በዕምነት ኃይለ ማርያም የ12ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ወደ እቴጌ መነን አዳሪ ትምህርት ቤቱ የገባችው በ2012 ዓ•ም ነው። የመጣችው ደግሞ ከኮልፌ ቀራኔዮ መድሃኒዓለም 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው።ወደ ትምህርት ቤቱ መግባት የቻለችው በስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና 97 ነጥብ1 አምጥታ ነው።
በእምነት እንዳጫወተችን መግቢያ ፈተና ወስዳለች።ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ከመጡ ተማሪዎች ጋር ተፈትና ፈተናውን በአብላጫ ውጤት ካለፉት አንዷ በመሆኗ ነው ወደ እቴጌ መነን የሴቶች ትምህርት ቤት የገባችው። ከገባች በኋላ ከወንድ ተማሪዎች በአጠቃላይ ከማህበረሰቡ መነጠሉ እጅግ ከብዷት ነበር። ቀስ በቀስ ግን እየለመደችው ስትመጣ መነጠሉ ጠቃሚ መሆኑን ተገነዘበች።
ቤተ መጽሐፍት 24 ሰዓት ክፍት በመሆኑ መሸብኝ፤ወንዶች ይተነኩሱኛል፤ ቤት ያስባሉ ሳትል ባመቻት ጊዜ ትጠቀማለች።የተሟላም አይስቲ ክፍል ተገልጋይ አድርጓታል።በ12ኛ ክፍል ፈተና 625 አምጥታ ወደ ዩኒቨርስቲ በመግባት የሕግ ትምህርት የማጥናት ፍላጎቷን ለማሳካት የሚያስችላትን ዝግጅትም ከወዲሁ ማድረግ አስችሏታል።ምሳ፤ቁርስና ራት እንዲሁም አዳር እዛው በመሆኑ እንደ ፊቱ በምልልስ የምታባክነው ጊዜ የለምና በቂ የጥናት ጊዜም አግኝታለች።በትምህርት ቤቱ በሚካሄዱ የእግር ኳስና የተለያዩ ክበባትም ለመሳተፍ አስችሏታል።
ቀራኔዮ መድሃኒአለም ሁለተኛ ደረጃ በነበረችበት ጊዜ ለጥናት የማይመቹ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ነበሩ።በተለይ ሴቶች ሰብሰብ ብለውም ሆነ በግል ሲያጠኑ በወንድ ተማሪዎች በተደጋጋሚ ይረበሹ ነበር።ለነሱ ጨዋታ ቢመስላቸውም እሷን ያናድዳታል።ጎድቷታልም።
ለምሳሌ በስምንተኛ ክፍል ፈተና 100 አምጥታ ነበር ወደ ዘጠነኛ ክፍል ማለፍ የፈለገችው። ሆኖም በነፃነት ማጥናት ባለመቻሏ ያሰበችውን ማምጣት አልቻለችም። በዕምነት እንደነገረችን ቤት ሆኖ መማርም ቢሆን ለሴት ተማሪ ውጤታማ የሚያደርግ ነው ብላ አታምንም።ምክንያቷን ስትገልጽም“ ‹‹ብዙ ጊዜ አብዛኞቹ ወላጆች የቤት ውስጥ ሥራ ሴቷ እንጂ ወንዱ ልጃቸው እንዲሰራ አይፈልጉም” ትላለች። እንዳከለችው ወንዱ ልጃቸው ውጭ፤ውጭ እንዲልና እንዲያጠናም ይፈልጋሉ።ኳስ እንዲጫወት ያደርጋሉ።ሴት ልጆቻቸው ግን በሥራ እንዲያግዟቸው ሲያደርጉ ነው የምታየው።በእርግጥ የእሷ ወላጆች እንደዚህ አይደሉም።የተሻለ ውጤት ማምጣትና አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ መግባት የቻለችውም ለዚህ ነው።ሆኖም የሚኖሩት ለወንዶች በሚያዳላ ማህበረሰብ ውስጥ እንደመሆኑ ከተጽዕኖው ነፃ ናቸው ብላ አታስብም።
“እኔም ብሆን ምንም ያህል ጥናት ቢኖርብኝም እናቴ በሥራ ተወጥራ እያየሁ ቁጭ ብዬ ማጥናት አልችልም።እኔ እንኳን ዝም ብል ማህበረሰቡ “ሴት አይደለሽ አታግዣትም” ማለቱ አይቀርም”ብላናለች ተማሪ በዕምነት።ይሄ በተግባር እንደገጠማትም አክላልናለች።
ከወንዶች ተነጥሎ ሴቶች ብቻ የሚማሩበት ትምህርት ቤት መማር ሴት ተማሪዎችን ከነዚህ ሁሉ ተፅዕኖዎች ነፃ እንደሚያደርጋቸው የምትናገረው የ11ኛ ክፍሏ ተማሪ ሂክማ ሲራጅ ነች።ተማሪዋ እንደምትለው ወደ ትምህርት ቤቱ የመጣችው ሳሪስ 58 ቀበሌ ከሚገኘው መጋቢት 28 ትምህርት ቤት ነው።ዘንድሮ ሦስተኛ ዓመቷ ነው።“በቆይታዬ ደስተኛ ነበርኩ ብላለች።ምክንያቷ ከወንድ ተነጥሎና ከተፅዕኖ መራቅ መሆኑንም ትጠቅሳለች።
ከሚያስተምሯቸው መምህራኖች አብዛኞቹ ወንዶች መሆናቸውን እንዴት እንደምታየውም አንስተንላት ነበር።“መምህሮቻችን እንደ ልጆቻቸው ነው የሚያዩን።እኛም እንደ አባትና ወንድም ነው የምናያቸው” ብላናለች። ባላቸው ግንኙነት ችግር አላጋጠማቸውም እንጂ ከጾታዊ ጥቃትና ካልተገባ ግንኙነት ጋር ብቻም ሳይሆን ማንኛውም ችግር ሲገጥም የሚፈታበት ስርዓት መዘርጋቱንም ተማሪዋ ታወሳለች።ተማሪ ቤተሰብ እንዳይናፍቅ ወላጅ በፈለገው ጊዜ መጥቶ ያያቸዋል።እነሱም በየ15 ቀኑ ሄደው ወላጆቻቸውን ያያሉ።በዚህ ላይ ከጊቢው ማህበረሰብ ጋር ያላቸው መስተጋብርም ቤተሰባዊ በመሆኑ ብቸኝነት አይሰማቸውም።
በመሆኑም በዚህ መልኩ የሚቋቋም የሴቶች ዩኒቨርስቲ ቢኖር መልካም ነው ትላለች። ከወንዶች ጋር ተቀላቅሎ መማሩ በተለይም ከዕድሜ መድረስ አንፃር የአቻ ግፊት ስለሚያይል ለብቻቸው መማሩ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ሴቶች ለብቻቸው ዕውቀት እንዲጨብጡ ማድረግ ከራሳቸው አልፈው ለቤተሰብና ለአገር የሚተርፉ ብቁ ሴቶችን ለማውጣት ያስችላል የሚልም ዕምነት አላት።
“የአዳሪ ትምህርት ቤትና የዩኒቨርስቲ ባህርይ ተመሳሳይ ነው”ያሉን ደግሞ የሳይኮሎጂ መምህርቷ ወይንሸት ክብረት ናቸው። በመሆኑም ዩኒቨርስቲ ሲገቡ ብዙውን ስለተለማመዱት አዲስ አይሆንባቸውም ።ከዚህና ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲመጣ ሊያጋጥማቸው ከሚችለው ተፅዕኖ ተጠብቀው እስከ መጨረሻው ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል በዩኒቨርስቲም ደረጃ ተነጥለው ቢማሩ የተሻለ ውጤታማ ይሆናሉብለው ያስባሉ። ብቃታቸውንና የሕይወት ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበትን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተማሪዎቹን ያማክራሉ።የሚያማክሩት በግልም በቡድንም ወደ እሳቸው የሚመጡትን ነው።ማነቃቃት ላይም ይሰራሉ።
መምህር መስፍን ዘውዴ ቴክኒካል ድሮዊንግ ነው የሚያስተምሩት።መምህሩ እንደሚሉት ከወንዶች ተለይተው በተለይም አዳሪ ሆነው መማራቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አለው። ተለይተው በመማራቸው ከቤት ውስጥ ሥራ ጫና ነፃ ሆነዋል።ትምህርታቸውን በትኩረት እንዲከታተሉ ያስችላቸዋል።እሳቸው ወንድ ቢሆኑም ስለታጩበት መስፈርት እንዳያወጉን ጥያቄ አንስተንላቸው ነበር፡፡
‹‹ የተመለመሉት በዩኒቨርስቲ ባመጡት ከፍተኛ ነጥብና በሙያዩ ባለኝ የተሻለ አፈፃፀም ነው።በውጤታቸው መሰረት ከተመዘገብኩ በኋላ አዲስ አበባ ሜትሮፖሊታንት በዩኒቨርስቲ ያወጣውን መግቢያ ፈተና አለፍኩ።ስለዚህም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ኃላፊነቱን ወሰድኩ ›‹›ብለውናል፡፡
ካደግንበት ማህበረሰብ እንደምንገነዘበው ሴት ልጆች እዚህና ቤተሰብ መካከል ሆነው መማራቸው ልዩነት አለው። ቤት ሆነው ሲማሩ ሴት ሆና እናቷ ሥራ እየሰራች ዝም ብላ አታይም።ከጥናት ይልቅ እናቷን በሥራ ታግዛለች።እዚህ ግን ሥራ ስለሌለ ትኩረቷን በትምህርት ላይ ብቻ ነው የምታሳልፈው።ይሄ ደግሞ ውጤታማ ያደርጋታል። ሴቶች ከእናትነት ድርሻቸው ጀምሮ በሕብረተሰቡ ውስጥ የጎላ ሚና ያላቸው ከመሆናቸው አንፃር ከማንኛውም ጫና ነፃ ሆነው የሚማሩበት በመሆኑ እንደ መነን ያለው አዳሪ ትምህርት ቤት በመላ አገሪቱ ቢሰፋ የሚል ዕምነት አላቸው።
ለመምህሩ አንዳንድ ሰዎች ተነጥሎና በአዳር መማር ለሴቶች ካለው ጠቀሜታ አንፃር በዩኒቨርስቲ ደረጃም መስፋፋት አለበት የሚል ዕምነት ያላቸው መሆኑን አንስተንላቸው ነበር።እንደምላሻቸው ታድያ አሁን ላይ በአዳር የምንቀበላቸው ህፃናት ናቸው።ዕውቀት መጨበጥና መያዝ የሚችሉትም በዚህ ዕድሜ ነው።ከዚህ ከሚያስተጓጉላቸው የቤት ውስጥ የሥራ ጫናና ሌሎች ተጽዕኖዎች ነፃ መሆን ያለባቸውም አሁን ነው። ዩኒቨርስቲ በሚገቡበት ጊዜ ያድጋሉ።በዕድሜም ይበስላሉ።ክፉና ደጉን ስለሚለዩና ለከፍተኛ ትምህርት መሰረት የሚሆናቸውን ዕውቀትም ቀድመው ስለሚይዙ በትምህርታቸው ለመጠንከርም ሆነ የአቻ ግፊትና ሌሎች ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም ይችላሉ።በዚህ ላይ ዩኒቨርስቲ በባህሪው ከነበሩበት ከአዳሪ ትምህርት ቤት ጋር የሚመሳሰልና ከቤት ውስጥ የሥራ ጫና የሚያላቅቅ በመሆኑ ተነጥለው መማራቸው አስፈላጊ ነው ብለው አያምኑም። ተቀላቅለው ቢማሩ በጋራ ለመኖር አስፈላጊ ጉዳዮችን እየተገነዘቡ ወደ ማህበረሰቡ ውስጥ መግባት ይችላሉ ይላሉ።
የትምህርት ቤቱ ዋና ርዕሰ መምህርት ሀና ፀጋዬም ሴቶች ተነጥለው በአዳሪነት መማራቸው የጎላ ጥቅም እንዳለው ነው በአፅዕኖት የሚናገሩት።‹‹እንደ ሴትም ሳየው ሴቶች ከወንድ ተነጥለው ብቻቸውን መማራቸው በጣም ጥሩ ነው›› ይላሉ ።እንደ እሳቸው ብዙ ጊዜ ሴቶች ብቻቸውን ተነጥለው መማራቸው በተለያየ መልኩ ችግር ያመጣባቸዋልና ማህበራዊ መስተጋብራቸውን ያላላል የሚሉ አንዳንድ ሰዎች አሉ።ሆኖም ከአንድ እስከ ስምንተኛ ክፍል ሲማሩ ከወንድ ተማሪዎች ጋር አብረው ነው የተማሩት። ወደ ዩኒቨርስቲም ሆነ ወደ ቤታቸው ሲሄዱም ከወንድሞቻቸው ጋር ይቀላቀላሉ። በተጨማሪም በእቴጌ መነን የሴቶች ትምህርት ቤት ውስጥ ካሉት 56 መምህራን መካከል 44ቱ ወንዶች ናቸው።ምንም የተለየ ነገር አይኖረውም ።እንደውም እርስ በእርስ ለመረዳዳት ያለባቸውን የቤት ውስጥ የሥራ ጫና ፤የቤተሰብ ተፅዕኖ ለመቅረፍ ፤በምግብ ፤መኖሪያ በማጣት፤ ዘመድ ጋር ተጠልለው ነጥብ አምጥተው የሚያስተምሯቸውንና የሥራ ጫና የሚበዛባቸውን ሥራ የሚያሰሯቸው ወላጆች ሁሉ ያሉበት ችግር ተማሪዎች እዚህ ትምህርት ቤት ገብተው በመማራቸው ይቀረፍላቸዋል። እኛ ባደረግነው ጥናት ማደሪያ የሌላቸው እና ነጥብ ያመጡ ሴቶች ስላሉ ትምህርት ቤቱ አዳሪ መሆኑ ጠቅሟቸዋልም ነው የሚሉት። አዳሪ ሆነው በመማራቸው በተግባርም የተሻለ ውጤት ሲያመጡ እየታየ ነው።እውነታው ጥናት ተደርጎ ተረጋግጧል። እንደ ትምህርት ሚኒስቴርም እንደዚህ ዓይነት አዳሪ ትምህርት ቤትን ለመክፈት ይቻል ዘንድ ከትምህርት ቤቱ ተሞክሮ ተወስዷል።
በተጨማሪም ልጃገረዶቹ እንደሌሎቹ ተማሪዎች በመጓጓዝ የሚያባክኑት ጊዜ የለም።የምልልሱ ጊዜ ማጠሩ በራሱ ለጥናት፤ለሌሎች የቤትና የክፍል ሥራዎቻቸው የሚያደርገው እገዛ የላቀ ነው። በዛ ላይ ምግብና መጠለያ እየተቸገሩ ይማሩ የነበሩ ጠንካራ ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ቤቱ የገቡ በመሆናቸው ቁርስ፤ምሳና እራት መዘጋጀቱ እንዲሁም አዳር መሆኑ በፊት ይቸገሩበት የነበረውን ሁኔታ በማስቀረት ትኩረታቸው ትምህርት ላይ ብቻ እንዲሆን ያደርጋል።በትምህርት ውጤታማ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።በዚህ ላይ ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ቤቱ የሚመጡት ቦርሳና ደብተራቸውን ብቻ ይዘው ነው። አንሶላና ትራስን ጨምሮ ብርድ ልብስና ፍራሽ የሚያቀርብላቸው ትምህርት ቤቱ ነው። ተደራራቢ አልጋም እንዲሁ ትምህርት ቤቱ ነው የሚያዘጋጅላቸው ።
በጠባቧ መኝታ ክፍል ስድስት ፤በሰፊው ደግሞ 12 ተማሪዎች ሆነው በተደራራቢው አልጋ ላይ በተናጠል ይተኛሉ። ክፍሉም ሆነ መኝታው በጋራም ሆነ በግል ለማጥናት ጭምር እንዲያመቻቸው ተደርጎ ነው የተዘጋጀው።ደህንቱም ቢሆን የተጠበቀ ነው።በተጨማሪም ይሄን ለማረጋገጥ ትምህርት ቤቱ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል።ከመምህራን ጋር ያላቸው ግንኑነት ችግር አለው የለውም በሚል ይፈትሻል። መምህራኖቹ ሲመረጡ የስነ ምግባር ችግር እንደሌለባቸው ተረጋግጦ ሌላ ትምህርት ቤት የተሻሉ ተብለው ነው የመጡት።መምህራኑ ወደ ትምህርት ቤቱ ከመጡ በኋላ በየጊዜው እየተፈተሸ ይሄዳሉ፡፡
አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ከሚያቀርቡላቸውና ክፍላቸውን ከሚያፀዱላቸው ሴት ፅዳት ሠራተኞች በስተቀር ወደ መኝታ ክፍላቸው የሚሄድ የለም።ትምህርቱና ቆይታቸው አዳር በመሆኑና መጓጓዝ ስለሌለባቸው የበለጠ ደህንነት ይሰማቸዋል።ከለከፋ ጀምሮ መንገድ ላይ የሚገጥሙ መሰናክሎችንም ያስቀርላቸዋል።ርዕሰ መምህርቷ ከጤና ጋር ተያይዞ ሊገጥማቸው የሚችለውን ከመፍታት አንፃር በትምህርት ቤቱ ያለውንም ሲናገሩ ከእንጦጦ ጤና ጣቢያ እና ከየካቲት 12 ሆስፒታል ጋር ትምህርት ቤቱ ባደረገው ትስስር በሚያማቸው ወቅት ይታከማሉ።መድሃኒት ይታዘዝላቸዋል። የተማሪዎቹ የሕክምና ወጪ ሙሉ በሙሉም ይሸፈናል።በወር ወይም በ15 ቀን አንድ ቀን ከትምህርቱ ጋር በማይጋጭ ሁኔታ ቤተሰባቸውን ጠይቀው እንዲመጡም ይደረጋል። ቀደም ሲል አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው በትምህርት ቤታችን አዳሪ ሆነው በመማራቸው ብዙም ደስተኛ አልነበሩም።ሆኖም ልጆቻቸው ውጤታማ እየሆኑ ሲመጡ ፤ጥቅሙን ሲያዩት፤ልጆቻቸውም እየወደዱት ሲመጡ ደስተኛ መሆን ችለዋል ይላሉም ርዕሰ መምርቷ ሀና ፀጋዬ።
በትምህርት ቤቱ እሳቸውን ጨምሮ አራት ርዕሰ መምህራን ሲኖሩ ሦስቱ የአካዳሚ ዘርፉን፤የተማሪዎች ምግብ መኝታቸውን የሚቆጣጠሩ ናቸው። የተማሪዎችም ዲን አለ።ፋይናንስ፤የሰው ኃይልና ሌሎችን የምታስኬድ ሴት ርዕሰ መምህርት አለች።በድምሩ 114 ሠራተኞች አሉ።ከነዚህ መካከል 56ቱ መምህራን ሲሆኑ ሌሎቹ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ናቸው።ከ56ቱ መምህራን መካከልም 44ቱ ወንዶች ናቸው። ወንዶቹ መምህራን ከተማሪዎቹ ጋር ያላቸው ግንኙነት ቤተሰባዊ ነውም ይላሉ።
የእቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ ትምህርት ቤት በአዲስ አበባ ከተማ ብቸኛው የመንግስት ትምህርት ቤት ነው።በየዓመቱ 500 ተማሪዎችን ይቀበላል።ትምህርት ቤቱ እያስተማረ የሚገኘው ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን ነው። ተማሪዎቹ አዲስ አበባ ከሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ተውጣጥተው የመጡ ሲሆኑ የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ወስደው ከ75ና በላይ ያመጡ ናቸው።
ትምህርት ቤቱ በ2012 ዓ.ም ትምህርት ሲጀምር የተቀበላቸው ልጃገረድ ተማሪዎች 300 ሲሆኑ የ11ኛ እና የ12ኛ ጥቂት ተማሪዎችንም ይዞ ነበር።ዘንድሮ ከተቀበላቸው 500 ተማሪዎች መካከል ሰባቱ ጠይቀው አዳማ አዳሪ ትምህርት ቤት ስለሄዱ 493ቱን እያስተማረ ይገኛል።ከነዚህ ውስጥም 177ቱ በዚህ ዓመት መጨረሻ የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱና በከፍተኛ ዝግጅት ላይ የሚገኙ ናቸው።
የቅበላ አቅሙን በየዓመቱ እየጎለበተ ሄዶም ዘንድሮ 500 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ደረጃ ላይ ደርሷል። ቁጥሩ እየጨመረ የመጣው የመኝታው፤ የምግቡና ሌላው አገልግሎት እየሰፋ በመሄዱ ሲሆን የቅበላ አቅሙ ከ500 በላይ ስለማይፈቅድም ከፍተኛ ነጥብ ያመጡና ለመግባት የተመለመሉ በርካታ ሴት ተማሪዎች ቢኖሩም ለማስተናገድ አልቻለም።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 25 /2015