ከየምግብ ቤቱ የሚወጣው ትርፍራፊ ምግብ በአራዶች ቋንቋ ቡሌ ይባላል። ቡሌ የተለያዩ ትራፊ የምግብ አይነቶች ተደባልቀው የሚገኙበት የእህል ስብስብ ሲሆን በጎዳና ተዳዳሪዎች ወይንም በየኔ ቢጤዎች ዘንድ ተወዳጅ ምግብ ነው። ቡሌ የማይዘው የምግብ ዘር የለም። ስጋ፤ ምስር፤ አተር፤ ድንች፤ ካሮት፤ ጎመን፤ ቀይ ወጥ፤ አልጫ ወጥ፤ ወዘተ ምድር ያፈራው ሁሉ ይገኝበታል።
ለወትሮው ከየምግብ ቤቱ በቀላሉ የሚገኘው ቡሌ ዛሬ ጥብስ እንደሆነ ተጠቃሚዎቹ ይናገራሉ። ቡሌን እንደቀድሞ ጊዜ ከየምግብ ቤቱ ለምኖ ማግኘት ዘበት ሆኗል ይላሉ ተጠቃሚዎቹ። ዛሬ ቡሌን ለማግኘት በቀላሉ ከ20 እስከ 30 ብር ማውጣት የግድ ብሏል።
‹‹ከዩኒቨርሲቲ ቀጥታ የሚወጣውን ቡሌ ስለማላገኘው እኔ የምገዛው ከሚያከፋፍሉት ላይ በእጅ ስፍር ነው›› ያለን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚወጣውን ትርፍራፊ ምግብ ሲጠብቅ ያገኘነው ህፃን ገላቲያ ማቲዎስ ነው። ህፃን ገላቲያ እንደነገረን የመጣው ከፈረንሳይ ጉራራ ኪዳነ ምህረት አካባቢ ነው። ቡሌውን እስከ አስር ብር ድረስ በእጅ ስፍር ነው የሚገዛው። ሆኖም ትንሽ ስለሆነች አያጠግበውም። ስለዚህም ለመጥገብ አራትና አምስት የእጅ ስፍር ያስፈልገዋል።
ተረፍ ያለ ገንዘብ ሲገኝ ለጠዋት ቁርሱና ለነገ ምሳው ገዝቶ በፌስታል ያሳድራል። ራቱን ከበላ በኋላ ወደ ፈረንሳይ በመመለስ ከጓደኞቹ ጋር ጎዳና ላይ ያድራል። አንዳንድ ጊዜ እንቅልፍ ጥሎት አርፍዶ ሲወጣ ስጋ ያለውን ቡሌ ተሸምተው ስለሚወስዱበት በባዶ የእንጀራ ፍትፍት ገዝቶ ለመመለስ ይገደዳል። ይህ እንዳይሆን ታዲያ ገላቲያ ጎህ ሳይቀድ ከእንቅልፉ ተነስቶ ቡሌ ለመግዛት ከተሰለፉት ቢጤዎቹ ጋር ይሰለፋል። በለስ ካልቀናውም ቀን 10 ሰዓት ላይ ድጋሚ በሚደምቀው የቡሌ ገበያ ለመሳተፍ ቀድሞ ይገኛል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ የሚወጣውን የተማሪዎች ትራፊ የሚመገበው ገላትያ ብቻ አይደለም። በቢል ጌት ድጋፍ ዩኒቨርሲቲው እያሰራ ባለው ግንባታ የሚሳተፉትን ጨምሮ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡና ወደ ሽሮ ሜዳ የሚጓዙ ጉልበት ሰራተኞችም ተመጋቢዎች ናቸው። ማታ ከ12 ሰዓት ጀምሮ አካባቢው ቡሌ ከዩኒቨርሲቲው መውጣትና አለመውጣቱን ከወዲያ ወዲህ ውር ውር በማለት የሚጠባበቁ ብዙ ናቸው።
በተለይ የጾም ቀናት ካልሆነ ያልቃል በሚል ስጋት 10 ሰዓት ቀደም ብለው በመምጣት የሚጠባበቁ ቁጥራቸው ብዙ ነው። ከተለያዩ ክልሎች ገና በጨቅላ እድሜያቸው ወደ አዲስ አበባ መጥተው ሚዛን የሚያከራዩ ህጻናትም የዕለት ምግባቸው ቡሌ እንደሆነ አንድ ህጻን አጫውቶኛል። ህጻኑ እንደሚለው ከተወለዱበት አካባቢ ወደ አዲስ አበባ ያመጧቸው አሰሪዎቻቸው ቀን የሰሩበትን ገንዘብ ከተረከቧቸው በኋላ ለህፃናቱ ገዝተው የሚሰጧቸው ራት ይሄንኑ በሁለት እጅ የሚሰፈር ቡሌ ነው።
ከዩኒቨርስቲው የሚወጣው ቡሌ ብዙ ፈላጊዎች አሉት። ሊስትሮን ጨምሮ ኪሱ ጎደል ያለና የእለት እንጀራ የጎደለበት ሁሉ ከቡሌ ይቋደሳል። ለእራት እጅ ባጠረበት አንዳንድ አላፊ አግዳሚም ይሸመታል። ቡሌ አይነቱ ብዙ በመሆኑና የተመጣጠነ የምግብ ይዘት ያለው በመሆኑ በብዙዎች ተመራጭ ምግብ ለመሆን በቅቷል። ይህንኑ ከሚያረጋገግጡት ውስጥ አቶ በዳሳ አለሙ አንዱ ናቸው።
አቶ በዳሳ እንደሚሉት ቡሌ ከስጋ እስከ ጎመን ድረስ የተመጣጠነ የምግብ ይዘት ያለው በመሆኑ ለጤና ተስማሚ ነው። ሆኖም አሁን በቀላሉ የሚገኝ ምግብ አይደለም። ቡሌ ድሮ ድሮ ከየሆቴሉ ለለመነ ሁሉ ይሰጥ እንደነበር አቶ በዳሳ ይናገራሉ። ዛሬ የሆቴል ቤቶች ይህንን የመረዳዳት ባህል ጥሰው ትራፊ ምግቦችን ሰብስበው መሸጥ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ለምኖ ሆዱን ይሞላ የነበረው ምስኪንም በሆቴል ቤቶቹ ጭካኔ ምክንያት ቡሌን ከገበያ ለመግዛት መገደዱንም አጫውተውናል። ‹‹በአሁኑ ወቅት ከጎዳና ተዳዳሪው መብዛትና ከየኔቢጤው መጨመር ጋር ተያይዞ ቡሌ ፈላጊው በዝቷል። እንዲያውም መንግስት የምገባ ማዕከላትን ባይከፍት ኖሮ ይሄ ሁሉ የጎዳና ተዳዳሪና የኔ ቢጤ ምን በልቶ እንደሚያድር ግራ ይገባል›› ሲሉ ሁኔታውን አቶ በዳሳ ይናገራሉ።
በዩኒቨርሲቲው አካባቢ ማርቆስ አቅራቢያ እንዲሁም ኤፍ ቢና አንበሳ ጊቢ አካባቢ ቡሌው ከሚከፋፈልባቸው ቦታዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ማርቆስ መታጠፊያ ባለው ፈርማታ በሊስትሮና በጀብሎ ሥራ የተሰማራው ወጣት ሱልጣኑ ሽፈራው ቡሌውን ከሚያከፋፍሉት አንዱ ነው። ሱልጣኑ ማከፋፈል ከጀመረ አንድ ዓመት ሆኖታል። በየቀኑ ከ10 እስከ 13 ማዳበሪያ እየተቀበለ ያከፋፍላል። ቡሌውን የሚያቀርቡለት ሦስት አቅመ ደካማ እናቶች ናቸው። እናቶቹ ቡሌውን ከዩኒቨርሲቲው እንደሚገኙ ሱልጣን አጫውቶናል።
እኛ እንዳስተዋልነውና ተጠቃሚዎች እንደነገሩን ሱልጣኑ ከሦስቱ አዛውንት አቅራቢዎቹ 15 ብር የተረከበውን 20 ብር በመሸጥ ይጠቀማል። ፈላጊ በማይኖርበት ጊዜ ደግሞ ቡሌውን በአቅራቢያው ባሉት የመድኃኒዓለምና የቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን በመውሰድ ለነዲያን እንደሚያከፋፍል ይናገራል። ግን እሱ መስራት በጀመረበት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ቡሌው ወሳጅ አጥቶ አያውቅም። እንዴውም ፈላጊው በዝቶ በማለቁ የሚቸገርበት ጊዜ ነው የሚበዛው።
ሱልጣን እንደሚለው ቡሌ ብዙዎችን ታድጓል። በአሁኑ ወቅት አንድ በያይነት ምግብ ገዝቶ ለመብላት ቢያንስ 50 ብር ያስፈልጋል። ቡሌን ግን በ20 ብር ሸምቶ ጠግቦ መዋል እንደሚቻል ሱልጣን ደረቱን ነፍቶ ይናገራል። ሆኖም ግን ሱልጣን በየመሃሉ መንግስት አቅመ ደካሞችን በየቀኑ ለማብላት እያደረገው ያለውን ጥረት በየንግግራችን መሃል ሲያመሰግን ይደመጣል። ሆኖም ነጋዴዎች መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት ካላገዙት እየጨመረ ከመጣው የህዝብ ቁጥርና ከኑሮ ውድነቱ አንጻር ሁኔታዎች አስቸጋሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይናገራል።
መንግስት የተለያዩ ማዕከላትን ከፍቶ አቅም የሌላቸውን ወገኖች እየመገበ ነው። ይህም ድርጊቱ ለህዝብ የሚያስብ መንግስት በሀገራችን ውስጥ መኖሩን ያሳያል። አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ግን ቀድሞ ለነዳያን የሚሰጡትን ምግብ አውጥተው መሸጥ ጀምረዋል። የነጋዴዎቹ ድርጊት ‹‹የእርስ በእርስ የመረዳዳት ባህላችንን የሚሸረሸር ነው።›› ይላል ሱልጣን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥር 4 ቀን 2015 ዓ.ም