ከኮምቦልቻ ሪጆፖሊታን ከተማ አስተዳደር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ኮምቦልቻ ከተማ 1943 ዓ.ም ነው የተቆረቆረችው። ኮምቦልቻ ከተማ በ1965 ዓ.ም ጀምሮ በማስተር ፕላን የምትመራ ዘመናዊ ከተማ ትሆን ዘንድ በብዙዎች ዘንድ ቀልብ ገብታለችና የከተማነት ክብርን ስትጎናጸፍ ጊዜ አልፈጀባትም። በደርግ ዘመነ መንግስትም የቃሉ አውራጃ ዋና ከተማ በመሆን ተወዳጅና ተመራጭ ከተማ በመሆን የመንግስታዊዎቹ የጨርቃጨርቅ፤ እንዲሁም የስጋና የቆዳ እንዲሁም የቢራ ፋብሪካዎችን አስተናግዳ የሥራ ከተማነቷንና ለኢንቨስመንት ምቹ መሆኗን አረጋግጣለች።
እስከ 2012 ዓ.ም በከተማ አስተዳደርነት ስትመራ የቆየችው እና በተለይም የባለሃብቶችን ቀልብ እየሳበች የመጣችው ኮምቦልቻ፤ በዘመናት ጉዞዋ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ተገንብተውባታል። የበርካቶችን ልብ መግዛትና መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈስሱ ያደረገችው ኮምቦልቻ ታዲያ 2013 ዓ.ም ላይ ከከተማነት ወደ ሪጆፖሊታን ከተማ አስተዳደር በማደግ የከተማዋን ዕድገትና የሕዝቦቿን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የምትገኝ ፈጣን ለውጥ እያስመዘገበች ትገኛለች።
የኮምቦልቻ ሪጆፖሊታን ከተማ አስተዳደር 124ነጥብ5 ሄክታር የቆዳ ስፋት ያላት ሲሆን፤ በምስራቅ ቃሉ ወረዳና የደሴ ዙሪያ ወረዳ፤ በደቡብ ቃሉ ወረዳ፤ በምዕራብ የጎፍ የመንግስት ደን፤ በሰሜን የተሁለደሬ ወረዳና የደሴ ዙሪያ ወረዳዎች ያዋስኗታል። ከተማዋ ወደ ሪጆፖሊታን ከተማነት ካደገች በኋላ በአራት ክፍለ ከተሞች፤ በ14 የከተማ እና ስድስት የገጠር ቀበሌዎች ተዋቅራለች። የአየር ፀባይዋ በወይናደጋነት የሚመደብ ሲሆን፤ ይህም ከተማዋን ለኑሮ የተመቸ አድርጎታል። የከተማዋ ነዋሪ አማርኛን፣አፋርኛን፣ አርጎብኛን፣ ኦሮምኛ ቋንቋን አዋዶና አጣጥሞ የሚናገርባት የአብሮነትና የፍቅር ተምሳሌት የሆነ ህዝብ ነው። ይሄም ብዙ ባለሃብቶችን መሳብ ከሚችለው መልክዓ ምድሯ ጋር ተዳምሮ ከተማዋን የኢንቨስትመንት መዳረሻ በመሆን ተወዳጅነትን አትርፎላታል።
የኮምቦልቻ ሪጆፖሊታን ከተማ አስተዳደር በሀገራችን በተለየ ትኩረት ከሚመሩ የኢንዱስትሪ ከተሞች መካከል በግምባር ቀደምትነት የምጥጠቀስ ሲሆን፤ በአንጋፋው የኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ፣ የስጋና የቆዳ እንዲሁም የቢራ ፋብሪካዎች በተጨማሪ በርካታ የመንግስታዊና የግል ፋብሪካዎችን በማካተት የኢንዱስትሪ ከተማነቷን አስመስክራለች።
ለኢንዱስትሪ ከተማነት ያስመረጣት ዋና ዋና ምክያች ደግሞ ለገቢና ወጭ ንግድ ምቹና ውጤታማ በመሆኗ ሲሆን፤ ለጅቡቲ ወደብ 440 ኪሎ ሜትር፣ ለአዲስ አበባ በ375 ኪሎ ሜትር፣ ለአሰብ ወደብ በ390 ኪሎ ሜትር፣ ለሰመራ ከተማ በ161 ኪሎ ሜትር ለክልሉ ዋና ከተማ ባህርዳር ደግሞ በ505 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መገኘቷ ተመራጭ አድርጓታል።
በከተማዋ የሚገኙት የደረቅ ወደብ፣ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ ደረጃውን የጠበቀ የኢንዱስትሪ ዞን፣ በከፊል የተጠናቀቀው የባቡር ሃዲድ፣ እንዲሁም የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ዋና መስመር መሆኗ ይበልጥ ተወዳጅና ተመራጭ ሆናለች። እስከ ቅርብ ጊዜ ባለው መረጃ መሰረት የኮምቦልቻ ሪጆ ፖሊታን ከተማ አስተዳደር ከ144 በላይ የሀገር ውሥጥና የውጭ ሀገር ባለሃብቶች መዋለ ንዋያቸዉን በማፍሰስ ከ180 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ገንብተውላታል። በኢንዱስትሪዎቿም ከ3000 በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎቿ የሥራ ዕድል ተፈጥረውላቸው ሕይወታቸውን ይመሩባታል።
እ.አ.አ. በ2017 ዓ.ም ጀምሮ በኮምቦልቻ ከተማ ኢንቨስትመንት እየተሳተፉ ከሚገኙ ድርጅቶች መካከል የጣሊያኑ ኩባንያ ካርቪኮ ኢትዮጵያ አንዱ ሲሆን፤ አቶ ግርማ መታፈሪያ የድርጅቱ ፕሮዳክሽና ሜንተናንስ ማናጀር ናቸው። ፋብሪካው በዋናነት የስፖርት፣ የዋና እና ሌሎች ልብሶችን የሚያመርት ነው። በዓለም ላይ እንደ አዲዳስ እና ናይክ የመሳሰሉ ድርጅቶች ደግሞ የዚህን ኢንዱስትሪ ምርት የሚቀበሉ ደንበኞች ሲሆኑ በዓለም ላይ በጥራት ተወዳዳሪ ከሆኑትም መካከል የሚጠቀስ እንደሆነ ይናገራሉ።
ይህ ፋብሪካ በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ይሰራ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የማስፋፊያ ቦታ በመውሰድ በሰፊው እየሰራ ነው። ኮምቦልቻ ለጅቡቲ ወደብ ያላት ቅርበት፣ የደረቅ ወደብ በከተማዋ አቅራቢያ መገኘቱ፣ የባቡር ትራንስፖርት መኖሩና ሌሎች መሰረት ልማቶች መኖራቸው ብሎም ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል መኖሩ ድርጅቱ ኮምቦልቻን ሊመርጥ ችሏል።
ይህ ፋብሪካ በሰፊውና የረጅም ጊዜ እቅድን ይዞ ይሰራ የነበረ ቢሆንም፤ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት ከአንድ አመት በፊት ኮምቦልቻም የጦርነቱ ክልል ውስጥ ስለነበረች የድርጅቱ አመራሮችም ሆኑ ሠራተኞች ድርጅቱን ትተው መውጣቸውን ያስታውሳሉ። በዚህም ወቅት ትልልቅ ማሽኖች ውድመት ደርሶባቸዋል፤ ለስርቆትም ተዳርገዋል። አስር እቃ ጫኝና አውራጅ ማሽኖች መሰበራቸውንና እስከ 30 ቶን የሚያንቀሳቅሱ ማሽኖች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል።
ይሁንና እነዚህ ሁሉ ውድመቶች ቢደርሱም ለባለሃብቶች መንግስት የሰጠው ትኩረት ከፍ ያለ በመሆኑና የድርጅቱ ባለቤትም በኢትዮጵያ ለሚያካሂዱት ኢንቨስትመንት ባላቸው ቁርጠኝነት በድጋሜ ወደ ሥራ ተመልሰዋል። ድርጅቱ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን 120 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያረገ ሲሆን፤ በቀጣይም ይህንን የሚያጠናክር ይሆናል። ለ250 ዜጎችም የሥራ ዕድል ይፈጥራል። በአሁኑ ወቅት ከተማዋ መነቃቃት ላይ መሆኗን ይመሰክራሉ። በተለይም ከጦርነት ማግስት ላይ ሆና ከቀድሞ ሥራዋ ያናጠፋትን ትካዜ በመተው ወደ ተሻለ እንቅስቃሴ ለመግባት እየተውተረተረች ነው። ይሁንና አሁንም ቢሆን የግንባታ ግብዓቶችና የሲሚንቶ እጥረት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት፣ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በተፈለገው ልክ አለመገኘቱና የመሳሰሉት ችግሮች የኢንዱስትሪ ፈተና መሆናቸውን ይጠቁማሉ።
አቶ መስፍን አያሌው፣ አማር የግብርና ምርቶችን፣ የጨውና፣ ስኳር፣ ዱቄትና ሌሎችን ምርቶችን ለማሸግ የሚፈይድ ከረጢት ማምረቻ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪጅ ሲሆኑ፤ ከተማዋ በጦርነቱ ወቅት የተፈጠረባትን ብዙ ችግሮችን አልፋ አሁንም ቢሆን ኢንቨስትመንትን እያፋጠነች መሆኑን ይናገራሉ። ባለፈው ዓመት ከተማዋ በጦርነት ቀጣና ውስጥ በነበረችበት ጊዜ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰ በማስታወስ፤ በወቅቱም ድርጅታቸው በዚህ ወቅት ክፉኛ ጉዳት እንደደረሰበት ይናገራሉ። ውድመት የደረሰባቸው ማሽኖች በብዛት ከውጭ ሀገር የሚገዙ ቢሆንም፤ የድርጅቱ ባለቤት ካላቸው ቁርጠኛ አቋምና ኢንቨስተመንት ፍላጎት የተነሳ በአጭር ጊዜ ማሽን ከውጭ በማስገባት ወደ ሥራ መመለሳቸው ይናገራሉ።
መንግስትም ለዘርፉ በሰጠው ትኩረትና እያደረገ ባለው ድጋፍ በአሁኑ ወቅት ሰራተኞችን ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ በማድረግ በሙሉ የማምረት አቅም ላይ መሆኑን ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅትም የድርጅታቸው የሥራ አፈፃፀም 75 ከመቶ ሲሆን በሂደት ወደ መደበኛ ሥራው ሙሉ ለሙሉ የሚመለስ ይሆናል። ምርቶቻቸውንም በመላ ሀገሪቱ ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ ለውጭ ሀገር ገበያ ለማቅረብም እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። ምንም እንኳን እነዚህ መነቃቃቶች ቢኖሩም አሁንም ቢሆን የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ጉዳት ለደረሰባቸው ፋብሪካዎች የብድር አመላለስና የብድር እፎይታ ሥርዓት የዘርፉ ፈተናዎች በመሆናቸው መንግስት በልዩ ትኩረት እንዲመለከተው ጠይቀዋል።
የኮምቦልቻ ሪጂኦፖሊቲያን ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሐብታሙ ኃይሌ እንደሚሉት፤ ከተማዋ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ባለሃብቶችንና ኢንቨስትመንት የመሳብ ልምድ ያላት በመሆኑ በርካቶች ቀልባቸውን ጥለውባታል። በአሁኑ ወቅትም 53 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት እየተካሄደባት የምትገኝ ከተማ ናት። በዚህም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ሊደግፉ የሚችሉ ኢንቨስትመንቶችን እያስተናገደች ሲሆን፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችም የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።
ለዓመታት ኢንቨስመንትን ስታሳልጥ የቆየችው ከተማ ግን ባለፈው ዓመት በነበረው ጦርነት ከፍተኛ ወድመት ደርሶባታል። በኢንዱስትሪዎች ላይ ትልቅ ዝርፊያ ተካሂዷል። ከኢንዱስትሪዎች በተጨማሪም አምራች ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በርካቶችም ከውጭ ሀገራት ያስመጧዋቸው ጥሬ ግብዓቶች ለዘረፋ፣ ውድመት እና ለብልሽት ተዳርገውባቸዋል።
ይሁን እንጂ አሁን ላይ ከተማዋ ከደረሰባት ወድመት ለማገገም ደፋ ቀና እያለች ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮችም ወደ ሥራቸው እየተመለሱ ነው። መንግስት ሠላም እና የሀገር ጥቅምን በማስቀደም ችግሮችን በድርድር ለመቋጨት መወሰኑም ከተማዋ ወደ ቀድሞ የኢንቨስትመንት ኮርደርነቷ ለመመለስ ምቹ እድል የሚፈጥር ነው።
እንደ አቶ ሐብታሙ ገለፃ፤ ምንም እንኳን ኢንቨስመንቱን የማነቃቃት ሥራዎች ከፌደራል ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር በትኩረት እየተሠራ ቢሆንም፤ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ኢንዱስትሪን የሚያንቀሳቅስ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት፣ የመሰረተ ልማቶች በሚፈለገው መጠን አለመሟለት ዛሬም ኢንቨስተሮች በተደጋጋሚ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች መሆናቸውን አልሸሸጉም።
የኮምቦልቻ ሪጂኦፖሊቲያን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሀመድአሚን የሱፍ እንደሚሉት፤ ከተማዋ በርካታ ፀጋዎች ያሏት ሲሆን በርካቶችንም ለኢንቨስትመንት መሳብ የምትችል ናት። እንደ ከተማ አስተዳደር በተያዘው ጠንካራ የፖለቲካ አቋምና ባለሃብቶችን የማስተናገድ አቅም በርካቶች ትኩረታቸውን ከተማዋ ላይ አድርገዋል። ይህም በመሆኑ በየዓመቱ በርካታ ገንዘብ ፈሰስ እየተደረገባት የምትገኝ ከተማ ናት።
ኢንቨስትመንቱን የሚፈታተኑ በርካታ ጉዳዮች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ መሀመድአሚን፤ በአሁኑ ወቅት መፍትሄ እየተበጀላቸው መሆኑንም አብራርተዋል። ለአብነትም የመንገድ መብራት ጉዳይ ለነዋሪዎችም ሆነ ለኢንቨስተሮች አንዱ ጥያቄ ነበር። የመብራት መሰረት ልማቶች በዋናነት በፌደራል መንግስት የሚሰሩ ቢሆኑም መንግስት ቀድሞ በከተማዋ ውስጥ የነበሩ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ሙሉ ለሙሉ በአዲስ ምሰሶዎች እንዲቀየሩ አድርጓል። ይህም ችግር በመፈታቱ የመብራት ችግርም እየተፈታ ሲሆን፤ እነዚህ ችግሮች ሲስተካከሉ ኢንቨስትመንቱን ያሳድገዋል።
ከተማዋ በ2000 ዓ.ም የመንገድ መብራት ተሰርቶላት ነበር። ይሁንና ግን የተሰራበት መንገድ የጥራት ችግር ስለነበረበት እስከዛሬም ድረስ ባለመስራቱ ጉዳዩ አከራካሪ ሆኖ ቆይቷል። ፍርድ ቤት ድረስ ሄዶም በኮንትራክተሩ እና በክልሉ የህግ ክፍል መካከል ክርክርም ሲካሄድ ቢቆይም፤ ችግሩ ለብዙ ዓመታ ሊፈታ አልቻለም። ከጥራት ጋር ተያይዞ ያለው ችግርም ሊፈታ አልቻለም። በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ በአዲስ መንገድ በ79 ሚሊዮን ብር በመበጀት በአዲስ መንገድ እየሠራው ነው። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም መንገዶቻችን ጨለማ ስለሆኑ ወንጀሎች ተበራክተው ነበር። ሕብረተሰቡ በዚህ የተነሳ ቅሬታ ያቀርብ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን የነዋሪዎችን ሆነ የባለሃብቶችን ቅሬታ ለማቃለል የተወሰደ አፋጣኝ መፍትሄ መሆኑንም ነው አቶ መሀመድአሚን ያብራሩት።
ከዚህም በተጨማሪ ከተማዋ ጦርነትው ካደረሰበት ጫና ወጥታ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴዋ እየተመለሰች መሆኗ ትልቅ ተስፋ ነው። በጦርነቱ ወቅት ገንዘብ ስናወጣ የነበረው ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና ለጥምር ጦሩ ደጀን ለመሆን ነበር። ጦርነት ባለበት አካባቢ ኢንቨስትመንት አይመጣም። የትግራይ ህዝብና የወሎ ህዝብም በመልክዓምድርና በአኗኗሩም የሚቀራረብና የሚዋሰን ነው።
በመሆኑም የወሎና የትግራይ ህዝብ ተመልሶ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ሕይወቱ እንዲተሳሰር እየሰራን ነው፤ ወደ ቀድሞ መስተጋብራቸው እንዲመለሱም እንፈልጋለን። እኔም እንደ ዜጋ ለዚህ ሠላም የሚከፈለውን ሁሉ መስዕዋት ለመከፍል ዝግጁ ነኝ። ስለዚህ ሠላሙ ማህበራዊ፣ ፖለቲከዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው በመሆኑ በትኩረት ልንሠራበት ይገባል። በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳትና ዝርፊያ ደርሶባቸው የነበሩ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ፣ በማገዝ እና በመከታታል ወደ ሥራ እየተመለሱ ሲሆን፤ የውጭ ኢንቨስተሮችም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ሥራቸውን እየጀመሩ መሆኑን አቶ መሐመድአሚን አረጋግጠዋል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 27 /2015