ወይዘሮ ዓለምበዛ ጌታቸው የተወለደችው ደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ ነው። እናቷ በሞት የተለየቻት ትንሽ ከፍ እንዳለች ቢሆንም በውል አታውቃትም። አባቷ ማን እንደነበርና ይሙት ይኑርም መረጃው የላትም። ‹ስለ አባቴ የምጠይቀውና የሚያውቅም ሰውም የለም› ትላለች። ምክንያቱም እናቷ ስትሞት አብራት ትኖር የነበረችው ታላቅ እህቷም እንደነገረቻት ሁለት ወንድሞችም ነበሯት። ሆኖም አንዱ በሽተኛ ነበርና ሞቷል። ሌላው ደግሞ ጦር ሜዳ እንደሄደ ባለመመለሱ ይሙት ይኑር አይታወቅም።
እናቷ እንደሞተች ከጥቂት ዓመት በኋላ እህቷም ሞተችባት፤ በዚህን ጊዜ ነበር ወደ አዲስ አበባ የመጣችው። ቢሆንም ያኔ ትንሽ በመሆኗ አመጣጧን አታስታውስም። ግን ደግሞ እህቴ ስትሞት ነው የመጣሁት ትላለች። እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ከደረሰች በኋላ አንድ ሰው እንደ ልጅ ያሳድጋት ነበር።
በዚህ ሰው እጅ ስለማደጓ ስታወራ ሳግ ይይዛታል። እንባዋም ተናንቋት ብቻ አያቆምም። ስቃዩ አሁን አሁን እየደረሰባት ያለ ይመስል እንባዋ እርግፍ እርግፍ ይላል። ሰውዬው ምክንያቱን ባታውቅም ይገርፋት የነበረው ሁልጊዜ ነው። ሲገርፋት አሁን አሁን ስታስበው ሰው ደርሶ እንዳያስጥለው በሩን ይዘጋል። በር በመዝጋት ብቻ ሳያቆምም አፏ ውስጥ ጨርቅ ይጠቀጥቅባታል። ህመሙ መፈጠሯን እንድትጠላ የሚያደርግ ነበር። ግርፋቱን ያቆም የነበረው ዛሬም ከጀርባዋ፤ ከእግሮቿ፤ እጆቿና ፊቷ ላይ ያልጠፋው ሰንበር በሰውነቷ ሲወጣ ነው።
በዚህ ምሬት ብን ብላ ከቤቱ ጠፋች። ሰው ቤት ስራ ተቀጥራም መሥራት ጀመረች። የሰው ቤት ሠራተኝነት ኑሮ እንደ ሰውዬው ቤት በግርፋት የምትሰቃይበት ባይሆንም ብዙ ጣጣ ስላለው አይመችም። ባልና ሚስት ቤት ስትገባ መልከ ቀና በመሆኗ ባሌን አየሽው ብላ ሚስት ትጣላታለች። ባል በበኩሉ ሚስት በአካባቢው ከሌለች ይጎነትላታል። ቢሆንም ከአንዱ ቤት አንዱ ቤት እያለች ሕይወቷን በሰራተኝነት ኑሮ መግፋቷን ቀጠለች። በዚህ መካከል የገባችበት ወንደላጤ ሳታስብ ደፍሯት አረገዘች። አጋጣሚ ሆኖ ልትወልድ ትንሽ ሲቀራት ያ ድሮ ያሰቃያት የነበረው ሰውዬ በመሞቱ እህቱ እሷ ጋር ልጇን እንድትገላገል አደረገች። መልካም ሰው ነበረችና በጥሩ ሁኔታም አረሰቻት። ግን በኑሮ ምስኪን ስለነበረች ልጇን ለማሳደግ የግድ እሷ እየሰራች ማገዝ ነበረባት።
ስለዚህ ነው ወደ ሳዑዲ ለመሄድ የወሰነችው። የሄደችው በህጋዊ ኤጀንሲ በአውሮፕላን በመሆኑ መንገድ ላይ የገጠማት መከራ የለም። የሄደችበት ቀን የረመዳን በዓል ነበርና አሰሪዋ ብዙ ቀጣሪዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ ከመካ ተቀብላት ወደ ቤት ይዛት ሄደች። ገላዋን ታጥባና የተሰጣትን ልብስ ለብሳ ወደሥራ ተሰማራች፤ ሥራው ከጉዞው ጋር ተዳምሮ እስኪያዳክማት ምግብ የሰጣት አልነበረምና ረሃብ ሲፀናባት አሰሪዎቿ አዛን ሲል ከሚቀምሱት ዳቦ ሰርቃ ጉያዋ ውስጥ በመደበቅ መብላቷን አትዘነጋውም።
ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰችው ቀጣሪዋ እዛም እዚህም በምታሰራት ሥራ ጫና ተማራ ነው። ስትመለስ ሁለት ዓመት ያገለገለችበትን ደመወዝ አልከፈለቻትም። “የሳዑዲ ቀጣሪዎች የሰሩበትን ደመወዝ ሲጠይቋቸው ሰርቃኛለች፤ ልጄን ደብድባብኛለችና ሰድባኛለች ብለው በሀሰት በመወንጀል ያሳስራሉ። በዚህ ምክንያት እስር ቤት ከምበሰብስ ደመወዜን ትቼ ብመጣ ይሻለኛል በማለት ከምትሰራበት ቤት መውጣቷን ትናገራለች።
አሁን ላይ እንደሷ መንግስት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ያደረጋቸውን አምስት ሴቶች በማህበር እንዲደራጁ አድርጎ ሸገር ዳቦ ላይ እየሰሩ ይገኛሉ። የሚሰሩት በፈረቃ ሲሆን አንድ ሳምንት አንዳቸው አንድ ሳምንት ሌላቸው መሆኑንም ዓለምበዛ አጫውታናለች። ወጣት ሰናይት ደበበ አባት የሌለውን ልጇን ከወለደች በኋላ ብዙ የሕይወት ውጣ ውረድ አሳልፋለች። ሰርታ ለማግኘት ልጇን የሚይዝላት ከማጣት ጀምሮ የሚላስ የሚቀመስ እስከማጣት ደርሳለች። ይሄ የመጀመሪያው ሲሆን ሁለተኛውን ምዕራፍ መከራዋ የጀመረው ደግሞ ገና አረብ አገር ሳትሄድ ነው። ገንዘቡ ስላልነበራት ሌት እና ቀን በየሰው ቤት ልብስ በማጠብና የተለያዩ የቤት ሥራዎችን በመሥራት ጥሪት መቋጠር ነበረባት።
ሆኖም አዲስ አበባ ውስጥ ጥሪት ለመቋጠር ያደረገችው ጥረት አልተሳካላትም። እናም እንደ ልማዷ ከአዲስ አበባ ጠፍታ ወደ ናዝሬት ሄደች። እዚያም በየሰው ቤት እየዞረች ልብስ በማጠብ ልትቋጥረው ያሰበችው ጥሪት ሊሞላላት አልቻለም። የቤት ኪራዩን እንኳን ለምትሸፍንበት አልተርፍ አላት። በመሆኑም ከሰው ቤት ሥራው በተጓዳኝ ማታ ማታ እየቆመች በሴት አዳሪነት ሥራ ልትደጉመው ሞከረች። የሴተኛ አዳሪነት ሥራው እጅግ የሚያማርርና መፈጠርን የሚያስጠላ አስቀያሜ ነበር። መልከ መልካም በመሆኗ ብዙ ወንዶች ቢፈልጓትም ከተጠቀሙባት በኋላ ሳይከፍሏት የሚሄዱ ይበዛሉ። ዳጎስ ያለ ብር የሚከፍሏት ደግሞ ያለ ኮንዶም ግንኙነት ማድረግ ይፈልጋሉ። ይሄ ደግሞ ለእሷ በፍፁም የሚታሰብ አልነበረም። ምክንያቱም ጤናማ ሕይወቷን ሰርታ ለማደርና ነፍሷን ለማቆየት ብቻ ሳይሆን አንድዬ ልጇንም ለማሳደግ ትፈልገዋለች።
እናም ናዝሬት አልሆን ሲላት በአንድ ሹፌር ወዳጇ መካሪነት ወደ ድሬዳዋ ተሻገረች። የቦቴ ሹፌሩ ወዳጇ እዛ እንዳደረሳት የለመደችውን የሰው ቤት ሥራ ቀጠለች። እዚህ ምንም የምትከፍለው የቤት ኪራይ ባይኖርም የጫትና የሲጋራ ሱሰኛ ለመሆን በመዳረጓ ያሰበቸውን ጥሪት መቋጠር አልሆነላትም። ከድሬድዋ ጅቡቲ ዘለቀች። እዚያ ያገኘቻትን አንዲት ሴት ከዚህ ቀደም እሷን ሳዑዲ አረብያ የላካት ሰው እንዳለና እሷንም እንደሚልካት ነገረቻት። ይሄ ሁሉ ሲሆን ልጇን ለያዘችላት ሴት ቤሳቤስቲን ሰጥታት አታውቅም ነበር ። ሰውዬው የተወሰነ ገንዘብ ከሰጠችው ሌላውን እዛ ከደረሰች በኋላ ሰርታ መክፈል እንደምትችል ሲነግራት ተደሰተች። ወደ ሳኡዲ አረቢያ በእግር ጉዞ ተጀመረ።
መነሻቸውን ጅቡቲ አድርገው መንገድ መጀመራቸውን እንጂ በየት ፤በየት አድርገው እንደሚሄዱ አልነገራትም። ግን በቶጎ ጫሌ በኩል አድርጎ ተመልሶ ወደ አርቲሼክ ነበር ያቀናው። የኮንትሮባንድ ከተማዋ አርቲሼክ ሲደርሱ ለደላላው ከአዲስ አበባ ስልክ ተደወለለት። በአይሮፕላን የሚወስዱ ኤጀንቶች ስላሉ በአዲስ አበባ በኩል ይሻላል አላት። ከሁለት ዓመት በላይ ጨቅላ ልጇን ለጣለችባት ምስኪን ሴት አንድ ነገር ሳትል መመለስ ስላሳፈራት 20ሺህ ብሯን እንዲመልስላት ጠየቀችው። እዚህ ድረስ የመጣሽበት ነው ብሎ ጥሏት ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ።
ጥቂት ጊዜ አርቴሽክ ስትሰራ ቆይታ ጀልባ ተፈናጣ በመኪና ሳውዲ በመጨረሻ ሳኡዲ ለመድረስ በቃች። ‹‹ሲያወሩት እንዲህ ቀላል ቢመስልም ጉዞው እጅግ አስፈሪ፤ ከባድና አስጨናቂ ነበር›› ትላለ ። ጉዞውን በህንድ ውቂያኖስ ባህር ውስጥ ያደረገው ጀልባ እንደ ሰርዲን ለታጨቁት ተሳፋሪዎቹ ዋስትና የሚሰጥ አልነበረም። ባህሩን እየቀዘፈ ወደ የመን ሲከንፍ ወደ ባህሩ ለሚወድቁት ሰዎች ከአፍ የወደቀ ጥሬን ያህል እንኳን ትኩረት አይሰጥም።
እሷ ቀደም ብላ በጀልባው ውስጥ ቦታ በመያዟና መካከል በመሆኗ ባህር ውስጥ ከመውደቅ ብትተርፍም በጉዞው ያሳለፈችው ስቃይ ቀላል አልነበረም። “በሰው መጨናነቅና ሙቀት ታፍኜ መፈጠሬን የጠላሁበት ስቃይ ገጥሞኛል። ምን አልባት ብችል ባህር ውስጥ አንደ ወደቁት መውደቅም አስመኝቶኛል” ትላለች። ከየመን ወደ ሳውዲ የገባችበት የጭነት መኪና እንዲሁ እንደ እሷ ሰርተው በብርቱ መለወጥ በሚሹ እህቶቿ በመጨናነቁ በሕይወት የመኖር እስትንፋስን የሚቆርጥ ነበር። መኪናውን ለመያዝ ረጅም በረሃ በእግሯ መጓዝም ነበረባት። ረሀቡ፤ውሃ ጥሙና ድካሙ መቼም የሚረሳት አልነበረም። እጅግ ተጎሳቁላና ከሰውነት ተራ ወጥታም ነበር። እንዲህ ሆና ሳዑዲ ደረሰች።
ከመኪናው ወርዳ ወደ ቀጣሪዋ የሚወስዳትን ሰው ሌሎች በርካታ ሴቶች የሚጠባበቁበት ሥፍራ ሆና ስትጠብቅ ፖሊስ ደርሶና አፋፍሶ እሷንና አብረዋት የነበሩትን በሙሉ ወደ እስር ቤት አስገባቸው። “ አብረውኝ እስር ቤት ከነበሩት ብዙዎቹ ወዲያው ወጥተዋል። ዓመትና ሁለት ዓመት ቆይተው የወጡም አሉ። ምክንያቱም እነሱ ያመጧቸው ደላሎች ጉዳያቸውን ይከታተሉላቸው ነበር። እኔን ያመጣኝ ደላላ ግን ከነጭራሹ ረስቶኛል” የምትለው ሰናይት በሳዑዲ እስር ቤት ከ10 ዓመት በላይ በእስር ቆይታ በኢትዮጵያ መንግስት አማካኝነት በቅርቡ ወደ አገሯ መመለሷን ትናገራለች። ሰናይት እንኳን ከባርነት ነፃ ወጥቼ ተመለስኩ። በሀገሬ ላይ ሰርቼ እለወጣለሁ የሚል ተስፋም ሰንቃለች። በተለይም መንግስት አዲስ በጀመረው የሌማት ትሩፋት ዘርፍ በመሰማራት በዶሮ እርባታ፤ በወተት ምርትና በተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ በመሳተፍ እራሷን ለመቀየር ዕቅድ አላት።
የገበሬ ልጅ የሆነችው ሰሚራ መሐመድ ሌላዋ በመንግስት አማካኝነት በቅርቡ ወደ አገሯ የተመለሰችና በአዲስ አበባ በሚገኝ በአንድ የተመላሾች መጠለያ ጣቢያ የምትገኝ ወጣት ናት። ዕድሜዋ 28 ሲሆን በሳዑዲ ያሳለፈችው የእንግልትና የመከራ ሕይወት የ40 ዓመት ሴት አስመስሏታል። ስለ ራሷና አካሄዷ እንደነገረችን አባቷና ቤተሰቦቿ ባለፈው ሦስት ዓመት በነበረው የእርስ በእርስ ግጭት መሞታቸውንና ቤት ንብረታቸው መውደሙን ሰምታለች።
በየማሳው እየዞረ የሆነ ያልሆነውን ቀባጥሮ የአርሶ አደር ልጆች በማታለል በሚያስኮበልል ደላላ አማካኝነት ነው ወደ ሳዑዲ አረብያ የሄደችው። በእርግጥ ደህና ብር ከአባቷ ተቀብላ ለደላላው በመስጠቷ የላካት በአውሮፕላን በመሆኑ እንደሌሎች እህቶቿ በመንገድ ላይ የደረሰባት እንግልትና መከራ አልነበረም።
ሳዑዲ እንደደረሰች ቀጣሪዋ ከመካ ተቀበለቻት። ፈጥናም ፓስፖርቷን ወሰደችባት። በወቅቱ ቆይታ ትመልሳልኛለች ብላ አስባ ስለነበር ምንም አልተናገረችም። እቤት እንደደረሱ ተፈተሸች። የያዘችውን ልብስ ጋርቤጅ አስጥላ አዳዲስ ልብሶች በመስጠት ገላዋን እንድትታጠብ አደረገቻት። ኢትዮጵያዊያዋ ሠራተኛዋ የእንቅልፍ ሰዓቷ ስለነበር ምንም ሳታርፍ ከመንገድ እንደመጣች ቀጥታ ወደ ሥራ እንድትገባ አደረገቻት። ቤት በማጽዳት ብቻ ሌሊቱ ነጋ።
በጽዳቱ ማዳም አልረካችም። ያፀዳችውን ቤት ድጋሚ እንድታፀዳ በቁጣ አዘዘቻት። ትዕዛዟ የንቀት ዕይታ የታከለበት ነበር። በእርግጥ ወደ ሳዑዲ ስትመጣ የቤት ጽዳትም ሆነ ሌላ የሙያ ስልጠና አልወሰደችም። ሌላው ቀርቶ የቀለም ትምህርትም አልነበራት። የቀጣሪዋ የንቀት አተያይ ቢያናድዳትም ልምድ የሌላት መሆኑን ታሳቢ አድርጋ ድጋሚ ቤቱን አፀዳች። ሰሚራ ሥራዋ ጽዳት ብቻ ነበር። የቤት ብቻ ሳይሆን ልብስን ጨምሮ ማንኛውም ጽዳት ሥራ እሷን የሚመለከት መሆኑን አወቀች። ሆኖም ይሄን ሥራ የምትሰራው ቀጣሪዋ ቤት ውስጥ ብቻ አልነበረም። እናቷ ቤት በመኪና ወስዳ ዕለት ከዕለት ታሰራት ነበር።
አንዲት ኢትዮጵያዊት ባልደረባዋ እስክትነግራትና ሁለት ዓመት እስኪሞላት የአሰራር ስርዓት እንጂ ማዳሟ የጫነችባት የበደል ቀንበር አይመስላትም ነበር። ከዕውነታው ጋር ተዳምሮ ጫናው እየሰለቻት፤ እየከበዳትና እያዳከማት ስትመጣ እናቷ ቤት ሄዳ ተጨማሪ ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ እንዳልሆነች ለአሰሪዋ ነገረቻት። በዚህም ከአሰሪዋ ጋር ተጋጩ። ከመካ ወደ ቤት ስታመጣ ተቀብላት ያስቀመጠችውን ፓስፖርቷን እንድትመልስላት ብትጠይቃት በካፋላ ሕግ ስርአት የሚቀመጠው እሷ ጋር በመሆኑ ልትመልስላት እንደማትችል ነገረቻት። ከቀጣሪዋ ቤት ለመጥፋት ዕቃዋን ስትሰበስብ ይሄን የባርነት የአሰሪና ሠራተኛ አገዛዝ እንድትቃወምና መብቷን እንድታስከብር ግንዛቤ ያስጨበጠቻት ኢትዮጵያዊቷ ባልደራዋ ሕገወጥ ተብላ በፖሊስ ለመያዝ ማቀዷን ገለፀችላት። ሰሚራ ሁለት ዓመት ሊሞላትና ኮንትራቷን ልትጨርስ የጥቂት ወራት ዕድሜ ስለቀራት እዛም እዚህም እንደ ባሪያ ሌት ከቀን እያገለገለች ቀጣሪዋ ጋር ለመቀመጥ ተገደደች።
ማዳሟ ቀደም ብላ ቀጥራት የነበረችውን ኢትዮጵያዊቷን ባልደረባዋን መክረሽ ልታበሪብኝ የነበርሽው አንቺ ነሽ በማለት ኮንትራቷ ሳያልቅ ወደ ኢትዮጵያ መለሰቻት። አሁን ይባስ ብሎ ወደ አገሯ የተመለሰችው ባልደረባዋ ትሰራው የነበረውን ጨምሮ አጠቃላዩ የቤት ሥራ የሰሚራ ሆነ። እስከ ሁለት ዓመት እንደምንም ተቋቁማው ቆየችና ወደ አገሯ እንድትመልሳት ጠየቀቻት። “ሆኖም ዛሬ ነገ እልክሻለሁ እያለች ቪዛና ውሏን ሳታድስላት ቀረች፤ ሰሚራ በዚህ ምክንያት ሳዑዲ ውስጥ መንቀሳቀስ ባለመቻሏ ጉልበቷ ለበርካታ ዓመታት በአሰሪዋ ሲበዘበዝ መቆየቱን በምሬት ትናገራለች።
ለመጥፋት በሞከረችበት ወቅት የተሳፈረችበት ታክሲ ሾፌር ደስ አልሽኝ በማለት አባላዋን ገፎ ሊስማት ሲሞክር በመቃወሟ፤ ”ለዚህ ነው እንዴ የሚገርምሽ” በማለት አሳቻ ቦታ ወስዶ ሊደፍራት በማሰብ አቅጣጫውን ለውጦ ሲነዳ ዘላ በመውረድ አደጋ ደርሶባታል። ለዓመታት በነፃ ስታገለግል ቆይታ በምሬት ጥላ በወጣችበት ወቅት ደግሞ ህገወጥ ተብላ ዘብጥያ ለመውረድ በቅታለች ፤ ከዓመታት በኋላ በመንግስት አማካኝነት ወደ አገሯ ለመመለስ መቻሏንም ታወሳለች።
‹በህገወጥ መንገድ ከሀገር ወጥተው በእንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ከሚገኙት መካከል ካለፈው ሚያዝያ 2014 ዓ∙ም ጀምሮ 84 ሺህ 258 ዜጎችን መልሰናል። አሁንም እየመለስን እንገኛለን›› የሚሉት ደግሞ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕገወጥ ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ድጋፍና ክትትል አስፈፃሚ ዳይሬክቶሬት ኃላፊ አቶ ደረጀ ፈቅይበሉ ናቸው። መንግስት ዜጎቹ በሀገራቸው ተከብረው እንዲሰሩ ለማስቻል ሁኔታዎችን አመቻችቶ በማህበር ተደራጅተውና በግል ወደ ሥራ እንዲገቡ እያደረገ ነው።
በተለይም በግብርና ዘርፍ እና የዚሁ አካል በሆነው በሌማት ትሩፋት ከአረብ ሀገር ተመላሽ ሴቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱንም ገልጸውልናል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥር 2/2015