የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ቻምፒዮኑ አትሌት ሰለሞን ባረጋ በስፔን ኤልጎይባር በተካሄደ የ10 ኪሎ ሜትር አገር አቋራጭ ውድድር ድል ቀንቶታል። በታሪካዊው ስፔናዊ አትሌት ሁዋን ሙጉዌርዛ መታሰቢያነት የሚካሄደው ይህ ዓመታዊ አገር አቋራጭ ከትናንት በስቲያ ለሰባ ዘጠነኛ ጊዜ ሲካሄድ ወጣቱ አትሌት ሰለሞን ባረጋ በድንቅ የአጨራረስ ብቃት ለሁለተኛ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ መሆን ችሏል።
ከቶኪዮ ኦሊምፒክ ድሉ በኋላ በተለይም ባለፈው አንድ ዓመት ያህል በኦሪገኑ የዓለም ቻምፒዮናና በተለያዩ የጎዳና ላይ ውድድሮች ከድል ርቆ የቆየው ሰለሞን ከሳምንት በፊትም ሱሉልታ በተካሄደው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ቻምፒዮና ውድድር ላይ በህመም ምክንያት ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል። በዚህም በቀጣይ አውስትራሊያ በሚካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን ከሚወክሉ አትሌቶች አንዱ ሳይሆን ቀርቷል። ይሁን እንጂ ሰለሞን በአስር ቀናት ልዩነት ትልቅ ትኩረት በሚሰጠው ኤልጎይባር አገር አቋራጭ ውድድር በ33 ደቂቃ ከ14 ሴኮንድ አሸናፊ መሆን ችሏል።
በወንዶች መካከል በተካሄደው የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ሰለሞን ባረጋ አስደናቂ የግል አጨራረስ ብቃቱን በመጠቀም በውድድሩ የመጨረሻ ሜትሮች ፍጥነቱን በመጨመር ከሌሎች ተፎካካሪዎቹ ተነጥሎ በመውጣት ነው ለድል የበቃው።
ሰለሞን የሁዋን ሙጉዌርዛ የአገር አቋራጭ ቻምፒዮናን ሲያሸንፉ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን እአአ በ2018 የውድድሩ አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል። በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ባህሬናዊው የሆነው አትሌት ብርሃኑ ባለው ሰለሞንን ተከትሎ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ፣ ትውልደ ሞሮኳዊው ስፔናዊ አትሌት አዴል ሜቻል ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
በተመሳሳይ በሴቶች መካከል በተካሄደው የ8 ኪሎ ሜትር ውድድር ኤርትራዊቷ አትሌት ራሔል ዳንኤል አሸንፋለች። ኬንያዊቷ አትሌት ኤዲናህ ጄቢቶክ ሁለተኛ እንዲሁም በትውልድ ኬንያዊ በዜግነት ባህሬናዊ የሆነችው አትሌት ዊንፍሬድ ያቪ በቅደም ተከተል ሁለተኛ እና ሶስተኛን ደረጃ ይዘዋል አጠናቀዋል።
በስፔን የኢንዱስትሪ ከተማ ኤልጎይባር በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ ውድድር እኤአ በ1937 ሕይወቱ ያለፈውን ታሪካዊውን ስፔናዊ የመካከለኛ ርቀት አትሌት ሁዋን ሙጉዌርዛ መታሰቢያ ሲሆን የዓለማችን ኮከብ አትሌቶችም ጠንካራ ፉክክር የሚያደርጉበት ነው። ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ከዚህ ውድድር ጋር ለረጅም ዓመታት የስኬታማነት ታሪክና ልዩ ቁርኝት አላቸው።
በስፔን ውስጥ በምትገኛዋ የባስክ ግዛት ኤልጎይባር ለረጅም ዓመታት ሲካሄድ የቆየው ይህ ውድድር እኤአ ከ1943 ጀምሮ ስያሜውን በእውቁ አትሌት ሁዋን ሙጉዌራዛ መታሰቢያ ያረገ ሲሆን እኤአ ከ1963 አንስቶ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የዓለም ታላላቅ አትሌቶችን ማፎካከር ችሏል።
በዚህም ኢትዮጵያዊው ታሪካዊ አትሌት ማሞ ወልዴ በወንዶች አሸናፊ በመሆን ከስፔናውያን ውጪ ውድድሩን ያሸነፈ የመጀመሪያ አትሌት መሆን ችሏል። አንጋፋው የኦሊምፒክ ጀግና አትሌት ማሞ ወልዴ በ1967 እና 1968 ይህን ውድድር ለተከታታይ ሁለት ጊዜ በማሸነፍ የማይረሳ ታሪክ መስራት ችሏል።
በዚህም ማሞ ሁሌም በዚህ ውድድር የማይዘነጋ አትሌት መሆን የቻለ ሲሆን ስፔናውያንም ለእርሱ በተለይ በግዛቷ ውስጥ ልዩ ቦታ እንዲሰጡት አድርጓል። ይህንንም በማሰብ አራት የአገር አቋራጭ ውድድር ባለድል በሆነባት ከተማ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ በኋላ በግዛቷ ሲወዳደር የሚያሳይ በአልሙኒየም የተሰራ ሃውልት አኑረውለታል።
ከማሞ በኋላም በርካታ ታሪካዊ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዚህ ውድድር አሸናፊ ሆነው መውጣት ችለዋል። ፊጣ ባይሳ፣ አዲስ አበበ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ታሪኩ በቀለ፣ ስለሺ ስህን፣ አየለ አብሽሮ፣ ሰለሞን ባረጋ በወንዶች ድል ያደረጉ አትሌቶች ናቸው። በተመሳሳይ በሴቶች ደራርቱ ቱሉ፣ ቁጥሬ ዱሌቻ፣ ገነት ገብረጊዮርጊስ፣ መስታወት ቱፋ፣ ውዴ አያሌው፣ ይመናሹ ታዬ፣ ገለቴ ቡርቃ፣ ህይወት አያሌው፣ ሰንበሬ ተፈሪ የውድድሩ አሸናፊ ሆነው የሚጠቀሱ አትሌቶች ናቸው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 2/2015