ዶክተር ረቤካ መስፍን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ ጠቅላላ ሃኪም ናት። በዚሁ ሆስፒታል በተቋቋመው ሴንተር ፎር ፕሮፌሽናል ኤንድ ኢንስቲትዩሽናል ዴቬሎፕመንት ውስጥ የፕሮጀክትና ቢዝነስ ዴቬሎፕመንት ፕሮግራም ኦፊሰር ሆናም ታገለግላለች።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የእሳት፣ የትራፊክ፣የኤሌክትሪክና ሌሎችም ድንገተኛ አደጋዎች እንደሚከሰቱ የምትናገረው ዶክተር ረቤካ፤ ከነዚህ ድንገተኛ አደጋዎች መካከል በተለይ ደግሞ በተሽከርካሪ የሚደርሰው አደጋ ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚወስድ ትጠቁማለች።
በሀገሪቱ ብሎም በዚሁ በአዲስ አበባ ከተማ ለነዚሁ ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ የሚሰጡ የተለያዩ ጤና ተቋማት ቢኖሩም ከአደጋው ብዛትና ስፋት አንፃር በቂ እንዳልሆኑ ትናገራለች። ተቋማቱ ለድንገተኛ አደጋ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችላቸውን የባለሙያ ቁጥርና የህክምና መሳሪያዎችን እንዳላሟሉም ነው የምትጠቁመው።
እርሷ በምትሰራበት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የድንግተኛ አደጋዎች ህክምና መስጫ ማእከል ምንም እንኳን በበቂ ባለሙያና የህክምና መሳሪያዎች የተሟላ ቢሆንም ባለው የባለሙያ ቁጥርና የህክምና መሳሪያ ለአደጋው ምላሽ በመስጠት ሂደት ክፍተቶች እደሚታዩም ትጠቅሳለች።
‹‹በቅርቡ ከእስራኤል ሀገር ፖሪያ ሜዲካል ትምህርት ቤት በመጡ የድንገተኛ ህክምና ባላሙያዎች ቡድን በድንገተኛ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የአራት ቀናት ስልጠና አግኝቻለሁ›› የምትለው ዶክተር ረቤካ፤ የህክምና አገልግሎቱ በኢትዮጵያ እየተሰጠ ቢሆንም አሰልጣኞቹ አገልግሎቱን ያሳዩበት መንገድ ከእኛ ሀገር የተለየ ነው ትላለች።
በተለይ ደግሞ በድንገተኛ አደጋ ህክምና ወቅት አንድ ነገር ቢከሰት በምን መልኩ ታካሚውን መንከባከብና ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ሰጥቶ ወደጤና መመለስ እንደሚቻል አይን በሚገልጥ መልኩ ከእነርሱ ሙያዊ እውቀት እንዳገኘች ታስረዳለች። በተለይ ደግሞ በድንገተኛ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ጨብጪያለሁ ብላ ታስብ እንደነበር፤ ነገር ግን ከስልጠናው በኋላ አገልግሎት አሰጣጡን ከተለያዩ አንግሎች እንድትረዳ እንዳስቻለት ታብራራለች።
በተለይ የህክምና ቡድኑ አባላት በዚሁ ዘርፍ የተለያዩ ልምዶች ያሏቸው በመሆኑና በተለያዩ ሀገራት በመንቀሳቀስ ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ ያካፈሉ እንደመሆናቸው በዘርፉ ያላትን የእውቀትና ክህሎት አድማስ እንዳሰፋላትም ነው ዶክተር ረቤካ የምትናገረው።
ይህም ቀደም ሲል በድንገተኛ አደጋ ህክምና ምላሽ አሰጣጣ በነበራት እውቀት ላይ ተጨማሪ ግንዛቤ እንዲኖራት ማስቻሉንም ትጠቁማለች። በተለይ ደግሞ በደንገተኛ አደጋ ህክምና አሰጣጥ ሂደት ምን አይነት ችግር ሊገጥም እንደሚችልና ይህን ችግር እንዴት መፍታት እንደሚቻል ከህክምና ቡድኑ በቂ ክህሎትና እውቀት እንዳገኘችም ትገልፃለች።
የስልጠና አሰጣጡም በሲሙሌሽንና በትክክልም ታካሚ በሚመስሉ አሻንጉሊቶች የተደገፈ መሆኑንም ጠቅሳ፤ እንስሳትንም ጭምር እንደታካሚ በመጠቀም አደጋ ቢደርስ እንዴት ማከምና ህይወት ማዳን እንደሚቻል እንደተማረች ታስረዳለች።
በኢትዮጵያ የድንገተኛ አደጋ ምላሽ የሚሰጡ የህክምና ተቋማት እንዳሉ ሆነው በውስጣቸው ለዚሁ ህክምና አገልግሎት የሚያግዙ የህክምና መሳሪያዎች ብዙም እንደሌሉ የምትናገረው ዶክተር ረቤካ፤ ይህን በማየት የህክምና ቡድኑ ድጋፍ ለማድረግ ቃል እንደገቡም ነው የምትጠቅሰው። በስልጠናው ወቅት ሲጠቀሙባቸው የነበሩትን አንዳንድ እቃዎችን አስረክበው ለመሄድ ዝግጁ መሆናቸውንም ትገልፃለች።
ከሁሉ በላይ ግን በኢትዮጵያ የድንገተኛ አደጋ ህክምና አገልግሎትን በተሟላ መልኩ ለመስጠት አሁንም ብዙ የሚቀሩ ነገሮች ቢኖሩም ባለው ሀብት ሌሎች አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም የህክምና አገልግሎቱን የተቃና ማድረግ እንደሚቻል ትልቅ ትምህርት መውሰዷን ትናገራለች።
ስልጠናው በድንገተኛ አደጋ ህክምና አገልግሎት ወቅት ‹‹ይሄ ስለጎደለ ይህን አይነት ህክምና መስጠት አይቻልም›› የሚለውን የሰበረና አማራጮች ሁሌም እንዳሉ ግንዛቤ ያስጨበጣት ስለመሆኑም ነው የምታስረዳው።
‹‹የህክምና ቡድኑ ከሰጠው የድንገተኛ አደጋዎች ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በቂ እውቀትና ክህሎት አዳብሪያለሁ›› የምትለው ዶክተር ረቤካ፤ የህክምና መሳሪያዎች እጥረት እንዳለ ሆኖ መሳሪያዎቹ ቢሟሉ ብዙ መስራት እንደሚቻልና ባይሟሉም ባለው መሰሪያ ተጠቅሞ ብዙ ማድረግ እንደሚቻል ከስልጠናው እንደተረዳች ትናገራለች።
በሌላ በኩል ደግሞ አሁን የተጀመረው ስልጠና በኢትዮጵያና እስራኤል መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ከድንገተኛ አደጋ ህክምና በዘለለ በሌሎችም የጤና ዘርፎች ያሉ ትምህርቶችን ለመቅሰም እድል እንደሚሰጥም ትጠቁማለች። ኢትዮጵያውን ከእስራኤላውያን በድንገተኛ አደጋ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪ ትልቅ ትምህርት እንደወሰዱ ሁሉ እስራኤላውያንም ከኢትዮጵያ ተመሳሳይ ትምህርት መውሰዳቸውን ትጠቅሳለች።
የህክምና ቡድኑ ስልጠናውን የሰጠው በንድፈ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጭምር በመሆኑ በስራ ላይ ተግበራዊ የሚሆንና እርሷም ያገኘቸውን የንድፈ ሃሳብና የተግባር ትምህርት በስራዋ ላይ ተግበራዊ እንደምታድርግም ነው የምትናገረው። እንዲህ አይነቱ ስልጠና በተመሳሳይ ለሌሎችም ኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎች ቢደርስ በዚሁ ህክምና ዘርፍ ያለውን ችግር በመጠኑም ቢሆን መቅርፍ የሚያስችል መሆኑንም ትጠቁማለች።
ዶክተር ባራክ ሊቪት እስራኤል ሀገር በሚገኘው ፖሪያ ሜዲካል ሴንተር አጠቃላይ የቀዶ ህክምና ክፍል የድንገተኛ አደጋ ህክምና ዩኒት ዋና ዳይሬክተር ናቸው። በዚሁ ክፍልም የድንገተኛ አደጋ ቀዶ ሀኪም ሆነው ይሰራሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት ከዚሁ የህክምና ማእከል የተውጣጣው ቡድን ወደ ኢትዮጵያ የመጣበት ዋነኛ ምክንያት በኢትዮጵያውያንና በእስራኤላውያን የህክምና ባለሙያዎች መካከል ያለውን እርስ በርስ ግንኙነት በሁለንተናዊ መልኩ ለማጠናከር ነው።
በተጨማሪም የህክምና ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በሁለቱ የህክምና ባለሙያዎች መካከል በተለይ ደግሞ በጤው ዘርፍ ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ አንዳቸው ለሌላቸው እንዲያጋሩ ብሎም እንዲማማሩ ያስችላል።
ወደ አፍሪካ ሀገራት በበጎ ፍቃደኝነት ሙያቸውን ለማካፈል ሲመጡ ኢትዮጵያ ሶስተኛቸው መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ባራክ፤ በኢትዮጵያና በእስራኤል መንግስትታ መካከል ባለው ጠንካራ ግንኙነት ተነሳሽነቱን ወስደው እንደመጡ ይናገራሉ።
በድንገተኛ አደጋዎች ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከአዲስ አበባ ከተማ ጤና ተቋማት ለተውጣጡና በዚሁ ዘርፍ ላይ ለሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ ለአራት ቀናት ከሌሎች የስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ስልጠናውን ሲሰጡ መቆየታቸውንም ይጠቁማሉ።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በነበራቸው የአራት ቀናት ቆይታ ኢትየጵያውያን ሀኪሞችና ነርሶች በድንገተኛ አደጋዎች ህክምና ዙሪያ ያላቸው ልምድና ተሞክሮ ብሎም ሙያዊ ብቃታቸው ከጠበቁት በላይ እጅግ እንዳስደነቃቸው ይናገራሉ። በዚሁ ህክምና ዘርፍ በደምብ የሰለጠኑ መሆናቸውንና ለስራውም የሚመጥኑ ስለመሆናቸው እንደተረዱም ይጠቁማሉ።
በድንገተኛ አደጋዎች የህክምና ዘርፍ በእስራኤልና በካናዳ ትምህርታቸውን መከታተላቸውን የሚናገሩት ዶክተር ባራክ፤ ኢትዮጵያውያንም በዚሁ የህክምና ዘርፍ ያላቸው እውቀትና የክህሎት ደረጃ ሌላው አለም ካለው ጋር የሚስተካከል እንጂ የማያንስ መሆኑን እንዳወቁ ይገልፃሉ። አዳዲስ አውቀት የመቀበል ዝንባሊያቸውም ከፍተኛ በመሆኑ የህክምና ቡድኑ ስልጠናውን ሲስጣቸውም ብዙም እንዳለተገሩም ነው የሚናገሩት።
በስልጠናው በአዲስ አበባ ከሚገኙ የጤና ተቋማት የተውጣጡና በተለያዩ ደረጃዎች በድንገተኛ አደጋዎች ህክምና አገልግሎት ላይ የሚሰሩ ነርሶችና ሀኪሞች መሳተፋቸውንና የስልጠና መስጫ ማእከሉን ያመቻቸው ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ ማመቻቸቱን ይጠቁማሉ። በዚህም የህክምና ቡድኑ በድንገተኛ አደጋ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ በኩል ያለውን ልምድና ተሞክሮ ለሰልጣኞች ማካፈሉን ይገልፃሉ።
እንደ ዶክተር ባራክ ገለፃ የህክምና ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የመጀመሪያው ሲሆን በዋናነት በድንገተኛ አደጋዎች ወቅት ስለሚሰጡ ህክምና አይነቶች፣ ቀዶ ህክምናዎችና በአደገኛ ጉዳቶች ወቅት ስለሚሰጡ የህክምና ምላሾች ዙሪያ ያለውን ልምድና ተሞክሮ አካፍሏል።
ግማሹ የስልጠና ክፍለ ግዜ ትምህርታዊ፣ ተግበራዊና የቀዶ ህክምና አሰጣጥ ሂደቶች ላይ ባሉ የንድፈ ሃሳብ ትምህርቶች ላይ አተኩሯል። በሌላው የስልጠና ክፍለ ግዜ ደግሞ ሰልጣኞች /trauma simulation/ በተግባር የተደገፈ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ፣ የቀዶ ህክምና ሂደትና ትምህርት እንዲወስዱ ተደርጓል።
በመጨረሻም ሰልጣኞች በንድፈ ሀሳብና በተግባር የወሰዱትን ትምሀርት በማቀናጀት ከዚህ ቀደም የነበራቸውን እውቀትና ክህሎት በማጣመር እንዲያሳዩ ተደርጓል።
በየትኛውም ሀገር በድንገተኛ አደጋዎች ህክምና አገልግሎት አስጣጥ ሂደት ክፍተቶች አሉ። በኢትዮጵያም የሚታየው ክፍተት ከሌላው አለም የተለይ አይደለም። ስልጠና በተሰጠበት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በሚገኘው የድንገተኛ አደጋዎች ህክምና ማእከል ውስጥ አንዳንድ ግዜ በአገልግሎት አሰጣጥ ስርአቱ ላይ ሌላ ግዜ ደግሞ የህክምና መሳሪያዎች በበቂ ሁኔታ ያለመኖር ክፍተቶች ይታያሉ። ነገር ግን እንዲህ አይነቱ ክፍተት ሌላው ሀገር ላይ ከሚታየው የተለየ አይደለም።
ከዚህ አንፃር የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ስርአቱን በማሻሻልና አገልግሎቱን ለመስጠት አስፈላጊ የሆኑ የህክምና መሳሪያዎችን በማሟላት ለድንገተኛ አደጋዎች የሚሰጠውን ምላሽ ማስተካከል ይቻል። በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ የድንገተኛ አደጋዎች ሀክምና አገልግሎትን የሚሰጡ የጤና ተቋማት ያላቸውን ሃብት በመከፋፈልና በሚፈለገው ቦታ ላይ በመመደብ ያለባቸውን ችግር ማቃለል ይችላሉ።
በተለይ ደግሞ በይበልጥ ህይወት ሊያድኑ የሚችሉ የህክምና መሳሪያዎችን በአግባቡ በመጠቀምና ከሌሉም በማሟላት በድንገተኛ አደጋ ህክምና ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት ይቻላል። በተቃራኒው ደግሞ ብዙም ወጪ የማያስወጡና ለህክምና አገልግሎቱ ብዙም የማያስፈልጉ የህክምና መሳሪያዎች ላይ የሚወጣውን በጀት መመጠን ያስፈልጋል።
በድንገተኛ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ኢትዮጵያውያን ከእስራኤላውያን የሚጋሯቸው በርካታ ተሞክሮዎች አሉ። በተለይ ደግሞ በእስራኤል ያለው የድንገተኛ አደጋዎች ህክምና አገልግሎት አሰጣጡ ምንም እንኳን ፍፁም ባይሆንም መልካም የሚባል በመሆኑ ውጤታም የድንገተኛ አደጋዎች ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ በመዘርጋት ሂደት ኢትዮጵያውያን ከእስራኤላውያን ብዙ ትምህርት ሊወስዱ ችላሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ እስራኤላውያን ለጤና ስርአቱ የሚመድቡት በጀት አነስተኛ ነው። ይህም ከኢትዮጵያውያን ጋር ያመሳስላቸዋል። ነገር ግን እስራኤላውያን በጀቱን ለምፈለገው ተግባር በአግባቡ በማዋል ላይ ጥሩ በመሆናቸው ኢትዮጵውያን ከዚህ ጥሩ ትምህርት ሊወስዱ ይችላሉ።
ዶክተር ባራክ እንደሚሉት በእስራኤል በርካታ የጦርነት ቀጠናዎች አሁንም እንዳሉና ድንገተኛ የሽብር ጥቃት ቢደርሱ እንኳን ለዚህ ምላሽ ሊሰጡ የሚችሉ የድንገተኛ አደጋዎች ህክምና ማእከላት እንዳሉ፤ በእንዲህ አይነቱ ክስት ወቅት ሀገሪቱ ሰፊ ተሞክሮ አላት። በጦተርነት ወቅት የድንገተኛ አደጋዎች ህክምና አገልግሎት ስርአት ውጤታማ ከሆነ በአገልግሎቱ የበርካታ ሰዎችን ህይወት ማዳን ይቻላል። ይህም የሚሆነው በርካታ የሚመለከታቸው ተቋማት ተቀናጅተው ሲሰሩና ሀብትን በአግባቡ ከፍፋሎ ጥቅም ላይ ማዋል ሲቻል ብቻ ነው።
በኢትዮጵያም በህክምና ዘርፉ ያለውን እውቀት፣ክህሎትና ሀብት በአግባቡ መድቦ በመጠቀም ጦርነቱ ካስከተለው የአካል ጉዳት በኋላ ያለውን የስነ ልቦና ስብራት ማከም ይቻላል። በዚህም አስራኤልና ኢትዮጵያ የቆየ ግንኙነት ያላቸው እንደመሆኑ እስራኤል ለኢትዮጵያ በህክምናው ዘርፍ እውቀትና ልምድን ከማካፈል ጀምሮ የህክምና መሳሪያዎችን በማቅረብ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትጠቀጥላለች።
በኢትዮጵያ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ቁጥር አነስተኛና ውስንና በከተሞች አካባቢ ብቻ የተገደበ መሆኑ ይነገራል። ካለው ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር አንፃርም ተመጣጣኝ የህክምና ተቋማትና በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሞያዎች አሉ ተብሎ አይታሰብም።
ከዚህ አንፃር ሀገሪቱ ባላት ውስን የድንገተኛ አደጋ ህክምና ተቋማትና የጤና ባለሙያዎች ዜጎቿ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የጎደለውን ሞልታ ያላትን ሀብት በተገቢው ቦታ መድባ መስራት ይጠበቅባታል።
ይህ ከሆነ በዚሁ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የሚታዩ ችግሮች ተቀርፈው ስርአቱ እስኪስተካከል ድረስ በድንገተኛ አደጋዎች የሚቀጠፉ የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ማዳን ይቻል። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎች ከእስራኤላውያን ብዙ ትምህርት ሊቀስሙ ይገባል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29 ቀን 2015 ዓ.ም