በወርሀ ታኅሳስ ዕለተ ቅዳሜ አንድ ቀን ከመሥሪያ ቤት ወጥቼ ወደ ማደሪያዬ ለመንጎድ ተነሳሁ። ከቢሮዬ እንደወጣሁ ዓይኖቼ ታክሲ ወደሚያዝበት አቅጣጫ አማተሩ። ትንሽ ሄድ እንዳልኩ “እ ና ትህ እን…….” የሚል ድምጽ ሰማሁ አንገቴን ወደ ኋላ ቀለስ አድርጌ ከእግር ጥፍሩ እስከ እራስ ፀጉሩ በግልምጫ ጠረባ ጥየው ጉዞየን ቀጠልኩ!
አዲስ አበባ ላይ ማህበራዊ መስተጋብር እየላላ ሄዷል ቢባልም፤ ታክሲ ውስጥ ግን ገና አልቀረም። ተቃቅፎ ሚስጥር እንደሚነጋገር ሰው አንዱ ባንዱ ጆሮ ስር ተወሽቆ፤ ያንደኛው እግር በሌላኛው ላይ ተረማምዶ አንዱ ሲረግጥ ሌላኛው ሲረገጥ ችግር የለውም “ችግር የለውም” ተባብሎ በፍቅር ሲጓዝ ይቆይና ፈርማታ ሲደርስ ሁሉም መንጫጫት የተለመደ ነው።
ታድያ በዚህ ጊዜ መደማመጥ ላይኖር ይችላል። “ወራጅ አለ” አንደኛው ተሳፋሪ ከኋላ ሆኖ ተጣራ። ማንም አልሰማውም። ደግሞ “ኧረ ወ..ራ..ጅ!” ከመታፈኑ የተነሳ ድምጹ ተቆራርጦ ነው የሚሰማው። በጣም ተናዶ “እንዴ ኧ ረ ወ ራ ጅ!” አለ። ሾፌሩ “እ፤ ወራጅ አለ?” ሲል ጠየቀ። ተሳፋሪው “አይሰማህም? እናትህ……” ጆሮዬን ጎረበጠኝ። እንደ መጀመሪያው እንዳልገለምጠው ሰው ከመተፋፈኑ የተነሳ ተናጋሪው አይታይም። ብስጭት አልኩ። እሱም ወዲያው እንዴት እንደወጣ ሳላየው ከዓይኔ ተሰወረ።
እኔም ከአንደኛው ወርጄ ወደሌላኛው ታክሲ ገባሁ። አሁን ምንም የለም። “እሰይ ተመስገን!” እንያልኩ ታክሲው እየከነፈ ሦስተኛው ፌርማታ ጋር አደረሰኝ። ወርጄ ሦስተኛውን ታክሲየን ለመያዝ ወደ ፊት እየተራመድኩ ከጎኔ እየተቀላለዱ ከሚሄዱ ሰዎች አጠገብ ደረስኩ። በንግግራቸው መሃል አንዱ “እናትህ…..” አለ። “እህ ለካ በቀልድም መሃል ይባላል?” ንዴት የቀላቀለ ግርምት አስተናግጄ ጉዞዬን ቀጠልኩ።
ሦስተኛው ታክሲ ላይ ገብቼ አረፍ እንዳልኩ አንዱ እቃ አሸክሞ መጣና “ረዳት እንካ ጫነው”። ረዳቱም ቀና ብሎ አየና “ከነራስህ….. ትከፍላለህ” አለ። ተሳፋሪውም ኮስተርተር ብሎ “እናትህ…….፤ ዘረፋ ነው የወጣሃው?” የሚገርመው ደግሞ እንዲህ ባዩ ትልቅ ሰው ነው፤ ማለቴ ያው በእድሜው ትልቅ ነው። እንዴ? የዛሬው ደግሞ አያምጣው ነው! አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሦስቴ? ሰቀጠጠኝ!
ከሌላ አካል እጣላ ይመስል ጆሮዬን ለምን ትሰማለህ ብዬ ለመቆጣት ዳዳኝ። ዳሩ ግን ከራሴ ጋር ግብግብ ከመግባት ውጪ ምንም ማድረግ እንደማልችል ሲገባኝ ቶሎ ከታክሲው ወርጄ ኮበለልኩ። ለማንኛውም የዛሬ ትዝብቴ ከትዝብትነት አልፎ ብስጭት አሳድሮብኛል። አንዳንድ ቀን ጆሮዬ ጠላቴ ሆኖ ቀኔን ያበላሸዋል።
ምን አለ ግን ጆሮዬ ለይቶ ቢሰማ ብዬ ከራሴ ጋር ግብ ግብ እገጥማለሁ። እርሱስ ይሁን ከፉንም ደጉንም መስማት መቼም ተፈጥሮው ነው፤ ግን ክፉውን ከበጎው ለይቶ የመያዝ ስልጣን የተሰጠው ሕሊናዬ ሥራው ምን ሆነና ነው እንዲህ ስሆን ዝም ብሎ የሚያየኝ? መቼስ ከራስ መጣላት አያደርገው የለ!
በቃ እንዲህ ዓይነቱን ቃል በሰማሁ ቁጥር ሁሌም እረበሻለሁ፣ ከራሴ ጋር እጣላለሁ። አንዳንዴ ሰዎች ከመሠረታቸው በእምቧይ ካብ የተገነቡ ይመስላሉ፤ የለበጣ ሳቅ ይሳለቃሉ፤ በእጃቸው የጎረሱበትን መሶብ በእግራቸው ይረግጣሉ። “እ ና ትህ/ሽ እንዲ ትሁን” የሚል እጅጉን ፀያፍ ቃል ይጠቀማሉ።
በእርሷ ዘንድ ያለልዩነት እኩል ትዳኛለህ። አንተ በጎም ሆንክ ክፉ፣ ለጋስም ሆንክ ንፉግ፣ አዋቂም ሆንክ አላዋቂ፣ ብልህም ሆንክ ሞኝ፣ ፉንጋም ሆንክ መልከ መልካም እዮርና ራማ በመሰለው ታዛህ እኩል ቦታ አለህ። ሰዓቱ ይለያይ እንጂ በአካላቷ ያልታዘልክበት ጊዜ የለም።
በሆዷ ተሸክማሀለች፤ በደረቷ አቅፋ በጡቶቿ ሕይወት ምግብ መግባሃለች፤ በጀርባዋ አመቻችታ አዝላሀለች፤ በከንፈሯ ስማሀለች፤ በእጆቿ ፈትፍታ አጉርሳሃለች፣ እርሷ ተንገላታ፣ ጠቁራና ከስታ አንተን አስመችታ አሳድጋሃለች።
ህልሟ ላንተ መኖር ነው! ከዚያ ውጪ ዓለም ለእርሷ ምኗም አይደለም። ሳይኖራት እራሷን መስዋዕት አድርጋ ያኖረችህን መላው ሰውነቷን በወርቅ ብስታጌጣት ውለታዋን ልትከፍላት አችልም። ምክንያቱ ደግሞ እርሷ ሳትሰስት ሁሉንም የሰጠችህ ከሌላት ላይ ሲሆን አንተ ግን ሰጠሁ ብትል እንኳን ኖሮህ ከተረፈህ ላይ ነው።
ይህ ሁሉ ግን በደግነትህ አይደለም። እናት የመሆኗ ድንቅ ሚስጥርና በማያልቀው ፍቅሯ የተነሳ እርሷው ያደረገችው እንጂ። “ዓባይን በጭልፋ እንዲሉ” የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል ትንሽ ስለ እውነታው ልሞነጫጭር አስቤ ነበር። ግን አልቻልኩም በምናብ ቀረሁ። እንዴያው በኮልታፋ አንደበቴ ያቅሜን ልንተባተብ ብዬ እንጂ ድሮስ በምን አቅሜ ችዬ እርሷን ልገልጻት፣ ስለእርሷስ መናገር እችላለሁ! ቃላት አጥንትን የመስበር ታላቅ ኃይል አላቸው ቢባልም እርሷን ለመግለጽ ግን አቅመ ቢሶች ናቸው።
በዓለም ላይ ውድ የሆኑ እንቁዎችን ገዝተህ ልታጌጥባቸው ትችል ይሆናል። እናትነትን ግን ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ቢል ልትገዛትም ልትሠራትም አትችልም። እሷ የፈጣሪ ስጦታ ናት። ግን እናትን ያህል ነገር ጠርቶ ጸያፍ ቃል መናገር ምን ያህል ትንሽነት ነው? ምን ያህልስ ከሰውነት መውረድ ነው? አንዳንዶች “እናትህ እንዲህ ትሁን፣ እናትህ…” ይሉህና ለምን ስትላቸው “እርድና ነው” ይሉሃል።
እናትንና ሀገርን ተሳድበህ የቀለድክ ቀን ያንተ ቂልነት ገደብ አጥቷል ማለት ነው። ይሁን እንጅ እንደዚህ ዓይነት ቃላትን መስማት እየተለመደ መጥቷል። ሥራ ቦታዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ መዝናኛ ቦታዎች፣ ታክሲዎች ውስጥና ታክሲ ተራዎች……። እንዲህ ዓይነት ሰቅጣጭ ቃላት ባላንጣ አንደበቶች በየቀኑ የሚሰናዘሯቸው የዕለት ተዕለት የአፍ ማሟሻዎች ሆነዋል።
በእርግጥ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለሁም እንደዚህ ዓይነት ቃላት “አራዳ ነን” ባዮች አቻዎቼ ይጠቀሙ እንደነበር አስታውሳለሁ። ግን እንደዚህ በትልልቅ ሰዎች አንደበት ጭምር በመስማቴ እጅጉን ገርሞኛል፣ አናዶኛልም። እናትነት ተቀድቶ የማይደርቅ የርህራሔ ምንጭ ነው። እናትነት ተነቦ ያላለቀ ሰምና ወርቅ ነው። ምን አለ ታድያ ውለታቸውን መክፈል ባንችል እንኳን ስማቸውን በመጥፎ ባናነሳ?
እንደዚህ ዓይነቱን ጸያፍ ቃላት የማይጠቀሙ ሰዎችስ ከጥፋተኝነት ድነው ይሆን? “ምናገባኝ” ብለን ዝም ለምንልስ? ለዚህ ጥያቄ መልሱ ሁላችንም ጋር ነው። የሚገስጽና እንደትውልድ ወደተሳሳተ ጎዳና ውስጥ ስንገባ አቅጣጫ የሚያመላክት መጥፋቱ ያሳስበኛል። ከባህል ወግ ልማዳችን ተራቁተን እርቃናችን የቀረን መስሎ ይሰማኛል። እናት ሁሉንም ቻይ ነች። ለሚያጎርሳትም ለሚነክሳትም እኩል ያው እናት ነች። ታድያ እኔ እናትን በምንም ይሁን በምን በበጎ እንጂ በመጥፎ ስሟ ባይጠራ መልካም ነው ባይ ነኝ። አይ ብለህ ብትጠራ ግን እናት ሀገር ናትና መሠረትህን በእምቧይ ካብ ሠርተሀልና መጨረሻህ መናድ ይሆናል። ክብር ለእናቶቻችን!!!
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29 ቀን 2015 ዓ.ም