ሁሌ ከእንቅልፌ የሚቀሰቅሰኝ የአያቴ ሰላላ ድምጽ ነው። ‹ማሞ..አንተ ማሞ? ትለኛለች..ካልጠፋ ስም ማሞን መርጣ። አያቴ ሳትጠራኝ ውላ አታውቅም..ቀኑ የሚመሸው እየጠራችኝ ነው፡፡
ማሞ አያቴ ያወጣችልኝ ስም ነው።ምን ማለት እንደሆነ ዛሬም አልደረስኩበትም። ከመዝገብ ስሜ ውጭ በአያቴ የወጡልኝ ሶስት የቤት ስሞች አሉኝ። ለሁለቱ ባዳ ነኝ..መች ጠርታኝ መች አቤት እንዳልኳት አላስታውስም። ቤት እንግዳ ሲመጣ ወይም ደግሞ ከሰው ጋር እያወራች በወሬዋ መሀል እኔ ካለሁ ነው እነዛን ስሞች የምትጠቀማቸው። አያቴ ማሞ ስትለኝ ትልቅ የሆንኩ ነው የሚመስለኝ። ከትልቅም አያትና ቅድመ አያት የሆንኩ ነው የሚመስለኝ። አርጅቼና ገርጅፌ በትንሹ እኔ ውስጥ ግዙፉን ሌላ ሰው አየዋለሁ። በዚህም ማሞ ስትለኝ አልወድም። አያቴ ስም ማውጣት ላይ ጎበዝ ናት።ሁሉም የልጅ ልጆቿ አያቴ ባወጣችላቸው ስም የሚጠሩ ናቸው። ግን ላንዳችንም የሚወደድ ስም አውጥታልን አታውቅም። አንዳንዴ በማይወደድ ስም ብትወዳደር ሻምፒዮን ትሆን ነበር እላለሁ። እኔን ማሞ እንዳለችኝ ሁሉ..ሌሎቹንም በሁለት ፊደልና አፍ ላይ በሚጎረብጡ ፊደላት የምትጠራን ነች።ማሞ እንኳንም ትምህርት ቤቴ ስም አልሆነ እንጂ ቢሆን ኖሮ አያቴን ስሜ በተጠራ ቁጥር የምቀየማት ሴት ትሆን ነበር።እንኳንም ቤት ውስጥ ቀረ። እንኳንም የውጭ ስሜ አልሆነ።አሁን ማሞ ምኑ ይወደዳል?
ከሁሉም የሚያስቀኝ የታናሽ እህቴ ስም ነው። ‹መሽኒያሽ ወርቅ..አያቴ ነች ያወጣችላት። እንኳን የውጭ ሰው እኔ ወንድሟ እንኳን በዚህ ስም ስጠራት አፍራለሁ። ቤተሰቡ ላይ ማዕቀብ ጥላ ከአያቴ በስተቀር ማንም አይጠራትም። ቤትም ሆነ ውጭ ከሰው ጋር የምትጣላው በዚህ ስሟ ሲጠሯት ነው። እህቴ ትክክለኛ ስሟ አደይ ነው። አባቴ ነው ያወጣላት። መስከረም መሀል ላይ የደመራ ሰሞን ነው የተወለደችው።አያቴ ‹መሽኚያሽ ወርቅ› ያለቻትም ከቁንጅናዋ ተነስታ እንደሆነ ስታወራ ሰምተናል። ቤት ውስጥ ያቺን መሳይ ቆንጆ ልጅ ‹መሽኚያሽ ወርቅ› መባሏ ከአያቴ ውጭ ማንም አልተዋጠለትም። አያቴ ስም ስታወጣ ለራሷ እንዲመቻት እንጂ ለሌላው ግድ የላትም፡፡
አይኔን እያሻሸሁ ወደ ደጅ ወጣሁ።ለምስራቅ ጣይ ጎኗን ሰጥታ አያቴን ደጅ ላይ አገኘኋት።የእኔና የአያቴ ታሪክ ሁሌም አንድ አይነት ነው። በሰላላ ድምጽዋ ተቀስቅሼ አይኔን እያሻሸሁ ወዳለችበት ስሄድ እንዲህ እንደ አሁኑ ለምስራቅ ጣይ ጎኗን ሰጥታ ነው የማገኛት።አያቴን የምቀየማት..በአንድ ነገር ነው። እሱም ያለምክንያት ስትጠራኝ ነው። እኔ ካልነቃሁ የነጋ አይመስላትም፡ እኔ ጎኗ ካልቆምኩ ደስ አይላትም።ለዛም ለሆነው ላልሆነው ትጠራኛለች፡፡
‹ምነው? ስላት..ምነው ተኝተህ ዋልክሳ..ከነጋ ቆየ እኮ› ትለኛለች፡፡
‹ምነው? ስላት ‹አይ እንዲያው ነው..መንጋቱን ከረሳኸው ላስታውስህ ብዬ ነው› ትለኛለች፡፡
‹ምነው? ስላት ‹ብቻዬን እንዴት ልሁን ብዬ› ነው ትለኛለች፡፡
የጠዋት እንቅልፍ እወዳለሁ..ሕይወትን ከማመሰግን ባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የጠዋት እንቅልፍ ነው። ሕይወት ያለጠዋት አትጥመኝም። ውበቷ፣ ድምቀቷ በማለዳ እንቅልፍ ውስጥ ነው የሚታየኝ። በማለዳ ለሽ ማለት ሕይወት የሚጀመርበት የመኖር አልፋ ነው እላለሁ። በዚህ ጣፍጦኝ በተኛሁት የጠዋት እንቅልፌ ውስጥ ነው የአያቴ ሰላላ ድምጽ የሚሰነቀርብኝ። ፈልጋኝ..አስፈልጌያት ብትጠራኝ እኮ ችግር የለውም..ግን እሄዳለሁ..ጠርታኝ ቀርቼ አላውቅም፡፡
‹አቤት? እላለሁ እንደሁልጊዜዬ እንቅልፍ ያልጠገቡ አይኖቼን እያሻሸሁ..ባልነቃና በደበተው ሁለት ድምጽ፡፡
‹ና እስኪ ዶሮ ላባ አምጣልኝ?
‹ለምንሽ?
‹ጆሮዬን ልኮረኩርበት› ትለኛለች።ከአያቴ ትዕዛዞች ውስጥ አብዛኞቹ የዶሮ ላባ ትዕዛዞች ናቸው።ጠርታኝ ዶሮ ላባ አምጣልኝ ሳትለኝ የቀረችበትን ጊዜ አላስታውሰ ውም። ልጅነቴ ያለቀው ለእሷ ጆሮ መኮርኮሪያ ዶሮ ላባ ሳመላልስ ነው፡፡
ትዕዛዟን ተቀብዬ ዶሮ ላባ ፍለጋ እኳትናለሁ። ግቢው ውስጥ ዶሮ ላባ ሳጣ ትልቁ የግራር ዛፍ ላይ ከሚሰፍሩት አሞራና ጉጉቶች ላባ ልፈልግ ወደዛ እሄዳለሁ። ብዙ አይነት መልክ ያላቸውን ብዙ ላባዎች ሰባስቤ ወደ አያቴ እመለሳለሁ። በላባዎቹ ውበት የአያቴን መደነቅ እያሰብኩ፣ በላባዎቹ ቀለም የአያቴን ምላሽ እያሰብኩ ወዳለችበት አዘግማለሁ፡፡
‹ምነው የውሀ ሽታ ሆንክሳ? አለችኝ ላባውን ልትቀበለኝ እጇን እየዘረጋችልኝ። አያቴ ልካኝ እንዲህ ሳትለኝ ቀርታ አታውቅም።ከታዘዝኩበት ስመለስ በዚህ ንግግሯ ነው የምትቀበለኝ፡፡
ላባዎቹን አገላብጣ ካየች በኋላ ‹አይ ያንተ ነገር! ዶሮ ላባ አልኩህ እንጂ የወፍ ላባ አምጣልኝ አልኩ? ይሄ ምኑ ሊረባኝ? ስትል የተቀየመ ፊት አስታቀፈችኝ። እንዳሰብኩት በላባዎቹ ውበት የአያቴን መደነቅ አላየሁም። እንዳሰብኩት በላባዎቹ ቀለም የአያቴን አግራሞት አላስተናገድኩም። አንዳንድ ነገሮች ለሁላችንም እኩል ውበት፣ እኩል ዋጋ የላቸውም። እኔን ያስፈነደቁኝ ላባዎች በአያቴ ፊት ምንም ሆነው አገኘኋቸው፡፡
ባለቀለም ላባዎቹን ተቀብዬ የምትፈልገውን አይነት ላባ ላመጣላት ከአጠገቧ እሸሻለሁ።ካለችበት ራቅ ብዬ በአይኖቼ ወዲያ ወዲህ ስል እያየችኝ ‹አሁን ዶሮ ላባ አጥተህ ነው..ሜዳው ሁሉ ዶሮ ላባ አይደል? ትለኛለች። ለአያቴ ሁሉም ነገር ቀላል ነው። ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ ነው የሚለው አባባል አያቴ ጋ ነው ቅልብጭ ብሎ የማገኘው፡፡
አፏ አያርፍም..
‹እስኪ ግድግዳው ላይ ፈለግ አድርገው፣ ለፋሲካ የታረዱት ዶሮዎች ላባቸው የት ይሄድና› አለችኝ ወደ ግድግዳው በአጋጭዋ እየጠቆመችኝ፡፡
‹ለፋሲካ የታረዱት ዶሮዎች? አልኩ በውስጤ..ከምጸት ሳቅ ጋር። ድምጽ አውጥቼ አያቴ ብትሰማኝ ደስ ባለኝ ነበር። አያቴ ነገር ታገናኛለች..ለፋሲካ እኛ ቤት ከአንድ በላይ ዶሮ ታርዶ አያውቅም።ራቅ ብላ በጠራራ ጸሀይ የጠላ ብቅል የምታሰጣውን ጎረቤታችንን መልካምን ለማስቀናት ብላ እንደተናገረች አላጣሁትም። ደግነቱ የአያቴ ድምጽ ስለማይሰማ ለመልካም ጆሮ አልደረሳትም። አያቴ ወዳለችኝ ቦታ ስሄድ ብዙ የዶሮ ላባ ግድግዳው ላይ ተሸጦ አገኘሁ። አንድ አራት መዝዤላት ተመለስኩ። ጎሽ ተባረክ ትላለች ብዬ ስጠብቅ ‹ይሄ ሁሉ ምን ይሰራልኛል..አንድ ይበቃኛል? ስትል ከታቀፍኩት ላባ መሀል አንድ መዛ ወሰደች። ነጭ ስለምትወድ ነጯን መርጣ..
ፊቷ እንደቆምኩ የዶሮውን ላባ በእጇ ፍቃ እንደ መጥረጊያ ጫፉ ላይ ጎፈሬ አበጅታ፣ ግራ መዳፏ ላይ ምራቋን ተፍታ የዶሮውን ላባ ምራቋ ላይ አንደባለለችው። ከዛም ወደበላት ቀኝ ጆሮዋ ላባውን ሰደደችው። በሌባ ጣቷና በአውራ ጣቷ ላባውን እያሽከረከረች..ጆሮዋ ውስጥ ታንደባልለው ጀመር። በዚህ ሁናቴ የአያቴ አይኖች በስሜት በትንሹ ተጨፈኑ፡፡
ከፊቷ ላይ ሳልሄድ ጆሮዋን ያከከችበትን ላባ አውጥታ ጆሮ ግንዷ ላይ ሰቀለችው። ከብዙ ሰዓት በኋላ ወዳለችበት ስመጣ አይኗን በስሱ ጨፍና ሌላኛውን ጆሮዋን ስትኮረኩር ደረስኩባት፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 5 ቀን 2015 ዓ.ም