ክልሉ በማእድን ሀብቱ ይታወቃል። ወርቅ፣ እብነ በረድና የድንጋይ ከሰል በስፋት እንደሚገኙበትም መረጃዎች ያመለክታሉ። በወርቅ ማእድን ልማቱ ግን ይበልጥ ይታወቃል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ባለፈው 2014 በጀት አመት ብቻ 22 ኩንታል ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ገቢ አድርጓል፤ 22 ኩንታል ወርቅ ነው ያልኩት። የተመረተው ደግሞ በዘመናዊ መንገድ አይደለም፤ በባህላዊ መንገድ፤ በአነስተኛ አምራቾች። በዚህ በጀት አመትም 34 ኩንታል ወርቅ በማምረት ለብሔራዊ ባንክ ለማስገባት አቅዷል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል።
የክልሉ ማእድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ካሚል ሀመድ እንደሚሉትም፤ ክልሉ በማእድን ሀብት የታደለ ነው፤ ከእነዚህም መካከል ወርቅ፣ ድንጋይ ከሰልና እብነ በረድ ይጠቀሳሉ። በክልሉ ወርቅ በዋናነት እየለማ ሲሆን፣ በአነስተኛ አምራቾች የሚከናወነው ይህ የወርቅ ልማት ስራ በኋላ ቀር መሳሪያዎች ሲካሄድ ነው የቆየው።
ባህላዊ የወርቅ ማምረት ስራው በክልሉ ለስራ እድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። በክልሉ በወርቅ ማምረት ስራ ላይ ከ400 /ከአራት መቶ/ ማህበራት በላይ ተሰማርተዋል። ሌሎች በርካቶችም በማህበር ተደራጅተው ለማምረት በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ላይ ናቸው ሲሉ ኃላፊው ይናገራሉ። ‹‹የክልሉ የወርቅ ሀብቱ በጥናት ተለይቶ አይታወቅም፤ እኛ ትንሽ ነው የለየነው፤ በተለምዶ ነው ቦታዎቹ እየተለዩት፤ በእጃችን እዚህ ወረዳ እዚህ አካባቢ ላይ ወርቅ ይመረት ነበር፤ ወርቅ አለ የሚል መረጃ ብቻ ነው ያለን ይላሉ።
የወርቅ አመራረቱን ለማዘመን እየተሞከረ መሆኑንም ኃላፊው ይገልጻሉ፤ ‹‹እኛም አመራረቱ እንዲዘመን እየሞከርን ነው፤ አምራቾቹም አመራረቱን ለማዘመን የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ናቸው›› ሲሉ ገልጸዋል። አብዛኞቹ አምራቾች ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ እንፈልጋለን፤ ኬሚካል የሚጠቀሙ መሳሪያዎች ጉዳት እንዳያስከትሉ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን ደግሞ ከኬሚካል ነጻ የሆኑ መሳሪያዎች እየመጡ ናቸው፤ እሱን ማስተዋወቅ ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በአነስተኛ አምራቾች እየተካሄደ ያለው የወርቅ ልማት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰነ መልኩም ቢሆን በተሻሻሉ መሳሪያዎች መካሄድ ጀምሯል፤ በዚህም የአልሚዎቹን ጉልበትና የጊዜ ብክነት መቀነስ እንዲሁም በሚገኘው ምርት ላይ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት እየተቻለ ነው። ሁሉም በእዚያ ልክ እንዲመጣ እየታሰበ ነው። በስልጠና በኩልም እየተሰራ ነው። በጥናት በኩልም ኩባንያዎች ዝም ብለው አይደለም ወደ ስራ የሚገቡት ፤ ጥናት አድርገው ነው፤ ክልሉም ቦታዎችን በጥናት መለየት ይኖርበታል።
በክልሉ የወርቅ ልማት አሁንም ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ያልገቡት ኩባንያዎች መሆናቸውን አቶ ካሚል ጠቅሰው፣ በቅርቡ የማእድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ በኩርሙክ ወረዳ በወርቅ ልማት የተሰማራ አንድ ትልቅ ኩባንያን እንቅስቃሴ ለመመልከት በስፍራው ተገኝተው እንደነበርም ይገልጻሉ። ኩባንያው ቦታ ወስዶ ወደ ስራ መግባት ሳይችል መቆየቱን አመልክተው፣ ስራ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንዲገባ በአካባቢው ያሉትን የተወሰኑ ግለሰቦች ማስወጣት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
ኩባንያው ለወርቅ ልማቱ ይዞ የሚመጣው የማምረቻ መሳሪያ ከሌሎች በዘመናዊ መንገድ ወርቅ ከሚያመርቱ ኩባንያዎችም የተለየ መሆኑን ነው ያመለከቱት። ብዙ ኬሚካሎችን እንዲሁም ድማሚት ሊጠቀም እንደሚችል ጠቁመው፣ በዚህም ሰዎች ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችልና ኩባንያው ስራ ውስጥ ቀጥታ እንዲገባ በአካባቢው ያሉ ሰዎች ከአካባቢው መውጣት እንዳለባቸው መጠቆሙን ተናግረዋል።
በክልሉ ያለውን እምቅ የወርቅ አቅም ለመጠቀም የሚያስችል አቅም ያለው ኩባንያ መሆኑን ጠቅሰው፣ እንደ ክልል እኛም የወርቅ ልማቱን አካባቢ ነጻ እናደርጋለን ብለን እናስባለን፤ በዚህ በኩል የሚጠበቅብንን ሁሉ ድጋፍ እያደረግን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በክልሉ ሜድሮክ ኩባንያም የተለያዩ ማእድን በማልማት ላይ መሆኑን ተናግረው፣ ኩባንያው በመተከል ዞን በእብነበረድ ልማት በአሶሳ ዞን ላይ ደግሞ በወርቅ ማምረት ስራ ላይ መሰማራቱን ጠቅሰዋል። በአሶሳ ዞን የማስፋፊያ ቦታ ጠይቆ እንደተሰጠውም ገልጸዋል።
የማእድን ሀብቱ ለክልሉ ህዝብ የስራ እድል በመፍጠር ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ለወርቅ ልማቱ እኛም ትኩረት ሰጥተን ድጋፍ እያደረግን እንገኛለን ይላሉ። ኃላፊው በክልሉ አብዛኛው ወርቅ የማምረት ስራ እየተከናወነ ያለው በባህላዊ መንገድ በልዩ አነስተኛ ወርቅ አምራች ማህበራት መሆኑን አመልክተዋል።
ክልሉ ከሚያስተዳድረው ማእድን ሀብት ስፋት አኳያ ቀደም ሲል በኤጀንሲ ደረጃ የነበረው የማእድን ልማት ስራ ወደ ቢሮ እንዲያድግ መደረጉን ተናግረዋል። ይህ በመሆኑም አመራሩ ከአንድ አመራር ወደ ሁለት አመራር እንዲያድግ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ብለዋል።
ብሔራዊ ባንክ ለወርቅ አምራቾች ከዓለም ገበያው የ35 በመቶ ጭማሬ በማድረግ ወርቅ ለመረከብ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ይታወቃል። ይህም ተደርጎ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ባንኩ በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል። ይህን ችግር ለመፍታትም በወርቅ አምራች ክልሎች ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ህገወጥ ግብይቱን የመቆጣጠር ስራ እየተሰራ ይገኛል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማእድን ልማት ቢሮ ኃላፊ እንዳሉትም የወርቅ ግብይቱ በኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ፈተና ውስጥ ገብቷል።
ብሔራዊ ባንክ ከዓለም የወርቅ ዋጋ ሲነጻጸር 35በመቶ ጭማሪ ማድረጉን የጠቀሱት ኃላፊው፣ የጥቁር ገበያው ደግሞ ከዚህ ጨምሮ ዋጋ እየሰጠ ነው ይላሉ። በጥቁር ገበያው ላይ ጠንካራ ቁጥጥርና እርምጃ መውስድ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
በማእድን ዘርፍ ላይ ጥሩ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ወርቅ ላይ እንደ ክልልም እንደ ሀገርም የኮንትሮባንድ ንግድ ትልቅ ፈተና መሆኑን አስታውቀዋል። ‹‹እኛም ይህን ህገወጥ ድርጊት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ግብረ ሀይል አቋቁመን ስንሰራ ቆይተናል፤ ውጤቱ ግን እኛ በምንፈለግው ልክ አልጋ ባልጋ እየሆነ አይደለም ሲሉ ጠቁመዋል።
ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ በማስገባት በኩል በኮንትሮባንድ ንግድ የተነሳ ችግር ገጥሞን ቆይቷል ሲሉ ጠቅሰው፣ የሚመረተውና ለብሔራዊ ባንክ ገቢ የሚደረገው ወርቅ መጠን ሰፊ ልዩነት እንዳለው አስታውቀዋል። በክልሉ ወርቅ በብዛት እንደሚመረት ገልጸው፣ እዚህ የሚታየው ቅናሽ ነው ብሔራዊ ባንክ ላይ በከፍተኛ ደረጃ ቅናሽ እንዲታይ እያደረገ ያለው ሲሉም አስታውቀዋል።
አቶ ካሚል እንዳሉት፤ በኮንትሮባንድ ንግድ ሳቢያ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን በጣም ቀንሷል። ቀደም ሲል በሳምንት አልገባም ከተባለ ሰኞ ሰኞ ብቻ 10 ኪሎ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ይደረግ ነበር። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ደግሞ ከ20 እስከ ሰላሳ ኪሎ ግራም ይገባ ነበር። ይህ መጠን አንዳንዴ 40 ኪሎ ግራምም ይደርስም ነበር። አሁን ግን ሰኞ ብቻ አስር ኪሎ ይገባ የነበረው ወርቅ ወደ ሁለት ኪሎና ሶስት ኪሎ ወርዷል። በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ አንድ ኪሎ የገባበት ጊዜም አለ።
ኃላፊው ክልሉ በተያዘው 2015 በጀት አመትም 34 ኩንታል ወርቅ ለማምረት ማቅዱን ጠቁመው፣ በዚህ ስድስት ወር ወደ 18 ኩንታል ወርቅ ለማምረት ታቅዶ እንደነበርም አስታውሰዋል። በዚህ ስድስት ወር ወደ ሶስት መቶ ኪሎ ግራም ነው ያገኘነው ይላሉ። ይህም በጣም ትንሽ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
በክልሉ በጣም ብዙ ወርቅ ይመረታል፤ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው ግን እየቀነሰ ነው፤ ለእዚህ ትልቁ ችግር ጥቁር ገበያ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ድርጊቱ የሚፈጸመው በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ችግር ለመፍጠር ሆን ተብሎም ሊሆን እንደሚችል ነው ያመለከቱት።
‹‹እኛ በአካባቢያችን የሚመረተው ወርቅ ሀገር ሊገነባ በሚችል መልኩ መገበያየት አለበት ብለን አቋም ይዘን እየሰራን ነው፤ የሚያስፈልገውን ጥበቃና ቁጥጥር ለማድረግ፣ እርምጃም ለመውሰድ ዝግጅት ተደርጓል ሲሉ ነው ኃላፊው የገለጹት። የኮንትሮባንድ መቆጣጠር ግብረ ሀይል በተለይ በወርቅ ላይ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ኃላፊው እንዳሉት፤ ወርቅ የሀገር ሀብት ነው፤ ማንም እንደፈለገው ብቻውን የሚያድግበት አይደለም፤ ወርቅ ለእኛ አካባቢ ደግሞ ዶላር ማለት ነው። በደንብ ካልሰራንበት ሌላ ችግርም ያስከትላል። ‹‹ቁጥጥር የሚያደርግ ግብረ ሀይል እንደ ክልልም አለ። ከፌዴራል አካልም ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው። በዚያ ልክ ግን ለውጥ ሊመጣ አልቻለም።
ህገወጥ ግብይቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በግብረ ሀይል ሁሌም እንደሚሰራ ተናግረው፣ ውጤት ያልመጣው ግን በሁለት ምክንያት ነው ይላሉ። ከወርቅ አዘዋዋሪ ነጋዴዎች ጋር በእዚህ ችግር ላይ ውይይት መደረጉንም ተናግረዋል። ‹‹ወርቅ በየትኛውም ስፍራ ግብይት ሊፈጸምበት የሚችል ነው። በየሞባይል ቤቱ፣ ሆቴል ቤቱ ወዘተ ሁሉ ይሸጣል፤፡ ማንኛውም ቦታ የምትገለገልበት ቦታ ሁሉ ሄደህ ልትሸጠው የምትችል በመሆኑ የቁጥጥር ስራውን ፈትኖታል ያሉት ኃላፊው፣ ይህን ችግር ለመፍታት የተወሰኑ መነሻዎችን ይዘን ቁጥጥር እያደረገን ነው ይላሉ።
ህጋዊ ወርቅ አዘዋዋሪዎች ህገወጦችን የሚያሰማሩበት ሁኔታም እንዳለም ነው ኃላፊው ያመለከቱት። እነዚህ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ፣ ህጋዊ ነጋዴዎችም በእኛ ፈቃድ ህገወጥ ተግባር መሰራት የለበትም የሚል አቋሙ እንዲይዙ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል። እዚሀ ላይ እርምጃ መውሰድ ይገባል፤ ያልተገባ ትርፍ አገኛለሁ በሚል ህገወጦችን በወርቅ ግብይት ውስጥ ማሰማራት ተገቢ አይደለም ብለዋል።
አየር መንገድ ላይም ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባም አስታውቀው፣ ባለን መረጃ መሰረት የወርቅ ማዘዋወሩ በሀገር ውስጥ ብቻ የሚፈጸም አይደለም፤ ውጭ ሀገር ድረስ ይዘልቃል ሲሉም አመልክተዋል።
እኛም ህገወጥ እና ህጋዊውን ነጋዴ መለየት ላይ ችግር እንዳለ ተረድተናል ሲሉም ጠቅሰው፤ ህገወጦች እንደፈለጉ የሆኑት በቁጥጥራችን መላላት ነው ብለን አይተናል ሲሉም ገልጸው፣ በደንብ ከተቆጣጠርን ህገወጡ ወደ ህጋዊነት የማይመጣበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር አስታውቀዋል።
የማእድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በቅርቡ በክልሉ የተገኙት አንድም ይህን ህገወጥ ተግባር መቆጣጠር በሚችልበት ሁኔታ ላይ በመነጋገር አቅም ለመፍጠር እንደነበር ኃላፊው አስታውሰው፣ ‹‹እኛም በዚህ ልክ እየሰራን ማገዝ ያለብንን ያህል እያገዝን የተመረው ወርቅ ለሀገር በሚጠቅም መልኩ ስራ ላይ መዋል አለበት በሚል አቋም እየሰራን ነው›› ብለዋል።
የወርቅ ግብይትን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ከመሆኑ አኳያ የሚያመልጡ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ ያሉት ኃላፊው፣ ይህን ችግር ለመፍታት ሁሉም ዜጋ /በማምረቱም ሆነ በግብይቱ የተሰማራም ያልተሰማራም/ የኮንትሮባንድ ንግዱን በመከላከልና በመቆጣጠሩ ስራ መሳተፍ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የነበረው የጸጥታ ችግር ተፈትቶ አንጻራዊ ሰላም መጥቷል፤ የገንዘብ እንቅስቃሴም በስፋት እየታየ ነው። ሰላም ካለ ሁሉም ገብቶ እንዲሰራ እንፈልጋለን ያሉት ኃላፊው፣ ሁሉም ግን ስርአት ይዘው እንዲሰሩ እንፈለጋለን፤ ከዚህ በኋላ ሁላችንም ቁርጠኝነት ወስደናል፤ በግብረ ሀይል ብቻ ሳይሆን ኬላዎች አካባቢ የሚሰራ አሻጥር ካለም መቆጣጠር ያስፈልጋል ብለዋል።
ኮንትሮባንዶችን መቆጣጠር ከቻልን እቅዳችንን ማሳካት እንችላለን ሲሉም አመልክተው፣ ወርቅ ስላልተመረተ አይደለም ዝቅተኛ አፈጻጸም የተፈጸመው፤ በኮንትሮባንድ ንግዱ ሳቢያ ነው ብለዋል።
እኛ የለየናቸው በመንግስት በኩል መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች አሉ። ኮንትሮባንዲስቶችን መቆጣጠር እንዲሁም በስራው ለተሰማሩ ሰዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር ከቻልን እቅዱን ማሳካት እንችላለን ብለዋል። በቂ ምርት አለ ፤ በተለይ ደግሞ ኩባንያዎች ላይ ትኩረት ካደረግን እቅዳችንን እናሳካለን ነው ያሉት።
ወርቅ በስራ እድል ፈጠራም በተለይ ኢኮኖሚን በማመንጨት፣ ለሀገር ትልቅ ድርሻ ያለው ስለመሆኑ በተለይ ከባለፈው በጀት አመት ጥሩ ትምህርት ወስደንበታል ሲሉ ኃላፊው ይናገራሉ። ‹‹የክምችት ልዩነት ካልሆነ በቀር፣ በእኛ ክልል ላይ ወርቅ የሌለበት ስፍራ የለም፤ ሁሉም ጋ አለ›› ሲሉ ኃላፊው ይጠቁማሉ፤ ቀደም ሲል በመተከልና ከማሼ ዞኖች ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ እንቅስቃሴዎች ተዳክመው እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን በአካባቢዎቹ ጥሩ ሁኔታዎች እንደሚታዩም ጠቁመዋል። ይህን አቅም ሁሉ ሰብሰብ አድርጎ በመጠቀም ክልሉ ለሀገር ጭምር የሚተርፍ ስራ ሊሰራ እንደሚችልም ነው ያመለከቱት።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ጥር 5 ቀን 2015 ዓ.ም