እንደነበር ተመለከቱ:: የወጋቸውን ነገር ሚስማር ነበርና ምንም አልተገረሙም:: ስለዚህም እዚያው ሚስማሩን ነቅለው ወደ ሥራቸው ተመለሱ::
በትኩሱም ወደ ሃኪም ቤት አልሄዱም:: ይህ ደግሞ እያደር ይጠዘጥዛቸው ጀመር፤ በወቅቱ በአፋጣኝ ወደ ህክምና መሄድ ሲገባቸው ባለመሄዳቸው ስቃያቸውን አበረታው:: ሁኔታውን ዘግይተው የተረዱት ቤተሰቦቻቸውም ወደ ህክምና ባይወስዷቸው ኖሮ ከዚህም የባሰ ሁኔታ ውስጥ ይወድቁ እንደነበር ያስታውሳሉ:: ምክንያቱም በሽታው ቲታነስ ሆኖ ተገኝቷል:: በዚህም ትናንት እንደልባቸው ይሮጡና ከራሳቸው አልፎ የቤተሰባቸውን ኑሮ የሚሞሉት አባወራ እግራቸው ዛሬ መንቀሳቀስ ተስኖታል:: የሰው እርዳታንም ሽቷል:: ይህም ቢሆን ግን መኖራቸውን ያመሰግናሉ:: ምክንያቱም የጤና መድህናቸው መድህን ሆኖላቸዋል:: ከዚህ የበለጠውን አደጋ እንዳይጋፈጡት አድርጓቸዋል:: እንዴት ከተባለ ህመማቸው በቀላሉ የሚታከም አልነበረም:: ብዙ ወጪና እንክብካቤን ይፈልጋል:: በእርሳቸው አቅም ደግሞ ይህ የማይታሰብ ነበር::
የጤና መድህን አባል በመሆናቸው ነገሮች እንደቀለሉላቸው በወቅቱ አባቱን ወደ ህክምና የወሰዳቸው ልጅቸው ሙባረክ በሃሩ ይናገራል:: ‹‹ አባቴን ወደ ህክምና ስወስደው መክፈል አለመቻላችን ተረጋግጦ አባል የሆንበትን የማህበረሰብ ጤና መድህን መታወቂያ ካርዳችንን ብቻ ይዤ ነበር:: መጀመሪያ ይዤው የሄድኩትም ወደ ቡታጅራ ጤና ጣቢያ ነው:: ከጤና ጣቢያ ባሻገር ተጨማሪ ህክምና እንደሚያስፈልገው የህክምና ባለሙያዎች ገለጹልን ወደ ቡታጅራ ጠቅላላ ሆስፒታል ሪፈር አደረጉን:: እዛም ቀዶ ህክምና ክፍል ገብቶ ታከመ:: ህክምናው ገና ባያልቅም የቀዶ ህክምናን ጨምሮ የተለያዩ የህክምና አገልግሎት ወጪዎች ተሸፍነውልናል:: በሆስፒታሉ ከአንድ ወር በላይም አልጋ ይዘን ቆይተናል:: ነገር ግን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና አገልግሎት አባል እና ተጠቃሚ በመሆናችን ምንም አይነት ገንዘብ ከኪሳችን አላወጣንም::››
ሙባረክ አባቱ የማህበረሰብ ጤና መድህን አባል ባይሆኑ ኖሮ ምን ሊሆኑ እንደሚችል ያሳስበዋልⵆ “ይሄ በጣም አስቸጋሪ ነው:: እኛ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ተብለን መደበኛ መዋጮውን እንኳን አላዋጣንም:: ይሄ ሁሉ ወጪ በኛ አቅም የሚታሰብ አልነበረም” ይላል:: ይህ ታሪክ በኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት ከተዘጋጀ መፅሄት ላይ ለማሳያነት የወሰድነው ይሁን እንጂ ከዚህ የባሱ ችግሮች ኖረውባቸው የተፈቱላቸው አያሌ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዳሉ ይታመናል:: ምክንያቱም ድርጅቱ በአስር ዓመት የሥራ ጉዞው ምን ያህል ሰዎችን ተጠቃሚ እንዳደረገ ሲያብራራ ነበር:: ድርጅቱ ልክ እንደ አቶ በሃሩ ሳሃፊ ሁሉ በህመማቸው ወቅት እንደልብ ከፍለው መታከም የማይችሉ እና ገቢያቸው ከእለት ጉርሳቸው የማያልፍ ሰዎችን ታድጓል:: ህመማቸውን ዋጥ አድርገው ለመኖር የተገደዱትንም አይዟችሁ ብሏል::
በ2003/04 ዓ.ም በአራት ክልሎች በተመረጡ አስራ ሶስት ወረዳዎች የተጀመረው የጤና መድህን ስርአት የሙከራ ትግበራው ለሁለት ዓመታት ከተተገበር በኋላ ያስገኘው ውጤት ብዙዎችን የፈወሰ እንደነበር የ10 ዓመታት ጉዞውን ባስቃኘበት ወቅትና የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ፕሮግራምን የሚመራ ብሔራዊ ምክር ቤት ይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ ዝግጅት በተከናወነበት ጊዜ ምክር ቤቱን የሚመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ሲመሰክሩለት ነበር::
በዝግጅቱ ላይ እንደተናገሩትም፤ ምክር ቤቱ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሽፋንን ወደ ሁሉን አቀፍ የጤና መድህን ሽፋን ለመለወጥና ሁሉንም ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀመጠውን አቅጣጫ የሚደግፍ ነው:: እናም መንግስት የመድህን ፕሮግራሙ ፋይዳና በቀጣይ የሚጠይቀውን ትኩረት ታሳቢ በማድረግ የራሱ የማቋቋሚያ አዋጅ አውጥቶ አገራዊ ፕሮግራም እንዲሆን እየሰራ ይገኛል:: እንደአጠቃላይ ያለው አፈፃፀምም ጥሩ የሚባል ነው:: ሆኖም ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ቁጥር አንፃር አሁንም ብዙ ይቀራል፤ በ2030 ሁሉን አቀፍ የጤና መድህንን ተደራሽ ለማድረግ የተቀመጠውን እቅድ ከግብ ለማድረስ ከዚህም በላይ ተግቶ መስራትን ይጠይቃል:: በጤናው ዘርፍ የሚያስፈልገውን በቂ የሰው ኃይል ማፍራትና ማሟላት፣ የግብአትና መድሃኒት አቅርቦትን ማሻሻል፣ በተደረጉ ሪፎርሞች በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የሰውን የጤና ንቃተ ህሊና ማሳደግ፤ ህብረተሰቡ ስለጤና መድህን ያለው ግንዛቤ ከፍ ማድረግን የመሳሰሉ ተግባራት አበረታች ውጤቶች የታየባቸው ቢሆንም በስፋት መከናወን ይኖርባቸዋል::
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰም ይህንን ሀሳብ ይጋራሉ:: እርሳቸው እንደሚሉትም፤ ይህ የማህበረሰብ ጤና መድህን ተግባራዊ መደረግ ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጣቸው ህፃናትና እናቶችን ታድጓል:: ጤናቸው ተሻሽሎ በተላላፊ በሽታ እንዳይጠቁ ጭምር አግዟቸዋል:: ህመምና ሞታቸውንም ቀንሷል:: የአገሪቱን አማካይ የእድሜ ጣሪያ ሁሉ ከነበረበት 46 ዓመት ወደ 66 ዓመት ከፍ እንዲል አስችሏል::
በ2014 ዓ.ም በተሰራው የጤና ካውንት ጥናት ውጤት ሪፖርት የአገራችንን የጤና ፋይናንስ የጤና ወጪ በአገር አቀፍ ደረጃ 32 በመቶ ከመንግስት፤ 34 በመቶ ከዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች፤ 30 ነጥብ 5 በመቶ በጤና አገልግሎት ዜጎች ከኪሳቸው ከሚከፍሉት፤ 2 ነጥብ 5 በመቶ ከኢንሹራንስ እንደሆነ ያሳያል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ይህም የጤና አግልግሎት ሽፋናችን እየጨመረ ቢመጣ በተለይ በውጭ አጋር ድርጅቶች ድጋፍ ላይና በአገልግሎት ሰዓት ዜጎች ከኪሳቸው የሚከፍሉት ክፍያ ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን ማስቀረት ላይ መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል::
በሌላ በኩል በአገራችን በነፍስ ወከፍ የጤና ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት እያሳየ እ.ኤ.አ በ1996 ከነበርንበት 4 ነጥብ 5 የአሜሪካ ዶላር በ2012 በተደረገው ጥናት ወደ 36 ነጥብ 37 ዶላር መድረሱን ያሳያል:: ይህ ከነበረበት ዝቅተኛ መጠን አንፃር ሲታይ እድገት ያሳየ ቢሆንም የዓለም ጤና ድርጅት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ለማሟላት ያስፈልጋቸዋል ብሎ ካስቀመጠው 85 ዶላር የነፍስወከፍ ወጪ አንፃር አሁንም ዝቅተኛ ነው:: በመሆኑም የጤና ፋይናንስ ስርዓቱን ለማጎልበትም ሆነ ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋንን ለማረጋገጥ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ዜጋ በፍትሀዊነት ለማዳረስ የጤና መድህን ስርዓት እጅግ ቁልፍ ነው ብለዋል::
የጤና መድህን ትግበራውን ወደ ሥራ ለማስገባት በርካታ እንቅፋቶች እንዳሉ የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ ናቸው:: ማህበረሰቡ ስለጤና መድህን የነበረው ግንዛቤ ዝቅተኛ ነበር፤ የሚከፈለውን መደበኛ ክፍያ ከከፈልኩ በኋላ ሳልታከም ብቀርስ የሚል ስጋት ነበራቸው:: አሁንም ቢሆን ይህ ችግር በተወሰነ መልኩ አለ:: ስለሆነም ሊሰራበት እንደሚገባ ያሳስባሉ::
የጤና መድህን ትግበራው በገንዘብ እጦት ምክንያት የህክምና አገልግሎት ሳያገኙ በየቤቱ ለተቀመጡ በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚደርስ ነው:: ችግራቸውን የፈታና እፎይታን ያስገኘላቸው ነው:: እናቶች የቤተሰብ አባላቸው ህመም ቢገጥመው ለህክምና የትዳር አጋራቸውን እጅ ሳይጠብቁ የጤና መድህን መታወቂያቸውን ብቻ በመያዝ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ መፍትሄ የሚያገኙበትም ነው:: እናም ይህንን መልካም እድል መጠቀም ያስፈልጋል ባይም ናቸው::
ጤና መድህን ከአግልግሎት ጥራት አንፃር አሁንም ችግሮች ይስተዋሉበታል የሚሉት ዳይሬክተሯ፤ የመድሃኒት አቅርቦት እጥረትና ማህበረሰቡን ስጋት ውስጥ ሊከተው ይችላልና ሊታሰብበት እንደሚገባም ያነሳሉ:: መድህኑ ደግሞ ይህንን እፈታለሁ የሚል ነውና ተቃራኒ ሀሳቦች ያጋጥማሉ:: ስለሆነም እንደአገር ይህንን ታሳቢ አድርጎ መስራት እንደሚያስፈልግ በንግግራቸው አሳስበዋል::
መደበኛ ባልሆነ የስራ ዘርፍ ለተሰማሩ ዜጎች የሚተገበረው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ቋሚ ገቢ የሌላቸው እና ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆነ የማህበረሰብ ክፍሎችን ያጠቃለለ የጤና መድህን አይነት ነው:: በቀጣይ በመደበኛ ሥራ ለተሰማሩና ለጡረተኞች የማህበራዊ የጤና መድህን ለማስጀመር እየተሰራ ይገኛል:: እናም በዚህ የታዩ ክፍተቶች በሌላውም እንዳይደገም ብሔራዊ ምክር ቤቱ ትልቁን ሚና እንደሚጫወትም እምነታቸውን ገልጸዋል::
በፕሮግራሙ ላይ እንደተባለው፤ የጤና መድህኑ 894 ወረዳዎችን ተደራሽ አድርጓል፤ አፈፃፀሙንም 84 በመቶ ማድረስ ተችሏል:: በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሽፋኑ ከ9 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ አባወራና እማወራዎችን ማካተት የተቻለ ሲሆን፤ ከ45 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የመድህን ሽፋኑ ያለምንም የክፍያ ስጋት፣ የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል:: በብዙዎቹ ክልሎች ላይ ውጤታማ አተገባበር የታየ ሲሆን፤ አማራ ክልል የታየው ግን ላቅ ያለ አፈጻጸም ተጠቃሽ ነው::
በክልሉ የነበረው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ትግበራ በሦስት ወረዳዎች የተጀመረ ሲሆን፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ አሁን ላይ በሁሉም ወረዳዎች ተስፋፍቶ የአገልግሎት ሽፋንም ወደ 80 ነጥብ 6 በመቶ ማድረስ ተችሏል::
የአማራ ክልል የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ ሀብቴ እንደተናገሩት፤ 14 ነጥብ 2 ሚሊዮን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል:: ማህበረሰቡ ህመም በሚያጋጥመው ወቅት ወደ ጤና ተቋማት ተመላልሶ የመታከም ልምዱ ጨምሯል:: እንዲሁም ማህበረሰቡ የጤና መድህን ፕሮግራም ላይ ያለው ግንዛቤ ከፍ ብሏል:: በዚህም ክልሉ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን በ2014 ዓ.ም ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ሰብስቧል:: ይህ ገንዘብ የጤና ዘርፉን ለማሻሻል እጅግ ይጠቅማል:: የመድህን ፕሮግራም ተጠቃሚውንም በቂ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ያደርገዋል::
ክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዘርፉ የሚያከናውናቸውን ተግባራት የሚያስተጓጉሉ በርካታ ችግሮች አጋጥመዉታል፤ ከእነዚህም መካከል ዋናው ጦርነት ነው የሚሉት ዶክተር መልካሙ፤ በጦርነቱ ብዙ የህክምና ተቋማት ወድመዋል፤ ብዙ ማህበረሰብም ተፈናቅሏል:: ይህ ችግር የጤና መድህን ፕሮግራሙን አተገባበር በትልቁ ስለሚጎዳ ለመፍታት እቅድ በማውጣት ተንቀሳቅሰናል:: በቅድሚያ ያደረግነውም እነዚህን ሰዎች የመድህን ሽፋኑ ተጠቃሚ ማድረግ ነበር:: በዚህም ክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት ምንም እንኳን በርካታ ተግዳሮቶች ቢገጥሙትም አቅም የሌላቸውና መደበኛውን ክፍያ መክፈል የማይችሉትን የማህበረሰብ ክፍሎች አቅም ያላቸው ሌሎች ሰዎች እንዲያግዟቸው አድርጓል::
ሰዎች የህክምና ወጪያቸው ቢሸፈንም ህክምናውን የሚያደርግላቸው ባለሙያና በቂ የህክምና ተቋማት ከሌሉ ዉጤት ማምጣት አይታሰብምና የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠትም ይህ ሥራ በእጅጉ ያገዛቸው እንደነበርም ይናገራሉ:: ስለዚህ የጤና መድህኑ ብዙዎችን የጠቀመና ያሻገራቸው ስለሆነ መጠቀሙ ይበጃል በማለት ለዛሬ የያዝነውን ሀሳብ አበቃን
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን ጥር 6/ 2015 ዓ.ም