አንዳንድ ጊዜ ሞቅ ያለ ጨዋታና ሳቅ ባለበት ቦታ እከሰታለሁ። ሰብሰብ ብለን አንዱን ስናነሳ ሌላውን ስንጥል፣ ስንተራረብ ብቻ የሚያነፋፍቅ ጨዋታ ይደራል። መቼ ተገናኝተን ያስብላል። ያንን ድባብ የሚያደምቀው ደግሞ ከእያንዳንዱ ሰው የሚወጣው ቀልድና ቁም ነገር ነው።
አንዱ በራሱ ላይ ይቀልዳል፤ በራስና በራስ ዙሪያ ባሉ ጉዳዮች ሊሆን ይችላል ብቻ ያንን አንስቶ በሰውነት እንቅስቃሴ ተደግፎ ሲቀርብ የተሰበሰበውን ሰው ፍርስ እስኪል እንዲስቅ ያደርገዋል። እንባ አስጨራሽ ሳቅ። የእውነት ሳቅ ከአጠገባችን በራቀበት በዚህ ዘመን ክትክት ብሎ እንደመሳቅ ምን የሚያስደስት ነገር አለ። እና መገናኘታችንን ሁላችንም እንናፍቀዋለን።
ሰዎች ብዙ ነገራችን ድብቅ አይደል!፤ በተለይ ከጾታዊ ግንኙነት ጋር ያለን ጉዳይ፤ እሱን የሚመለከት ቀልድ ከታከለ ደግሞ ጨዋታው ሁሉ ይሞቃል። እንዴ ይሄ ጉዳይ የሁሉም ነው እስኪያስብል ድረስ። አንዳንዱ አይጻፍ እንጂ ብጽፈው አንባቢም ሆዱ እስኪቆስል ሊስቅ ይችላል። ብቻ በራስ ላይ መቀለድ፤ የሰሙና ያዩትን አስመስሎ ማቅረብ ለብዙ ሳቅ ምክንያት ነው። እንዲህ ሆድን ይዞ የሚስቅ ወይም የሚያስቅ ማግኘት መታደል አይደል።
ይሄ የመገናኛ መድረክ ጠፋ ሲል ታዲያ ምነው የመሰባሰቢያ በዓላት ራቁን? ምነው ልደት ጠፋ? ማህበርም የለም? ካልሆነ ልጄ በትምህርት ቤት ደጃፍ አለፈች ብለንም ቢሆን እንሰባሰብ የሚለው ሰው ይበዛል። ምክንያቱ ምንም አይደለም ነገሮቻችንን ቀለል አድርገን በፍቅር ስለምንሳሳቅ ነው። በዚህ መካከል ማንም ሰው ለወግ ማጣፈጫ ጣል በሚደረጉ ቀልዶች ምክንያት ብሄሩ ወይም ሀይማኖቱ ተነካ ብሎ አያውቅም፤ ምናልባት በቀልዱ መካከል ለሳቅ ምንጭ መሆኑ ያስደስተው ይሆናል እንጂ።
በሀብትም፣ በእውቀትም፣ በሀይማኖትም፣ በብሄርም፤… እንደየ ፈርጁ በሚገለጸው ብዝሃነት ውስጥ ያለው ይሄን መሰል የወግ መድረከኛ የመንግስት ሰራተኛውም ሆነ ነጋዴው ታዲያ በየአጋጣሚው እንደየአዋዋሉ ተረቡን መቅመሱ አይቀርም። ለምሳሌ፣ የመንግስት ሰራተኛ ተብሎ በድህነት ሚዛን መነሳቱ አይቀሬ ነው።
ግን አንድ ነገር እመኑኝ በመካከላችን የፖለቲካ ቀልድ ይነሳል፤ አንዳንዱ ከብሄር ጋር ተያይዞ ንጹህ የሆነ ሂስም ይሰነዘራል። ትክክል በማይመስለው ደግሞ ተገቢ አይደለም የሚለው ክርክር ይጦፋል። እዚህ ላይ ሳቅ የለም ጉዳዩ ሲሪየስ ነዋ! ያን ግዜ ሴቶች እንደ ፈንዲሻ በተን በተን ይላሉ። ምክንያቱም እናቶችን የሚናፍቀው ደስም የሚያሰኘው ሳቅ ጨዋታ እንጂ አስጨናቂና አሳዛኝ ወሬ መስማት አይደም። የሰማነውንም፣ ያልሰማነውንም፣ በየፌስቡክና ቲክቶክ የተመረርንበትንም ዳግም ወደጆሯችን እንዲገባ አንፈቅድም።
ግን ደግሞ አንድ ነገር ሳንወድ እንድንመሰጥ ያደርገናል። የኑሮ ውድነት፤ ምክንያቱም የኑሮ ውድነት የማይነካው የማይመለከተው የለምና አንዱ አንድ ነገር ሲል ወይም ስትል ሌሎችም ተመሳሳይ ሲጨምሩ ወሬው ይደራል። ከዚህኛው ወግ ተጓዳኝ ደግሞ እገሌ/እገሊት በዚህ ሁሉ ወንጀል ውስጥ እጁ /እጇ አለ ከሚለው ጀምሮ፤ ይሄንንማ ለእኛ ተውት ብሎ የሀጢያቱን ጥግ በአንዱ ትከሻ ላይ እስከሚያሸክመው ይሰማል።
ከእነዚህ የሌብነትና የፖለቲካ አሻጥር እንቅስቃሴ ውስጥ እጃቸው ያሉ አካላት ደግሞ ራሳቸውን ከተጠያቂነት የሚያድኑበት ስልት እንዳላቸው አብሮ ይወሳል። በዚህም አንዳንዱ ወይ ሀይማኖት ወይ ብሄሩ ውስጥ የሚሸጎጥ ስለመሆኑም ይተነተናል። እንግዲህ ፖለቲካው ይሄ ነው። ይሄን ለተገነዘበ ደግሞ አሁን አሁን የፖለቲካ ገበያው ደርቷል ለማለት ይቻላል። ለዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂዎቹ ታዲያ ሚስጢር ይጠብቃሉ፣ አገር ያሻግራሉ፣ አገር ይመራሉ ብለን በየደረጃው የስልጣን ባለቤት ካደረግናቸው አመራሮች ይጀምራል።
ምክንያቱም የሰሙትን በሆዳቸው የማያሳድሩ በመኖራቸው የምስጢራዊ ስብሰባ አጀንዳን አደባባይ ማስጣት እየተለመደ መጥቷል። በዚህ መልኩ እያፈተለኩ በሃሜት አደባባይ በሚወጡ ወሬዎች መሰረት ደግሞ አንዳንዱ ይሆናል ተብሎ በማይጠበቅ መልኩ በሙስና ይዘፈቃል። ሲነቃበት ብሄሩን አጥር ለማድረግ ይሞክራል፤ ይሄንን ያንን ጉዳይ ስላጋለጥኩ፣ ሴራቸውን ስለደረስኩበት… ወዘተ የሚል ሰበብ ይደረድራል።
ድሮ የትነህ ያልተባለው ብሄር እና ሀይማኖት አሁን ከጎኔ ቁም የሚል መልዕክቶች ከዚህም ከዚያም ይደርሰዋል። ግን አንድ ነገር እንወቅ። አካሄዱ የራስን ስራ ለመሸፈን ብሄርን እንደ ጥላ መጠቀም ነው። ሲያገኙ ሲበሉ ሲሰሩ አንድም ጊዜ የትነህ የሚሉት አልለበሩም፤ አይደሉምም። የሆነ ተጠያቂነት ሲመጣ ታዲያ የፖለቲካ ገበያው በመከለያ ፍለጋ ይደራል።
ግን እመኑኝ ይሄንን የሚያደርጉት የፖለቲካ ነጋዴዎች ናቸው። አንዴ በብሄር፤ ሌላ ጊዜ በእምነት፣ ይሄ ሳይሆን ሲቀር በፖለቲካው ይገባሉ። በአገር ላይ ሰላም እንዳይሰፍን የሰላም ስምምነቱን ይገፋሉ፤ የሰላምን መንገድ በጎሪጥ ያያሉ። ምክንያቱም ሰላም ከሰፈነ ህዝቡ የሰላሙ ተቋዳሽ ከሆነ እነሱ በምን ትርፍ ያገኛሉ። የአየር ባየር ገቢ ከየት ይመጣል፤ ገንዘብ ማዘዋወር፣ መሳሪያ መንገድ፣ መሬት መውረርና ማስወረር፣ ሙስና እና ሌላውም ለሌላ የሚያመች ገበያ እና ግርግር ይከስማል።
ስለዚህ ጭር ሲል አይወዱም። እናም ጊዜ እየጠበቁ የሆነ አጀንዳ ይለቅቃሉ፤ ያንን ይዞ ማራገብ፣ ያንን ይዞ ከእውቀት የነጻ ትንታኔ ይቀጥላል። በአንዱ ሀይማኖት ላይ ሌላውን ማነሳሳት፤ በየብሄሩ ማጋጨት…ይቀጥላል። በተለይ ደግሞ የሀይማኖት በዓላት ሲደርሱ የአደባባይ በዓላቱ ሲቃረቡ ህዝብን ስጋት ላይ የሚጥል ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት አጀንዳ ይለቀቃል።
ቤተክርስቲያን፣ መስጅድ ወይም ደግሞ ሌላ እንዲህ ተባለ የሚለው የተባለ ዜና ምድሩን ይሞላል። ምክንያቱም ይሄን ካላደረገ የፖለቲካው ገበያ ኪሱ ሊነጥፍ ነው። ኪሱ ማበጥ የሚችለው በረብሻ ነው። ኪሱ የሚሞላው የሰዎች ህይወት አለፈ የሚለው ወሬ ሲቸበቸብ ነው። ኪሱ የሚዳጉሰው ህዝብ ከቀዬው ሲፈናቀል ነው። ለዚህ ደግሞ የግጭት ቅስቀሳ ስራን እንቅልፍ አጥቶ መስራት ይኖርባቸዋል። የፖለቲካ ትርፍ ማግኛውም ይሄው ነው።
ግን ደግሞ አንድ ነገር ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል። አዋቂ ከሚባሉት ጋር መመካከር። ለሰማነው ነገር ተገዢ አለመሆን። “እህልን አላምጦ ነገርን አድምጦ” እንደሚባለው የአበው ተረት ነገሮቻችን ግራ ቀኙን አይተን አድምጠንና አላምጠን መሆን አለበት። ለማንም የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ ገበያ መሆን አይገባም። ስለዚህ ነገርን አድምጦ ፖለቲካንም በስሜት ሳይሆን በስሌት መያዝ፤ እውነታውን ማግኘቱ ላይ ማተኮር ይገባል።
አንዳንዴም ስራ ለሰሪው ማለትም ያስፈልጋል። እኔ መስራት ያለብኝን ስራ አድምቼ ልስራ፤ ሀኪሙም በተመሳሳይ፣ መምህሩም እንደዛው ሌላውም… ሌላውም … የሚጠበቅበትን የእውቀቱንና የሙያውን ይወጣ፤ ያኔ ያተርፋል። ነገር ግን ሁላችንም በአንድ ሙያ ላይ እምንጨፍር፤ ምግቡም ልብሱም ፖለቲካ ከሆነ አይሆንም። ይሄ ከሆነ ፖለቲካው በእውቀት ስለማይመራ ድፍርስርሱ ይወጣል። በመሆኑም ሁሉንም በእውቀትና በሙያችን እናድርገው። የፖለቲካ ቸርቻሪዎችን ከመሀላችን እናውጣ፤ የፖለቲካውን ለሙስና፣ ለራስ ጥቅም፣ ለአገር ማፍረሻነት አናውለው። የፖለቲካው ገበያም የትርፍ ማግኛ መሆን የለበትም።
አዶኒስ (ከሲኤምሲ)
አዲስ ዘመን ጥር 4 /2015