የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለዜጎች የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ብዙ ምልልሶችና እንግልቶች የበዛባቸው፤ ለአላስፈላጊ ወጪና ለምሬት የሚዳርጉ የቅሬታ ምንጭ ሆነው ቆይተዋል። ይህን አሰራር ለመለወጥ የሚያስችሉ ስልቶች በመቀየስ የሕዝቡን ቅሬታ ለመፍታት ሲሰራ ቢቆየም፣ ከችግሩ ግዝፈትና ስፋት አኳያ በሚፈለገው መልኩ የዜጎችን ምልልሶችና እንግልቶች እንዲሁም የሀብትና ጊዜ ብክነትን ማስቀረት ሳይቻል ቀርቷል ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በአገልግሎት አሰጣጡ ረገድ የተለያዩ የአሠራር ማሻሻያዎች እየተደረጉና መሻሻሎች እየታዩም ናቸው። ምስጋና ለቴክኖሎጂ ይሁንና አሁን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች መሻሻል እየታየባቸውና ተስፋ ፈንጣቂ እየሆኑ መምጣታቸውንም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
ባለንበት የዲጅታል ዘመን የዜጎችን ኑሮ ቀላል በማድረግ ፈጣን ፣ጊዜንና ወጪን የሚቆጥብ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እጅግ ወሳኝ ነው። ሀገራችን እየተገበረችው በሚገኘው የአሥር ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ ላይ እንደተመላከተው፤ በኢትዮጵያ ዲጅታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ያለመውን ግብ ለማሳካት የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ወደ ዲጅታል መቀየር ልማት እንዲፋጠን ማድረግ ነው። ይህንን እቅድ ከግብ ለማድረስ አገልግሎቶችን ማዘመን ያስፈልጋል፤ ይህ ስራ ወጪ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ዜጎች ለእንግልት ሳይዳረጉ ባለቡት ሆነው አገልግሎቶችን በቀላል ዘዴ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች በማልማት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግን ይጠይቃል።
ቴክኖሎጂዎችን የማልማት ኃላፊነት የተሰጠው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እያደረገ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥም አንዱ የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያዘመኑ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የወረቀት ሥራን በማስቀረት አገልግሎቶችን ማሻሻል የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች በማበልጸግ ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረግ ነው።
በዚህም የመንግሥት ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን የሚያስችል የአንድ መስኮት አገልግሎት ወይም ኢ-ሰርቪስ( eservices) አገልግሎት ሥራ እንዲውል አድርጓል። ይህንን ቴክኖሎጂ እየተጠቀሙ ያሉ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በኢ-ሰርቪስ ዘዴ/ ፕላትፎርም/ በኤሌክትሮኒክስ ተጠቅመው አገልግሎት አሰጣጣቸውን እያዘመኑ ናቸው። አገልግሎት አሰጣጣቸውን በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ/ ኢ-ሰርቪስን/ ያደረጉ ተቋማት ደግሞ የክፍያ ሥርዓታቸውን በማስተሳሰር አገልግሎት አሰጣጣቸውን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ እየሰሩ ይገኛሉ።
በዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አምዳችን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያበለጸገው የኤሌክትሮኒክስ /ኢ-ሰርቪስ/ አገልግሎት በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ፤ አገልግሎት አሰጣጣቸውን በኢ-ሰርቪስ ያደረጉ ተቋማት እንዴት እየተጠቀሙበት ስለመሆናቸው ዳሰናል።
የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት/ ኢ-ሰርቪስ/
የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት/ ኢ-ሰርቪስ/ ማለት ዜጎች ከመንግሥት ተቋማት የሚፈልጉትን አገልግሎት ባሉበት ቦታው ሆነው በበይነመረብ (በኢንተርኔት) አማካይነት ማግኘት የሚችሉበት ነው። የኢ-ሰርቪስ አገልግሎት አሰጣጥ ከዚህ በፊት ዜጎችን ለእንግልትና ለምልልስ የሚዳርጉ አሠራሮችን በመቀየር አገልግሎቶችን ወደ አንድ በማምጣት በኤሌክትሮኒክ ዘዴዎች ተጠቅመው አገልግሎት እንዱሰጡ ያስችላል። ይህ ደግሞ ከዚህ በፊት ዜጎች አገልግሎቱን ለማግኘት የሚያጠፉትን ጊዜና የሚያወጡትን ያልተገባ ወጪ በማስቀረት ባሉበት ቦታ ሆነው የሚፈልጉትን የትኛውንም አይነት አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል።
የኢ-ሰርቪስ አገልግሎት የሦስትዮሽ ጥምረትን ይፈልጋል፤ አገልግሎት ፈላጊ ዜጎች /የህብረተሰብ ክፍሎችን/፤ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት እና ቴክኖሎጂውን የሚያቀርቡ አካላትን አንድ ላይ አጣምሮ የሚይዝና ቅንጅታዊ ሥራ የሚጠይቅ ነው።
ኢ-ሰርቪስ አገልግሎት ፈላጊ አካላት ባሉበት ሆነው በሞባይል ፣ በላፕቶብ ወይም በማንኛውም ኢንተርኔት መጠቀም የሚያስችል ቁስ ተጠቅመው የሚፈልጉትን አገልግሎት መጠየቅ የሚችሉበት ነው። አገልግሎት ፈላጊዎች www.eservices.gov.et የሚለውን ጽረገጽ በመጠቀም ለአገልግሎት አሰጣጡ አስፈላጊ የሆነ መረጃዎች በፕላት ፎርሙ ላይ ይጫኑና ጥያቄያቸውም በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በኩል ይታያል፤ አስተያየት የሚያስፈልገው ከሆነ ባሉበት ሆነው በዚያው በፕላት ፎርም አማካይነት ምላሽ እንዲያገኙ ይደረጋል። በመቀጠልም ክፍያ የሚያስፈልግ ከሆነ ክፍያ የሚከፍሉበትን ዘዴም እዚያው ላይ ያገኛሉ። ይህንን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ በመጨረሻም የሚደርሳቸውን አጭር የጽሐፍ መልዕክት በመያዝ አንድ ጊዜ ብቻ አገልግሎቱን ወደ ሚፈልጉበት ተቋም ይሄዳሉ።
ቴክኖሎጂውን በማልማት ለተቋማት የሚያቀርበው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተቋማት ለተጠቃሚዎች የተሻለ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ቀልጣፋ እንዲሆኑ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል። በዚህ በኢ-ሰርቪስ /ፕላትፎርም/ አገልግሎት እስካሁን 25 ተቋማት የተካተቱ ሲሆን፣ 326 አገልግሎቶች በቀጥታ ስርጭት/ በኦንላይን አገልግሎት እየተሰጡ ናቸው። በእነዚህ አገልግሎቶች ውስጥ የክፍያ ሥርዓት አብሮ እንዲሰጥ ለማድረግ በተሰራው ሥራ ከክፍያ ሥርዓት ጋር የተሳሰሩ አገልግሎቶች ይኖራሉ። ቀሪዎቹን ደግሞ ከክፍያ ሥርዓት ጋር የማስተሳሰር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ነው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ የሚያመላክተው።
የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ተቋማት
የኤሌክትሮኒክ አገልግሎትን ከተቀላቀሉት ተቋማት መካከል የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለስልጣን አንዱ ነው። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ቴክኖሎጂውን ካለማው በኋላ ባለስልጣኑ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ወደ ኢ-ሰርቪስ ሲሰተሙ በማስገባት ቀዳሚ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆኑን የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ሰጠኝ ገላን ገልጸዋል።
አቶ ሰጠኝ እንዳብራሩት፤ አሁን ላይ ወደ 72 የሚደርሱ ተቋማት በቋሚነት አገልግሎቱን እየተጠቀሙ ናቸው፤ 123 ጨረታዎች በጽረ ገጻቸው www.Egp.ppa.gov.et በቀጥታ ስርጭት /በኦንላይን/ ላይ ይገኛሉ። የባለስልጣኑ ድረገጽ ሲከፈት የሚያሳየው የጨረታዎችን ብዛት፣ እየተገመገሙ ያሉ ጨረታዎችን ፣ ምንያህል አቅራቢዎች እንደተመዘገቡ እና የመሳሰሉትን መረጃዎች ነው። በዚህ አሠራር በመጠቀም እስካሁን ድረስ ወደ 292 ጨረታዎች ወጥተዋል። 5ሺ540 የሚሆኑ አቅራቢዎች ተመዝግበዋል፤ ይህ የሚያሳየው አሠራሩ ግልጽነት የተሞላበትና ትስስር ያለው እንደሆነ ነው።
የኤሌክትሮኒክስ አሠራር ብዙ ለውጦችን ያመጣና ጊዜን የሚቆጥብ እንዲሁም ጥራት የሚጨምር ነው ያሉት አቶ ሰጠኝ፣ ጨረታው ለሁሉም ክፍት በመሆኑ ሁሉም መሳተፍ ይችላል ሲሉ ይጠቁማሉ። ይህ መሆኑም የተጫራቾች ቁጥር እንዲጨምር ያደርጋል፤ የተጫራቾች ቁጥር ሲጨምር በአነስተኛ ዋጋ የማቅረብ ሁኔታ ስለሚጨምር ለመንግሥት የሚያስገኘው ጠቀሜታም ይጨምራል። ሙስናንም ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ይቻላል ባይባልም፣ በጣም መቀነስ ይቻላል ሲሉ አብራርተዋል።
የኤሌክትሮኒክ ዘዴን በመጠቀም አገልግሎት መስጠት በርካታ ጠቀሜታዎች አንዳሉት የሚናገሩት አቶ ሰጠኝ፤ የክፍያ ሥርዓቱም ቢሆን ከባንክ ሲስተም ጋር የተያያዘ ክፍያ እንደሆነ ይገልጻሉ። በዚህ ሂደት የጨረታው አሸናፊዎች ወደ ተቋማት (ጨረታውን ወደ አወጣው አካል ዘንድ) መሄድ የሚጠበቅባቸው እቃ ለማቅረብ ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ተቋማት አገልግሎታቸውን ወደ ኤሌክትሮኒክ ዜዴ ከመቀየራቸው በፊት የለመዱትን አሰራር በመከተል በፍጥነት ቴክኖሎጂውን ለመቀበል ተቸግረው እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ሰጠኝ ፤ ይህም ተቋማት ለቴክኖሎጂው ሰጥተው የነበረው ትኩረት አነሳ መሆኑን እንደሚያሳይ ይናገራሉ። አሁን ላይ ግን ተቋማትን ወደ ሲስተሙ እንዲገቡ ግፊት በማድረግ ብዙ ተቋማት ወደ ሲሰተም እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን ያመለክታሉ።
በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የተቋሙ ተገልጋዩች አገልግሎቱን አስመልክቶ እየሰጡ ያሉት አስተያየት አበረታች ነው ያሉት አቶ ሰጠኝ፤ ተገልጋዩች ጊዜያቸውን እና ወጪያቸውን እንደቆጠበላቸው መግለጻቸውን ይናገራሉ ። ለአብነት የባለስልጣኑ ተገልጋዮች የጨረታ ሰነድ ለመግዛት እንዲሁም ጋዜጣ ለማገላበጥ የሚያወጡትን ወጪ ጊዜና ጉልበት የቀነሰላቸው መሆኑን በመጥቀስ፣ አገልግሎቱን ሊቀጠል የሚገባው ሲሉ መግለጻቸውን ነው አቶ ሰጥኝ ያብራሩት።
እስካሁን ወደሲስተሙ ያልገቡ ተገልጋይ መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ሰጠኝ፣ እነዚህ አካላት በሀገራችን ብዙ አቅራቢዎች ያሉ ሲሆን የመንግሥት ግዥ ባለስልጣን ኢ ጂፒ ፖርታል/ e-GP Portal /ገብተው ሲመዘገቡ ብቻ ነው ጨረታ ላይ መሳተፍ የሚችሉት ይላሉ፣ ይህን አውቀው ራሳቸውን ከመዘናጋት ማውጣት እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና የኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ሂክመት አብደላ በበኩላቸው፤ ተቋሙ ከተመሰረተ ሁለት ዓመት እንዳልሞላው ጠቅሰው፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሰርቨር በመጠቀም ወደ ኢ-ሰርቪስ አገልግሎት በመግባት አገልግሎቱን በመጠቀም ተቋሙ ቀዳሚ ከሆኑት ተርታ መሰለፉን ይናገራሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ኢ-ሰርቪስ አገልግሎት የተቋማቸውን አገልግሎት አሰጣጥ እያዘመነና ቀልጣፋ እያደረገ ነው። ተቋሙ የኢ-ሰርቪስ አገልግሎት ከጀመረ በኋላ ሲቸገር የነበረው የክፍያ ሥርዓት አብሮ ባለመካተቱ እንደነበር አስታውሰው፣ የክፍያ ሥርዓቱን ከቴሌብር ጋር በማስተሳሰር አገልግሎት መስጠት እንዲጀመር መደረጉ ለችግሩ መፍትሔ መገኘቱን አመላክተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሁሉንም የመንግሥት አገልግሎቶች ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ እና ዜጎች ባሉበት በአጭር ጊዜ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል የአንድ መስኮት አገልግሎት ዘዴ በማልማት ሁሉም ማህበረሰብ ተጠቃሚ እንዲሆን እየሰራ እንዳለ ይታወቃል። የኤሌክትሮኒክ ሥርዓቱ የመንግሥት ተቋማትን የአሠራር ሥርዓት በማዘመን ቀልጣፋ አሰራር እንዲኖር የሚያግዝና ዜጎች የመንግሥት አገልግሎቶችን በቀላሉ የሚያገኙበትን ዘዴ በመቀየስ ምቹ፣ ቀልጣፋና ተጠያቂነት ለማምጣት የሚያስችል ዘዴ ነው።
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያ የእድገት ግቦቿን ለማሳካት ሁሉን አቀፍ ዲጅታል ኢኮኖሚ መፍጠር እንደሚያስፈልጋት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ይናገራሉ።
በመንግሥት ተቋማት ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን / አይ.ሲ.ቲን/ በመጠቀም በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። ከእነዚህም ሥራዎች ውስጥ የብሔራዊ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት አስተዳደር ሥርዓት ዘዴ /ፕላትፎርም/ ወይም የአንድ መስኮት የኢ-ሰርቪስ አገልግሎትን ማጎልበት ይገኝበታል። ይህ የአሠራር ሥርዓት የመንግሥት ተቋማት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ የቀጥታ /የኦንላይን/ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል የመረጃ ሥርዓት በመዘርጋት ለዜጎች የሚሰጡ አገልግሎቶች የተሳለጡ እንደሆኑ የሚያስችል መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ አብራርተዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ በሀገራችን የተጀመረው የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት አሰጣጥ የመንግሥት አገልግሎቶችን በቀጥታ /ኦንላይን/ መስጠት ከማስቻሉ ባሻገር መረጃዎችን ዲጅታል ማድረግና ሰነድን ማስቀመጥ ያስችላል። ተገልጋዮች አገልግሎት ለማግኘት ወደ መንግሥት ተቋማት የሚደርጉትን አላስፈላጊ ምልልስ መቀነስ እና በጊዜ ሂደት ምልልስ እንዳይኖር ለማድረግም ያስችላል።
ይህ አሠራር በኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቶች የተለያዩ ተቋማት የመረጃዎችን አሰጣጥ አገልግሎት ተናባቢ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቅሰው፣ የመንግሥት ተቋማትም ለሚያቀርቡት አገልግሎት የተሰጡ አስተያየቶችንና ግብረ መልሶችን በቀላሉ ለማወቅ እንደሚያስችላቸው ይናገራሉ። ለአብነትም መረጃዎች ግልጽና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ በቀላሉ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ አንደሚያስችልም ያመለክታሉ።
ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት፤ ይህ የኢ-ሰርቪስ አሰራር /ፕላትፎርም/ www.eservices.gov.et በሚል ድረገጽ አድራሻ ውስጥ በመግባት የተለያዩ ተቋማት አገልግሎቶችን ወደዚህ ፕላት ፎርም በማስገባት ለደንበኞቻቸው አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላቸዋል ። በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የአሥር ዓመት የልማት እቅድ መሠረት በ2015 በጀት ዓመት መጨረሻ ወደ ሰባት መቶ የሚሆኑ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቶችን በማልማት ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ ነው። 2ሺ 500 አገልግሎቶች ወደ ዲጅታል የሚቀየሩ ሲሆን፤ በዚህም 85 በመቶ የሚሆነውን ህብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል።
በዚህ መሠረት በርካታ ተቋማት አገልግሎታቸውን ለህብረተሰቡ እያሳወቁ እንደሚገኙ የተናገሩት ዴኤታዋ፤ የክፍያ ሥርዓት ትስስሩም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የሚፈጠር መሆኑን አመላክተዋል። ዜጎች በአገልግሎት ብቻ ሳይሆን የክፍያ ሥርዓቱን በቀጥታ /በኦንላይ/ በቴሌ ብር አማካይነት እንዲያገኙ መደረጉ አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ እንዲሆን እና በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቀነስ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 25 /2015