በቀደሙት ኦሊምፒኮች ከአትሌቲክሱ ቀጥሎ ሀገሪቱ ትወከልበት እንደነበረ የሚነገርለትን ብስክሌት ወደ ቀድሞ ስምና ክብሩ ለመመለስ ከሚታትሩ የሀገሪቱ ክፍሎች አዲስ አበባ ይጠቀሳል። ከሜልቦርን እስከ ባርሴሎና ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በብስክሌት የነበራት ተሳትፎ እስከ ቅርብ ጊዜ ጠፍቶ ቆይቷል። ሆኖም በአውሮፓ በተለያዩ ሀገሮች አዘውትሮ በሚካሄዱ የብስክሌት ውድድሮች ላይ በወንዶችም ሆነ በሴቶች ተስፋ የሚሰጡ ተወዳዳሪዎች ታይተዋል። በዚህም ሪዮ ኦሊምፒክ ላይ በወንድ፣ ቶኪዮ ላይ ደግሞ በሴት ብስክሌተኞች ወደ ተሳትፎ መመለስ ተችሏል።
የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ስፖርቱን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር ተስፋ የሚጣልባቸው እንቅስቃሴዎች እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በከተማ አስተዳደር ደረጃም የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለከተማው ብስክሌት ስፖርት ውጤታማነት የተለያዩ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች ነድፎ በመተግበር ላይ ይገኛል። ከዕቅዶቹ መካከል ፌዴሬሽኑ ጠንካራ የፋይናንስ አቅም እንዲኖረው የሚደረገው የስፖንሰርሽፕ ስምምነቶች ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዝ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ከመደበኛ የውድድር መርሐ ግብሮች ጎን ለጎን የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ላይ የሚደረገው እንቅስቃሴ ነው።
ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ብስክሌቱን በከፍተኛ በጀት እያንቀሳቀሱ ከሚገኙት የትግራይና የአማራ ክልሎች አንፃር ይህ ነው የሚባል ጠንካራ የበጀት ድጋፍ የለውም። በዚህ ረገድ የከተማውን የብስክሌት ስፖርትና ውድድር በላቀ ደረጃ ለማሳደግ የአጋር ባለድርሻ አካላት ሚና የላቀ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብስክሌት ፌዴሬሽን የከተማዋን የብስክሌት ውድድር ደረጃውን ለማሳደግ ከፍቅር ያሸንፋል በጎ አድራጎት ማኅበር ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የሁለትዮሽ የፊርማ ስምምነት ሰሞኑን አካሂዷል።
በፕሮግራሙ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ረዘነ በየነ የከተማዋን የብስክሌት ስፖርት ወደ ቀድሞ ክብሩና ተወዳጅነት ለመመለስ ፌዴሬሽኑ በበጀት ዓመቱ በርካታ ዕቅዶችን አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም ከፍቅር ያሸንፋል በጎ አድራጎት ማኅበር ጋር የተደረገው ስምምነት ለከተማዋ የብስክሌት ስፖርትና ለታዳጊ ብስክሌተኞች ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አብራርተዋል።
የፍቅር ያሸንፋል የበጎ አድራጎት ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ሚስባህ ከድር በበኩላቸው፣ በሀገራችን ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅ የሆነውን የብስክሌት ስፖርት ውድድር እንደ አዲስ አበባ ከተማ ውጤት እንዲመጣና ተተኪዎች በስፖርቱ እንዲሳቡ ከፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ ለመሥራት የስምምነት ፊርማው ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።የጋራ የስምምነት ሰነዱ መነሻ ሀሳቦች ይዘትን የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ ተረፈ አቅርበዋል ።
በፕሮግራሙ የተገኙት የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ማኅበራት ማደራጃና ውድድር ዳይሬክተር አቶ አያሌው ታደለ በበኩላቸው፣ ስፖርት ሕዝባዊ መሠረትን ይዞ እንዲስፋፋ ከመንግሥት ድጎማ መላቀቅና የራሱን ገቢ ማስገኛ ዕቅዶች መንደፍ ተገቢ በመሆኑ በአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽንና በፍቅር ያሸንፋል በጎ አድራጎት ማኅበር መካከል የተደረገው ስምምነት ለሌሎች ፌዴሬሽኖችም አርአያነት እንዳለው አስረድተዋል።
የሁለትዮሽ የሥራ ውል ስምምነቱ በአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በአቶ ረዘነ በየነና በፍቅር ያሸንፋል በጎ አድራጎት ማኅበር ፕሬዚዳንት በአቶ ሚስባህ ከድር መካከል ተፈርሟል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 1/2015