ባለፈው እሁድ ታኅሳስ 23 ቀን (ጃንዋሪ 1) የነጮች አዲስ ዓመት መግቢያ ቀን ነበር። የአሜሪካው የቴሌቭዥን ጣቢያ ሲ ኤን ኤን ከዋዜማው ጀምሮ ከፍተኛ ሽፋን ነበር የሰጠው። በዕለቱ ደግሞ ሙሉ ቀን ቀጥታ ሥርጭት እና ልዩ ዝግጅት ነበር። በተለያዩ አገራትና ግዛቶች ያለውን ድባብ የሰዓታት መቁጠሪያ (Count down) እያሳየ አዲስ ዓመት መቀበላቸውን ያበስራል።
ኢትዮጵያ ከዓለም የሥልጣኔ አስጀማሪ አገራት አንዷ መሆኗ ማሳያው የራሷ የዘመን አቆጣጠር ያላት መሆኑ ነው። ይህን የመሰለ የራሳችን ቀመር እያለን ግን አሁንም የውጭ ናፋቂነት አለ። ብዙ ዝግጅቶችና ‹‹የእንኳን አደረሰን›› መልዕክቶች በፈረንጆች የቀን አቆጣጠር የምንጠቀም የሚያስመስሉ ነበሩ።
በነገራችን ላይ ይህ የፈረንጆች ቀን አቆጣጠር በተለምዶ ነው ‹‹የፈረንጆች›› የሚባለው እንጂ ‹‹የግሪጎሪያን አቆጣጠር›› ተብሎ ነው የሚጠራው። የአውሮፓ አቆጣጠር እየተባለም ይጠራል። ምክንያቱም ፖፕ ግሪጎሪ በተባለ አውሮፓዊ (የሮማ ሊቀ ጳጳስ) ነው የተዋወቀው።
ይህን በአንድ የሮማ ሊቀ ጳጳስ የተዋወቀ የዘመን አቆጣጠር ከኢትዮጵያ በስተቀር የአፍሪካ አገሮች ሁሉ የዘመን መቀየሪያ ነው። በአውሮፓ (ግሪጎሪ) አቆጣጠር ነው ዘመናቸውን የሚቀይሩት። አውሮፓውያን ራሳቸውን የበላይ አድርገው ማስተዋወቅ ስለሚችሉበት ዓለም አቀፍ መቁጠሪያ እየሆነ ነው።
የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ግን ‹‹የኢትዮጵያ›› ተብሎ እንጂ የቄስ እገሌ ወይም ጳጳስ እገሌ ተብሎ አይጠራም። ስለዚህ ኢትዮጵያ ራሷ የቀመረችው፣ አሥራ ሁለቱንም ወራት 30 ቀናት ያላቸው እና የተፈጥሮ ሕግጋትን የተከተለ የራሷ አቆጣጠር አላት።
ዳሩ ግን የቴክኖሎጂው ተፅዕኖ እና የምዕራባውያኑ የበላይነት የብዙዎችን ቀልብ ወደዚያ ስለወሰደ የፈረንጆችን አዲስ ዓመት ከእነርሱ በላይ አክባሪ ለመሆን የሚዳዳው ሁሉ እየታየ ነው።
በነገራችን ላይ በዚሁ እግረ መንገድ፤ የቀን አቆጣጠራችን ነገር ዝብርቅርቁ የወጣ እየሆነ ነው። እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ በፈረንጅ የቀን አቆጣጠር ብቻ የሚጠቀሙ መስሪያ ቤቶች አሉ።
ወዲህ ደግሞ ለአገር ታሪክ ተቆርቋሪ ነን ወደሚሉት ምሁራን እንምጣ! ጥናት ሰራን ብለው የሚያቀርቡት በፈረንጅ ቋንቋ በፈረንጅ የቀን አቆጣጠር የተሰራ ነው። እንግዲህ አቆጣጠሩን በአገርኛ ማድረግ ካልቻሉ ታዲያ ምኑን ተመራመሩት? ጉዳዩ የውጭ ቢሆን እኮ ችግር አልነበረውም፤ ስለአገር ውስጥ በሚሰራ ጉዳይ ‹‹እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር›› ይባላል።
እዚህ ላይ ግን የአንድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሲያወሩ የሰማሁት ነገር ሁሌም ትዝ ይለኛል። በእርሳቸው ትዝብት ጥናቶች በፈረንጅ ቋንቋና አቆጣጠር የሚሆኑበት ምክንያት ለኩረጃ ስለሚያመች ነው፤ በቀላሉ ከበይነ መረብ ላይ ለቃቅሞ ማቅረብ ስለሚያስችል ነው። ጥናቱ ሁሉ እንዲህ በኩረጃ ስለሚሆን በይነመረብ ላይ እንኳን በአገር ውስጥ ቋንቋ እምብዛም ማግኘት አይቻልም፤ ከተገኘም ብሄርን ከብሄር የሚያበጣብጥ የጥላቻ ጽሑፍ ነው።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ከሥርዓተ ትምህርቱ ጀምሮ ኢትዮጵያዊነትን የሚያስታውስ ነገር ብዙም የለም፤ አቆጣጠሩ በፈረንጅኛው ነው። ለዚህም ነው ብዙዎች ከፈረንጅኛው ይልቅ ኢትዮጵያዊው ቀን የሚጠፋባቸው። በስልኮቻቸው እንኳን ሰዓትና ቀን የሚሞሉት በውጭው አቆጣጠር ነው።
የዚህ ሁሉ ውጤት ነው የሰሞኑን የፈረንጆችን አዲስ ዓመት ከእንቁጣጣሽ በላይ እንድናክበረው ያደረገን። ‹‹ከእንቁጣጣሽ እንኳን አልበለጠም›› እንዳትሉኝ፤ የበለጠበትን ምክንያት ልጨምርላችሁ። በራሱ በእኛው አዲስ ዓመት የሚከበረው እንቁጣጣሽም አንዳንድ ቦታ ላይ በፈረንጅኛው የሰዓት አቆጣጠር የሚከበር መሆኑ ነው።
ከሦስት ዓመት በፊት አዲስ ዓመት መግቢያ ዋዜማ በአንድ ዝግጅት ተጋብዤ ሄጄ ነበር። በዚህ ዝግጅት ላይ የነበረው ሽር ጉድ ከሌሊቱ 6፡00 የሚገባውን አዲስ ዓመት መቀበል ነበር። ባይሆን እንኳን ክርክሩ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የሚገባው ማታ 12፡00 ነው ወይስ ጠዋት 12፡00 ነው የሚለው ነው እንጂ ሌሊት ይገባል ብሎ የተከራከረ የሃይማኖት አባትም ሆነ የታሪክ ባለሙያ የለም። ይሄ ሙሉ በሙሉ ከፈረንጅ አቆጣጠር የተቀዳ ነው። በፈረንጆች ከሰዓት(PM) እና ጠዋት(AM) የሚቀያየረው በእኛ ሌሊት 6፡00 ላይ ነው። እነርሱ ጋ በዚህ ሰዓት ቀን የሚቀየረው ንጋት ስለሚሆን ነው። እኛ ጋ ደግሞ ገና ሌሊት ስለሆነ ተቀየረ ማለት አይቻልም።
እሺ አሁን እንግዲህ ለፈረንጆች ‹‹እንኳን አደረሰን!›› ነው ወይስ ‹‹እንኳን አደረሳቸው›› ነው የምንል? ‹‹እንኳን አደረሳቸው›› እንጂ ‹‹እንኳን አደረሰን›› የምልበት ምክንያት አይታየኝም፤ ከተባለም ለገና በዓል እንጂ ለፈረንጆች ጥር 1 አይደለም። ስለዚህ ባይሆን እንኳን መባል ያለበት ‹‹እንኳን አደረሳቸው›› እንበል!
እንኳን አደረሳቸው መባል እንዳለበት አምናለሁ፤ ምክንያቱም የዓለም ጉዳይም ጉዳያችን ነው። በዚያ ላይ ኢትዮጵያ ብዙ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች አሉባት። እነዚህ ዓለም አቀፍ ጉዳዮቿ የተጻፉት በፈረንጆች አቆጣጠር ነው። ስለዚህ አይመለከተንም ብለን አንደመድምም፤ ታሪክ ስናነብም ሆነ ስንጽፍም ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን በማጣቀስ ነው። የሌሎች አገራትንም ተሞክሮ እየወሰድን ነው። ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን በራሱ በውጭው ዐውድ እንጂ የኛው አቆጣጠር አድርገን መሆን የለበትም።
ሌላ ግን ግራ የምንታዘበው ነገር፤ የኢትዮጵያንና የፈረንጆችን አቆጣጠር የሚያደበላልቁት ናቸው! የምንጠቀምበት የራሱ ቦታ እኮ ነበረው። ለምሳሌ የእንግሊዘኛ ጽሑፍ ውስጥ በኢትዮጵያ ዓመተ ምህረት ተጽፎ እናገኛለን፤ በአማርኛ ጽሑፍ ውስጥ በፈረንጆች አቆጣጠር ተጽፎ እናገኛለን።
ይገባኛል! በእንግሊዘኛ ጽሑፍ ውስጥ የኢትዮጵያ ዓመተ ምህረት በአማርኛ ጽሑፍ ውስጥም የፈረንጆች አቆጣጠር የሚያስፈልግበት አጋጣሚ ይኖራል። ይህ ሲያጋጥም ግን ጽሑፉ የእንግሊዘኛ ከሆነ ‹‹E.C›› የአማርኛ ከሆነ ‹‹እ.አ.አ›› የሚል መኖር አለበት። የምናየው ነገር ግን የተደበላለቀ ነው። አቆጣጠሩ በየትኛው እንደሆነ የሚያውቀው ሁነቱን የሚያውቅ ብቻ ነው። እንግዲህ ይህን ያህል ተደነባብረናል!
በውጭ የተጻፈውን እንኳን ወደኢትዮጵያ አቆጣጠር መመለስ ይቻላል እኮ። ለምሳሌ ክስተቱ ከመስከረም እስከ ጥር ባለው ወር ውስጥ ከሆነ ከውጭው ዘመን ላይ 7 መቀነስ ነው። እነርሱ ጥር ላይ አዲስ ዓመት ስለሚቀበሉ ከጥር እስከ ነሐሴና ጳጉሜ ባለው ወር ውስጥ ከሆነ ደግሞ 8 መቀነስ ነው። ለቀንም እንደዚሁ። በእያንዳንዱ ወር ውስጥ ያለን ልዩነት ይታወቃል። ለምሳሌ ዛሬ በፈረንጆች ጥር 4 ቀን 2023 ነው። ይህን በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር እናስቀምጠው ቢባል ቀኑ ታህሳስ 26፣ ዓመተ ምህረቱ ደግሞ 2015 ይሆናል። ምክንያቱም የእነርሱ የጥር ወር 31 ቀን ነው። ወራቸው 31 ሲሆን 8 ቀን እንቀንሳለን፤ ከጥር 4 ላይ 8 ቀን ወደኋላ ስንመለስ ታኅሳስ 26 ይሆናል ማለት ነው። ዓመተ ምህረቱ ደግሞ ከጥር በኋላ ስለሆነ 8 እንቀንሳለን ማለት ነው። በዚህ ዘመን ደግሞ የቀን መቀየሪያ መተገበሪያም አለ።
እንግዲህ ይሄ ሁሉ ውስብስብ ከሆነብን እንኳን ቢያንስ ‹‹እ.እ.አ›› የሚለውን እንጠቀም፤ የእንገሊዘኛ ጽሑፍ ሆኖ በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከሆነም ‹‹E.C›› እንጠቀም፤ ምክንያቱም ጽሑፉ እንግሊዘኛ ሲሆን ዘመኑም በፈረንጆች ስለሚመስል።
ሰሞኑን የፈረንጆች አዲስ ዓመት ስለሆነ ነው እንግዲህ ስለጉዳዩ ያወራነው። በዚያ ላይ ደግሞ ለእኛም ለእነርሱም የጋራ የሆነው ደግሞ የገና በዓል ነው። ምንም እንኳን የእነርሱን አከባበር እየተከተልን ቢሆንም ገናም የራሳችን የሆነ ባህላዊ አከባበር ያለው ነው።
ለእኛም ለእነርሱም መልካም በዓል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26 /2015