የህብረት ሥራ ማህበራት የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን ምርታማነት ለማሻሻል በግብዓት አቅርቦትና ሥርጭት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ በሀገሪቱ ለተመዘገበው የምርትና ምርታማነት እድገት የማህበራቱ ሚና ተጠቃሽ እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ማህበራቱ ግብርናውን ወደ መካናይዜሽን ለማሳደግም እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ይሁንና የተሰሩት ሥራዎች ግን በቂ እንዳልሆኑ የዘርፉ ኃላፊዎች ይገልጻሉ።
የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአርሶና አርብቶ አደሩ አካባቢ ያሉ የህብረት ሥራ ማህበራትን በመጠቀም የትኩረት አቅጣጫውን ግብርናውን ማዘመን ላይ አድርጓል። በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት ምርት በሚሰበሰብበት ወቅት የድህረ ምርት ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባሮች በቂ ባይባሉም ተስፋ የሚጣልባቸው እንደሆነ ይገለጻል።
በፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ የእቅድ ፕሮጀክትና መረጃ ዳይሬክተር አቶ አብዱ አደም ቡሰርም እስካሁን በሀገሪቱ አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን በማህበራት በማደራጀት ተጠቃሚ የሚሆኑባቸውን በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ግብርንና በማዘመን የግብርና መካናይዜሽንን በማስፋፋት ረገድ የተሠራው ሥራ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ይጠቁማሉ።
በተለይም ድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ ዘመናዊ መንገዶችን በመጠቀም ረገድ ሲከናውኑ የነበሩት እንቅስቃሴዎች የተቀዛቀዙ መሆናቸውን ተከትሎ አርሶ አደሩ ብዙ ደክሞ ያገኘው ምርት ለከፍተኛ ብክነት እየተዳረገ መሆኑን ነው የሚጠቁሙት።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህብረት ሥራ ማህበራት በኩል እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል። አርሶ አደሩ በምርት ወቅትና በድህረ ምርት ውጤታማነቱን ሊያሳድጉ የሚችሉ በሀገር ውስጥ የተመረቱም ሆነ ከውጭ የሚመጡ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋትና በማህበራቱ በኩል ማዳረስ እንዲቻል የተጀመሩት እንቅስቃሴዎች አጥጋቢም ባይሆኑ መሪ ውጤት የታየባቸው ናቸው።
ማህበራቱ እስካሁን በግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት የተሰማሩ 11 የኅብረት ሥራ ማህበራትና 76 የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች 900 የቅድመ እና 150 የድህረ ምርት አገልግሎት መስጫ ማሽነሪዎችን በመያዝ አገልግሎቱን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በዚህም እነዚህን መሳሪያዎች ለማግኘት አርሶ አደሩ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመሄድ ለምርት ወቅትና ድህረ ምርት አገልግሎት የሚያደርገውን ወጪ 25 በመቶ ለመቆጠብ ችሏል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታትም በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልል ለድህረ ምርት መሰብሰቢያ የሚጠቅሙ ኮምባይነሮችንና መውቂያዎችን ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ እየሰሩ ያሉ የህብረት ስራ ዩኑየኖች አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን አቶ አብዱ ይጠቅሳሉ።
የእነዚህን ተሞክሮ በማስፋፋት ወደእዚህ ሥራ ያልገቡ ዩኒየኖችን ለማስገባት በፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ በኩል ሰፊ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ በቅርቡም ለግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁስን ለመግዛት ለሚፈልጉ የኅብረት ሥራ ማህበራት ከልማት ባንክ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ መረጃ የማደራጀት እንዲሁም ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ይጠቁማሉ።
ከግብዓት በተጓዳኝ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክፍተት አንዱ ችግር ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ይህንንም ችግር ለመፍታትም መሠራቱን ይጠቅሳሉ፡፡ በኤጀንሲው በኩል የኅብረት ሥራ ማህበራት የሜካናይዜሽን አገልግሎት ትግበራ ሰነድ (የአሰራር ማንዋል) መዘጋጀቱን፣ ህንድ አገር የሚገኘው ‹‹ቲኤኤፍኢ›› /TAFE/ የተሰኘ የሜካናይዜሽን አምራች ድርጅት በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ከሚገኘው ወደራ የኅብረት ሥራ ዩኒየን ጋር በመቀናጀት የሥልጠና፣ የተግባር ትምህርትና ሠርቶ ማሳያ ማዕከል ለመክፈት የዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ይናገራሉ። የሥልጠናና የልምድ ልውውጡ በሁሉም ክልሎች እንዲዳረስ ለመሥራት የተያዘ እቅድ መኖሩንም ጠቁመዋል።
ድህረ ምርት ብክነት የአማራ ክልል አርሶ አደር ቀዳሚ ችግር መሆኑን የክልሉ ህብረት ሥራ ማህበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይለ ልዑል ተስፋ ይገልጻሉ። ሥራ አስኪያጁ እንደሚያብራሩት፤ የክልሉ አርሶ አደር ችግር የድህረ ምርት ብክነት ነው፡፡ ይህም በአብዛኛው ምርቱ እቤት ከደረሰ በኋላ የሚከሰት በመሆኑ ዜሮ ፍላይ (Zero Fly) ማደበሪያ (የእህል ማቆያ ከረጢት) በማህበራቱ በኩል እንዲደርስ በማድረግ ችግሩን ለመፍታት እየተሠራ ይገኛል።
ከዚህ በፊት ይህንን ችግር ለመቅረፍ እንደ አማራጭ ጥቅም ላይ ይውል የነበረው ኬሚካል መጠቀም ነበር። ነገር ግን ኬሚካሉ ከዋጋ፤ ከአቅርቦትና ከጎንዮሽ ጉዳት ጋር በተያያዘ አስተማማኝ አይደለም። አሁን ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ያለው ዜሮ ፍላይ የእህል ከረጢት ግን እነዚህን ችግሮች የሚያቃልል ነው።
ከረጢቱ ሦስት ዓመት ድረስ እህሉ ሳይበላሽ እንዲቆይ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው፣ በክልሉ በአዊ ዞን በአድማስ ህብረት ሥራ ዩኒየን የፒፒ ፋብሪካ የሚመረት በመሆኑ በቀላሉና በተመጣጣኝ ዋጋ አርሶ አደር የሚያገኘው እንደሆነም ይጠቅሳሉ።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ፤ በክልሉ በቅድመ ምርትና ድህረ ምርት መካናይዜሽን አገልግሎት በኩል ባለፉት ስምንት ወራት በተጉለት የዘር ብዜት ልማትና ግብይት ኅብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ለ16 አርሶ አደሮች 14 ሄክታር መሬት የእርሻ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል። ሦስት ዘመናዊ ኮምባይነር ሃርቨስተሮችን በመጠቀምም የ1ሺ334 አርሶ አደሮችን ምርት አጭዶ በመውቃት ሊደርስ የሚችለውን ብክነት መቀነስ ችሏል፡፡ 45 የስንዴ መውቂያ ትሬሸሮችን በወደራ ዩኒየን አማካኝነት በማስመጣትና በአባል መሠረታዊ ህብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ለ 226 አርሶ አደሮች እንዲቀርብ ተደርጓል፤ በዚህም የአርሶ አደሩን ጊዜ፣ የምርት ጥራትን መቀነስንና ብክነትን ማስቀረት ተችሏል።
በዚህም ከሌሎች አቅራቢዎች አንጻር በኩንታል ከ20 – 30 ብር ቅናሽ አገልግሎቱን በማቅረብ የህብረት ሥራ ማህበር አባላት የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። በተያዘው በጀት ዓመት በ26 ህብረት ሥራ ማኀበራት 38 የእርሻ ትራክተሮች፤ በ5 ዩኒየኖች 13 ዘመናዊ ኮምባይንድ ሃርቨስተር ግዥ ለመፈፀም ታቅዶ ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ 15 ትራክተር ከእነመለዋወጫው ግዥ ተፈጽሟል።
‹‹የተከናወኑት ተግባሮች ውጤታማ ናቸው ቢባልም በሚሊየኖች አርሶ አደር ላሉበት ክልልም ሆነ በማህበራት ከታቀፉት አርሶ አደሮች ቁጥር አንፃር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም›› ያሉት ሥራ አስኪያጁ። ለቀጣይ በውድ ዋጋ ከውጭ ተገዝተው የሚገቡ የእርሻ መሳሪያዎችን በሀገር ውስጥ አስመስሎ ለማምረትና ተደራሽ ለማድረግ በክልሉ ከሚገኙ ከዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ጋር ማህበራቱ በትብብር ለመሥራት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የትግራይ ክልል የህብረት ሥራ ኤጀንሲ የልማት፤ እቅድና ክትትል ዳይሬክተር አቶ መብራህቶም እምባዪ የክልሉ የህብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲ ማህበራት ግብርናን ወደ መካናይዜሽን ለማምጣት በሚሠሩ ሥራዎች ላይ እንዲያተኩሩ የተደረገው ከአምስት ዓመት በፊት ጀምሮ ነው ይላሉ።
እንደ አቶ መብራህቶም ፍላጎቱ በክልሉ መንግሥትም በማህበራቱም በኩል ያለና ለዓመታት የተሠራበት መሆኑን ጠቅሰው፣ የማህበራቱ አቅም ለመካናይዜሽን እርሻ የሚያስፈልጉትን ትላልቅ መሣሪያዎች ለመግዛት በቂ አይደለም ይላሉ። በፌደራል መንግሥት በኩል ለማዳበሪያ አቅርቦት እንጂ ለመካናይዜሽንና ለአግሮ ፕሮሰሲንግ የብድር አገልግሎት ማግኘት ዛሬም ድረስ አስቸጋሪ መሆኑን የሚጠቅሱት ዳይሬክተሩ፣ ውጤቱ ሲጀመር በታሰበው ደረጃ አመርቂ መሆን እንዳልቻለም ይናገራሉ።
እንደ አቶ መብራሀቶም ማብራሪያ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በማህበራቱ በኩል ሃምሳ ትራክተሮች፤ አስራ ስምንት የእህል መውቂያ ኮምባይነሮች፤ አስራ አንድ የመኖ ማቀነባበሪያ፤ ሁለት የወተት ማቀነባበሪ፤ አንድ የማር ማቀነባበሪያ፤ አስራ ሰባት የሩዝ መፈልፈያና አምስት የበቆሎ መፈልፈያ ማቅረብ ተችሏል። እንዲሁም በተያዘው በጀት ዓመት በቦህራ ዩኒየን በቀን አምስት ሺ ሊትር ወተት የማሸግ አቅም ያለው የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ተጀምሯል።
የኦሮሚያ ክልል ህብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ሺፈራውም የድህረ ምርት ብክነት የክልሉ ችግር መሆኑን ይገልጻሉ። እስካሁን በማህበራቱ በኩል ትኩረት ተሰጥቶ ሲሠራ የነበረው ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁና ከውጭ በሚገቡ ማሽኖች ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀላል ወጪ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ማሽኖች አዋጭ ቢሆኑም በቂ የቴክኖሎጂ ሽግግር ስለሌለ እነሱንም የመጠቀሙ እንቅስቃሴ ውጤታማ አልነበረም ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ አቶ ዳኛቸው ገለጻ፤ አርሶ አደሩ በእጁ ላይ ያሉትን የተለመዱ ቴክኖሎጂዎችና አሰራሮችን በመጠቀም ብክነትን መቀነስ የሚችል ቢሆንም ግንዛቤ መፍጠሩ ግን አልተሰራበትም። ነገር ግን በአንዳንድ አካባቢዎች የተሠሩ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት አርሶ አደር ምንም አይነት ግብዓት ሳይጨምር አሁን እየሠራበት ያለውን አሰራር በሙያተኛ በማስደገፍ ብክነትን መቀነስ ይቻላል። ይህንንም ለማድረግ ከአውድማ አዘገጃጀት ጀምሮ በመውቃትና በመጓጓዝ እንዲሁም እቤት ውስጥ ምርት የሚቀመጥበትን አካሄድ በባለሙያዎች ምክር ማስተካከል ይጠበቃል።
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የኦሮሚያ ክልል ህብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲ በክልሉ ካለው የምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን የጀመራቸው ሥራዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ አርሶ አደሩ በቀላሉ ሊጠቀምባቸው የሚችላቸውን ማሽኖች ምርምሩ እያፈለቀ እንዲያቀርብ ብሎም በሌሎች ሀገራት ያሉ ተሞክሮችንና ቴክኖሎጂዎችን ለማዳረስ ከማህበራቱ ጋር የመቀነጀት ሥራ እየተሠ-ራ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
ማህበራቱ የግብርና መካናይዜሽንን በመጠቀም የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ መንቀሳቀስ መጀመራቸው የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር ጥሩ ጅምር ተደርጎ ይወሰዳል። የግብርና መካናይዜሽን ጉዳይ መንግሥትም በትኩረት ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት መካናይዜሽን ላይ እንደሚሠራ የሚገልጸውን ያህል በፋይናንስ አቅርቦት፣ በሥልጠና እና ሌሎች ድጋፎች ላይም መሥራት ይኖርበታል፡፡ ሥራውን በራሱ እስከሚሠራው ድረስም የማህበራቱን ጥረት ላቅ ያለ ደረጃ ላይ ለማድረስ ተጨባጭ ድጋፍ በማቅረብ መሥራት ይኖርበታል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ