መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን ለማድረግ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ተብለው ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል የኢንዱስትሪ ፓርኮች (Industrial Parks) ልማት አንዱ ነው። እነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሦስት ዋና ዋና መሰረታዊ ተልዕኮዎች አሏቸው። እነዚህም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ፣ የሥራ እድል ፈጠራን ማስፋት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማከናወን ናቸው። ፓርኮቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ለሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል ስራ በመፍጠርና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የሥራ ከባቢ እውን በማድረግ ለአገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተመራጭ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል በርካታ አገልግሎቶችን አንድ ሥፍራ ላይ ሰብሰብ አድርገው የሚያቀርቡ መሆናቸው፣ ተገቢ መሰረተ ልማት የሚገነባላቸው እንዲሁም ከሌሎች አምራቾች ጋርም የሚያገናኙ መሆናቸው ይጠቀሳሉ።
ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያም ብዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም እንዲሁም ርካሽ የሰውና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን፣ ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባትን፣ የብድር አቅርቦትን፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እንደማበረታቻ በማቅረብ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፋብሪካዎቻቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፍቱ ጥረቶች ተደርገዋል።
በእርግጥም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የማምረቻ መናኸሪያ እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት ለማቀላጠፍ እንዲሁም የሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል ተብሎ የተጣለበት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ውጤቶች ተገኝተውበታል። በተለይም ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድሎችን በመፍጠር ቀላል የማይባል አስተዋፅዖ አበርክተዋል።
በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ ሲሆን በስራ እድል ፈጠራ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ለአገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ቀላል የማይባል አስተዋፅዖ እያበረከቱ ይገኛሉ። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የማምረቻ መናኸሪያ እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት ለማቀላጠፍ ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል ተብሎ ኃላፊነት የተጣለበት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ውጤቶች ተገኝተውበታል። ለአብነት ያህል እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም በተጠናቀረ መረጃ መሰረት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በቀጥታ በምርት ተግባራት ላይ የተሰማሩ 81ሺ ሰራተኞች አሉ። ይህ ቁጥር ከፓርኮቹ ውጭ ያሉና ተዘዋዋሪ በሆነ መንገድ የሥራ እድል የተፈጠረላቸውን ሰዎች አይጨምርም። በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ የሚገኙ አምራቾች ከፓርኮቹ ውጭ ካሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር የስራ ትስስር ስላላቸው በዚህ ሂደትም በርካታ የሥራ እድሎች ተፈጥረዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስራ ከጀመሩበት ጊዜ ወዲህ ከ61 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶች ለአገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ገበያ ቀርበዋል። በሌላ በኩል ፓርኮቹ ስራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ፣ ለውጭ ገበያ የቀረበውና በተኪ ምርቶች የተገኘው ዋጋ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሆኗል። ከዚህ ውስጥ፣ 930 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው ገንዘብ ለውጭ ገበያ ከቀረቡ ምርቶች የተገኘ ገቢ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ተኪ ምርቶችን የማምረት ተግባርም (Import Substitution) ጥሩ ውጤት እየተመዘገበበት እንደሆነ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃዎች ያሳያሉ።
በተለይም የግብርና ውጤቶችን እሴት በመጨመር በብዛትና በጥራት ተወዳዳሪ የማድረግ አቅም እንዳላቸው የታመነባቸው የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን ያሳካሉ ከተባሉ የኢንዱስትሪ ፓርክ ዘርፎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለአርሶ አደሮች የግብይት ሰንሰለቱን ቀላል በማድረግ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የገበያ ትስስር ይፈጥራሉ። ባለሀብቶች የግብርና ግብዓቶችን ከአርሶ አደሮች እንዲቀበሉ በማድረግ አርሶ አደሮች የልፋታቸውን ያህል እንዲጠቀሙ አወንታዊ አስተዋፅዖ ያበረክታሉ። መንግሥት አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት እስካሁን ድረስ 30 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንና ይህ ወጪ ባለሀብቶች በፓርኮቹ ውስጥ ገብተው በምርት ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ።
በሲዳማ ክልል የሚገኘው የ‹‹ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ›› በአገሪቱ ከተገነቡ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች (Integrated Agro-Industry Parks) መካከል አንዱ ነው። የፓርኩ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው በ2013 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ስራ የጀመረ ሲሆን የግብርና ምርቶችን የሚያቀነባብሩ አምራቾች የሚሰማሩበት የኢንዱስትሪ ፓርክ ነው። ስለ‹‹ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ›› ወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴ የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ መምህሩ ሞኬ በተለይ ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ የሰጡትን ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
የፓርኩ አጠቃላይ ገጽታና አቅም
የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ በአገር አቀፍ ደረጃ ከተገነቡና የመሰረተ ልማት አገልግሎት ተሟልቶላቸው ወደ ስራ ከገቡት የተቀናጁ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አንዱ ነው። በአገሪቱ ከሚገኙ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል ቀድሞ ወደ ስራ የገባው ይህ ፓርክ፣ 152 ሼዶችን መያዝ የሚችል የለማ መሬት የተዘጋጀለትም ነው። ግንባታው በሦስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የሚከናወነው ፓርኩ በ294 ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ እስካሁን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል። ቀሪዎቹ ሁለት የግንባታ ምዕራፎች በባለሀብቶች የሚገነቡ ሼዶች ግንባታን ያካትታሉ።
የፓርኩ የመሰረተ ልማት ግንባታ ከ75 በመቶ በላይ ተጠናቋል። ሦስት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ፤ በቀን 12ሺ ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ማመንጨት የሚችል የውሃ፤ 12 ሜጋዋት የማይቆራረጥ ነባር የኃይል አቅርቦት (በአሁኑ ወቅት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለ ኃይል)፤ የባንክ፣ የጉምሩክና ሌሎች አገልግሎቶችን ያካተተ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና 200 ኪዩቢክ ሜትር የቆሻሻ ማጠራቀሚያ መሰረተ ልማቶች አሉት። ከዚህ በተጨማሪም 50 ሜጋዋት ኃይል የሚያቀርብ የሰብስቴሽን ግንባታም በፓርኩ ውስጥ እየተከናወነ ይገኛል።
በፓርኩ ውስጥ 11 ሞዴል ሼዶች በመንግሥት ተገንብተዋል። መንግሥት መገንባት የሚችለው ጥቂት ሼዶችን ብቻ በመሆኑ የሼዶቹ ግንባታ በወጣላቸው ደረጃ መሰረት የግል ባለሀብቶችና ፍላጎት ያላቸው አልሚዎች መሬት በሊዝ ወስደው የራሳቸውን ሼድ ገንብተው የሚገቡበት ፓርክ ነው። በዚህም 12 ሼዶች በግል ባለሀብቶች አማካኝነት እየተገነቡ ይገኛሉ።
የፓርኩ የምርት ስራዎች
በአሁኑ ወቅት 23 አልሚዎች ከኮርፖሬሽኑ ጋር ውል ፈፅመው በተለያየ የትግበራ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ሼድ ከተከራዩ 11 አልሚዎች መካከል ሦስት ኩባንያዎች በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ ነው። ሁለት ድርጅቶች ደግሞ በሙከራ ምርት እንዲሁም አንድ ኩባንያ ማሽን በመትከል ላይ ይገኛል። አንድ ኩባንያ ደግሞ የራሱን ሼድ እየገነባ ነው። ሌሎች አምራቾች ደግሞ የባንክና ሌሎች አገልግሎቶችን የማሟላት ደረጃዎች ላይ ይገኛሉ። ኩባንያዎቹ በአቮካዶ፣ በቡና፣ በማር፣ በወተት፣ በስጋ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በአኩሪ አተርና በሌሎች ምርቶች ማቀነባበር ተግባራት ላይ የተሰማሩ ናቸው። በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ የሚገኙት ኩባንያዎች፤ የአቮካዶ ዘይት በማቀነባበር ለውጭ ገበያ፣ ወተት እና የተለያዩ የፍራፍሬ ጭማቂዎችን በማቀነባበር ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እንዲሁም የማር ምርትን ለአገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርቡት አምራቾች ናቸው።
የአቮካዶ ዘይት በቀጥታ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ነው። በዚህ ዓመት ደግሞ የውጭ ምርትን የሚተኩ የማንጎ፣ እንጆሪና ሌሎች ጭማቂዎች እየተመረቱ ነው። የወተትና የጭማቂ ምርቶችን ለአገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ ወደ ሱዳን ለመላክ ጥረት እየተደረገ ነው። ፓርኩ ስራ ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ (የዘንድሮን ሳይጨምር) ከአምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ አስገኝቷል።
የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ
በይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ያለው የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ አበረታች ነው። ወደ ፓርኩ ለመግባት ስምምነት ከፈፀሙት ባለሀብቶች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ናቸው። የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያግዙ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች አሉ። ማበረታቻዎቹ በአገሪቱ የኢንቨስትመንት ሕግጋት መሰረት የሚፈፀሙ ናቸው።
ባለሀብቶች ወደ ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲገቡ ለማበረታታት ያለመ የፓርኩን ገፅታና አቅም ለባለሀብቶች የማስተዋወቅ መርሃ ግብር ባለፈው ጥቅምት ወር ተካሂዶ ነበር። በዚህ ትልቅ አቅም ያላቸው ባለሀብቶች በተሳተፉበት መድረክ ከተገኙ ከ350 በላይ ባለሀብቶች ውስጥ 106 ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ ለመግባት ቃል ገብተዋል። ከነዚህም መካከል 43 ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ ለመግባት በሂደት ላይ ናቸው። 10 ባለሀብቶች እቅዶቻቸውን አቅርበው ስምምነት እየፈፀሙ ነው።
የገበያ ትስስርና የስራ እድል
የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ለምርት የሚያገለግለውን የጥሬ እቃ አቅርቦቱን የሚያገኘው ከአካባቢው ማኅበረሰብ ነው። በዚህም ከ142ሺ በላይ የአካባቢው አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸዋል። አርሶ አደሮቹ የፓርኩ መጋቢ በሆኑ ሦስት የገጠር ሽግግር ማዕከላት (በንሳ ዳዬ፣ አለታ ወንዶ እና ሞሮቾ አካባቢዎች የሚገኙ) እና በኅብረት ስራ ማኅበራት በኩል የአቮካዶ፣ የማር፣ የወተት፣ የቡናና ሌሎች የግብርና ምርቶችን በፓርኩ ውስጥ ለተሰማሩ ለአልሚዎች እያቀረቡ ነው። ይህ ተግባር የሥራ እድል የመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ወጪን የማስቀረትና ገቢ ምርቶችን የመተካት ድርብርብ ዓላማዎች አሉት።
በአሁኑ ወቅት የአቮካዶ ምርት የሚያቀርቡ 56 የኅብረት ስራ ማኅበራት አሉ። የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የማር እንዲሁም የወተት ምርት የሚያቀርቡ ሌሎች በርካታ ማኅበራትም አሉ። እነዚህ ግብዓት አቅራቢ ማኅበራት ግብዓቶችን የሚሰበስቡት በገጠር የሽግግር ማዕከላት በኩል ነው። ፓርኩ ግብአቶችን በማቅረብ የገበያ ትስስርና የገቢ ምንጭ ከፈጠረላቸው አርሶ አደሮች በተጨማሪ በየዓመቱ በአማካይ ለ10ሺ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል።
ከሦስት ዓመታት በፊት የነበረው የአቮካዶ ምርት ሰፊ ገበያ አልነበረውም። አሁን ግን ደረጃ ወጥቶለት አርሶ አደሩ ምርት በስፋት እያቀረበ፣ ገቢ እያገኘና አዳዲስ ዝርያዎችን እያለማ ነው። ፓርኩ አርሶ አደሩ ጥሬ እቃን በብዛትና በጥራት እንዲያቀርብ እድል እየፈጠረ ነው። ይህም የግብርና ምርታማነት እንዲጨምርና የአርሶ አደሩ ሕይወት እንዲሻሻል እያደረገ ነው።
የምርት ስራ ተግዳሮቶች
ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ ገብተው ሲያለሙ የብድር አቅርቦት ያስፈልጋቸዋል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ጥሩ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ባንኮች የሚጠይቋቸው የብድር መጠየቂያ መስፈርቶች ጊዜ ይወስዳሉ። እነዚህ መስፈርቶች በስራ ሂደት ላይ መጓተቶችን ይፈጥራሉ። ከዚህ ውጭ የሚጠቀስ ሌላ አንኳር መሰናክል የለም።
አዲስ ዘመን ጥር 4 ቀን 2015 ዓ.ም
አንተነህ ቸሬ