የሞባይል ስልክ ቴክኖሎጂ በየጊዜው ይቀያየራል። ቴክኖሎጂው በአሁኑ ወቅት ብዙ አገልግሎት የሚሰጥበት ሆኗል። ገብስ ገብሱን ብጠቅስ አንኳ በሬዲዮና ቴለቪዥን የሚገኙ መረጃዎችን በስልኩ ማግኘት ይቻላል።
ሰአት፣ የሂሳብ መሳሪያ እና የመሳሰሉት አገለግሎቶችም በሞባይል ስልክ ውስጥ ተቀምጠዋል። የባንክ ሂሳብ ይንቀሳቀስባቸዋል፤ የጤና ክትትል ይደረግባቸዋል፤ እረ ስንቱ። ዋጋቸው እየናረ ሆኖ እንጂ አገልግሎታቸውማ የትየለሌ ነው፤ ምን ገንዘብ ባይፈጅ ነው የተባለው።
ስልኮቹ ተፈላጊነቸው እየጨመረ በመምጣቱም በሌቦች ቀልብ ውስጥ በእጅጉ ወድቀዋል። የሞባይል ስልክ ንጥቂያ እና ስርቆት በእጅጉ ደርቷል። ዱሮ ወርቅ ከጠፋ አይገኝም ይባል ነበር፤ ዘንድሮ ደግሞ እንዲሁም ሞባይል ስልክ ቢባል በእጅጉ ያስኬዳል። የሞባይል ስልክ ጠፍቶበት የተገኘለት ጥቂት ነው ሊሆን የሚችለው።
የሞባይል ስልኮችን ደህንነት እና የደንበኞችን ሚስጢር ለመጠበቅ ሲባ ልም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ስራ ላይ እንዲውሉ እየተደረገ ነው። ባለቤቱ ብቻ እንዲከፍታቸው በሚል የማለፊያ ቃል ይዘጋጅላቸዋል፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአሻራ የሚከፈቱበት ስርዓት ተፈጥሯል። በፊት ምስል ላይ ተመስርተው የሚከፈቱም ስራ ላይ ውለዋል።
በዚያው ልክም ይህን ሁሉ ቴክኖሎጂ ማርከሻ ይዘው የሚመጡ ሌቦችም በር ክተዋል። ሰሞኑን በቻይና አንድ ሆቴል መኝታ ክፍል ውስጥ የታየውም ይሄው ነው። አገር አማን ብሎ ስልኩን ይዞ ጋደም ያለን ሰው ጉድ ለማድረግ ሌቦች የተጠቀሙበት ዜዴም ይህንኑ ያመለክታል።
በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን በሞባይል ስልኮች የሚፈጸም ወንጀልም እንዲሁ ተበራክቷል ያለው ሰሞኑን ለንባብ የበቃ የኤንዲቲ ዘገባ ግለሰቡ አገር አማን ብሎ በተኛበት ሆቴል መኝታ ክፍል ውስጥ ሌቦች ይገባሉ። ከዚያም ስልኩ በፊት ምስል የሚከፈት መሆኑን ከተረዱ በሁዋላ የተኛውን ሰው ፊት በመጠቀም ስልኩን ይከፍታሉ። ከዚያም አስር ሺ ዩዋን ከግለሰቡ የዊቻት የሒሳብ ቁጥር ወደራሳቸው የባንክ ሂሳብ ያዞሩና ምንም እንዳልተፈጠረ አርገው ወደ ስራቸው ይመለሳሉ።
ወንጀሉ የተፈጸመው በቻይና ኒንግቦ ከተማ ሲሆን፣ ግለሰቡ ገንዘቡ መወሰዱን ያወቀው በማግስቱ ነበር።ወዲያውኑም ለፖሊስ ያመ ለክታል። ፖሊስ ወንጀል ፈጻሚዎቹ ላይ ለመድረስ ብዙም አልተቸገረም። ግለሰቡ ያረፈበት ሆቴል ሰራተኞች የሆኑት ሊዩ እና ያንግ በጉዳዩ ተጠርጣሪ ሆነው ይገኛሉ።
ያልተለመደ የዘረፋ ድርጊት በመፈጸም ወንጀል ተጠርጥረውም በፖሊስ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የቻይናን ሲና የዜና አገልግልት ዋቢ ያደረገው የኤንዲቲ ዘገባ ያመለክታል። በየማለፊያ ቃሉ ያሰርናቸው የሞባይል ቀፎዎች ሲሰረቁ የሚታደገን ቴክኖሎጂና ፖሊስ እኛስ የምናገኘው መቼ ይሆን።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8/2011