‹‹ማምሻም እድሜ ነው›› የሚለው አገርኛ አባባል በዋዛ የሚታለፍ ወይም የሚታይ እንዳልሆነ የሰሞኑ ትዝብቴ ጥሩ ምሳሌ ይሆን ይመስለኛል:: በግርምት መልኩ “የጊዜ ነገር!” እንድልም አድርጎኛል:: ሰዎች አይናቸው ስቃይ ከማየት፣ ጆሮአቸውም ሰቆቃ ከመሥማት፣ በሞትና በህይወት መካከል ሆኖ የዕለት ኑሮን ለመግፋት ከመታገል፣ ከራስ ጭንቀት በላይ ለሌላው ከመጨነቅ እፎይ ብለው የሰላም አየር ለመተንፈስ በቅተዋል:: ትናንትን ወደኋላ ትተው ዛሬን ለመኖር ከኑሮ ጋር ግብግብ ጀምረዋል:: ለዚህ ደግሞ በተለይም በክርስትና እምነት ተከታዩ ማሕበረሰብ ዘንድ የእየሱስ ክርስቶስ ልደት (የገና በዓል) ለማክበር ከዝግጅት ጀምሮ ሲያደርጉ የነበረው እንቅስቃሴ ጥሩ ማሳያ ሆኖ አገኘሁት::
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ አካላቸው ጎድሎ ሥነልቡናው ስብራትም ደርሶባቸዋል:: የመንግስት ተቋማት፣ የሕዝብ ሃብትና ንብረት እንዲሁም የመሰረተ ልማት አውታሮች ወድመዋል:: ከጥቅሉ ከፍ ያለ ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ደርሷል:: ይህ ሁሉ የተፈፀመው ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ በወንድማማቾች መካከል በተፈጠረ ግጭት መሆኑ ደግሞ ነገሩን የከፋ ያደርገዋል::
ሆኖም ክስተቱ ገና ከሰው አእምሮ ውስጥ የወጣ ባይሆንም አሁን ላይ የተገኘው እፎይታ ለሰው ልጅ የሰጠውን ተስፋ በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ኩነቶችን እንድናይና እንድንታዘብ አድርጎናል:: ሰሞኑን የታየው የገና በዓልን ድባብ ደግሞ ከሁለት ዓመታት በላይ በጦርነት እና በጭንቅ ውስጥ የቆዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ሰላም በማግኘታቸው ምን ያህል እንደተደሰቱ፤ ተስተጓጉሎ የቆየው ግብይት በመጀመሩም ነጋዴውና ሸማቹም ሲገበያዩ ያን የጦር አውድማና የስጋት ቀጠና የነበረውን አካባቢ ሲያደምቁ በተለያየ የመገናኛ ዘዴ ለማየት ችለናል::
እኛም ችግሩን ከጦርነት ቀጠናው በርቀት ላይ ሆነን ስንከታተል ለነበርን ወገኖች እንኳን በጦርነቱ የተፈጠረብን ጫና ከፍተኛ በመሆኑ፤ በአካባቢው የነበረውን ድባብ በተለየ ሁኔታ እንድናየው ብቻ ሳይሆን የደስታው ተካፋይ እንድንሆን አድርጎናል::
እነዚህ ወገኖች በሰላሙ ጊዜ በዓሉን እንደሚያከብሩት ቤታቸውን ሙሉ አድርገው ባይሆንም፤ ስለበዓሉ ማሰባቸው በራሱ ለነርሱ ትልቅ ዋጋ አለው:: ከጉዳታቸው ለማገገም ገና ብዙ ድጋፍና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው እንደሆነ ቢታወቅም፤ እነርሱ ግን እንዳቅማቸው በዓሉን ለመዋል ተንቀሳቅሰዋል:: ምክንያቱም ለእነሱ ወጥቶ መሸመቱ ብቻ ሳይሆን የሚሸምቱትን ማግኘት እና ቢያንስ በተነጻጻሪነት መግዛት በሚችሉት ዋጋ ማግኘታቸው በራሱ ትልቅ ተስፋ ነው:: ለምን ቢባል፣ በችግሩ ጊዜ ከቤት ወጥቶ ለመገበያየት ቀርቶ የገበያው ዋጋም ከአብዛኛው ማህበረሰብ አቅም በላይ እንደነበር መናገሩ ለቀባሪው አረዱት ይሆንብኛል::
ዛሬ ግን ለሰላም በተከፈለው ዋጋ የሰላም ስምምነት ተፈርሞ የሰላም አየር መንፈስ ጀምሯል:: ሰላሙን የበለጠ ለማጽናትም በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አፈጉባኤ የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች የተካተቱበት የልዑካን ቡድን መቀሌ ላይ ተገኝቶ ከሕወሓት መሪዎች ጋር ሰላማዊ ንግግር አድርገዋል:: ይሄም ቀድሞ የተጀመረውን የሰብዓዊ ድጋፍ፣ የመልሶ ግንባታና የአገልግሎት ማስጀመር ተግባራትን የበለጠ ለማሳለጥ እድል ሰጥቷል::
በዚህ መልኩ የሰብዓዊ ድጋፉ መቀጠሉ፣ የወደሙ መሰረተ ልማቶች በፍጥነት እየተጠገኑና እየተደራጁ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉ፤ የባንክ፣ የስልክ፣ የመብራትና የትራንስፖርት አገልግሎቶች መጀመራቸው፤ የአየር በረራ ዳግም መጀመሩ፣… የነበረው እንቅስቃሴ በአካባቢው ማህበረሰቡ ላይ የተፈጠረው ስሜት ከፍ ያለ ሆኗል:: ምክንያቱም የተራራቀ ተገናኝቷል፤ የተነፋፈቀ ተቃቅፏል፤ የተራበ የሚበላው አግኝቷል፤ የታመመ የሚታከምበት እድል ተፈጥሮለታል፤… ሁሉም ወደነበረበት እየተመለሰ መሆኑ በሁሉም ላይ ከፍ ያለ ደስታን ፈጥሯል::
በኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያውን የትራንስፖርት አገልግሎት አግኝተው ወደ ቤተሰቦቻቸው የሄዱ መንገደኞች ከደስታቸው ብዛት መሬት ሲስሙ የነበረበት አጋጣሚም ልብን የሚነካ ነበር:: ወደኋላ መለስ ብለን ታሪክ እንድናስታውስ አድርጎናል:: ሰላም በፈጠረው ምቹ ድባብ የተራራቁ ሲገናኙ፣ የተነፋፈቁ ተቃቅፈው በእንባ የታጠቡ ቤተሰቦችን ማየት፣የተጠፋፉ ወላጆችና ልጆችን ሲገናኙ የነበረው ስሜት እንኳን በችግሩ ላለፉት ሩቅ ለሆኑትም እንዴት ስሜት የነካ ነበር::
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከሁለት ዓመት በላይ የዘለቀው ጦርነትም ወደ ሰላም ሲቀየር፣ ምንም እንኳን ጦርነቱ አሳዛኝ የሆኑ ክስተቶችን ጥሎ ያለፈ ቢሆንም፤ ያለፈው ጉዳት በደስታ ተተክቶ ደግሞ ሰዎች ጭንቅ ከሆነ ነገር ውስጥ በመውጣታቸው ሀሴት ሀሴትን አድርገዋል:: በወቅቱ የነበረውን ስሜት ማህበራዊ ድረገጽን ጨምሮ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃኖች አጋርተዋል:: በእነዚህ የመረጃ ማሰራጫዎች ቀርበው የሰዎችን ልብ ከነኩት መካከልም ቤተሰቦችዋ በአንድ መንፈሳዊ ዝግጅት ላይ ተሰባስበው እየበሉና እየጠጡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሳፍራ ድንገት ቤተሰቦችዋ መካከል ከነልጇ ስትገኝ ወላጆችዋ ልጃቸውን ሲያዩዋት የነበረው የደስታ አገላለጽ ልዩ ነበር:: ደስታም ያሰክራል የሚለውን አባባል እንዲቀበሉ የሚያደርግ ነበር ስሜቱ::
እንዲህ ለአብነት አነሳሁላችሁ እንጂ በመገናኛ ብዙሃኑ ዐይን ያልገቡ ብዙ አጋጣሚዎች ይኖራሉ:: ለሰላም ስምምነቱ ማህበረሰቡ ብቻ ሳይሆን በሕወሓት አመራሮች በኩልም የታየው በጎነት ለሰላም የተሰጠውን ዋጋ ያረጋግጣል:: ለህዝብ ደህንነት፣ የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነትና የመሠረተ ልማት ተጠቃሚነት ላይ የታየው መቆርቆር ሌላው ሰላምን አጥብቆ የመፈለግ ማሳያ ነው:: ሰላም በአፍ ከሚነገረውም በላይ እንደሆነ ያየናቸው ክስተቶች በሙሉ ማረጋገጫ ነው::
ሆኖም የነበረውን ችግር በወጉ የሚገነዘበው በውስጡ ያለፈ ብቻ ነው:: እናም አሁን ላይ የተፈጠረውን ሰላም መነሻ በማድረግ እና በቀናነት ካለመቀበል በመነጨ እንዲህ ነው እንዲያ ነው በማለት ወደኋላ ለመመለስ ለሚደረጉ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ጆሮ መስጠት አያስፈልግም:: አንዴ የተገኘውን ሰላም አጥብቆ መያዝ ያስፈልጋል:: ምንም እንኳን ድርሻው የመንግሥት ነው የሚለው ጎልቶ የሚነገር ቢሆንም ከመንደር እስከ ከፍተኛው እርከን ያለው ማህበረሰብም ያገባኛል በማለት የፖለቲካ ነጋዴዎችን ከመካከሉ ማውጣት ይጠበቅበታል፡
ምክንያቱም እነዚህ የፖሊቲካ ነጋዴዎች የሰው ህይወት አየቀጠፉና ንብረት እያወደሙ እስከመቼ ነው? ብሎ መጠየቅና በቃ ማለት ይገባል:: ኢትዮጵያም ቀና ብላ ከሌላው ዓለም ጎን መሰለፍ የምትችለው የውስጥ ሰላሟን አስጠብቃ፣ በኢኮኖሚ አቅሟን ለመገንባት የሚያስችላትን የልማት ሥራ አጠናክራ ስትቀጥል ነው:: ይህን ማሳካት የሚቻለው ደግሞ ህዝቦችዋ በተባበረ ክንድ መሥራት ሲችሉ እንደሆነም መዘንጋት የለበትም::
ያሳለፍነው ጦርነት ደስታን በሚፈጥረው፣ በእነዚህና ሌሎችም በሚገለጹ ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጫናና ምስቅልቅሎሽ ውስጥ ያሳለፈን፤ በአንድ በሚያሰባስበውና አብሮነትንም በሚያጠናክረው መንፈሳዊና ህዝባዊ በሆኑ በዓላት ላይም ጭምር አሉታዊ ተጽእኖ ያሳረፈ ነው:: አሁን ግን በተፈጠረው ሰላም የማህበረሰቡ አብሮነት እንደቀደመው ሁሉ ሊጠናከር እንጂ መልካም የሆነውን እሴቱን ሊያጣበት አይገባም:: በተከፈለው የሰላም ዋጋ ማህበራዊ መሰረቶቻችንንም፤ የበዓሉን ድባብም መልሶልናል ይሄንኑ ማጠናከር የተገባ ነው::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ጥር 6/ 2015 ዓ.ም